Skip to main content
x
ጉራማይሌው የክለቦች አደረጃጀትና እየጋለ የመጣው የሙያተኞችና የደጋፊዎች ጥያቄ
ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ማኅበር የበላይ ጠባቂ አቶ በቃሉ ዘለቀና የስፖርት ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ሰለሞን

ጉራማይሌው የክለቦች አደረጃጀትና እየጋለ የመጣው የሙያተኞችና የደጋፊዎች ጥያቄ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተደጋግሞ ሰሞነኛ ወሬ ሆኖ ሲደመጥ የሚስተዋለው ከስፖርቱ አዎንታዊ ጎን ይልቅ አሉታዊ ጎን ነው፡፡ ከአሉታዊ ጎኖቹ መካከል ክለቦች የመኖርና ያለመኖር ሕልውናና በእግር ኳሱ ምክንያት ክቡር የሆነው የሰው ሕይወትና ንብረት ውድመት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ለእግር ኳሱ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ብቻ ሳይሆን፣ ለኅብረተሰቡ በሚሰጡት ማኅበራዊ ግልጋሎት ጭምር ትልቅ ስምና ዝና ያላቸው ‹‹ውጤት›› ወይም ደግሞ ‹‹ተገቢ ክብር አልተሰጠንም›› በሚል እንዲፈርሱ የተደረጉና ለመፍረስ ከጫፍ የደረሱ ክለቦች ቁጥር እየበረከተ መምጣቱን የሚናገሩ አሉ፡፡ ከነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል የኢትዮጵያ ባንኮች ስፖርት ማኅበር ደጋፊዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

የስፖርት ማኅበሩ ደጋፊዎች፣ ‹‹የንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር የአደረጃጀትና የአሠራር ችግር፤›› በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና የስፖርት ማኅበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ በቃሉ ዘለቀ ጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ በስፖርት ማኅበሩ ያለውን ችግር አስመልክቶ በዝርዝር አሳውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ማኅበር በያዝነው የውድድር ዓመት መጀመርያ የወንዶቹን ዋናውን የእግር ኳስ ቡድንና በሥሩ ያሉት የተስፋውና የ‹‹ቢ›› ቡድኖች ‹‹ውጤት›› የላቸውም በሚል እንዲፈራርሱ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

እግር ኳሱ በተለይም በአሁኑ ወቅት ከውጤት አኳያ ደረጃውን በምን መልኩ ማስቀጠል እንደሚቻል፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ማኅበር የሥራ ኃላፊዎች በኩል በውል ባይገለጽም፣ እንደ ስፖርት ማኅበሩ ደጋፊዎች ግን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር በአገሪቱ ካሉ ከፍተኛ ክለቦች አንዱ ሲሆን፣ ከሦስት አሠርታት በላይ ዕድሜ ከማስቆጠሩ ባሻገር ለስፖርቱ ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ እንደነበር ያምናሉ፡፡

ስፖርት ማኅበሩ ከያዛቸው ስፖርቶች አንዱ አትሌቲክስ መሆኑን የሚጠቅሱት ደጋፊዎቹ፣ በአትሌቲክሱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአህጉራዊም ይሁን በዓለም አቀፍ መድረኮች የአገሪቱ ስምና ዝና ከፍ እንዲል ያስቻሉ ብርቅዬ አስትሌቶችን ማፍራት መቻሉን ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና ይህ የአትሌቲክስ ገናና ታሪክና ስም በተለይም በአሁኑ ወቅት አመርቂና ተስፋ ሰጪ እንዳልሆነ፣ በክትትልና በቁጥጥሩ ማነስ መፍረሳቸው በይፋ የተነገረላቸው የእግር ኳሱ ቡድኖች ቀደም ባለው ጊዜ በቁጥር ብዙና ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን ያፈራና ለስፖርቱ ትልቅ ታሪክ ያለው የስፖርት ማኅበር እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

ከስድስት ዓመታት ወዲህ የስፖርት ማኅበሩ ከአቻ ክለቦች በተሻለ በጀት እየተበጀተለት ተጠናክሮ እንዲሄድ ድርጅቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ በመልካም አስተዳደር ችግር ከስፖርት ማኅበሩ አቅምና ፍላጎት ጋር በማይጣጣም እንቅስቃሴ ውስጥ በመጓዙ፣ ውጤቱ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት መሆኑን ለበላይ ጠባቂው ያሳወቁት ደጋፊዎቹ፣ የፈረሰው የወንዶች እግር ኳስም ሆነ የሌሎች ስፖርቶች ጠንካራና ደካማ ጎን በዝርዝር በመገምገም፣ ሁሉም አካላት ባሉበት ችግሩንም ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በማስቀመጥ አሠራሩን ማስፈጸም ሲገባ ‹‹ቡድን ወረደ›› ብሎ እንዲፈርስ ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢ አለመሆኑን ጭምር ይጠቁማሉ፡፡

የስፖርት ማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ሊያውቁትና ሊረዱት የሚገባው ሲሉ በደብዳቤያቸው ያካተቱት ሌላው፣ ‹‹በአትሌቲክሱም ሆነ በሌሎች ስፖርቶች በአገር ውስጥ፣ በአፍሪካና በዓለም የውድድር መድረኮች ተወዳዳሪዎች በጥራትና በብቃት ማፍራት ሲገባ፣ በአገር ውስጥ ብዙ ክለቦችና ምርጥ ስፖርተኞች በማይሳተፉበት ውድድር ላይ በመካፈል ዋንጫ በማምጣት መኩራራት እንጂ ለከፍተኛ ውጤት የማይሠራ ማኅበር ስለሆነ ነው፤›› በማለት የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ደብዳቤው ይጠቅሳል፡፡

ደጋፊዎቹ ለይተው ካስቀመጧቸው የአሠራር ክፍተቶችና ችግሮች መካከል፣ ቡድኑ በአዲስ መልክ ሲደራጅ ቦታውን የያዙት ሰዎች በተግባር ያልተፈተኑ፣ በወረቀት ሪፖርት ብቻ የሚያምኑ መሆናቸው፣ ስፖርቱን እንዲመሩና እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡና ስብዕና በተላበሰ መልኩ ያለመምራት ችግር ያለባቸው ስለመሆናቸው ጭምር ያትታል፡፡

እንደ ደጋፊዎቹ ደብዳቤ ከሆነ ‹‹አንድ ሰው በዓለም ላይ የሌለ በወረቀት ብቻ በሥልጠናና በማሠልጠን ሳያልፍ የአትሌቲክስ፣ የእግር ኳስና የጠረጴዛ ቴኒስ ለዚህ ሁሉ የቴክኒክ ኃላፊ ሆኖ መሥራት መሠረታዊ ችግር ነው፤›› ብሎ ሌሎች ክለቦች የሚፈርሱት በበጀት ችግር እንደሆነና ንግድ ባንክ ግን የፈረሰው በአመራር ዕጦት መሆኑ፣ ስፖርት ሁልጊዜ ውጤትን መሠረት ያደረገ መሆኑና የአገሪቱም ሆነ የዓለም ተሞክሮ የሚያሳየው ይህንኑ እንደሆነ ያሳያል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር ግን ውጤት ሲቀንስም ሆነ ሲጠፋ፣ እንዲሁም ውጤት ሲመጣ፣ በጊዜውና በወቅቱ የሚያመላክትና ዕርምጃ የሚወስድ አካል ማጣት ችግር መኖሩ፣ ለቦርዱ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ከወረቀት በዘለለ የስፖርቱን ነባራዊ እውነታ የማይገልጽና በቃላት ድርድር ላይ በማተኮር ብቻ ውጤት የማያመጣ መሆኑን የንግድ ባንክ ስፖርት የኋላ ተሞክሮ እንደሚያሳይም ደብዳቤው ይጠቁማል፡፡

የደብዳቤው ይዘት ሲቀጥል፣ የሁሉም ስፖርቶች ሥልጠናና ውድድር በተገቢው ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ትክክለኛውን ዕቅድ አቅዶ ስፖርቱን ማሳደግ የሚያስችል ባለሙያ ዕጦት፣ የስፖርት ማኅበሩ እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን የሥራ ዕቅድ አውጥቶ መሥራት የሚችሉ ብቃት የሌላቸው ደካማና አቅም የሌላቸውን ተመልካችና ተከታታይ በመጥፋቱ ምክንያት በክለቡ ውስጥ በመሰግሰጋቸው ባንኩ የሚፈልገው ውጤት እንዲያስመዘግብ ምክንያት ስለመሆኑ ጭምር ያትታሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የአሠልጣኞች ምርጫና ቅጥር በዝምድናና በቀረቤታ እንጂ መርህና መስፈርት የሌለው መሆኑ እንዲሁም ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች እግር ኳስ ቡድኖች ተጨዋቾችና አሠልጣኞች የሚከፈላቸው ወርኃዊ ክፍያ ከሌሎች ክለቦች አንፃር በጣም  የተጋነነ መሆኑ፣ ይህንኑ የስፖርት ማኅበሩ የበላይ ጠባቂ በውል እንዲያውቁት የሚጠይቀው ደብዳቤ፣ የረዥም ዓመታት ውጤታማ ቡድን በመፍረሱ ምክንያት በኅብረተሰቡ፣ በአካባቢውና በየሠፈሩ የድርጅቱ ስም መነጋሪያ እንዲሆን ማድረጉን ይጠቀሳል፡፡ 

በመሆኑም የበላይ ጠባቂው ይህንኑ አውቀውና ተረድተው በድርጅቱ ላይ የሚነገረው ስም ጥሩ ስላልሆነና በአቶ በቃሉ ዘለቀ የአመራር ጊዜ መበተንና በአጠቃላይ ቡድኑ እንዲፈርስ በምክንያት ከተጠቀሰው አንዱ የኦዲት ሪፖርት ውጤት ይፋ ሳይደረግ መደበቁ አግባብነት የሌለው ስለመሆኑ ጭምር የደጋፊዎቹ ደብዳቤ ይጠይቃል፡፡

ለበላይ ጠባቂው የተጻፈው ደብዳቤ ሲጠቃለልም፣ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንደ መነሻ እንጂ በድርጅቱ ላይ የሚነሱ በጣም ብዙ ችግሮች እንዳሉት እነዚህ ችግሮችም የስፖርት ቤተሰቡን በእጅጉ የሚያሳስቡና የሚያበሳጩ መሆናቸውንም ያትታል፡፡ ለቡድኖቹ መፍረስም ሆነ ውጤት ማጣት ‹‹ስላላዋጣን›› የሚለውን በመጥቀስ፣ የስፖርት ማኅበሩ በድርጅቱና በመንግሥት ይሁንታ ሲቋቋም ለስፖርቱ ዕድገትና ለኅብረተሰቡ ማኅበራዊ ግዴታውን ለመወጣት እንደሆነ በዓላማው ላይ መጠቀሱንም ደብዳቤው ያሳያል፡፡

አትሌቲክሱን ጨምሮ በ1975 ዓ.ም. ‹‹ፋይናንስና መድን›› በሚል መጠሪያ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር፣ በስፖርቱ ታሪክ ውስጥ ከሦስት አሠርታት በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ከሰሞኑ የህልውናው ጉዳይ ማክተሙ የተነገረለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በተቋቋመ በዓመቱ ከሦስተኛ ዲቪዚዮን ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ማደጉን ተከትሎ መጠሪያው ፋይናንስና መድን መባሉ ቀርቶ የባንክ እግር ኳስ ቡድን ተብሎ መዝለቁ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ልማት ባንክ፣ ንግድ ባንክና ቤቶችና ቁጠባ (ቢዝነስ ባንክ) በወቅቱ ቡድኑን በባለቤትነት ሲያስተዳድሩት ቆይተው፣ በ1996 ዓ.ም. የግል ባንኮች ማለትም አዋሽ ባንክ፣ ወጋገን ባንክና ኅብረት ባንክ በባለቤትነት እንዲካተቱ ተደርጎ የኢትዮጵያ ባንኮች ስፖርት ማኅበር በሚል መጠሪያ እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ የስፖርት ማኅበሩ የበላይ ጠባቂ በነበሩት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ መመርያ በ2003 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲተላለፍ ተደርጎ በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስና በጠረጴዛ ቴኒስ ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡