Skip to main content
x

ነሲባዊነት የነገሠባቸው በርትዕ የሚወሰኑ የጉዳት ካሳዎች

በውብሸት ሙላት

ውልን መሠረት ያላደረጉ የፍትሐ ብሔር ጉዳቶች ሲያጋጥሙ የካሳ አከፋፈሉን ሁኔታ የሚወሰነው በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2090 እና ተከታዮቹ አማካይነት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት ካሳ ለማግኘት ጉዳት መኖር አለበት፡፡ ጉዳቱ በእርግጥም የደረሰ ወይም ወደፊት የሚደርስ ሊሆን ይችላል፡፡ ጉዳቱ የሚያስከትለው ኪሳራ ሊኖር ይገባል፡፡ ኪሳራው አንድም ገንዘብን  አንድም ሞራልን (ህሊናን) የሚነካ ሊሆን ይችላል፡፡

ጉዳቱ የሚደርሰው ወደፊት በሚሆንበት ጊዜ ካሳውን በእርግጠኝነት መወሰን፣ መቁረጥ፣ ማስላት አዳጋች መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ የሆነው ሆኖ የገንዘብ ጉዳት ሲኖር ደግሞ የተጎጅውን ሀብትና ገንዘብ ማራቆቱ የማይቀር ነው፡፡ ተጎጅው በሚራቆትበት ጊዜ ጉዳት አድራሹ (አራቋቹ) ባራቆተው ልክ እንዲክስ ሕግ ያስገድዳል፡፡ በመሆኑም የደረሰው ጉዳት ተለክቶ ወደ ገንዘብ ተቀይሮ በብር ተተምኖ መከፈል አለበት ማለት ነው፡፡ ጉዳቱና ካሳው እኩል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሕጉም በምን ሁኔታ ቢካስ ከጉዳቱ ጋር እንዲመጣጠን ማድረግ እንደሚቻልም ደንግጓል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ካሳው ከጉዳቱ ሊቀንስ የሚችልባቸው ሁኔታዎች እንደሚኖሩ በማሰብ የካሳውን መጠን ዳኞች ትክክል በመሰላቸው መንገድ እንዲቀንሱ ሥልጣን የተሰጠባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ለአብነት ጉዳት አድራሹ የፈጸመው ድርጊት ሌላ ሰውን እንደሚጎዳ ባለማወቁ የተፈጸመ ሲሆን፣ ድርጊቱ የተፈጸመው በበላይ ኃላፊ ትዕዛዝ በሆነ ጊዜ፣ ጉዳቱ ይደርሳል ተብሎ የማይታሰብ ከሆነ ዳኞች ካሳውን ለመቀነስ ይችላሉ፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ ጉዳቱ ታውቆ ነገር ግን የካሳውን መጠን መወሰን የሚያስቸግርበትም አጋጣሚ አለ፡፡

ካሳውን ለመቀነስም ይሁን የካሳውን መጠን በእርግጠኝነት እንቅጩን ማስቀመጥ የማይቻል ከሆነ ዳኞች ሁኔታዎችን በመመርመር፣ በመተንተን ትክክል ነው ብለው ያመኑበትን በመወሰን ፍትሕ እንዲያሰፍኑ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ከላይ የተገለጹትን ሁኔታዎች መነሻ በማድረግ ፍርድ የሚሰጠው በ‹ርትዕ› ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ የሚዳሰሰው ጭብጥ የካሳውን መጠን በእርግጠኝነት ማስላት የማይቻል በሚሆንበት ጊዜ ዳኞች በርትዕ የሚወስኑበትን ሥልጣናቸውን የሚመለከት ነው፡፡ ለጽሑፉ መነሻ የሆኑት በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጡት ውሳኔዎች ቅጥ የሌላቸው መሆናቸው ነው፡፡ በእርግጥ ርትዕ ለዘፈቀዳዊነት የታጋለጠች ናት፡፡ ይህ ማለት ግን በነሲብ፣ ያለ ምክንያት፣ ያለ መርሕ፣ መረን አልባ በሆነ ዘፈቀዳዊነት ይወሰናል ማለት ግን አይደለም፡፡ በዚህ ጽሑፍ ስምንት የሰበር ውሳኔዎች ተዳስሰዋል፡፡ ርትዕን በመጠቀም ካሳ የተወሰነባቸው ወይም እንዲወሰን ለሥር ፍርድ ቤት ጉዳዮቹን እንዲመለስ የተደረጉባቸው መዝገቦች ናቸው፡፡

የርትዕ ምንነት

ርትዕ ምን ማለት እንደሆነ ቁርጥ ባለ አኳኋን ሊገለጽ አይችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ይዘቱን እንዲህና እንዲያ በማለት ሊወሰን የሚችል ጽንሰ ሐሳብ አይደለም፡፡ የርትዕ፣ ከይዘቱ ይልቅ ሚናው፣ ፋይዳውና ጠቀሜታው ይታወቃል፡፡ ግቡም ፍትሕን ማስፈን ነው፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹በመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› ብለው በሰየሙት ዘመን አይሽሬ መጽሐፋቸው ላይ ‹‹ርትዕ››› የሚለውን የግዕዝ ቃል በአማርኛ ሲፈቱት ‹‹እውነተኛ ፍርድ፣ የቀና፣ የተካከለ፣ ሐሰትና ግፍ የሌለበት›› ይሉታል፡፡

ብላክስሎው በሚባለው የሕግ መዝገበ ቃላትም ለርትዕ (ኤኩቲ) ‹‹ፍትሐዊነት (ፌይርነስ)፣ አለማዳለት፣ አንድን ውሳኔ ትክክልኛ ፍትሐዊ መሆን የሚያሳይ መርሕ፣ የተፈጥሮ ሕግ ወይም ፍትሕ፣ አከራካሪ የሆነው ጉዳይ ላይ እልባት ለመስጠት ሕጉ በቂ ሳይሆን ከቀረ ክፍተቱን ለመሙላት ሥራ ላይ የሚውል›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ ታላቁና ዕውቁ የግሪኩ ፈላስፋ፣ አርስጣጣሊስ በአንድ ድርሰቱ የርትዕን ፋይዳናና ከፍትሕ ጋር ያለውን ተዛምዶ አብራርቷል፡፡ ፋይዳውን ሲገልጽ ሕግ ለራሱ ደንቦችና መርሆች የመገዛት የግትርነት አመልና ፀባይ ስላለው አንዳንዴ ፍትሕ ለማምጣት ታስቦ የወጣው በተቃራኒው ኢፍትሐዊነትን ሊያስከትል ስለሚችል ይህንን ችግር ለመቅረፍ ርትዕ መፍትሔ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የሕግ ደካማ ጎን ወይም ጉድለት ለማረም ይረዳል፡፡ ፍትሕን ለማስፈን ዳኞች በሕግ ከተደነገገው በመውጣት ወይም ሕጉ ራሱ በአንዳንድ ተለይተው በተገለጹ ጉዳዮች ላይ ርትዕን እንዲከተሉ ሲፈቅድ ከሕግ ይልቅ ህሊናቸው ትክክል ነው የሚለውን እንዲመርጡ እንዲወስኑ የሚፈቅድ መርሕ ነው፡፡

ርትዕ የሚያመለክተው የተፈጥሯዊ ሕግጋትን በመጠቀም ፍትሕን መስጠት ነው፡፡ ሕግ ግትርነት፣ አስቀድሞ ጥብቅ ደንብ ማውጣትን ይወዳል፤ ፀባዩም ነው፡፡  የርትዕ ተጨማሪ ፋይዳዎችም አስቀድሞ የተቆረጠው ሕግ ትክክለኛ ፍትሕ ላያስገኝ ስለሚችል አከራካሪ ለሆነው ጉዳይ እንደ ማስረጃዎቹና ሁኔታው በሕግ ገመድ መታሰር ሳይኖር ፍትሕ ለማስገኘት ይበጃል፡፡ አስቀድሞ እርግጠኛ በመሆን ደንብ ማበጀት ሲያስቸግር፣ ቁርጥ መፍትሔ ማስቀመጥ ሲከብድ፣ ጉዳት አድራሹ ድርጊቱን የፈጸመበት ምክንያት ከቁጥጥሩ ውጭ በሆነ ጊዜ ባደረሰው ጉዳት መጠን ካሳ መክፈል ከህሊና ግምት ውጭ ስለሚሆንና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮችን ለመቅረፍ ያገለግላል፡፡

ይሁን እንጂ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳቶችም አሉት፡፡ የርትዕ ይዘት ምንነቱ ቀድሞ የተወሰነ የተለየ የታወቀ እንደሆነ ከላይ ገልጸናል፡፡ ርትዕ፣ ጉዳዩን በሚዳኘው የህሊና ዳኝነት ላይ የተንጠለጠለ ስለሚሆን እርግጠኝነትና ተገማችነት አይኖረውም፡፡ በርትዕ ለሚወሰኑ ጉዳዮች  ውጤታቸውን በእርግጠኝነት ቀድሞ መወሰን አይቻልም፡፡ በተመሳሳይ ጉዳይ በተለያዩ ዳኞች የተለያዩ ፍርዶችን ማግኘትም የተለመደ ነው፡፡ ዘፈቀዳዊነት ይበዛዋል፡፡ ለሙስና ሥልጣንን አላግባብ ለመጠቀምም የተጋለጠ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥለን የምንመለከተውም በዋናነት ይህንን ዘፈቀዳዊነት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ከርትዕ ይልቅ ነሲባዊነት የተንፀባረቀባቸውን የካሳ አተማመን በሚመለከት የሰበር ውሳኔዎች ዋቢ እያደረግን እርስ በርሳቸው እናነፃፅራለን፡፡

ተጎጂ እንደ ዝቅተኛ ተከፋይ ሠራተኛ

የመጀመርያው ነሲባዊነት የተንፀባረቀበትን ውሳኔ እንመለከት፡፡ ታሪኩ በአጭሩ ይህን ይመስላል፡፡ ተከራካሪዎቹ ዘይነባ ሐሰንና ፍሬው ተካልኝ ናቸው፡፡ የውሳኔው የመዝገብ ቁጥሩ 19338 ሲሆን፣ በቅጽ አምስት ላይም ታትሟል፡፡ አቶ ፍሬው የዘይነባን አንድ ዓይን በድብደባ ያጠፋል፡፡ ዘይነባ ለሕክምና፣ ለትራንስፖርት፣ ለምግብ፣ ለመድኃኒት፣ ለሰው ሠራሽ ዓይንና ሞራል ካሳ ብር 12,830 እንዲሁም ትምህርቷን ጨርሳ በዝቅተኛው የመንግሥት ደመወዝ ብር 120 ብትቀጠርና እስከ 55 ዓመት ብትቆይ 40,000 ብር ታገኝ እንደነበር ተገልጾ ክስ ይቀርባል፡፡ ፍርድ ቤቱ አንድ ዓይኗን ማጣቷ ከአጠቃላይ የመሥራት አቅሟ የቀነሰው አርባ በመቶ ብቻ በመሆኑ ብር 16,800 እና ያወጣችውን ወጭዎችና የሞራል ካሳ ተደማምሮ ብር 21,378 ይገባታል በማለት ወሰነ፡፡ ይህንን ውሳኔ በይግባኝ የቀረበለት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም አጸናው፡፡

ነገር ግን የዚሁ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ግን አንድ ዓይኗን ማጣቷ ገቢ ከማግኘት ስለማይከለክላት ካሳ አይገባትም ብሎ ወሰነ፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግን በርትዕ መወሰን እንደሚገባው ምክንያት በማቅረብ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጸናው፡፡

ዘፈቀዳዊነቱ የሚጀምረው ክሱ ሲቀርብ ለካሳው መነሻ ሆኖ የቀረበው ላይ ነው፡፡ ክሱ ሲቀርብ ትምህርቷን ያልጨረሰችና ገና ሥራ ያልያዘች በመሆኗ ወደፊት የመንግሥት ሥራ ብትይዝ እንዲሁም ደመወዟ በወቅቱ በነበረው ዝቅተኛው መጠን እንዲሆን ተመርጧል፡፡ የወደፊት የገቢ መጠኗ አመራረጡ በራሱ ዘፈቀዳዊ ነው፡፡ በተጨማሪም ዘይነባ ዕድሜ ልኳን ደመወዟ በዚያው መጠን ብቻ እንደሆነ መውሰድ ርትዓዊ ሊባል አይችልም፡፡ ለአብነት አሁን ያለው ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን 600 ብር ነው፡፡ ለዘይነባ ግን ያው 120 ብር ብቻ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በተጨማሪም ዘይነባ ከዝቅተኛው የደመወዝ መጠን በላይ ልትቀጠር ወይም ልታገኝ ትችላለች፡፡ ደመወዟም እየጨመረ ሊሄድ ይችላል፡፡ ማንም አመዛዛኝ ህሊና ያለው ሰው ዘይነባ ዕድሜ ልኳን ብር 120  ብቻ እየተከፈላት ትኖራለች በማለት አይፈርድም፡፡ ልቦናውም ይህን ብቻ ይከፈላት አይልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚስተዋለው ሌላው ጉዳይ ዘይነባን አንድ ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ብትሆን የሚል ግምት በመውሰድ ቀጥሎ ደግሞ አንድ ሠራተኛ በሥራው ምክንያት ጉዳት ቢደርስበት ካሳ የሚከፈልበትን ሥርዓት መውሰዱ ነው፡፡ ዘይነባ ወደፊት ነጋዴ ትሁን፣ መሐንዲስ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህንን ዓይነት አሰላል በርትዕ እንደተወሰነ ተቆጥሯል፡፡ ርትዕ ግን በሕግ እንኳን አጠራጣሪ የሚሆንን ነገር እንደ ሁኔታው አመዛዝኖ ፍትሕ የሚሰጥበት አሠራር ነው፡፡ እርግጥ ነው በደረሰባት ጉዳት ወደፊት ምን ያህል ገቢ ሊቀርባት እንደሚቻል በትክክል ማስላት አይቻልም፡፡

ሰበር ችሎቱ በነሲብ የወሰናቸው

ቀጣዩ የሰበር ውሳኔ (የመዝገብ ቁጥር 34314) በቅጽ ዘጠኝ ላይ ታትሞ የወጣ ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ ይህን ይመስላል፡፡ ወ/ሮ ግምጃ የ30 ዓመት ዕድሜ የነበረው ልጃቸው አዱኛ ደበሌ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ በሚመጣበት ጊዜ የነበረበት መኪና ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ሕይወቱ ያልፋል፡፡ ልጃቸው በግብርና ሙያ የሚተዳደርና እሳቸውንም ይረዳቸው ስለነበር ቢያንስ ለተጨማሪ አሥር ዓመታት ቢኖር ኖሮ ብር 104,000 ሊረዳኝ ይችል ነበር በማለት ዳኝነት ይጠይቃሉ፡፡

የፌደራሉ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ለጉዳቱ ኃላፊ የሆኑትን ለይቶ ጥፋተኛ በማለት ነገር ግን ወ/ሮ ግምጃ ዕድሜያቸውን ስላልገለጹ እንዲሁም ለወደፊት ምን ያህል ዘመን ሊኖሩ እንደሚችሉ ስላላስረዱ ካሳ ሊያገኙ አይገባም በማለት ወሰኗል፡፡ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱም አጽንቶታል፡፡ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግን ጉዳት መድረሱ ስለተረጋገጠ ዕድሜያቸውንና ለምን ያህል ዓመት መኖር እንደሚችሉ አለማስረዳታቸውን ብቻ ምክንያት በማድረግ ካሳ እንዳያገኙ መከልከል ተገቢ ስላልሆነ የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመሻር በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ  2102 መሠረት በርትዕ ብር 25,000 እንዲከፈላቸው ወሰነ፡፡ ይህንን ጉዳይ በርትዕ ለመወሰን ፍርድ ቤቱ በመለኪያነት ከግምት ያስገባቸው ነገሮች የሉም፡፡ የአመልካች ዕድሜንም አላጣራም፡፡ ይረዳቸው የነበረውን ገንዘብም እንዲሁ አልታወቀም፡፡ ብቻ አመልካቿ ኢኮኖሚያዊ ዕርዳታ ያደርግላቸው የነበረውን ልጃቸው በመኪና አደጋ በማጣታቸው ምክንያት በነሲብ 25,000 ብር ተከፈላቸው፡፡ ወ/ሮ ግምጃ ልጃቸው ከሞተ በኋላ 25 ዓመታት በሕይወት ኖሩ ቢባል በዚህ ብር ብቻ ይኖራሉ ወይ?

በሌላ መዝገብ የተሰጠ ውሳኔን ደግሞ እንመልከት፡፡ በእነ አቶ አየለ አድማሱና ወ/ሮ አጀቡ ሹሜ መዝገብ (ቅጽ አሥር፣ የመዝገብ ቁጥር 42962) የመኪና ግጭት በመከሰቱ ምክንያት 18 በመቶ የአካል ጉዳት ስላጋጠማቸው ለደረሰባቸው ጉዳት ብር 50,000 ቢጠይቁም፣ የፌዴራሉ የመጀመርያ ፍርድ ቤት ግን ከሳሿ ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ያገኙት የነበረው ገቢ ስለመኖሩ ባለማረጋገጣቸው የተቋረጠ ገቢ አለ ማለት ስለማይቻል ካሳ ሊከፈላቸው አይገባም በማለት ውሳኔ ሰጠ፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም ይሄንኑ አጸናው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ግን ጉዳት መድረሱ ከተረጋገጠ ወደፊት ሊያገኙ ይችሉ የነበረው ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡ መጠኑን በተመለከተ ግን ወደፊት ምን ያህል ገቢ ሊቀርባቸው እንደሚችል በእርግጠኝነት መወሰን ስለማይቻል በርትዕ ብር 30,000 እንዲከፈላቸው በመወሰን የሥር ፍርድ ቤቶቹን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ በርትዕ ሲወስን ግን በመለኪያነት የተጠቀማቸው መሥፈርቶች ግን የሉም፡፡ ለምን 30,000 ብር ወሰነ ቢባል ከፍርዱ የሚገኘው ምንም ነው፡፡

ሌላ በዘፈቀዳዊነት የተሰጠ ውሳኔን እንጨምር፡፡ በቅጽ 11 ላይ የታተመ የመዝገብ ቁጥሩ 38117 የሆነ በአቶ ብርሃኑ ፈይሳና በናይል ኢንሹራንስ መካከል ተካሄደ ክርክር ነው፡፡ የ11 ዓመት ዕድሜ ያለው የአቶ ብርሃኑ ልጅ በናይል ኢንሹራንስ መኪና ተገጭቶ በመሞቱ ወደፊት ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን ዕገዛና ዕርዳታ ስለሚቀርባቸው ካሳ ይጠይቃሉ፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው የሰሜን ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሳሹ የቀረባቸውን ጥቅም ምን ያህል እንደሆነ ስላላረጋገጡ የሞራል ካሳ ብር 800 እንጂ ሌላ ካሳ አይገባቸውም በማለት ይወስናል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም አፀደቀው፡፡

የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግን ልጁ አገልግሎት ይሰጣቸው እንደነበር የተካደ ባለመሆኑ ወደፊትም ሊያገኙ ይችሉት የነበረው ተቋርጧል ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ የሚቀርባቸውን ጥቅም ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል በገንዘብ ተምኖ በእርግጠኛነት መወሰን ስለማይቻል በርትዕ ብር 12,000 እንዲከፈላቸው ወስኗል፡፡ በርትዕ ለመወሰን ግን ከግምት ያስገባቸው መለኪያዎች አሁንም አልተገለጹም፡፡ የሉም፡፡ እንግዲህ እነዚህ ከላይ የተገለጹት የካሳ መጠናቸው በነሲብ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ለውሳኔው መነሻ የሆኑ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ አይታወቅም፡፡

በርትዕ እንዲወሰኑ የመለሳቸው

ከላይ ከቀረበው ከእነ ወ/ሮ ግምጃ ጉዳይ በተለየ መልኩ የተሰጡ ውሳኔዎችን ደግሞ እንመለከት፡፡ ጥሩቀለም ደምሴና ባለቤታቸው የ11 ዓመት ልጃቸውን ታክሲ ስለገጫት የቀኝ እግር ታፋዋ ላይ መካከለኛ ጉዳት ስለደረሰባት ጉዳቱ ያስነክሳታል፡፡ ወደፊት ሥራ የመሥራት አቅሟ ስለሚቀንስ በራሷ ገቢም እንዲሁም ወላጆቿን መርዳትም ስለሚያቅታት ባለታክሲው ብር 100,000 እና የሞራል ካሳ እንዲከፈላቸው ዳኝነት ጠየቁ፡፡

ጉዳዩ የቀረበለት የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ግን ምንም እንኳን ጉዳቱ የደረሰባት ቢሆንም በእዚህ ምክንያት ወላጆቿን ልትረዳ አለመቻሏና ለራሷም ሊቀርባት የሚችለው ጥቅም መኖሩ አጠራጣሪ በመሆኑ የሞራል ካሳ ብቻ ብር 800 ይገባታል ሲል ይወስናል፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም ስላጸናው ለሰበር ይቀርባል፡፡ የሰበር ችሎቱም ጉዳቱ የሚያስነክሳት ከሆነ ወደፊት ስለሚደርሰው ቁሳዊ ጉዳት ማስረዳት ስላልቻሉ ካሳ አይገባም በማለት ውድቅ ማድረግ ተገቢ ስላልሆነ በርትዕ እንዲወስን ለሥር ፍርድ ቤት መለሰው፡፡ ይህ ጉዳይ በቅጽ 9 ላይ የመዝገብ ቁጥር 35034 ተሰጥቶት ታትሟል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እና በሌላ መዝገብም እንዲሁ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ቀድሞ እንደወሰናቸው በራሱ አልወሰነም፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይም ይሁን በሌሎች የሚስተዋሉ የካሳ አተማመን ችግሮች አሉ፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ የተንፀባረቀ ልዩ ሁኔታ እንመልከት፡፡ አንድ ሰው የአካል ጉዳት ሲያጋጥመው የካሳው መጠን መተመን የሚኖርበት የሰውየው ሙያ ምንም ይሁን ምን፣ ጉዳት የደረሰበት አካሉ ለሙያው የሚኖረው ጠቀሜታ ከግምት ሳይገባ ማንኛውም ሰው ሊያጋጥመው የሚችለውን የመሥራት አቅም መቀነስ (General Utility) ያህል ነው መታስብ ያለበት? ወይስ ከጉዳቱ በፊት ሲሠራ የነበረውን ሥራ ለመሥራት ጉዳቱ ያስከተለው ልዩ ጫና (Specific Utility)  ከግምት መግባት ያለበት? የሚሉት አማራጮች አከራካሪ ናቸው፡፡ የትኛው ነው በተሻለ መልኩ ፍትሐዊ የሚሆነው የሚለውም ላይ ስምምነት የለም፡፡

ከላይ ባየነው  በዘይነባና በፍሬው ጉዳይ ላይ፤ ፍርድ ቤቱ የተጠቀመው መርሕ እንደ ሰው የመሥራት አቅም መቀነስን ነው፡፡ በአሁኑ ውሳኔ ደግሞ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በተሻለ ሁኔታ ፍትሐዊ እንደሆነ የገለጸው ጉዳት የደረሰበትን ሰው ቀድሞ ሲሠራው በነበረው ላይ ያሳደረውን ልዩ ተፅዕኖ ነው፡፡ የሥር ፍርድ ቤትም ከግምት ማስገባት እንዳለበት በሐተታው ላይ አስፍሯል፡፡ እንደሰውና በአጠቃላይ የመሥራት አቅም በመቀነስ ስሌት፣  የአትሌት (ሯጭ) እና የድምፃዊ እግርም ምላስም ዓይንም  እኩል ዋጋ ሲኖራቸው፤ ቀድመወው ሲሠሩት ከነበረው ላይ ልዩ ጫና በማድረስ ከሆነ ለሯጭ እግሩ ወይም ዓይኑ መጎዳቱ ልዩ ጫና ሲያደርስበት ለድምፃዊው ደግሞ ምላሱ መጎዳቱ ልዩ ጫና ይፈጥርበታል፡፡ እንግዲህ ካሳ የሚከፈለው  ከደረሰው ወይም ከሚደርሰው ጉዳት ጋር እኩል መሆን ካለበት ሯጩ እግሩ ላይ ጉዳት ሲደርስበት መሮጥ ስለሚያቆም በዚህ ምክንያት የሚያጣውን በካሳ መልክ ሲከፈል ከጉዳቱ ጋር እኩል ይሆናል፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው ታስቦ የሚከፈለው ከሆነ ግን ከካሳው ይልቅ ጉዳቱ በእጅጉ ስለሚያመዝን ፍትሐዊ አይሆንም፡፡

ከላይ በአቶ አየለ አድማሱና ወ/ሮ አጀቡ ሹሜ ጉዳይ ጉዳቱ የደረሰው በእግራቸው ላይ ሲሆን፣ የተሰላውም እንደሰው የመሥራት አቅም መቀነስን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ ከተሰጠም በኋላ ቢሆን ሰበር ሰሚ ችሎቱ ልዩ ጫና የሚለውን ሳይሆን እንደሰው የመሥራት አቅም መቀነስን በመከተል ነው እየወሰነ ያለው፡፡ ይህ ደግሞ ለጉዳቱ ተስተካካይ የሆነ ካሳ የመክፈል ሕጋዊ ግዴታ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ የሚከተለውም መርሕም እንዲሁ አንድ ጊዜ አንዱን ሌላ ጊዜ ሌላውን በመሆኑ ዘፈቀዳዊነቱን አባብሶታል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ከእንደገና በርትዕ ለመወሰን የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት መግባት እንዳለባቸው ያሳሰበበትን ውሳኔ እንመልከት፡፡   በቅጽ 19 የታተመ፣ የመዝገብ ቁጥሩ 108251 የሆነ፣ በኢትዮጵያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ድርጅትና በአቶ አመከክ ከሊፋ መካከል የተካሄደ ክርክር ነው፡፡ ጉዳዩም፣ የአራተኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ልጃቸው ተከሻሹ የሠራውን የውኃ ጉድጓድ በተገቢው መንገድ ሳይከድን በመቅረቱ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ይሞታል፡፡ ሟቹ ከትምህርት መልስ ውኃ በአህያ እያመላለሰ አንድ በርሜል በ25 ብር ለሠፈሩ ሰው በመሸጥ በቀን በአማካይ 200 ብር፣ በወር ብር 6,000 ወላጆቹን ይረዳ ስለነበር ትምህርቱን እስከሚጨርስ በዚሁ መንገድ ይረዳቸው የነበረው ገቢ ስለተቋረጠ የሞራል ካሳና የመቃብር ማስፈጸሚያውን ጨምሮ ብር 580,000 ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡ የሸበሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግን የካሳ መጠኑን እርግጠኛ ሆኖ ማሰላት ስለማይቻል በርትዕ ብር 500,000 እንዲከፈል ይወስናል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልም ይሄንኑ ውሳኔ ያጸናዋል፡፡ ጉዳዩን በሰበር የተመለከተው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን ካሳው በርትዕ መወሰኑ ተገቢ ቢሆንም በርትዕ ሲወስኑ ምን ምን ጉዳዮችን ከግምት እንዳስገባ የሥር ፍርድ ቤቱ ስላልገለጸ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2153 የተደነገጉትን የነገሩን አጋጣሚ ሁኔታ፣ ሊገመቱ የሚገባቸውን ትክክለኛውን መንገድ በመያዝ፣ ከአዕምሮ ግምት ውጭ እንዳይሆን፣ ከዝንባሌ በፀዳ መልኩ ሊወሰን ስለሚገባ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በርትዕ ሲወስን እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት የገቢ ሁኔታዎችም በግልጽ በመወሰን በርትዕ ከእንደገና እንዲወሰን ቀድሞ የሰጠውን ውሳኔ በመሻር በድጋሜ ይወሰን ዘንድ መልሶታል፡፡

ካላይ ባየናቸውም ይሁን ከዚህ በታች በሚጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ራሱ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን ከግምት አላስገባም፡፡ መመለሱ ከግምት የገቡትን ነገሮች ፍርድ ቤቱ እንዲለይ ለማድረግ ይመስላል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በርትዕ ለመወሰን የተለያዩ ጉዳዮችን ከግምት መግባት እንዳለባቸው የተገነዘበበትም ጉዳይ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሥር ፍርድ ቤት የካሳውን መጠን ለመወሰን በመነሻነት የቀረበውም ትኩረት የሚስብ ነው፡፡  በእነ ብርሃኑ ፈይሳና በናይል ኢንሹራንስ ጉዳይ ላይ ሟቹ ከትምህርት ቤት ሲመለስ ከብቶችን በመጠበቅ ይረዳቸው ስለነበር ይኼንኑ ወደ ገንዘብ በመቀየርና እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ቢቀጥል ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን መነሻ በማድረግ የቀረበ ቢሆንም፣ ሰበር ሰሚው ግን ጉዳት እንደደረሰባቸው በማመን ነገር ግን በእርግጠኝነት የሚያጡትን ግን ማወቅ እንደማይቻል ቆጥሮ ነው ውሳኔ ያሳለፈው፡፡ በሌሎች ጉዳዮች ብዙዎቹ የሥር ፍርድ ቤቶቹ ካሳ አይገባም ሲሉ በአመከክ ከሊፋ ጉዳይ ላይ ግን በርትዕ ብር 500,000 እንዲከፈል ተወስኗል፡፡ እዚህ ላይ አንድ የሚስገርም ነገር አለ፡፡ ልጅ ወላጆቹን የሚረዳው 12ኛ ክፍል እስከሚደርስ ድረስ መሆኑ፡፡ በእዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኝ ልጅ ወላጅ ልጅን የመንከባከብ የሕግ ግዴታ እንዳለበት እየታወቀ በተቃራኒው የመወሰን አዝማሚያዎች ግን ርትዓዊ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡

ወጭዎችን በርትዕ መወሰን

በሜሪስቶፕስና በሰናይት ዓለማየሁ መካከል የነበረውን ክርክር (የመዝገብ ቁጥሩ 64590፣ቅጽ 11) እንመለከት፡፡ በሜሪስቶፕስ ኖርፕላንት የሚባል የወሊድ መከላከያ በክንዷ ላይ ካስቀበረች በኋላ ሕመም ስላስከተለባት የሜሪስቶፕስ ባለሙያዎች እንዲወጣ አደረጉ፡፡ ባለሙያዎቹ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው ለተለያዩ ሕመሞች ተጋለጠች፡፡ ሕክምናውን በአገር ውስጥ ማድረግ ስላልቻለች ውጭ እንድትታከም ይወሰናል፡፡ እሷም በሕመሟ ምክንያት ያጣችውን ገቢና ካሳ ትጠይቃለች፡፡ ታይላንድ ሄዳ ለመታከም፣ የሞራል ካሳና በመታመሟ ያጣችውን በዝርዝር በማቅረብ ብር 694,918 ጠየቀች፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም ወጭዎቹ በእርግጠኝነትና በትክክል ለማወቅ ስለማይቻል በርትዕ ብር 300,000 ይከፈላት በማለት ወሰነ፡፡ ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ግን አመልካች ያቀረበቻቸው ማስረጃዎች እንደሚሳዩት የሕክምና ወጪዎቹ ከፍተኛ በመሆኑ፣ አስታማሚ ስለሚስፈልጋት፣ ወጭዎቹን ከወዲሁ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል የምንዛሪ መጠን መውረዱም  ወጪውን ስለሚጨምረው  በርትዕ ብር 694,918 እንዲከፈላት በመወሰን የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ይሽረዋል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎቱም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በርትዕ ሲወስን ሊገመቱ የሚገባቸውን፣ በትክክለናው መንገድ፣ ትክክለኛ የአገማመት ሥልት የተከተለና ከአዕምሮ ግምት ውጭ ስላልሆነ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡ እዚህ ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በርትዕ ለመወሰን የተለያዩ ጉዳዮችን ከግምት አስገብቷል፡፡ ይሁን እንጂ የሕክምና ወጪዎች በርትዕ የመወሰን ሕጉ አስቀድሞ ያሰበው ነው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከላይ በሜሪስቶፕስና ከሰናይት ዓለማየሁ ጉዳይ ጋር የሚቀራረብ ነገር ግን አሁን ከርተዕ ይልቅ ነሲባዊነት የተንፀባረቀበትን ውሳኔ እንመልከት፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ በሐያት ሆስፒታልና በአስቴር ሰለሞን መካከል የነበረውን (ቅጽ 19፣ የመዝገብ ቁጥር 96548) የተከናወነ ነው፡፡ ወ/ሮ አስቴር የእርግዝና ክትትል ሲያደርጉ በነበረበት ሆስፒታል ይወልዳሉ፡፡ በሚወልዱበት ጊዜ ግን ባለሙያዎቹ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው የተወለደችው ልጅ ላይ በርካታ ቋሚ የአካል ጉዳት ይደርስባታል፡፡ ሕፃኗ ያጋጠማትን ጉዳት በአገር ውስጥ ልትታከም እንደማትችልም ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም፣ ሕፃኗ ወደፊት 59 ዓመት ብትኖር ራሷን ችላ መንቀሳቀስ ስለማትችል ለረዳት፣ ለሾፌርና ዕድሜ ልኳን ለምታደርጊው የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት፣ ለፀጉር ማስተከያ፣ ለምትወልዳቸው ሦስት ልጆች መንከባከቢያ በድምሩ ብር 4,111,686 ጠይቃ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ግን ለሠራተኛ ብር ቀድሞ ከተጠየቀው ከ800 ሺሕ ገደማ 689 ሺሕ ውጭ ለመታከም ከ410 ሺሕ ብር 346,250፣ ለፊዚዮቴራፒ ከተጠየቀው 1,611,811 ላይ 1,453,035 የሞራል ካሳን ጭምሮ ብር 2,489,334 ይወስናል፡፡ ሌሎቹን ዳኝነቶች ግን ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ይኼንኑ አጸናው፡፡ ሰበር ችሎቱ ግን በደረሰባት ጉዳት ረዳት ሠራተኛ እንደሚያስፈልጋት ቢታወቅም ምን ያህል ገንዝብ ያስፈልጋል የሚለው ግን በእርግጠኝነት መወሰን ስለማይቻል በርትዕ ብር 300,000 እንዲሆን፣ ለጂምና ለፊዚዮቴራፒም በቀን፣ በወርና በዓመት ምን ያህል መከፈል እንዳለበት በትክክል ማወቅ ስለማይቻል በተመሳሳይ መልኩ በርትዕ ብር 500,000 እንዲከፈል በመወሰን የሕክምናውን ግን እንዳለ አጽንቶታል፡፡ እንግዲህ በዚህ ጉዳይም ከ689 ሺሕ ወደ 300 ሺሕ የፊዚዮቴራፒውንም ለምን ወደ 500 ሺሕ ዝቅ ሲያደርግ ምክንያቶቹ አልተገለጸም፡፡ የሕክምና ወጪንም እንዲሁ በርትዕ መወሰን ፍትሐዊ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ከፍም ዝቅም የማለት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

በአጠቃላይ ርትዕ በሕግ ከተቀመጠው ድንጋጌ በተሻለ ሁኔታ ፍትሕን ለማስፈን የሚረዳ ቢሆንም፣ ለዘፈቀዳዊነት የተጋለጠ መሆኑ ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ በተመለከትናቸው ሁሉም ጉዳዮች ላይ የተስተዋሉት እጅግ ዘፈቀዳዊነት መንገሡን ነው፡፡ በመሆኑም ርትዕና ነሲባዊነት የተለያዩ በመሆናቸው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡