Skip to main content
x
የእንግሊዝ ኩባንያ ለማዳበሪያና ባዮጋዝ ማምረቻ የሚውሉት የፕላስቲክ ምርቶችን ይፋ አደረገ

የእንግሊዝ ኩባንያ ለማዳበሪያና ባዮጋዝ ማምረቻ የሚውሉት የፕላስቲክ ምርቶችን ይፋ አደረገ

ቢዩታል ፕሮዳክስት ግሩፕ የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ፣ ከእንስሳትና ከሰው ብሎም ከሚጣሉ ቆሻሻዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያና ባዮጋዝ ማምረት የሚያስችል ምርትን ጨምሮ እስከ 1.6 ሚሊዮን ሊትር ውኃ ማጠራቀም የሚችሉ የፕላስቲክ ታንከሮችን ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

እንደ አኳታብስ ያሉትን የውኃ ማጣሪያ ምርቶች በማስመጣት ለአገር ውስጥ የሚያቀርበው ሲትረስ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኩባንያ ጋር በመሆን ምርቶቹን ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ የጀመረው ቢዩታል ግሩፕ፣ ‹‹ፍሌክሲጄስተር ቪ80›› የሚል መጠሪያ የሰጠውን ምርት በማምረት ለገበያ ማቅረቡን ጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት ያስታወቁት የኩባንያው የሽያጭ ዳይሬክተር ክሬግ ቦል ናቸው፡፡

እንደ ሚስተር ክሬግ ማብራሪያ በኢትዮጵያ ሰፊ ተጠቃሚ እንዲያገኝ የሚፈልጉት ይህ ምርት፣ ከሽንት ቤት የሚወጣ ፍሳሽን በማጠራቀም ወደ ባዮ ማዳበሪያነት መቀየር የሚችልበት ማብላያ ያለው ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም የማብሰያ ጋዝ ለማምረት የሚያስችል ነው፡፡ ከሽንት ቤት ፍሳሽ በተጨማሪም የእንስሳት አዛባ፣ የምግብ ትርፍራፊዎችን፣ የቤትና የአካባቢ ቆሻሻን በማቀነባበር ማዳበሪያና ባዮጋዝ ማምረት ይችላል ያሉት ሚስተር ቦል፣ ምርቱ ሲቀነባበር ምንም ዓይነት ሽታም ሆነ የጋዝ ልቀት እንዳይኖረው ተደርጎ እንደሚመረት አብራርተዋል፡፡

ለሳምንታት ማብላላት የሚጠይቀው ይህ ቴክኖሎጂ፣ ከ10 ሺሕ እስከ 80 ሺሕ ሊትር ማዳበሪያም ሆነ ባዮጋዝ የማከማቸት አቅም ባላቸው ከረጢቶች መከማቸት የሚችል ነው፡፡ እንደ ባለሙያው ከሆነም ከ40 እስከ 300 ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉና እስከ 60 ቀናት ውስጥ ማዳበሪያና ባዮጋዝ ማምረት የሚያስችሉ ምርቶች በኩባንያው ይመረታሉ፡፡ የምርቱ ዋና ጠቀሜታ የአካባቢን ንፅህና ወይም ሐይጂን ለማስጠበቅ የሚያግዝ እንደመሆኑ፣ በአብዛኛው በገጠራማና መኖሪያ አካባቢዎች፣ በጊዜያዊ መኖሪያ ካምፖች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በእርሻዎችና በሌሎችም አካባቢዎች በቀላሉ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ነው፡፡

በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የኤልሻዳይ ሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ከከብቶች የሚመነጨውን አዛባ ወደ ማዳበሪያነት ለመቀየር ጥቅም ላይ መዋል እንደጀመረ ሚስተር ቦል ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ግዙፍና በቀላሉ ከቦታ ቦታ የሚጓጓዙ፣ የሚነቃቀሉና የሚገጣጠሙ የፕላስቲክ ታንከሮችን በማምረት የሚታወቀው ቢዩታል ግሩፕ፣ O2Tanker የሚል ስያሜ የሰጠውን ይህንኑ ምርት በኢትዮጵያ ማቅረብ እንደጀመረም ታውቋል፡፡ በአፋር ክልል 60 ሺሕ ሊትር ውኃ ማጠራቀም የሚችሉ ታንከሮችን ጨምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች በአያት አካባቢ ለሚያስገነቡት መኖሪያ ሠፈር የመጠጥ ውኃ ማጠራቀሚያነት የሚያገለግሉና 600 ሺሕ ሊትር በአንድ ጊዜ ማከማቸት የሚችሉ ታንከሮችን አቅርቧል፡፡

እስካሁን ከተለመዱት የኮንክሪት ታንከሮች ይልቅ ውኃ ሳይበከልና ቃናው ሳይቀየር ለረዥም ጊዜ ማቆየት እንደሚችሉ የተነገረላቸው እነዚህ ታንከሮች፣ በዋጋ ደረጃም ከ50 እስከ 60 በመቶ ቅናሽ እንደሚታይባቸው የገለጹት የሲትረስ ኢንተርናሽናል ሥራ አስኪያጅ አቶ ምናሴ ክፍሌ ናቸው፡፡ ሆኖም ቀረጥ የሚጣልባቸው በመሆናቸው ዋጋቸው ጭማሪ እንደሚታይበት አልሸሸጉም፡፡ ከቀረጥ ነፃ የሚያስገቡ ድርጅቶች ከኮንክሪት ታንከሮች አኳያ ያለውን የዋጋ ልዩነት ብቻም ሳይሆን ለ25 ዓመታት ያለምንም የጥገና ወጪ የሚገለገሉበት ቴክኖሎጂ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

እንደ ድርቅና ረሃብ ባሉ አደጋዎች ወቅት ለሚያስፈልጉ ድንገተኛ የነፍስ አድን ሥራዎች ምርቶችን ለዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ሲያቀርብ የኖረው ቢውታል ግሩፕ በተለይ እንደ ኦክስፋም ዩኬ ላሉት ድርጅቶች ምርቶችን በማቅረብ ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀ ተሞክሮ እንዳለው ታውቋል፡፡ ድርቅ በተደጋጋሚ በሚከሰትባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የቢውታል ምርቶች ሲቀርቡ መቆየታቸውን ሚስተር ቦል አብራርተዋል፡፡