Skip to main content
x
‹‹የኛ በኢትዮጵያ ወጣቶችን የሚወክል ትልቅ የሐሳብ ብራንድ ነው››

‹‹የኛ በኢትዮጵያ ወጣቶችን የሚወክል ትልቅ የሐሳብ ብራንድ ነው››

ሚስስ ፋራህ ራምዛን ጎላንት፣ የገርል ኢፌክት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሚስስ ፋራህ ራምዛን ጎላንት በኢትዮጵያ ‹‹የኛ›› በሚል ስያሜ የሚታወቀውን የልጃገረዶች ፕሮግራም ጨምሮ፣ በበርካታ አገሮች ውስጥ በልጃገረዶች ጉዳይ የሚንቀሳቀሰውን ‹‹ገርል ኢፌክት›› የተሰኘ ማኅበራዊ ተቋም በዋና ሥራ አስፈጻሚነት መምራት ከጀመሩ ሁለት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ ከ12 ዓመታት በፊት በታዋቂው የስፖርት ትጥቅ አምራች ናይኪ ኩባንያ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፋውንዴሽንና በሌሎችም አጋሮች አማካይነት ተመሥርቶ የሚንቀሳቀሰው ገርል ኢፌክት፣ በኢትዮጵያ የኛ ፕሮግራምን መምራት ከጀመረም አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የኛ ፕሮግራም በአምስት ልጃገረዶች በሚተላለፉ የሬዲዮ ፕሮግራሞች፣ ሙዚቃዎችና ድራማዎች አማካይነት በሴቶች ላይ የሚደርሱ አሉታዊ ጫናዎችን፣ ፆታ ተኮር ተፅዕኖዎችን፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ የመሳሰሉትንና ሌሎች ግፊቶችን ለመቀነስ አስተማሪ ፕሮግራሞችን ሲያቀርብ የቆየ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያም የእንግሊዝ መንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ ሲሰጠው የቆየ ተቋም ለመሆን ቢበቃም፣ ባለፈው ዓመት ግን የፋይናንስ ድጋፉን እንዳቆመ የእንግሊዝ መንግሥት ማስታወቁ አይነዘጋም፡፡ ድጋፉ ለምን እንደቆመ፣ ፕሮግራሙ ወደፊት እንዴት እንደሚቀጥል፣ ‹‹የኢትዮጵያ ስፓስ ገርልስ›› በሚል ቅጽል መጠሪያ መታወቅ የጀመሩት የአምስቱ ልጃገረዶች የወደፊት ዕጣ ፈንታና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት፣ ብርሃኑ ፈቃደ ሚስስ ፋራህ ጎላንትን በማነጋገር ያጠናቀረው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ‹‹የኛ›› ፕሮግራም በመነጋገር እንጀምር፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት በልጃገረዶች መብት ጥበቃ ላይ በማተኮር እንደ ያለ ዕድሜ ጋብቻ ያሉት ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ፕሮግራሙ በአሁኑ ወቅት ስለሚገኝበት ሁኔታና ሚናው ምን ሊነግሩን ይችላሉ?

ሚስስ ፋራህ፡- የኛ አምስት ዓመታት ያስቆጠረና በኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን፣ በኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያውን በመነጨ ሐሳብ የተፈጠረ ፕሮግራም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ውስጥ 70 በመቶው ከ30 ዓመት ዕድሜ በታች እንደመሆኑ የሚዲያው መስፋፋት፣ የሞባይል ሥርጭት፣ እንዲሁም ሰፊ ተደማጭነት ያላቸው ፕሮግራሞች መብዛት፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ፕሮግራሞች መበራከት ለኢትዮጵያ ወጣቶች የተለየ ቦታ ፈጥረዋል፡፡ የኛ ፕሮግራም ወጣቶች በራሳቸው ቋንቋ ስለእውነታዎች የሚናገሩበትንና ራሳቸውን መግለጽ የሚችሉበትን መሣሪያ የፈጠረ ብራንድ ነው፡፡ ፕሮግራሙ የተፈጠረው እኔ ተቋሙን ከመቀላቀሌ በፊት ነው፡፡ እኔ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ከሁለት ዓመት በፊት ብቀላቀልም፣ የኛ ግን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በአማራ ክልልም ሰፊ ተደማጭነትን አትርፏል፡፡ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን ወጣት ቁጥርና በአገሪቱ የሚታየውን ለውጥ በመገንዘብ ፈጠራዊ ጥበብ በታከለበት ፕሮግራም ላይ ኢንቨስትመንታችንን አውለናል፡፡ እርግጥ ፈተናዎች አይጠፉም፡፡ ሆኖም ዋናው አጀንዳ ግን በዘመናዊዋና እያደገች ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ የወጣቶች ተሳትፎን ማስፋት ነው፡፡ በዚህ አኳኋን ነው የኛ የተወደደውና የተስፋፋው፡፡ የመጀመሪያውን ምዕራፍ በምናገባድድበት ወቅት አብረውን የተጓዙ አጋሮች አግዘውናል፡፡ የኛ ፕሮግራም በሙዚቃ ኃይል፣ በቴሌቪዥን ኃይል፣ እንዲሁም በሬዲዮ ድራማና በቶክሾው ውስጥ በሚተላለፉ ኃያልና በሳል መልዕክቶች አማካይነት ሰዎች የሚሳተፉበት መድረክ ለመሆን በቅቷል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብዙ ተምረንበታል፡፡ በብዙም አድገናል፡፡ የፕሮግራሙ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲያልቅ ግልጽ ሆኖ እንደታየው ከፍተኛ ቁጥር ያለው አድማጭና ተከታታይ ለማፍራት ችሏል፡፡ ፕሮግራሙ ሀብት ነው፡፡ በመሆኑም በተከታዩ ምዕራፍ ኢንቨስት ለማድረግም የሚያበቃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታታይ ማፍራቱ ትልቅ ቁምነገር ነው፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ የኛ ፕሮግራም ብሔራዊ ተደራሽነት እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡ በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ብቻ ወደ አሥር ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ዘንድ መድረስ ችለናል፡፡ ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ አሥር በመቶውን ማዳረስ መቻል ትልቅ ሊባል የሚችል ውጤት ነው፡፡ በመሆኑም ሐሳባችንን የሚጋሩ አጋሮችን እየፈለግን ነው፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ የኛ በርካታ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን እንዲያዳርስ፣ ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው የሚያደምጡትና የሚነጋገሩበት መድረክ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዝርዝር ጉዳዮች ከመነጋገራችን በፊት የኛ ፕሮግራም በአገር ውስጥ ቋንቋዎች የሚሠራጭ እንደመሆኑ መጠን፣ እንቅስቃሴውንና ውጤታማነቱን እንዴት ነው የምትከታተሉት? ፕሮግራሙ የሚያሳድራቸውን ተፅዕኖዎችስ እንዴት ትቃኛላችሁ?

ሚስስ ፋራህ፡- አንድ ትልቅና ጠንካራ ብራንድ የሚለካው በሚፈጥረው ተፅዕኖ ነው፡፡ ለ28 ዓመታት በግሉ ዘርፍ ውስጥ በተለይም በሚዲያ፣ በሞባይልና በቴሌቪዥን ዘርፎች ካካበትኩት ልምድ አኳያ ብዙ መመዘኛዎችን መጥቀስ ቢቻልም በዚህ አግባብ ግን ስለተፈጠረው ግንዛቤ መፍጠር፣ ተሳትፎና ሰዎችን መድረስ ስለሚቻልበት አግባብ ነው የሚለካው፡፡ አገራዊና ወካይ ጥናቶችን እናደርጋለን፡፡ በመስክ ክትትል በማድረግና በጣም ውስብስብ ሥልቶችን በመጠቀም ጭምር እንለካለን፡፡ በመሆኑም አንደኛው የክትትል መስክ ምን ያህል ሰዎች ግንዛቤው አላቸው የሚለው መመዘኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምን ያህል ሰዎች ያዳምጡታል? ምን ያህል ሰዎች ወደ ዳንኪራ ቦታዎች ይሄዳሉ? ምን ያህል ሰዎችስ በትምህርት ቤት ውስጥ ስለፕሮግራሙ ይወያያሉ? የሚሉት ሁሉ ይታያሉ፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ ሲካተት የአድማጭ ተሳትፎ የምንለውን መለኪያ የሚሰጠን ዘዴ ነው፡፡ ይህንን ከለካን በኋላ ተፅዕኖ ጠቋሚ ወደሆኑት ጉዳዮች እናመራለን፡፡ በጥቅሉ አራት ነገሮችን ነው የምንለካው፡፡ የዕውቀት ሽግግር ስለማምጣታችንና የዕውቀት ክፍተትን ስለመሙላታችን ትኩረት እንሰጣለን፡፡ በአስተሳሰብ ላይ ለውጥ ማምጣት መቻል ሁለተኛው መለኪያችን ነው፡፡ በርካታ ገንዘብ ኢንቨስት የምናደርገውም እዚህ ላይ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ሥራ ብቻችንን ሳይሆን፣ ከአጋሮቻችን ጋር ሆነን የምንተገብረው ነው፡፡ እንደ ግሎባል አሊያንስ ፎር ቫክሲንስ ያሉ የልማት አጋሮች አብረውን አሉ፡፡ እነሱ እንዲያውም የራሳቸው ተፅዕኖ መለኪያ መንገድ አላቸው፡፡ ምን ያህል ሰው የኛ ፕሮግራምን ያውቀዋል? ይረዳዋል? በትምህርት ቤትስ ምን ያህል ተሳትፎ ይደረግበታል? የሚሉ መመዘኛዎችን ይከተላሉ፡፡ ስለዚህ መመዘኛው በጣም ጠንካራ ነው፡፡ ነገር ግን በልበ ሙሉነት ለመናገር የሚያስችለን ይህ በሚዲያና በሞባይል የሚደረግ እንቅስቃሴ እያበበ ላለው ትውልድ ትልቅ ቁልፍ መሣሪያ በመሆን የሚያመጣው ለውጥ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የእንግሊዝ መንግሥት ግን ዓለም አቀፍ የዕርዳታና የልማት ተቋም የሆነው ዲኤፍአይዲ ለእናንተ ሲሰጥ የቆየውን የፋይናንስ ድጋፍ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ማንሳቱን አስታውቆ ነበር፡፡ እርስዎ ግሩም ውጤት የተገኘባቸው ሥራዎች መከናወናቸውን ቢገልጹም፣ ዲኤፍአይዲ ግን በዚህ የሚስማማ አይመስልም፡፡ ምንድነው የተፈጠረው? እነሱ በሥራችሁ ማመን ያልቻሉበት ምክንያት ምንድነው?

ሚስስ ፋራህ፡- በግልጽ ማለት የምፈልገው በዲኤፍአይዲ ቦታ ሆኜ መናገር እንደማልችል ነው፡፡ ነገር ግን ፍፁም የሆነውን እውነታ ለማስቀመጥ ደስተኛ ነኝ፡፡ ከጅምሩ ዲኤፍአይዲ ጠንካራ አጋራችን ነበር፡፡ ወደ እኛ ፕሮግራም በመምጣት ከእኛ ጋር ኢንቨስት አድርጓል፡፡ በፈጠራ የታገዘ ሥራ ነው፡፡ እኔ መናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር፣ ዲኤፍአይዲ የራሱን የድጋፍ ዑደት ተከትሎና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች፣ እንዲሁም የአዲሱን አመራር የቅድሚያ ጉዳዮች በመከተል ለውጥ ያደረገባቸው አካሄዶች ታይተዋል፡፡ የአጀንዳ ለውጥም ተደርጓል፡፡ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደተጫወቱ አስበዋል፡፡ እውነትም ተገቢውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ግንኙነታችን ባበቃበት ወቅትም ሁኔታው ራሳችንን ዳግመኛ በመመልከት እንድንፈትሽ አግዞናል፡፡ ከተከሰተው አሉታዊ ክስተት ባሻገር በመጨረሻው የታየው ነገር ቢኖር የኛ በአሁኑ ወቅት ምን ይመስላል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ እስካሁን በምን አኳኋን እንደ መጣና ወደ ተከታዩ ምዕራፍ እንዴት ይጓዛል የሚለውን አሳይቶናል፡፡ በእኛ መመዘኛ መሠረት በልበ ሙሉነት ልንናገር የምንችለው የኛ ጠንካራና ትልቅ እየሆነ ከመምጣቱ በላይ፣ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም በሚዲያ፣ በሞባይልና በአድማጮች ተሳትፎ ላይ መሥራት የሚፈልጉ አጋሮችን እያፈላለግን ነው፡፡ ከዲኤፍአይዲ ጋር መልካም ግንኙነት ነበር፡፡ በጥሩ ሁኔታ ተደምድሟል፡፡

ሪፖርተር፡- ዲኤፍአይዲ ግን እስካሁን ከአምስት ሚሊዮን ፓውንድ በላይ በየኛ ፕሮግራም ላይ ኢንቨስት ማድረጉን፣ ከዚህ በኋላ እንደማይሳተፍ ያስታወቀው በፕሮግራሙ ብዙም እንደላመነበት በመጥቀስ ነው፡፡ እርስዎ በቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን አማካሪ ቦርድ ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በመሆኑም የእንግሊዝ መንግሥት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ ያለውን ፍላጎት ማወቅዎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን በውሳኔያቸው ለየኛ ፕሮግራም የሚሰጡትን ድጋፍ ማቋረጣቸው ግድ ሆኗል፡፡ 

ሚስስ ፋራህ፡- አሁንም መናገር የምፈልገው በዲኤፍአይዲ ቦታ ሆኜ መናገር እንደማልችል ነው፡፡ መናገር የምችለው ስለገርል ኢፌክት እንዲሁም እዚህ በገነባነው ነገር ላይ ስላለን እምነት ነው፡፡ ልነግርህ የምችለው ማንኛውም መመርመር የሚፈልግ ሰው መረጃውን ማግኘት እንደሚችል ነው፡፡ ዲኤፍአይዲ ራሱ ባውጣው የፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ሪፖርት፣ የኛ ፕሮግራምን በ‹‹ኤ›› ደረጃ የመዘነ ውጤት ነበር ያስቀመጠው፡፡ ዕድሎችን ተመልክተው በምን አግባብ እንደሚወሰኑ አላውቅም፡፡ ይህን ማወቅ ሥራዬም አይደለም፡፡ ስለሁኔታው ሲነሳ የተረጋጋ ስሜት ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም ለእንደዚህ ዓይነቱ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው ራሳቸው ያስቀመጡት የውጤት መመዘኛ ስለሆነ ነው፡፡ የሰጡን ውጤት መመዘኛ ስለእኛ የሚናገር ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የኛ የሚመራበት ፍልስፍና ለየት እንደሚል ይታሰባል፡፡ አንዳንዶች ‹‹የኢትዮጵያ ስፓይስ ገርልስ›› በሚል ቅጽል የሚጠሯቸውን አምስት ልጃገረዶች የሚጠቀመው ፕሮግራሙ፣ በልጆቹ አማካይነት በአገሪቱ የሚተላለፈው መልዕክት ምን ያህል ግቡን እንደሚመታና ለተፈላጊው ታዳሚ በአግባቡ ስለመድረሱስ ማረጋገጫችሁ ምንድነው?

ሚስስ ፋራህ፡- በርካታ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን አሉን፡፡ ተመሳሳይ ነገሮችን የሠራንባቸው ገበያዎች አሉን፡፡ በሩዋንዳ ወጣቶችን የሚያሳትፍ የራሳችን ፕሮግራም አለን፡፡ በማላዊም እንደዚያው፡፡ በናይጄሪያም ጠንካራ ሥራ የሚሠራ ፕሮግራም አለን፡፡ በደቡብ አፍሪካ፣ በኢንዶኔዥያና በፊሊፒንስም እየሠራን ነው፡፡ በየኛ አማካይነት እዚህ የምንሠራው ሥራ ከጀርባው ጠንካራ የሆነ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያለው ነው፡፡ ምንም እንኳ አገርኛና እዚህ ባለው ባህል ላይ ሥር የሰደደ ሆኖ ቢመሠረትም፣ የገርል ኢፌክት ዓለም አቀፍ ደጀን ሆኖት የሚንቀሳቀስ ፕሮግራም ነው፡፡ ገርል ኢፌክት የ15 ዓመታት ዕድሜ ያካበተ በዘርፉ በርካታ ተሞክሮ ያባደረ ተቋም ነው፡፡ በዓለም ከሚገኙ 150 አጋሮች ጋር በ90 አገሮች ውስጥ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ከመነሻው ገርል ኢፌክት በናይኪ ፋውንዴሽንና በበርካታ አጋሮቹ አማካይነት የተመሠረተ ነው፡፡ ለየት ያለና ከተመለደው አካሄድ የሚያፈነግጥ አቀራረብን መከተል በመፈለጋቸው የመሠረቱት ተቋም ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ነው ወደ የኛ ፕሮግራም ለመምጣት ድፍረቱን የሰጠን፡፡ ከኢትዮጵያ የሚመሳሰል ፕሮግራም ቀደም ብሎ በሩዋንዳ ተጀምሮ ነበር፡፡ ሴቶችን እንዴት ከተፅዕኖ ማላቀቅ እንደሚቻል፣ አስፈላጊውን መሣሪያ በማቅረብ ድራማ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል፣ ቶክ ሾው በማዘጋጀትና በመሳሰሉት አማካይነት በሩዋንዳ እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ በአምስቱ ልጃገረዶች ላይ ተመሥርቶ የተጠነሰሰው ሐሳብ ፈልቆ ነው ወደ ተግባር የተገባው፡፡ በርካታ ጥናቶችን አካሂደናል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ሰዎች ምን እንደሚፈልጉ በማዳመጥና ከእነሱ በመማር በርካታ ሐሳቦችን ለማግኘት ችለናል፡፡ ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ግን ሴቶች የሚደርስባቸውን ጎጂ የመገለል ተፅዕኖ የሚቋቋሙበትን የጓደኝነት ኃይል በማምጣት የሚያጋጥሟቸውን ወሰኖች ማለፍ የሚችሉባቸውን መንገዶች እንዲያገኙ ማገዝ መቻል ነው፡፡ አንዱ ከአንዱ ይማራል፡፡ አንዱ የሌላውን ታሪክ ይጋራል፡፡ ጓደኝነት በብዙ መልኩ ለመደጋገፍና ለመተጋገዝ ይጠቅማል፡፡ ይህ ነው በጣም ሥር በመስደድ ደጋግሞ ሲነሳ ያስተዋልነው፡፡

እርግጥ ነው በትምህርት በኩል፣ እንዲሁም በድህነት በኩል ሊነሱ የሚገባቸው ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ይሁንና ጓደኝነት ከሁሉም ልቆ የሚታይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ቡድን በሙዚቃ አማካይት ለየት ያለ የኢትዮጵያዊ ለዛ ያለው ነገር መፍጠር ችሏል፡፡ ለምሳሌ አቤት በሚለው ሙዚቃ ውስጥ ያሉትን ስንኞች ስትመለከት የሙዚቃ ኃይል የአፍሪካ ሴቶችን ድምፅ በኢትዮጵያዊ መንገድ የሚያስተጋባና ስደትን የሚቃኝ ሆኖ ታገኘዋህ፡፡ ሙዚቃ እንደፈጠሩ የታወቀ ነው፡፡ እያንዳንዷ ልጃገረድ የምትወክለው ገጸ ባህሪይ በሕዝቡ ዘንድ በደንብ የሚታወቅ ነው፡፡ እያንዳንዷ ልጃገረድ ለሌላው አርዓያ የምትሆንበትና የምትወክለው ሰው አለ፡፡ አንዷ ከተሜ፣ ሌላኛዋ በጣም የገጠር ልጅ ስትሆን፣ አንዷ ደግሞ ዘመናይ በመሆን ጠንካራ ገጸ ባርያትን በመወከል በፈጠሩት ሙዚቃ ጠንካራ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ በሚጫወቱት ድራማ ውስጥ የሚፈጥሩት ገቢር ተመልካቹ ይህ ታሪክ እኔን ነው የሚወክለው፣ ስለእኔ ነው የሚናገሩት እንዲል የሚያደርግ፣ የእኔን ማንነት ነው የሚጫወቱት ብሎ እንደሚያስብ የሚገፋፋ ታሪክ ይከስታሉ፡፡ የሚመረጡት ጉዳዮችም በጣም ጠንካሮች ናቸው፡፡ በጊዜ ሒደት እያጠራን የመጣነው ሐሳብና የሙዚቃው ኃይል ከአዲስ አበባና ከአማራ ክልል ያለፈ ተደማጭነት ለመፍጠር ያስቻለ አቅም ፈጥረዋል፡፡ ሐሳቡ በአመዛኙ ወዳጅነት ወይም ጓደኝነት ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ መተሳሰብንና ወደፊት የሚፈለገው ቦታ ለመድረስ ያለንን መካፈልን የሚገልጽ ይዘት አለው፡፡

ሪፖርተር፡- ልጃገረዶቹን በማሳተፍ የሚተላለፈው መልዕክት እንዴት ነው የሁሉንም ሕይወት የሚነካው? በዚህ አካሄድስ ሁሉንም ሰው ማሳመን ይቻላል ብለው ያምናሉ?

ሚስስ ፋራህ፡- ሁሉም ሰው በዚህ አካሄድ ያምናል ብዬ መናገር አልችልም፡፡ ነገር ግን በርካቶች የሚሳተፉበት ሁኔታ እየታየ ስለመሆኑ መናገር እችላለሁ፡፡ ሁሉ ቦታ ስንሄድ ሁሉም ተመልካች አፀፋውን ወይም ምላሹን ላይሰጠን ይችላል፡፡ ነገር ግን በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ስለመንካቱ ማየት የሚያስችል ኃይል ያለው እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡ ይህ ሐሳብ ተመልካቹን እስካሳተፈ ድረስ አስፈላጊ ነው ማለት ነው፡፡ ያዝናናል፡፡ ትምህርታዊና የመተሳሰብ መንፈስን የሚፈጥር ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ አብዛኞቹን ብራንዶች ስናይ እንዲህ ያለውን ውጤት ለማግኘት የማይፈነቅሉት ነገር አይኖርም፡፡ ሆኖም ሰዎችን ማሳመን የእኔ ሥራ አይደለም፡፡ ይህ የኢትዮጵያውያን ክስተት ነው፡፡ ሰዎች ተቀበሉትም አልተቀበሉትም ክስተቱ ግን እያደገና እየተስፋፋ ነው፡፡ በዚህ ነገር አምናለሁ ብትልም ባትልም እያደገና በርካቶችን እያሳተፈ ነው፡፡ በሌላ መንገድ ብናየው ትኩረታቸው ወደዚህ ነገር የተሳበ አጋሮች የሉም ወይ የሚለውን ነጥብ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየኛ ፕሮግራም ደስተኛ ነው፡፡ ለየት ባለ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ በሴቶች የበረራ ባለሙያዎች በተመራውና ከአዲስ አበባ ባንኮክ በተደረገው በረራ ወቅት የኛ ፕሮግራም ተጋባዥ በመሆን ዝግጅት ማቅረቡ፣ ብራንዱ ሴቶችን ስለማብቃት የሚናገር አቅም ያለው መሆኑ ታምኖበት ነው፡፡ ስለዚህ ፕሮግራሙ ሰዎችን ያሳምናል ወይ ለሚለው አየር መንገዱ ማስተላለፍ ለፈለገው ሐሳብ ተስማሚ ብራንድ ሆኖ ያገኘው ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ በኩባንያህ ምልከታ ነው ብራንድህ የሚፈረጀው፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ጥር የኛን በመጋበዝ ዝግጅቱን እንዲያቀርብ ማድረጉ፣ የእኛ ኢትዮጵያን የሚወክል ብሔራዊ ሀብት ይሁን እንጂ የአፍሪካ ሴቶች ድምፅ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች እንደሚያምኑበት የሚያመላክቱ ጠቋሚዎችን ከፈለግህ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከአፍሪካ ኅብረት፣ እንዲሁም ከዓለም የልማት ድርጅት ከሆነው ከግሎባል አሊያንስ ፎር ቫክሲን ጋር ያለንን ነገር ማየት ነው፡፡ ግሎባል አሊያንስ በየኛ ፕሮግራም ላይ ኢንቨስት የሚያደርገው አንድ ለየት ያለ ነገር መፈጠሩን በማየቱ ነው፡፡ የኛ በወጣቶች መካከል መቀራረብን እየፈጠረ ነው፡፡ እንደማስበው እነዚህ ሰዎች በየኛ አስፈላጊነት ላይ እምነቱ አድሮባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኛ እንደ ሀብት ይታይ ቢባል እንዴት ይመዝኑታል? በገንዘብ ቢተመን ምን ያህል ነው ዋጋው? እናንተስ በየዓመቱ ምን ያህል ወጪ ታደርጉታላችሁ?

ሚስስ ፋራህ፡- በማስተዳድራቸው በርካታ ኩባንያዎች ውስጥ አንድ ምርት ቢኖር ያ ምርት ትርፍ ማስገኘት ይኖርበታል፡፡ ከሚያገኙት ትርፍ ባሻገር ግን ማኅበራዊ ጉዳዮችንም የሚያካትቱ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ይህ ዓላማቸው ከትርፍና ከዕድገት ባሻገር የሚታይ ነው፡፡ ለማኅበራዊ አጀንዳ ማዋል የሚገባህ ነገር ይኖራል፡፡ እዚህ ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ዓላማ ቢኖረንም፣ የምንከተለው ግን የግሉ ዘርፍ የሚመራበትን ዓይነት ዲሲፕሊን ነው፡፡ የሚዲያ፣ የመረጃ፣ የቴክኖሎጂና የብራንድ ዲሲፕሊኖችን እንከተላለን፡፡ የኛን እንደ ሀብት ወስደን በገንዘብ እንተምነው ብንል በርካታ ነጥቦች ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ከንግድ አኳያ በመነሳት ለመመልከት ከሞከርክ፣ ለሴቶችና ለወንዶች ልጆች ድምፅ መሆኑ የሚያስገኘውን ጥቅም ኢንቨስትመንት ከሚያስገኘው ጥቅም አኳያ በምን መመዘኛ ነው የምትለካው? ከዚህ አኳያ በምን አግባብ ነው በሀብትነት የምትመዝነው የሚለው አስፈላጊ ነው ይመስለኛል፡፡ እንደሚገባኝ የኛ ዋጋ አይወጣለትም፡፡ የኛ በኢትዮጵያ ወጣቶችን የሚወክል ትልቅ የሐሳብ ብራንድ ነው፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያን አሥር በመቶ ሕዝብ ማዳረስ ችለናል፡፡ ወደ 50 በመቶ ማደግ ብንችል የሚፈጠረውን ማሰብ ትችላለህ፡፡ ያኔ የምትመዝንበት መንገድ የተለየ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በገንዘብ ደረጃ አይለካም እያሉ ነው ማለት ነው?

ሚስስ ፋራህ፡- ገንዘብ ከሚያስገኘው ይልቅ ተፅዕኖ የሚያስገኘው ውጤት ላይ የሚመሠረት ነው፡፡ በገንዘብ ለማስቀመጥ በጣም ውስብስብ ሞዴል መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው ቢቀር ምን ያህል ወጪ እንደሚወጣበት መናገር ይችላሉ?

ሚስስ ፋራህ፡- አንዳንዱ ወጪ በጥሬ ገንዘብ አንዳንዱም በዓይነት የሚወጣ ነው፡፡ አንዳንድ የፋይናንስ ምንጮችን ከአጋሮቻችን በምናገኘው አስተዋጽኦ ስለምንሸፍን፣ በዚህ ወቅት በገንዘብ በኩል ይህን ያህል ወጪ እናወጣለን ብዬ ማስቀመጥ ይቸግረኛል፡፡ ምን ያህሉን በጥሬ ገንዘብ ምን ያህሉን በስፖንሰርሺፕ እንደምናገኝ መለየት ያስፈልገናል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ብትጠይቀኝ ግን በአግባቡ የተደራጀ ምላሽ ልሰጥህ እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ልጆቹ አሁን አድገዋል፡፡ የሁሉም ዕድሜ ወደ 20ዎቹ መጀመሪያና አጋማሹ ላይ ደርሷል፡፡ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ምን ይሆናል?

ሚስስ ፋራህ፡- አስደሳች የሆነ ነገር አዘጋጅተናል፡፡ ምን እንደሆነ ግን አሁን አልነገርህም፡፡ አስደሳች የለውጥ ጉዞ እየመጣ ነው፡፡ ለሴቶቹ ያዘጋጀናቸው ነገሮች አጓጊ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለኝም፡፡ በንግድ ዓይን ካየነው እያንዳንዱ ብራንድ በራሱ የለውጥ ሒደት ውስጥ ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡  የራሱን አዲስ ገጽታ ማግኘት አለበት፡፡ ላለፉት ስድስት ወራት ይህንን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ሊያስገርሟችሁ የሚችሉ አዳዲስ ነገሮችን እያዘጋጀን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የእንግሊዝ መንግሥት የኛ ፕሮግራምን እንዴት ይመለከቱታል?

ሚስስ ፋራህ፡- በአንዳንድ ጽሑፎችና ዘገባዎች ላይ ተከታትለህ እንደሆነ ትልቅ ስም ያላቸው የእንግሊዝ ባለሥልጣናት ስለ የኛ ብዙ ብለዋል፡፡ ስማቸውን መጥቀስ አልፈልግም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ ገጣሚውና ደራሲው ለምን ሲሳይ አንዱ ነው፡፡

ሚስስ ፋራህ፡- አዎን፡፡ ግን ከፍተኛ ቦታ ያላቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፓርላማ አባላት ጭምር ስለየኛ የተናገሯቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የተናገሯቸውን መመልከት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እንዴት ይታያል ለሚለው ከእኔ ይልቅ እዚህ የኛን የሚያንቀሳቅሱ ሰዎች ናቸው የሚያውቁት፡፡ ከመንግሥት አካላት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም፡፡ ባለፈው የመጣሁ ጊዜ ከቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ጋር የመገናኘት ዕድል ነበረኝ፡፡ በጣም ጥሩ ሰው ናቸው፡፡ ሲያከናውኑ የነበሩትንም ሥራ አደንቃለሁ፡፡ ሆኖም ከመንግሥት ጋር የሥራ ግንኙነት መፍጠር የእኔ ሚና አይለደለም፡፡ በኢትዮጵያ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ሰው ናቸው ይበልጥ ምላሽ መስጠት የሚችሉት፡፡ እርግጥ ነው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በትምርት ሚኒስቴርና በሌሎችም መሥሪያ ቤቶች በኩል ተሳትፎ እንድናደርግና የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት የተጠየቅንባቸው መስኮች ይኖራሉ፡፡ ዝርዝሩን ግን አላውቅም፡፡ በዚህ ጉብኝት ወቅት እንኳ ከመንግሥት ወገን ማንንም አላገኘሁም፡፡ ምናልባት ከሚዲያም ቢሆን ከሪፖርተር ጋር ብቻ መነጋገሬ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ጊዜ ከነበረዎ ተሳትፎ አኳያ የኛ ዓይነት ፕሮግራም በመንግሥት ዕውቅና እንዲያገኝ ማድረግዎን እገምታለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ በአዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ መንበረ ሥልጣን ወቅት የእንግሊዝ መንግሥት ዳግመኛ ድጋፍ መስጠት እንዲጀምር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይኖር ይሆን?

ሚስስ ፋራህ፡- እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ፡፡ የገርል ኢፌክት ሥራ አስፈጻሚ ከመሆኔ በፊት ነበር በዴቪድ ካሜሮን ካቢኔ ውስጥ የቢዝነስ ዘርፍ አማካሪ ቦርድ አባል የነበርኩት፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ መንግሥት ውስጥ ተሳትፎ የለኝም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሯ የራሳቸውን ሰዎች መርጠው ሰይመዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የማደርገው ግንኙት ወይም ምክክር የለም፡፡ ይህም ሲባል ግን ሰዎች የሉኝም፣ በቴሬሳ ሜይ ካቢኔ ውስጥ ጓደኞች የሉኝም ማለት አይደለም፡፡ ሐሳብ እንዲሰጡኝ በምፈልግበት ወቅት የማማክራቸው ሰዎች አይጠፉም፡፡ ቀድሞም ቢሆን ግን የነበረኝ ግንኙነት በፖለቲካው መስክ ሳይሆን፣ በቢዝነስ መስክ ላይ ያተኮረ ግንኙነት መሆኑን መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቢዝነስ የነበራቸው አማካሪ ቦርድ ከኤሮኖቲካል፣ ከሞተር ኢንዱስትሪ፣ ከችርቻሮ ንግድ ሥራ፣ ከኪነ ጥበባት ኢንዱስትሪዎች የተውጣጡ ተወካዮችን ያሳትፉ ነበር፡፡ እኔም የሥነ ጥበባትና የኪነ ጥበባት ዘርፉን በመወከል ነበር እሳተፍ የነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- ዲኤፍአይዲን ዳግመኛ ወደ ድጋፍ ሰጪነቱ ማምጣት ይፈልጋሉ?

ሚስስ ፋራህ፡- ስለዚህ ጉዳይ ጊዜው ሲደርስ ወደ ፊት በራሱ ጊዜ ራሱ ቢናገር ይሻላል፡፡