Skip to main content
x
ባለቤት አልባው የአካል ድጋፍ ማደራጃ

ባለቤት አልባው የአካል ድጋፍ ማደራጃ

ትዕግሥት ተፈራ የ16 ዓመት ወጣት ናት፡፡ ትውልድና ዕድገቷም ሰሜን ወሎ ራያ ነው፡፡ በሕፃንነቷ ከአልጋ ላይ ወድቃ ከወገቧ በታች ያለው ሰውነቷ መንቀሳቀስ ተስኖታል፡፡ በዚህም የተነሳ የአካል ድጋፍ ተሠርቶላታል፡፡ ትዕግሥትን ያገኘናት በሰው ሠራሽ የአካል ድጋፍ ማደራጃ ድርጅት፣ ከወገቧ በታች በተገጠመላት የአካል ድጋፍ መራመድ ስትለማመድ ነው፡፡

‹‹ከሕፃንነት ዕድሜ አልፌ ነፍስ ሳውቅ በራሴ ጥረት አዲስ አበባ አለርት ማዕከል ለሕክምና መጣሁ፡፡ ሆስፒታሉም ተገቢውን ሕክምና ካደረገልኝ በኋላ አካል ድጋፍ እንዳገኝ ወደዚህ ድርጅት ላከኝ፡፡ በፊት በእንፉቅቄ ነበር የምንቀሳቀሰው፡፡ አሁን ቆሜ ለመንቀሳቀስ በቃሁ፤›› ብላለች፡፡

በፊዚዮቴራፒ ክፍል ያገኘናት ገነት ሙሉጌታ የተባለችው ታካሚ ደግሞ ከአንድ ወር በፊት አስፋልት ላይ ወድቃ በደረሰባት አደጋ አንገቷ ዲስክና ነርቭ ላይ ጉዳት እንደደረሰባት ነግራናለች፡፡ መጀመርያ አልትራሳውንድና ራጅ ከታየች በኋላ የመረመራት ሐኪሟ ለፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ወደ ድርጅቱ እንደላካት የምትናገረው ገነት፣ የፊዚዮቴራፒ ሕክምና ከጀመረች አራት ቀናት ሆኗታል፡፡ በተጎዳው አካሏ ላይ ለውጥ መታየቱንም ገልጻለች፡፡

‹‹ይህንን የፊዚዮቴራፒ ሕክምና ከማግኘቴ በፊት ያመኛል፣ መተኛትም አልችልም ነበር፡፡ ጉዳት የደረሰበት አካሌ ውስጡ ይበላኝና ይቆረጥመኝ ነበር፡፡ አሁን ግን መብላቱና መቆርጠሙ ቆሟል፤›› ብላለች፡፡

አቶ መካ ኑሩ የፊዚዮቴራፒ ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ከነርቭና ከአጥንት ጋር በተያያዘ ችግር የደረሰባቸው በርካታ ታካሚዎች የፊዚዮቴራፒ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ሕክምናው የሚሰጠውም ትርፍን ሳይሆን አገልግሎትን ባማከለ መልኩ ነው፡፡ ባለሙያዎችም የአቅማቸውን ያህል ጥሩ ሕክምና ይሰጣሉ፡፡

ከታካሚዎቹም መካከል አብዛኛዎቹ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ ከሐኪሞቻቸው ይዘው የሚመጡ ናቸው፡፡ አንደኛው ከሌላው በመስማት አገልግሎቱን ለማግኘት የሚመጡም አሉ፡፡ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ለሚመጣውም አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም፣ አንድ ቀን መጥተው በሚቀጥለው ቀን ስለማይመጡ ተከታታይ ሕክምና ለመስጠት አይመችም፡፡ በሐኪሞች ትዕዛዝ ለሚመጣ ታካሚ ግን የሕክምናውን ግብረ መልስ ጭምር ለሐኪሙ እንዲደርስ ይሠራል፡፡

ፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡት አዛውንት፣ ጎልማሶች ወይስ ወጣቶች ናቸው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ መካ ሲመልሱ፣ ‹‹አገልግሎቱ ሁሉንም ዓይነት ዕድሜ ያማክላል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ጎልማሶች ናቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ የተለያዩ የአካል መተሳሰር ወይም እግር ላይ ችግር ለሚያጋጥማቸው ሕፃናት አገልግሎት እንሰጣለን፤›› ብለዋል፡፡

ቤተሰብም እነዚህን ችግሮች በምን መልኩ መወጣት እንዳለበት የሚያስገነዝብ ትምህርት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተረፈ የባለሙያ እጥረት እንዳለ፣ ባለሙያዎችም ከዩኒቨርሲቲ በፊዚዮቴራፒ ሥልጣና የተመረቁ ሳይሆኑ እዚሁ ሠልጥነው የተመደቡና በሥራ ልምድ ሙያውን የቀሰሙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከዩኒቨርሲቲ በዚሁ ሙያ በመሠልጠን ላይ ያሉት ተማሪዎች እዚህ መጥተው የሥራ ላይ ልምምድ ሥልጠና እንደሚከታተሉ፣ እዚሁ ለመቀጠር ግን ከክፍያው አነስተኛነት የተነሳ ፍላጎት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ባልሄር ናቸው፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የሰው ሠራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማደራጃ ድርጅት በዓመቱ ከ26 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ አካል ጉዳተኞች የሰው ሠራሽ አካል ድጋፍ፣ የመንቀሳቀሻ መርጃ መሣሪያዎች አቅርቦትና የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት በክፍያ ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ ሦስት ቁልፍ ችግሮች ተጋርጠውበታል፡፡ በእነዚህም ችግሮች ሳቢያ የአቅሙን ያህል አገልግሎት ለመስጠት ተስኖታል፡፡

ከቁልፍ ችግሮቹም መካከል በዋናነት የአደረጃጀት ችግርና የሕጋዊ ዕውቅና አለመኖር ሲሆን፣ የበላይ ተጠሪ የሚሆንለት መሥሪያ ቤትም የለውም፡፡ አካል ጉዳተኞች የሚረዱበት ድርጅት በመሆኑ እንጂ ሕጋዊ አካልና ዕውቅና ሳይኖረው ለአንድ ቀን እንኳን መንቀሳቀስ እንደማይችል አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

እንደ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ጉዳዩ በይበልጥ ከሚመለከተው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ዕውቅና እንደሌለው፤ የግል ድርጅት ነው እንዳይባል በንግድ ሚኒስቴር እንዳልተመዘገበና እንዲያው በአጠቃላይ በአየር ላይ የተንሳፈፈ ወይም ባለቤት አልባ ድርጅት ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ ሕጋዊ ያልሆነ አቋምና የአደረጃጀት ችግር መፍትሔ የሚያገኝበትን እንዲሁም በመንግሥት ሥር እንዲሆንና ለአካል ጉዳተኞች ነፃ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበትን መፍትሔ የሚጠቀም ጥናት ተሠርቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት ቀርቧል፡፡ ጥናቱም በቅርቡ ተቀባይነትን አግኝቶ ተግባራዊ ይሆናል የሚል ተስፋ አሳድሯል፡፡

በመላ ኢትዮጵያ ይህንኑ ድርጅት ጨምሮ ወደ 13 የሚጠጉ የማቋቋሚያ ድርጀቶች እንዳሉ፣ ከእነሱም ውስጥ የሰው ሠራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማደራጃ ድርጅት ብቻ ገንዘብ እያስከፈለ አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆን፣ የቀሩት ነፃ አገልግሎት እንደሚያበረክቱ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

የማደራጃው ድርጅት ገንዘብ ለማስከፈል ያነሳሳው እንደተቋቋመ ገንዘብ ድጋፍ ያደርጉለት የነበሩት በጎ አድራጊ ግለሰቦች ስለተበታተኑ ሲሆን፣ የቀሩት ድርጅቶች ግን በነፃ አገልግሎት ለመስጠት የቻሉት ከመንግሥት በጀት ስለሚመደብላቸው ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ማደራጃው ድርጅት የሚያመርትባቸው መሣሪያዎች ቀደም ሲል በዕርዳታ የተገኙ ከመሆናቸውም በላይ ከአገልግሎት ብዛት የተነሳ እየተበላሹ፣ እያረጁና በዚህም የተነሳ ሥራ እያቆሙ ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ ማምረት የሚገባውን ያህል እንዳላመረተና የአገልግሎት ፈላጊዎችን ጥያቄ በአቅም ውስንነት ምክንያት በተሟላ መልኩ እየመለሰ አይደለም፡፡

በድርጅቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ሠራተኞች የኦርቶፖዲክስ ቴክኒሺያኖችና የፊዚዮቴራፒ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የፊዚዮቴራፒ ባለሙያዎች የሚያሠለጥነው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በቅርቡ የማስተርስ ፕሮግራም ጀምሯል፡፡ ቴክኒሺያኖቹም ከተጠቀሰው የትምህርት ተቋም ሠልጥነው የወጡ ሳይሆን፣ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመፈራረም ለሦስት ዓመት ያህል የሰጠውን የኦርቶፖዲክስ ሥልጠና የተከታተሉ ናቸው፡፡ ፕሮጀክት በማብቃቱ የተነሳ ሥልጠናው ቆሟል፡፡

በዚህም የተነሳ የሙያተኞች እጥረት እንዳለ፣ ይህንንም እጥረት ለመቋቋም ሲባል በብረት ሥራ ላይ ለተሠማሩት በሥራ ላይ ሥልጠና ወይም አጫጭር ሥልጠና እየተሰጣቸው ወደ ሰው ሠራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማምረት ተግባር ላይ እንዲሠማሩ እየተደረገ ነው፡፡

ቀደም ሲል ድጋፍ ይሰጡ የነበሩ ድርጅቶች ድጋፋቸውን ያቋረጡት የአደረጃጀቱ አቋም ባለመታወቁ ምክንያት ነው፡፡ ይህም ማለት አደረጃጀቱ ከመንግሥት ጋር ነው? ወይስ የግል ድርጅት ነው? አቋሙና አመዘጋገቡ ይገለጽልን የሚል ጥያቄ አቅርበው መልስ በማጣታቸው ነው፡፡

የሰው ሠራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማደራጃ ድርጅት ‹‹ድኩማን ረድዔት ድርጅት›› (ፈንድ ፎር ዘ ዲስኤብል) በሚል መጠሪያ በ1954 ዓ.ም. በቀድሞው ልዕልት ፀሐይ (ጦር ኃይሎች) ሆስፒታል ቅጥር ግቢ እንደተቋቋመ፣ ያቋቋሙትም ንጉሣውያን ቤተሰቦችና መሳፍነት እንደሆኑ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

የአካል ድጋፍና የመንቀሳቀሻ መሣሪያዎች፣ ማለትም ዊልቸር ዎኪንግ ፍሬም፣ የመሳሰሉት እያመረተና ለአካል ጉዳተኞች በነፃ የማቅረብና የፊዚዮቴራፒ አገልግሎትም በነፃ የመስጠት ዓላማ ለነበረው ለዚሁ ድርጅት፣ በወቅቱ ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘው ከቀድሞው አገር ግዛት ሚኒስቴር ነው፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የድርጅቱ የበላይ ጠባቂ እንደነበሩ፣ በየዓመቱም አሥር ሺሕ ብር ይለግሱና በየጊዜውም እየመጡ እንቅስቃሴውን ይከታተሉ እንደነበር አቶ አሰፋ አስታውቀዋል፡፡

ድርጅት በ1960 ዓ.ም. አሁን በሚገኝባት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በስተጀርባ ካለው አጥር ጋር ተያይዞ ባለው ቦታ ላይ በ65,000 ብር ወጪ አሁን ያለውን ሕንፃ አስገንብቶ እንደገባ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቀድሞ ስሙ ተቀይሮ አሁን ያለውን መጠሪያ እንደያዘ አስረድተዋል፡፡

ወዲያውኑም አብዮቱ የፈነዳ ሲሆን፣ መሥራቶቹ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ተበተኑ፡፡ በዚህም የተነሳ አገሪቱን በወቅቱ ያስተዳድር ለነበረው ለጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ድርጅቱን የሚመራ አካል እንዲመደብለት ተጠየቀ፡፡ በዚህም የተነሳ በቦርድ እንዲተዳደር ተወሰነ፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቦርድ ሰብሳቢ ሲሆን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የጀግኖች አምባ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር የቦርድ ዳይሬክተሮች ሆነው እንዲሠሩ ተደረገ፡፡ አሁንም ያለው አወቃቀር የቀድሞውን የተከተለ ነው፡፡ ነገር ግን በጀግኖች አምባ ምትክ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ተተክቷል፡፡

ይህም ቢሆን ከበላይ ሆኖ የሚያስተዳድረው አካል እንደሌለው፣ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ ከአፍሪካ ሆርን፣ ከዓለም አቀፍ ኦርቶዶክስ፣ ከዩኤስኤአይዲ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ ያገኝ እንደነበር አይዘነጋም፡፡