Skip to main content
x
የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ መጓተቱን የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ
በግንባታ ላይ ያሉ የ20/80 ኮንዶሚኒየም ቤቶች

የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ መጓተቱን የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ

በአዲስ አበባ ከተማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለማግኘት ተመዝግበው በየወሩ እየቆጠቡ የሚገኙ ቢሆንም፣ ግንባታው ግን አዝጋሚ መሆኑ በፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ተገለጸ፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በ20/60 እና በ40/80 ቤቶች ፕሮግራም ሳይቶች ላይ ባካሄደው ቅኝት  ግንባታው በተያዘለት ዕቅድ ከመሄድ ይልቅ እየተጓተተ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በስምንት ሳይቶች ቅኝት ካካሄደ በኋላ ባቀረበው ሪፖርት፣  በሁለቱም መርሐ ግብሮች የተጀመሩ ግንባታዎች በሚፈለገው መጠን እየሄዱ አይደለም ብሏል፡፡

ለግንባታው መቀዛቀዝ አሉታዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብለው ከቀረቡ ምክንያቶች መካከል የሠራተኛ እጥረት፣ ለግንባታ የሚያስፈልጉ ዕቃዎች አቅርቦት ችግር፣ የሥራ ተቋራጮች አቅም ደካማ መሆን፣ የንብረት አያያዝ ዘመናዊነት የሚጎድለው መሆኑ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍፊ ድልጋሳ፣ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ መጓተት የሚታዩ ችግሮችን በሚገባ መፈተሽና ከሚመለከተው አካላት ጋር በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 132,380 ቤቶች በግንባታ ላይ ሲሆኑ፣ መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት ለ20/80 ፕሮግራም አሥር ቢሊዮን ብር፣ ለ40/60 ቤቶች ፕሮግራም እንዲሁ አሥር ቢሊዮን ብር፣ በድምሩ 20 ቢሊዮን ብር በጀት መድቧል፡፡

ይህ በጀት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ይገነባሉ ለተባሉ 750 ሺሕ ቤቶች በየዓመቱ 150 ሺሕ ቤቶች ለመገንባት ከተያዘው ዕቅድ አንፃር ሲታይ አነስተኛ ቢሆንም፣ ከሌሎች ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ትልቁ በጀት መሆኑ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፣ ቋሚ ኮሚቴው የተመለከተው የግንባታ መዘግየት ትክክል እንደሆነ አምነዋል፡፡

‹‹ለግንባታ መጓተቱ አስተዋጽኦ ያላቸውን ችግሮች በመፍታት ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከ900 ሺሕ በላይ የከተማው ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ለመሆን ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ግንባታው በወቅቱ እየተካሄደ ባለመሆኑ እያሳሰባቸው መሆኑን ተመዝጋቢዎቹ ባገኙት አጋጣሚ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡