Skip to main content
x

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በስድስት ወራት

  • ለወጪ ካዘጋጀው 2.3 ቢሊዮን ብር የተጠቀመው 990 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው
  • 347 ኪሎ ሜትር መንገድ መጠገኑንና መገንባቱን ገልጿል

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በ2010 ግማሽ በጀት ዓመት ከ992 ሚሊዮን ብር ወጪ የጠየቁ ሥራዎችን ያከናወነ መሆኑ አስታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ በመጀመርያው ስድስት ወራት ሥራ ላይ እንዲውል አቅዶ የነበረው 2.3 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ የተጠቀመው ገንዘብ ግን 992 ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ የሆነው መለቀቅ ያለባቸው ክፍያዎች ስለዘገዩ በመሆኑ ክፍያዎቹ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ሲለቀቁ ከዕቅዱ ጋር እንደሚጣጣም ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ ይህም ሆኖ ባለፉት ስድስት ወራት 347.8 ኪሎ ሜትር የሚሆን የመንገድ ግንባታና ጥገና ማድረጉን ይገልጻል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በ2010 በጀት ዓመት የመጀመርያው ስድስት ወራት ውስጥ ለማከናወን ከታቀዱ ሥራዎች መካከል 260 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታና ጥገና አንዱ እንደነበር የስድስት ወራቱን አፈጻጸም የተመለከተው ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡  

በጥገና ሥራ ውስጥ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በከተማዋ የሚገኙትን የአስፋልት መንገዶች እንደየጉዳት ደረጃቸው በጥናት እየለየና ቅደም ተከተል እያወጣ በማያቋርጥ መንገድ በመጠገን የአገልግሎት ዘመናቸው ማራዘምና ለተሽከርካሪና ለእግረኛ ምቹ የማድረግ ኃላፊነት ለመወጣት የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ባሳለፍነው ስድስት ወራት የ3.6 ኪሎ ሜትር የመደበኛና 24.6 ኪሎ ሜትር የወቅታዊ አስፋልት ጥገናና የፓቺንግ (መንገዶችን ቆርጦ የመጠገን) ከፍተኛ ሥራ ተከናውኗል፡፡  ጥገና ከተከናወነላቸው የከተማው መንገዶች ውስጥ ኢምፔሪያል ገርጂ፣ ሳዓሊተ ምሕረት-ወሰን መጋጠሚያ፣ ስድስት ኪሎ-ሚኒሊክ፣ ሳሪስ አቦ-ባቡር ጣቢያ፣ ቦሌ ሩዋንዳ-አትላስ፣ የካቲት 12-ዓይነ ሥውራን ማኅበር፣ ገላን ኮንዶሚኒየም፣ 18 ቁጥር ማዞሪያ-አውቶቢስ ተራ፣ ኮካ አደባባይ-አማኑኤልና ሰሜን ሆቴል-አዲሱ ገበያ ይገኙባቸዋል፡፡  

ከዚህም በተጨማሪ የካዲስኮና ሳሪስ አቦ አደባባዮች ፈርሰው ትራፊክ መብራት ተተክሎላቸው መስቀለኛ መንገድ ሆነው የተሠሩ ሲሆን የላምበረት፣ ዓለም ባንክ ኪዳነ ምሕረት፣ እንዲሁም የዊንጌት አደባባዮች የሲሚንቶ ኮንክሪት ደረጃ ከፍተኛ ጥገና የተደረገባቸው በዚህ ግማሽ ዓመት እንደሆነ ተገልጿል፡፡  

በበጀት ዓመቱ 91.9 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ፉካና ቦይ ጠረጋ የታቀደ ቢሆንም፣ 152 ኪሎ ሜትር ለማከናወን መቻሉን አስታውቋል፡፡ ይህም ከዕቅዱ በላይ እጅግ ከፍተኛ አፈጻጸም የታየበት ክንዋኔ ነው የሚለው የባለሥልጣኑ መግለጫ፣ በስድስት ወራት 4.6 ኪሎ ሜትር ፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን ለማደስና ለመጠገን አቅዶ 5.2 ኪሎ ሜትር መሥራት መቻሉን ገልጿል፡፡ ይህም 112 በመቶ የሚደርስ አፈጻጸም ያገኘሁበት ክንውን ነው ብሏል፡፡

በከተማው የሚገኙት አብዛኛው መንገዶች ለእግረኛ ምቹ ያልሆኑ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት፣ በስድስት ወራት ውስጥ 5.6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እግረኛ መንገድ መጠገን መቻሉንም አስታውቋል፡፡ ዕቅዱ ግን 3.8 ኪሎ ሜትር በመሆኑ አፈጻጸሙ 149 በመቶ እንደሆነ አመልክቷል፡፡  

በራስ ኃይልና በግል ኮንትራክተሮች የሚያሠራቸው የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንዳሉት የሚጠቅሰው ባለሥልጣኑ፣ በግማሽ ዓመቱ በጠቅላላው 15.7 ኪሎ ሜትር ለማከናወን ታቅዶ 10.6 ኪሎ ሜትር በመሥራት 68 በመቶውን ማሳካት ችያለሁ ብሏል፡፡ በግል ኮንተራክተሮች በጠቅላላው 57 ነባር ፕሮጀክቶችና 12 አዳዲስ ፕሮጀክቶች በድምሩ 69 ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ በዕቅድ የተያዙ እንደሆነም ይገልጻል፡፡ በተመሳሳይ በራስ ኃይል በበጀት ዓመቱ 35 ነባር ፕሮጀክቶችና ስድስት አዳዲስ ፕሮጀክቶች በዕቅድ የተያዙ ሲሆን፣ ለበጀት ዓመቱ በጠቅላላ 40.2 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውሷል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በአጠቃላይ ግንባታ እንቅስቃሴ ያደረጉ 17 ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፣ 8.5 ኪሎ ሜትር ለማከናወን ታቅዶ 5.8 ኪሎ ሜትር ሲገነባ አፈጻጸሙም 68 በመቶ ሆኗል፡፡

ከባለሥልጣኑ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው አከናውናቸዋለሁ ካላቸው ግንባታዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ከዕቅድ በታች አፈጻጸም የታየባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ እገነባቸዋለሁ ያላቸው ግንባታዎች ይገኙበታል፡፡  ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ 16.8 ኪሎ ሜትር የጋራ መኖሪያ ቤቶች የመንገድ ግንባታ ለማከናወን አቅዶ የነበረው 6.3 ኪሎ ሜትር የተገነባ ሲሆን፣ ይህም አፈጻጸሙ 38 በመቶ ብቻ መሆኑን ከሪፖርቱ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ ይገነባል ተብሎ የታቀደው የመንገድ ግንባታ አፈጻጸም ዝቅተኛ አፈጻጸም የተመዘገበበት ምክንያት የጨረታ ሒደት መጓተት ነው ተብሏል፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ ፕሮጀክቶች ለመጀመር ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በጨረታ ሒደት መጓተት እንዲሁም የወሰን ማስከበር ሥራዎች አለመጠናቀቅ ለአፈጻጸሙ ማነስ እንደ ምክንያት ቀርቧል፡፡

በኮብል ስቶን ግንባታ ረገድም የዕቅዱን ያህል ያልተጓዘ ስለመሆኑ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ በግማሽ ዓመቱ 61.2 ኪሎ ሜትር የኮብል ስቶን ንጣፍ ሥራ የተገነባ ሲሆን፣ ከዕቅዱ አንፃር አፈጻጸሙ 51 በመቶ ነው፡፡ በኮብል መንገዶች ግንባታ ዙሪያ የዕቅዱን ግማሹን ያህል ብቻ የተከናወነበት ምክንያት እንዲህ ያሉ ግንባታዎች ከኅብረተሰብ ተሳትፎ የሚመጡትን የግንባታ ጥያቄዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ዕቅድ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህም በታቀደው መሠረት ከኅብረተሰብ ተሳትፎ የመጣው ጥያቄ አነስተኛ በመሆኑ፣ ከዕቅዱ አንፃር አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ሊሆን እንደቻለ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት ጋር የተያያዙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በኮብል ስቶን ንጣፍ መንገድ ዝግጅት ሥራና አስፋልት ግንባታ ሥራዎች ስለመከናወናቸው በሚገልጸው የሪፖርቱ ክፍል ደግሞ፣ ባለፋት ስድስት ወራት 12.8 ኪሎ ሜትር ውስጥ ለውስጥ በኮብል ስቶን ሰብ ቤዝ ዝግጅት ለማድረግ ታቅዶ 5.2 ኪሎ ሜትር ተከናውኗል፡፡ ይህ የዕቅዱን 41 በመቶ ብቻ ያሳካ መሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም ኮንዶሚኒየም ቤቶች አስፋልት መንገድ ግንባታ ጋር በተያያዘ በተለያየ አካባቢ ከሚገነቡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ጋር ተያይዞ አራት ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ለማከናወን ታቅዶ መሠራት የቻለው 1.1 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የሚገኙ የጠጠር መንገዶች 84.5 ኪሎ ሜትርና በኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ የ110 ኪሎ ሜትር በጠቅላላው የ199.5 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገዶች ጥገና ለማከናወን ታቅዶ፣ የ58.5 ኪሎ ሜትር የጥገና ሥራ ተከናውኗል፡፡ በበጀት ዓመቱ የ64.98 ኪሎ ሜትር የኮብል ስቶን መንገዶች ጥገና በዕቅድ ተይዞ፣ 7.69 ኪሎ ሜትር ሊከናወን መቻሉ ዝቅተኛ አፈጻጸም ከታየባቸው ውስጥ ተካቷል፡፡ 

ከኮብል ስቶን ምርት ጋር በተያያዘም ባለሥልጣኑ በአምስት ማምረቻ ሳይቶች 2,451 አምራች ኢንተርፕራይዞችን ወደ ሥራው በማሰማራት የተለያየ መጠን ያላቸውን 93.5 ሚሊዮን ጥርብ ድንጋይ ምርቶች አምርቷል፡፡ ለዚህም ምርት አጠቃላይ 312.4 ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኖ እንደተከፈለም ከሪፖርቱ መገንዘብ ተችሏል፡፡

እነዚህን ሥራዎች ለማከናወን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ያመለከተው የባለሥልጣኑ ሪፖርት፣ ከገጠሙኝ ችግሮች ውስጥ የወሰን ማስከበር አንዱና ዋናው ነው  ብሏል፡፡ የተራጮች አቅም ማነስ፣ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ችግር፣ ኅብረተሰቡ የተሠሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ከመጠበቅና ከመንከባከብ ጋር ተያይዞ ያለው ተሳትፎ አናሳ መሆንና በመንገዶች ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራትም እንደተግዳሮት ከጠቀሳቸው ውስጥ ተካተዋል፡፡