Skip to main content
x
የዓለም አቀፍ ፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ኢትዮጵያን አደነቀ
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተስፋዬ ይገዙ ከዋዳ ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ሮበርት ኮህለር ጋር

የዓለም አቀፍ ፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ኢትዮጵያን አደነቀ

  • አሁንም ከአምስቱ የችግሩ ተጠቂ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ትገኛለች

የዓለም አቀፍ ፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዋዳ) ኢትዮጵያ በዘርፉ እያደረገች ያለውን ቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም በዚሁ እያስመዘገበች ያለውን ውጤት አደነቀ፡፡ አገሪቱ ለዋዳ ፀረ አበረታች ቅመሞች ዘመቻና ለሦስትዮሽ ፕሮግራሞች ትክክለኛ ማሳያ መሆኗን የዋዳ ምክትል ዳይሬክተር ሮበርት ኮህለር ገልጸዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ፣ ኢትዮጵያ በተለይ በአትሌቲክሱ ዓለም ላይ ያላትን የበላይነት ግምት ውስጥ በማስገባት አበረታች ቅመኞች በይበልጥ ይመለከታቸዋል በሚል ለይቶ ካስቀመጣቸው አምስት አገሮች አንዷ አድርጎ ሲመለከታት ቆይቷል፡፡ በዚሁ መነሻነት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ችግሩን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ፣ ብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት በማቋቋም እንቅስቃሴ ስታደርግ መቆየቷ አይዘነጋም፡፡

ባለፈው እሑድ ጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. የዋዳ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአፍሪካ ቀጣናዊ ቢሮ ዳይሬክተር እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ ፀረ አበረታች ቅመሞች ተቋም የሥራ ኃላፊዎች፣ በአዲስ አበባ ጁፒተር ሆቴል ኢትዮጵያ በጉዳዩ እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴና የአፈጻጸሟን ሒደት አስመልክቶ ግምገማዊ ውይይት አድርገዋል፡፡

ከውይይቱ በኋላም በሦስቱ አካላት ማለትም በኢትዮጵያ፣ በዓለም አቀፍና በአፍሪካ ቀጣናዊ ተቋማት መካከል የሦስትዮሽ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ስምምነት ከተፈራረሙበት እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ ያለውን የትብብር ማዕቀፍ በጋራ በሰጡት መግለጫ አድንቀዋል፡፡

አገሪቱ በዘርፉ እያደረገች ያለውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ለዚሁ ተብሎ ያቋቋመችውን ብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈትን ጨምሮ በተደረገው ግምገማ፣ የዓለም አቀፍም ሆነ የአህጉራዊው ተቋማት ኃላፊዎች ኢትዮጵያ በማሳያነት ከሚጠቀሱ አገሮች አንዷ ልትሆን እንደሚገባ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ አሁንም ዋዳ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በጥርጣሬ ከፈረጃቸው አምስት አገሮች ዝርዝር እንደተካተተች ነው፡፡

እንደ ዋዳ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከሆነ ግን፣ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ጽሕፈት ቤቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ፣ የአሠራር ሥርዓቶች በመዘርጋት ረገድ እንዲሁም የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት፣ በየደረጃው ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ የተለያዩ የትምህርት፣ የሥልጠናና የሕዝብ ንቅናቄ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት እያደረገች ያለውን ጥረት ሳያደንቁ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት፣ ዋዳ ማስጠንቀቂያ ከሰጠበት ማግሥት ጀምሮ የስፖርተኞችን ደምና ሽንት ምርመራ በማካሄድ እንዲሁም የፀረ አበረታች ቅመሞች ሕግን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሯ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ የዋዳ ኃላፊዎች አድንቀዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በስፖርት አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ከጀማሪነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ፈጻሚነት ተሸጋግራለች፡፡ በቀጣይም ይህንኑ እንቅስቃሴዋን አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል፡፡ ለዚሁ ከመንግሥት በጀት ከመመደብ ጀምሮ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፤›› በማለት በአገሪቱ ያለውን ነገር መግለጻቸው ታውቋል፡፡

በግምገማው የታደሙት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ንፁህ ስፖርትና ስፖርተኞችን ትፈልጋለች፡፡ ይህንኑ አጠናክሮ ለመቀጠል የመንግሥት ቁርጠኝነት ይቀጥላል፤›› ብለው፣ መገናኛ ብዙኃኑን ጨምሮ በአገሪቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ከብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት ጋር እጅና ጓንት በመሆን በፀረ አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ውስጥ በተለያየ መልኩ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጠባቡን ክፍል ይዞ የቆየው ብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ስታዲየም አቅራቢያ ይሓ ሲቲ ሴተር ሕንፃ ፊት ለፊት ወደ ሚገኘው ሕንፃ እንዲዛወር ተደርጓል፡፡ የዋዳ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች አዲሱን ጽሕፈት ቤት መጎብኘታቸው ታውቋል፡፡