Skip to main content
x
በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ተገለጸ
የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ

በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ተገለጸ

በበልግ አብቃይ የአገሪቱ ክፍሎች የዝናብ እጥረት ሊያጋጥም ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ቀጣዩን የበልግ ወቅት አስመልክቶ ቅዳሜ ጥር 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ይፋ እንዳደረገው፣ ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ የውኃ እጥረትና በእንስሳት ላይ አደጋ ሊያስከትል የሚችል የአየር ንብረት ለውጥ ስለሚኖር፣ ከወዲሁ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት እንዲደረግም አመልክቷል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በመጪው የበልግ ወቅት አካባቢዎቹ የአየር ፀባይን ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲንቀሳቀሱ፣ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ያለባቸው አካላትም ይህንኑ የአየር ፀባይ አሉታዊ ተፅዕኖን ለመቋቋም መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው የበልግ ወቅትን አስመልክቶ በሰጠው በትንበያ መሠረት የበልግ ዝናብ ዋነኛ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች፣ በሰሜን ምሥራቅና በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ሊኖር ይችላል፡፡ በአንፃሩ የምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ግን በአብዛኛው መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ አቶ ፈጠነ ገልጸዋል፡፡

በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ ክፍሎች የዝናብ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል የተናገሩት አቶ ፈጠነ፣ ኅብረተሰቡ በመጪው በልግ ወቅት የሚጠበቀውን የአየር ፀባይ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በዚህ ወቅት የሚካሄደውን የግብርና ሥራና ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክንውኖች ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር በአግባቡ እንዲያከናውን አሳስበዋል፡፡

በተለይ ሁለተኛው የዝናብ ወቅታቸው የሆኑት የደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በአብዛኛው ከመደበኛው በታች ዝናብ እንደሚኖራቸው ስለሚጠበቅ፣ የሚስተዋለውን ተለዋዋጭ የአየር ፀባይ ግምት ውስጥ በማስገባት ቅድመ ዝግጅት ሊደረግ ይገባል ተብሏል፡፡  በተለይም አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ የሚገኘውን እርጥበት በአግባቡ እንዲጠቀምበት፣ በመጪው በልግ ወቅት ከእርጥበት ማነስ ጋር ተያይዞ በሚያካሂደው የግብርና፣ በሌሎች የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ክንውኖች ላይ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማስወገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ኤጀንሲው በመግለጫው አሳስቧል፡፡

የዘንድሮው የበጋ ወቅት ከመግባቱ በፊት የተሰጠው የበጋ የአየር ፀባይ ትንበያ በአብዛኛው ከተስተዋለው የአየር ፀባይ ጋር የተጣጣመ እንደነበር ከኤጀንሲው የትንበያ መረጃ መረዳት ተችሏል፡፡

ኤጀንሲው በሁሉም ክልሎች ካሉ የሚቲዎሮሎጂ ጽሕፈት ቤቶች ጋር ያደረገው የምክክር መድረክ፣ ወቅታዊና የመጪውን ጊዜ የአየር ትንበያዎችን በዝርዝር ያቀረበበትና መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ አማራጮችን የጠቆመበት ነው፡፡ ይህንኑ ትንበያ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርሳቸው በማድረግ፣ ትንበያውን መሠረት ያደረገ ዕርምጃ እንዲወሰድ ይደረጋል ተብሏል፡፡