Skip to main content
x

እየቀነሰ የመጣው የገቢ ንግድ

በአገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድ መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት አሁንም እንደቀጠለ ቢሆንም፣ አገሪቱ ለገቢ ንግድ የምታውለው ወጪ ቅናሽ እያሳየ መሆኑ ተመለከተ፡፡ የአገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድ ዓመታዊ ተከታታይ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በተለይ ባለፉት አሥር ዓመታት የገቢ ንግዱ በአማካይ ከ20 በመቶ እያደገ ቢሆንም፣ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ አገሪቱ ለገቢ ንግድ የምታውለው የውጭ ምንዛሪ በተወሰነ ደረጃ እየቀነሰ ነው፡፡ ሰሞኑን ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የ2009 ዓመታዊ ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰውም፣ በ2009 በጀት ዓመት ለወጪ ንግድ የወጣው ወጪ ከቀደመው በ5.5 በመቶ ቀንሷል፡፡ 

ይህም በጀት ዓመቱ የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛን ጉድለቱ መጠነኛ መሻሻል እንዲያሳይ ማድረጉን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡  

እንደ ሪፖርቱ በ2009 በጀት ዓመት 12.9 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ሚዛን ጉድለት ተመዝግቧል፡፡ ይህ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ6.9 ከመቶ በመቀነስ መሻሻል ያሳየ ሲሆን፣ ይህም ሊሆን የቻለው ለገቢ ንግድ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ መጠነኛ ቅናሽ በማሳየቱ ነው፡፡ በሌላም በኩል በአገሪቱ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ በተመሳሳይ መጠነኛ ዕድገት ሊያሳይ መቻሉ ለንግድ ሚዛን ጉድለቱ አነስተኛ መሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጉን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በተከታታይ የወጡት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለገቢ ንግድ ወጪ መጠነኛ ቅናሽ ከታየባቸው ምክንያቶች አንዱ የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ መቀነሱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2009 ሪፖርት እንደጠቀሰው ደግሞ፣ ወደ አገር የሚገባው የገቢ ምርት ወጪ 15.8 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡ ይህ ወጪ ከቀዳሚ ዓመት ጋር ሲነፃፀር 5.5 ከመቶ ቅናሽ ሊያሳይ የቻለው የካፒታል፣ የጥሬ ዕቃዎች ገቢ ምርት፣ ከፊል የተጠናቀቁ ምርቶችና የፍጆታ ሸቀጦች ምርቶች ዋጋ ከመቀነሳቸውና የሚገባውም ምርት ከመቀነሱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የነዳጅ ምርት ወጪ መቀነስ ጎልቶ የታየው ግን በ2007 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በ2009 ዓ.ም. የነዳጅ ወጪ በ11 በመቶ ቢጨምርም አጠቃላይ የገቢ ንግድ ወጪው ግን 15.8 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡

በ2007 ዓ.ም. አገሪቱ ለነዳጅ ያወጣችው ወጪ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህ ወጪ ከ2006 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር በ20.7 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ነበር፡፡ ከአጠቃላይ የገቢ ንግድ ወጪ 2006 ዓ.ም. ነዳጅ ከነበረበት 18.8 በመቶ ድርሻ በ2007 ዓ.ም. ወደ 12.4 በመቶ አውርዶታል፡፡

ከ2007 ዓ.ም. በኋላም ቢሆን ለነዳጅ የወጣው ወጪ እየቀነሰ መጥቶ በ2008 ዓ.ም. ለነዳጅ ግዥ የወጣው ወጪ 1.33 ቢሊዮን ዶላር ሆኖ፣ ከጠቅላላው የገቢ ንግድ ወጪ ውስጥ የነዳጅ ድርሻ ስምንት በመቶ ብቻ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ ይህ ወጪ ወደ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሎ፣ ከ2008 ዓ.ም. የበለጠ ወጪ አስወጥቷል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከሌሎች የገቢ ንግድ ምርቶች ቅናሽ ጋር ተያይዞ 2009 ዓ.ም. የአገሪቱን የገቢ ንግድ ወጪ ከመቼው ጊዜ ያነሰ ዕድገት የታየበት ሆኗል፡፡

ይህ አኃዝ ከአገሪቱ የገቢ ንግድ ተከታታይ ዓመታት በዚህን ያህል ደረጃ የቀነሰበት ዓመት ጊዜ እንዳልነበር ያሳየ ነው፡፡ እንደ መረጃው በ2008 ዓ.ም. የአገሪቱ ጠቅላላ የገቢ ንግድ ወጪ 16.7 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ የ2009 ዓ.ም. የገቢ ንግድ ወጪ ለመቀነሱ የተጠቀሰው ምክንያት ደግሞ ከሁሉም በላይ የሸመታ ፍጆታ ሸቀጦች 4.9 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ይህ ወጪ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ7.7 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ነው፡፡  

በተለይ አላቂ ዕቃዎች ይወጣ የነበረው ክፍያ በ13.7 በመቶ ቀንሷል፡፡ በተመሳሳይ በከፊል ለተጠናቀቁ ሸቀጦች የወጣው ወጪ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ9.5 በመቶ መቀነሱም ለአጠቃላይ የገቢ ዕቃዎች መቀነስ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

በአንፃሩ በ2009 ዓ.ም. በተለይ ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት ሆኖ የተዘመገበው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ግብዓቶች ናቸው፡፡ ለዚህ ምርት የወጣው ወጪ 11.4 በመቶ ጨምሯል፡፡

የካፒታል ሸቀጦች የገቢ ምርት 11.7 በመቶ እንደቀነሰም ይኸው መረጃ ያሳያል፡፡ ለዚህም የካፒታል ሸቀጦች ገቢ ንግድ ለመቀነሱ ዋናው ምክንያት የሚገቡ ምርቶች እንዲቀንሱ በመደረጉ ነው፡፡

እንደ 2009 ዓ.ም. ሁሉ በተያዘው በጀት ዓመት የገቢ ንግዱ ወጪ አሁንም ሊቀንስ ይችላል የሚሉ ጠቋሚ ክስተቶች አሉ፡፡ ይህም የገቢ ንግድ ወጪው በ2010 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ቅናሽ እንደሚኖረው የሚገመተው፣ በተለይ ከጥቅምት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው የብር ምንዛሪ ለውጥ ጋር ተያይዞ ተግባራዊ የተደረጉ አሠራሮች ናቸው፡፡

ይህ የገቢ ንግድ ወጪ መቀነስ በወጪና ገቢ ንግድ መካከል ላለው ሰፊ ልዩነት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ልዩነት የሚያመጣ መሆኑ ነው፡፡ በ2009 በጀት ዓመት የወጪና ገቢ ንግድ ጉድለት የተወሰነ መሻሻል የታየው የገቢ ንግድ ወጪው በመቀነሱ ብቻ ሳይሆን መጠነኛ የወጪ ንግድ ዕድገት በመኖሩ ነው፡፡

እንደ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት አገሪቱ ኤሌክትሪክን ጨምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ ውጭ የተላከው የወጪ ንግድ በ1.4 ከመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ምርቶች ውስጥ ከፍተኛ ገቢ ዕድገት የተመዘገበው ከቡና 22.2 በመቶ፣ ከቅባት እህሎች 20.5 በመቶ፣ ከጫት አራት በመቶ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ 4.5 በመቶ፣ ከሥጋና ከሥጋ ውጤቶች 2.3 በመቶ፣ ከኤሌክትሪክ 133 ከመቶ  የገቢ ዕድገት በማሳየታቸው ነው፡፡

ከቡና የወጪ ንግድ ገቢ ዕድገት ሊመዘገብ የቻለው፣ በዓለም አቀፍ የቡና ገበያ ውስጥ የዋጋ ዕድገት 7.5 ከመቶ ጭማሪ በማሳየቱና ወደ ውጭ የተላከው የቡናው ምርት መጠን የ13.6 በመቶ በመጨመሩ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከጠቅላላው ኤክስፖርት ውስጥ፣ የቡና ምርት ያለው ድርሻ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 25.2 በመቶ ወደ 30.4 በመቶ ሊያድግ ችሏል፡፡ የዘይት እህሎች ኤክስፖርት 26.4 በመቶ ቅናሽ በማሳየቱ የተገኘው ገቢ 351 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ዋጋው በ3.7 በመቶና የተላከው ምርት መጠን በ23.6 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡

በዚህም ምክንያት የቅባት እህሎች በኤክስፖርት ገቢ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ወደ 12.3 በመቶ ሊወርድ ችሏል፡፡ በሌላ በኩል ከወርቅ ኤክስፖርት 208.8 ሚሊዮን ዶላር ቢገኝም፣ ገቢው ከቀዳሚው ጋር ሲነፃፀር በ28.2 በመቶ ሊቀንስ ችሏል፡፡

ይህም ሊሆን የቻለው ወደ ውጭ የተላከው የወርቅ መጠን በ30.4 በመቶ በመቀነሱ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወርቅ ዋጋው በ3.2 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ቢሆንም፣ የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ግን ሊጨምር አልቻለም፡፡ በመሆኑም ወርቅ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ውስጥ ያለው ድርሻ 7.2 በመቶ ብቻ እንዲሆን ተገዷል፡፡

በብሔራዊ ባንክ ሪፖርት መሠረት፣ በሪፖርት ዓመቱ ከጫት ኤክስፖርት የተገኘው ገቢ በአራት በመቶ ሊጨምር ችሏል፡፡ የጫት ገቢው ሊጨምር የቻለው ወደ ውጭ የተላከው የጫት ምርት መጠን በ3.9 ከመቶ የጨመረ በመሆኑ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ የነበረው ዋጋ ቅናሽ ያሳየው በ0.1 በመቶ ብቻ በመሆኑ ከጫት ለተገኘው ገቢ ድርሻው ከፍ ሊል ችሏል፡፡ በዚህም የተነሳ የጫት ምርት የወጪ ንግድ ገቢ ከጠቅላላው ያለው ድርሻ 9.4 በመቶ ሆኗል፡፡ 

በሌላም በኩል ከቁም ከብቶች የተገኘውም ገቢ በ54.2 በመቶ ሊቀንስ እንደቻለ የማዕከላዊው ባንክ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የተቀመጠው፣ ወደ ውጭ የተላከው የቁም ከብት መጠን በ53.6 በመቶ መቀነሱ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው ቀንሶ የነበረው በ1.3 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ከቁም ከብቶች የወጪ ንግድ ድርሻ በፊት ከነበረበት 5.2 በመቶ ወደ 2.3 በመቶ ሊወርድ ችሏል፡፡

ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኤክስፖርት የተገኘው ገቢ በ1.1 በመቶ ሊቀንስ የቻለው፣ የኤክስፖርት መጠኑ በ1.6 በመቶ በመቀነሱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከኤሌክትሪክ ኤክስፖርት የምታገኘው ገቢ ዕድገት እያሳየ እንደመጣ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በ2009 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገሮች የላከችው የኤሌክትሪክ ኤክስፖርት መጠን በ133 በመቶ ሊያድግ እንደቻለ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ይህም ዕድገት ሊገኝ የቻለው የተላከው የኤሌክትሪክ መጠን በ155.3 በመቶ በመጨሩና ዋጋው በ8.8 በመቶ ሊያድግ በመቻሉ ነው፡፡ በዚህ ዕድገት ምክንያት ኤሌክትሪክ ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ገቢ ከ1.4 በመቶ ወደ 2.5 በመቶ ሊያድግ ችሏል፡፡

በ2009 ዓ.ም. የአገሪቱ ምርቶች ዋነኛ መዳረሻ ከሆኑት አካባቢዎች እስያ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዟል፡፡ አውሮፓና አሜሪካም ተጠቃሽ መዳረሻዎ ቢሆኑም፣ 37.7 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ምርት መዳረሻ እስያ ነው፤ ከዚህም ውስጥ ቻይና 20.7 በመቶ ድርሻ ሲኖራት ሳዑዲ ዓረቢያ 17.9 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ በመቀጠል የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች 10.9 በመቶ፣ ጃፓን ዘጠኝ በመቶና እስራኤል ስድስት በመቶ ይደርሳቸዋል፡፡