Skip to main content
x
የብሔራዊ ባንክ ውሳኔን የሚጠብቀው የባንክ ዳይሬክተሮች ሹመት

የብሔራዊ ባንክ ውሳኔን የሚጠብቀው የባንክ ዳይሬክተሮች ሹመት

የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት በአገሪቱ ሕግ መሠረት ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴያቸውን የሚያሳይ ሪፖርት በማጠናቀር በውጭ ኦዲተሮች ተመርምሮ የተመሰከረ የሒሳብ ሪፖርታቸውን ባለአክሲየኖች ለሚታደሙበት ጠቅላላ ጉባዔ ያሰማሉ፡፡

የፋይናንስ ተቋማቱ ከሌሎች የአክሲዮን ኩባንያዎችና በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ከተመለከተው ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግጋትና መመርያዎችን የተከተሉ ጉባዔዎችን የማካሄድ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ከመስከረም እስከ ታኅሳስ 2010 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ ውስጥ ከባለአክሲዮኖቻቸው ጋር በጉባዔ ተገናኝተው ትርፍና ኪሳራቸውን ሲያሳውቁ ቆይተዋል፡፡ በጉባዔው ውሳኔ መሠረትም አብዛኞቹ ተቋማት በበጀት ዓመቱ ለትርፍ ክፍፍል የቀረበውን ገንዘብ፣ እንደየአክሲኖቹ ድርሻ ለማከፋፈል ሲወስኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ትርፋቸውን ለካፒታል ማሳደጊያነት እንዲውል ሲወስኑ ታይተዋል፡፡ ሌሎቹ የትርፍ ድርሻውን መውሰድ የሚፈልግ ባለአክሲዮኖች እንዲወስድ፣ የትርፍ ድርሻዬ ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያነት ይዋል ያለም በምርጫው ይወስን በማለት ዕድሉን ክፍት ሲያደርጉ መታዘብ ተችሏል፡፡

በርካታ ባንኮች በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የምርጫ መመርያ መሠረት፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ አካሂደዋል፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ያካሄዱ ባንኮች፣ በአብላጫ ድምፅ አግኘተው የተመረጡ ዘጠኝ የቦርድ አባላትና ተጠባባቂዎችን ያካተተ ሰነድ ለብሔራዊ ባንክ አቅርበዋል፡፡

በየባንኮቹ ከፍተኛ የኃላፊነት ድርሻ ያላቸውና በባለአክሲዮኖች የተመረጡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትም ወደ ሥራቸው ለመግባት የብሔራዊ ባንክን ይሁንታ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክን ይሁንታ ከሚጠብቁት ባንኮች መካከልም አቢሲኒያ፣ እናት፣ ዳሸን፣ ቡና፣ ደቡብ ግሎባል፣ አዋሽ፣ ንብ፣ ብርሃንና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንኮች ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህ ባንኮች እስካሁን ሲያገለግሉ የቆዩትን ጨምሮ አዳዲስ የቦርድ አባላትን  በመምረጥ ብሔራዊ ባንክ እንዲያፀድቅላቸው የምርጫ ሒደቱን የሚያመለክቱ መረጃዎችና ውጤቱን የሚያሳይ ሰነድ በመላክ የገዥውን ባንክ ውሳኔ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ ከአንዳንድ ባንኮች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በተካሄደው ምርጫ ለቦርድ አመራርነት የተመረጡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ሹመት ሳይፀድቅ የቆየው ብሔራዊ ባንክ ከባንኮቹ ተጨማሪ መረጃዎች እንዲቀርቡለት ጥያቄ በማቅረቡ እንዲሁም የእያንዳንዱን ተመራጭ ማኅበር በባንኮቹ ከተላከው ቃለ ጉባዔና ባንኮቹ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ላይ የቀረቡ መረጃዎችን እየመረመረ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ የባንኮች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ሹመት እስኪፀድቅ ጊዜ መውሰዱ ታውቋል፡፡

 ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሹመትን ለማፅደቅ ጊዜ የፈጀበት የእያንዳንዱን ተመራጭ የኋላ ታሪክ፣ ብሎም በሕግ የተቀመጠውን መሥፈርት ስለማሟላታቸው ለማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተመራጮቹን ሹመት ለማፅደቅ የሚያግዙ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ብሔራዊ ባንክ ለተቋማቱ በማቅረቡ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ባንኮች በዚሁ ጥያቄ መሠረት፣ ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄዎች ምላሽ እንዳልሰጡ ታውቋል፡፡ ሆኖም ዘንድሮ ምርጫ ካካሄዱ ባንኮች የአንዳቸውም ዕጩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ሹመት እንዳልፀደቀ ተጠቁሟል፡፡

በባንኮቹ ሹመታቸው እንዲፀድቅ ከተላኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ዝርዝር መረዳት እንደሚቻለው አዳዲስ የቦርድ ሊቀመንበር እንደሚሾሙ የሚጠበቁት እናት ባንክና ዳሸን ባንክ ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ባንኮች በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩ የቆዩት ግለሰቦች፣ በዘንድሮው ምርጫ ባለመካተታቸው፣ ብሔራዊ ባንክ በዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ ያቀረቧቸው አባላትን ካፀደቀላቸው በኋላ አዲስ የቦርድ ሊቀመንበር እንደሚሰይሙ ይጠበቃል፡፡

በዘንድሮው ምርጫ የተለየ ውጤት የነበረው አቢሲኒያ ባንክ ሲሆን፣ እያገለገሉ የሚገኙትን ዘጠኙንም የቦርድ አባላት በድጋሚ በማስመረጥ ሹመታቸውን እንዲያፀድቅለት ለብሔራዊ ባንክ አቅርቧል፡፡ ሌሎቹ ባንኮች ከነባሮቹ የተወሰኑትን አካተዋል፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ነባር የቦርድ ሊቀመንበሮችን አካተው ካስመረጡት መካከል፣ ደቡብ ግሎባል፣ ንብ፣ ዘመንና ብርሃን ባንክ ይገኙበታል፡፡

ከዳይሬክተሮች ምርጫ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ውዝግብ ውስጥ የቆየው ንብ ባንክ፣ የዘንድሮውን ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ ባደረገው ምርጫ፣ ከፍተኛ ድምፅ ካገኙ ዘጠኝ የቦርድ አባላት ውስጥ አምስቱን ከነባሩ ቦርድ አራቱን ደግሞ በአዳዲሶች በመተካት ለብሔራዊ ባንክ ዝርዝራቸውን ልኳል፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ ካካሄዱ ባንኮች ውስጥ የተሰየሙት የቦርድ አባላት እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ግን የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው፡፡