Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ከቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ጠዋት ከሚስታቸው ጋር ቁርስ እየበሉ እያወሩ ነው]

 • ሳረሳው አንድ ነገር ልንገርሽ፡፡
 • ምንድነው የምትነግረኝ?
 • ወቅቱን በደንብ ታውቂዋለሽ ብዬ እገምታለሁ፡፡
 • እንግዲህ ይኼ የጥምቀት ወቅት ነው፡፡
 • አንቺ ከእንዲህ ዓይነት ነገር ተላቀቂ አላልኩሽም እንዴ?
 • እዚህ ላይ ወራጅ አለ፡፡
 • መጀመርያስ ማን ተሳፈሪ አለሽ?
 • አንተ ሃይማኖት የለህምና ስለእኔ ሃይማኖት አስተያየት መስጠት አቁም፡፡
 • እኔም እኮ ሃይማኖት አለኝ፡፡
 • ምን የሚሉት ሃይማኖት ነው ያለህ አንተ ደግሞ?
 • አብዮታዊ ዴሞክራሲ፡፡
 • ለነገሩ የእናንተን ታቦት አውቀዋለሁ፡፡
 • የምን ታቦት?
 • የሙስና፡፡
 • እ. . .
 • እናንተ ታቦታችሁን በየጊዜው ነው የምታነግሡት፡፡
 • ሴትዮ ምንድነው የምታወሪው?
 • ስለአንተ ሃይማኖት ነዋ፡፡
 • ለማንኛውም አሁን ስለሃይማኖት ላወራሽ አይደለም የፈለግኩሽ?
 • ስለምንድን ነው ልታወራኝ የፈለግከኝ?
 • ሰሞኑን ወሳኝ የሆነ ስብሰባ በከተማችን ውስጥ ይደረጋል፡፡
 • የምን ስብሰባ?
 • የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ነዋ፡፡
 • ደግሞ ሰሞኑን ልታሰቃዩን ነዋ፡፡
 • ምን ሆነሽ ነው የምትሰቃይው?
 • በቃ በየሰዓቱ መንገዱን እየዘጋችሁ መግቢያ መውጫ ልታሳጡን ነው፡፡
 • ስሚ ስብሰባው እኮ ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ አለው፡፡
 • በነገራችን ላይ ሰሞኑን በየሚዲያው የምታሰሙት መግለጫ ያስገርመኛል፡፡
 • ምኑ ነው የገረመሽ?
 • ያው መንገድ ምናምን ሊዘጋ ስለሆነ ይኼ ጨዋ ሕዝብ ምናምን እያላችሁ ታሞካሹታላችሁ፡፡
 • ሌላስ ጊዜ ቢሆን?
 • ሌላ ጊዜማ እናንተ ላይ ጥያቄ ሲያነሳባችሁ ፀረ ልማት፣ ፀረ ሰላም እያላችሁ ታብጠለጥሉታላችሁ፡፡
 • አሁን ያልተጠየቅሽውን ለምን ታወሪያለሽ?
 • ለማንኛውም ለእኔም የቪአይፒ ፓስ ብታስወጣልኝ ደስ ይለኛል፡፡
 • ሴትዮ እንደዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ አትክተቺኝ፡፡
 • አንተ ድሮም እኔን መጥቀም አትፈልግም፡፡
 • ይኸው የሚጠቅምሽን ነገር ልነግርሽ አይደል እንዴ?
 • ምድነው እሱ?
 • በዚህ ስብሰባ አሪፍ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡
 • ምን ዓይነት ሥራ?
 • ለስብሰባው የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎች መሆናቸውን ታውቂያለሽ?
 • እሱማ አውቃለሁ፡፡
 • ስለዚህ ከፍተኛ ዶላር ይዘው ነው የሚመጡት፡፡
 • ታዲያ ምን ይጠበስ?
 • ስሚ ባለፈው ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰብን ረሳሽው?
 • የምን ኪሳራ ነው የምታወራው?
 • መንግሥት ብርን ዲቫልዩ ሲያደርገው እኮ ሀብታችን በ15 በመቶ ነው የቀነሰው፡፡
 • አልገባኝም?
 • አንቺ መቼ እንደዚህ ዓይነት ነገር ይገባሻል?
 • ምን እያልክ ነው?
 • ገንዘባችንን በብር በማስቀመጣችን ምክንያት ብር ዲቫልዩ ሲደረግ ሀብታችን በ15 በመቶ ቀንሷል፡፡
 • እ. . .
 • በዶላር አስቀምጠነው ቢሆን ግን ሀብታችን በ15 በመቶ ይጨምር ነበር፡፡
 • ታዲያ ምን ማድረግ እንችላለን?
 • ገንዘባችንን በዶላር ማስቀመጥ አለብን፡፡
 • ዶላር ታዲያ ከየት ይመጣል?
 • የስብሰባ ተሳታፊዎቹ የውጭ ዜጎች ስለሆኑ ዶላር ነው የሚጠቀሙት፡፡
 • እኔ ባንክ አይደለሁ፣ እኔ ጋር አይመነዝሩ?
 • እሱን እኮ ነው የምልሽ?
 • እንዴት?
 • በየሆቴሉ ማቋቋም አለብሽ፡፡
 • ምን?
 • የውጭ ምንዛሪ ቢሮ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ እንደገቡ የሞተር ፑል ኃላፊውን ጠርተው እያነጋገሩት ነው]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እስቲ ተቀመጥ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር?
 • በጣም ላፋጣኝ ጉዳይ ነው የፈለግኩህ፡፡
 • ምን ነበር ክቡር ሚኒስትር?
 • ስንት መኪና ነው ያለን?
 • የምን መኪና ነው?
 • ማለቴ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስንት መኪና አለው?
 • የእርስዎን ጨምሮ ወደ አርባ ይጠጋሉ፡፡
 • ከአርባዎቹ መኪኖች ለሰው እየተጠቀምንበት ያለው ስንቱን ነው?
 • አብዛኛዎቹ የፊልድ መኪናዎች ናቸው፡፡
 • ስለዚህ ስንቶቹ ናቸው ሰው የሚጠቀምባቸው?
 • አሥራ አምስት ይሆናሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ ሃያ አምስት መኪኖች ነፃ ናቸው እያልከኝ ነው?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በቃ እነዚህን መኪኖች ቶሎ ኪራይ እናስገባቸዋለን፡፡
 • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰማኸኝ አይደል እንዴ መኪኖቹ ኪራይ ይገባሉ፡፡
 • የምን ኪራይ?
 • ስማ ከተማው ውስጥ ከፍተኛ እጥረት እንዳለ አታውቅም?
 • የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው?
 • በዚህ ወቅት መኪና ራሱ እንደ ውጭ ምንዛሪ ይሆናል፡፡
 • እ. . .
 • በዚህ ወቅት ከፍተኛ የኪራይ መኪና እጥረት አለ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ከተማ ውስጥ ምን እንዳለ አታውቅም?
 • ምን አለ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሚዲያ አትከታተልም እንዴ?
 • ባለፈው ቲቪዬን መብራት ስላቃጠለው ዜና ካየሁ ቆየሁ፡፡
 • ለምን ቲቪ አትገዛም?
 • ኧረ ከውሸት ስለተገላገልኩ ደስ ብሎኛል፡፡
 • ለማንኛውም ሰሞኑን የመሪዎች ስብሰባ አለ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ስለዚህ መኪኖቹ ሥራ መግባት አለባቸው፡፡
 • እ. . .
 • አንተ ከዚህ ሥራ ትጠቀማለህ?
 • በምን?
 • ኮሚሽን ታገኛለህ፡፡
 • ስለዚህ መኪኖቹ ይከራዩ እያሉኝ ነው?
 • እንዲያውም የእኔ ቪ8 ይከራይ፡፡
 • እርስዎስ?
 • እኔ እከራያለሁ፡፡
 • ምን?
 • ቪትስ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ምንድነው የያዙት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼ አሪፍ መጽሐፍ ነው፡፡
 • ምን ዓይነት መጽሐፍ?
 • ፊክሽን ነው፡፡
 • ፊክሽን ያነባሉ እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ከፊክሽን ውጪ መቼ አነባለሁ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ፊክሽን በጣም ነው የሚያስደስተኝ፡፡
 • ይኼን ያህል?
 • በተለይ ይኼኛው ጸሐፊ በጣም አሪፍ ጸሐፊ ነው፡፡
 • መጽሐፉ ግን ትልቅ ይመስላል?
 • እኔ እኮ ይኼን መጽሐፍ በሦስት ቀን ነው የምጨርሰው፡፡
 • ምን ይቀልዳሉ?
 • ቮራሺየስ አንባቢ ነኝ እኮ፡፡
 • ቪሸስ ነው ያሉኝ?
 • ቮራሺየስ ነው ያልኩህ፡፡
 • እኔ እኮ እንግሊዝኛ ላይ ብዙም አይደለሁም፡፡
 • ለማንኛውም ይኼ ስለአንድ ባለሥልጣን ነው የሚያወራው፡፡
 • ምን ዓይነት ባለሥልጣን?
 • በቃ ይኼ ባለሥልጣን ሲስተሙን እንዴት አድርጎ እንደሚጫወትበትና እንደሚያምታታው ታያለህ በዚህ መጽሐፍ፡፡
 • በጣም ይገርማል፡፡
 • ሰውዬው እንዴት ባለሀብቶችና ፖለቲከኞች ላይ እንደሚጫወትባቸው ታያለህ?
 • እና እንደዚህ ዓይነት መጽሐፍ ነው የሚወዱት?
 • ሱስ ሆኖብኛል ስልህ?
 • ከፊክሽን ውጪም አያነቡም?
 • ለሌላው ብዙም ግድ የለኝም ስልህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ፊክሽን ግን በሰዎች ምናብ የሚፈጠሩ ታሪኮች አይደሉም እንዴ?
 • ታዲያ ምን ችግር አለው?
 • ማለቴ እርስዎ እንደ ፖለቲከኛ እውነታ ላይ ያተኮሩ መጽሐፎችን ቢያነቡ ይጠቀማሉ ብዬ ነው፡፡
 • ለእኔ እንዲያውም የሚጠቅመኝ ፊክሽኑ ነው፡፡
 • አሁን አገሪቷ ላይ ምን እየተጫወታችሁ እንደሆነ ገባኝ፡፡
 • ምንድነው የምንጫወተው?
 • ዕቃ ዕቃ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]

 • መቼም ስለእርስዎ የማልሰማው ጉድ የለም ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሰማህ ደግሞ?
 • የእርስዎ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ሥልት እየተራቀቀ ከመምጣቱ ብዛት ለእኛም ራስ ምታት እየሆነብን ነው፡፡
 • እናንተ አስተሳሰባችሁ ሊቀየር ስላልቻለ ነው፡፡
 • ወደ ምን?
 • ወደ ዲጂታል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን በእርስዎ ተስፋ እየቆረጥን ነው፡፡
 • ዋናው ዋራንት አለመቁረጣችሁ ነው፡፡
 • የምን ዋራንት ነው?
 • የእስር ቤት ነዋ፡፡
 • እውነቱን ተናገር ካሉኝ ለእርስዎ የሚገባው እስር ቤት ነው፡፡
 • መቼም እሱ የሚያመጣውን ጣጣ ታውቁታላችሁ?
 • የምን ጣጣ ነው የሚያመጣው?
 • ከእኔ ጋር ያልተነካካ የለም፡፡
 • እሱን ችግርማ እናውቃለን፡፡
 • ስለዚህ እንደ ዶሚኖ ተያይዘን ነው የምንወርደው፡፡
 • የት?
 • ማረሚያ ቤት ነዋ፡፡
 • እኛም እሱ ነው የሚያስፈራን፡፡
 • ስለዚህ ይኼን ሐሳብ ተውት፡፡
 • እንዲህ ሆነው መቀጠል ግን አይችሉም፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • ከፍተኛ የአቅም ችግር አለብዎት፡፡
 • ማን የሌለበት አለ?
 • በዚያ ላይ ኪራይ ሰብሳቢ ነዎት፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ አለ ዘፋኙ፡፡
 • ስለዚህ ጡረታ ቢወጡ ይሻላል፡፡
 • እኔ ብዙ የለመድኩ ሰው ነኝ፣ የጡረታ ገቢ መቼ ትጠቅመኛለች?
 • ይኼኛው ለየት ያለ ጡረታ ነው፡፡
 • ምን ዓይነት ጡረታ?
 • የሹመት ጡረታ፡፡
 • የምን ሹመት?
 • የአምባሳደርነት!