Skip to main content
x
ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚጠበቅበት ቡና በስድስት ወራት 382 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል

ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚጠበቅበት ቡና በስድስት ወራት 382 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል

በዚህ ዓመት ወደ ውጭ ይላካል ተብሎ ከሚጠበቀው ከ270 ሺሕ ቶን ቡና ውስጥ ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 382 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱ ታውቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ግብይትና ልማት ባለሥልጣን የተገኘው ሪፖርት እንደሚያትተው፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ማለትም ከሐምሌ 2009 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 2010 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከቡና ምርት 381.83 ሚሊዮን በላይ ዶላር ገቢ አግኝታለች፡፡

ሪፖርተር ከባለሥልጣኑ ባገኘው ሪፖርት መሠረት፣ በስድስት ወራት ውስጥ 107,302 ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቧል፡፡ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 85,385.84 ቶን ቡና ወደ ውጭ ተልኮ 313.33 ሚሊዮን ዶላር ገቢ  መገኘቱን ያስታወሰው ባለሥልጣኑ፣ በዘንድሮው ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ የታየው አፈጻጸም ካለፈው ዓመት አኳያ ሲነፃፀር፣ በመጠን 21,916 ቶን በላይ ብልጫ ማስመዝገቡን ጠቅሷል፡፡ በገቢ በኩልም ከ68.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕድገት ታይቷል ብሏል፡፡ ይህ አፈጻጸም በመጠን 25.67 በመቶ እንዲሁም በገቢ በኩል 21.86 በመቶ ጭማሪ ስለማሳየቱን ተጠቅሷል፡፡

ይሁንና በተሸኙት ስድስት ወራት ውስጥ ከቡና ይጠበቅ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ436 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነበር፡፡ በአንፃሩ ወደ ውጭ እንደሚላክ ታቅዶ የነበረው መጠን ከ102 ሺሕ ቶን ብዙም ፈቅ አይልም ነበር፡፡ ሆኖም ከ107 ሺሕ ቶን በላይ ሊላክ ችሏል፡፡ ባለሥልጣኑ ምንም እንኳ በቡና የወጪ ንግድ በኩል በመጠን የታየው አፈጻጸም ከታቀደው በላይ ቢሆንም ቅሉ፣ በዋጋ በኩል የታየው ቅናሽ በዓለም ገበያ ከታየው የቡና ዋጋ መቀነስ ጋር እንደሚያያዝ ተገልጿል፡፡

ይህም ሆኖ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከሚላከው 270 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ የባለሥልጣኑ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ባለፈው ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበው ከ882 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመገኘቱ እስካሁን ከቡና ከተገኘው ከፍተኛው ገቢ ሆኖ መመዝገቡ አይዘነጋም፡፡ ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ የተላከው የቡና ምርት መጠን 225,667 ቶን ሲሆን፣ ዘንድሮ ይላካል ተብሎ የሚጠበቀው ግን 270,388 ቶን እንደሆነ ታውቋል፡፡

በስድስቱ ወራት ቡና የተላከባቸው አገሮች ከ60 በላይ ሲሆኑ ቀዳሚዋ ጀርመን ነች፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ አሜሪካ፣ ጃፓንና ሌሎችም አገሮች ሲካተቱ እንደ ሲሼልስ ያሉትም የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በሌላ በኩል በስድስት ወራት ውስጥ ከ5.9 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘበት የቅመማ ቅመም የወጪ ንግድም በባለሥልጣኑ ሪፖርት ውስጥ ተካቷል፡፡ ከቅመማ ቅመም የሚጠበቀው የታቀደ ገቢ ከአሥር ሚሊዮን ዶላር በላይ ነበር፡፡ በክንውኑ ግን ግማሹ ተገኝቷል፡፡ በመጠን ረገድም ከአምስት ሺሕ ቶን በላይ ይላካል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ከአራት ሺሕ ቶን ብዙም ፈቅ ያላለ መጠን ለውጭ ገበያ መቅረቡን የባለሥልጣኑ ሪፖርት አስፍሯል፡፡

‹‹እስከ ታኅሳስ ወር 2010 ዓ.ም. ድረስ 4,219.6 ቶን የቅመማ ቅመም ምርት ወደ ውጭ ተልኮ 5.9 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፤›› ያለው ሪፖርቱ፣ ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ወደ ውጭ ከተላከው 3,204.04 ቶን ቅመማ ቅመም እንዲሁም ከተገኘው 5.72 ሚሊዮን ዶላር አኳያ፣ በመጠን 1,015.58፣ በገቢ ግን 0.19 ዶላር ለውጥ የታየበት አፈጻጸም ስለመሆኑ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

ከቡናና ከቅመማ ቅመም ባሻገር፣ በስድስቱ ወራት 1,077 ቶን የሚጠጋ የሻይ ቅጠል ምርት ለውጭ ገበያ እንደቀረበ ታውቋል፡፡ በመንፈቀ ዓመቱ የሻይ የወጪ ንግድ አፈጻጸም በመጠንም ሆነ በገቢ ረገድ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ብልጫ እንዳሳየ የባለሥልጣኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 1,077 ቶን የሚጠጋ የሻይ ቅጠል ምርት ለውጭ  ገበያ ቀርቦ 2.132 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ባለፈው ዓመት 948.12 ቶን የሻይ ቅጠል ምርት ተልኮ፣ 1.78 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተመዝግቦ ነበር፡፡