Skip to main content
x
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም የጥራት መድረክ በአሸናፊነት መጓዙን የሚሞግቱ ምልከታዎች

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም የጥራት መድረክ በአሸናፊነት መጓዙን የሚሞግቱ ምልከታዎች

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም መድረክ በተለይም በየዓመቱ በአሜሪካ በሚካሄድ የቡና ቅምሻ ውድድር ላይ በበላይነት ለማጠናቀቅ የሁሉም ተወዳዳሪዎች ምርጫ ሆኖ ከሰነበተ በጥቂቱ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ልዩ ልዩ የምግብ ጣዕሞችና ጥራታቸው በሚፈተሽበት በአሜሪካው ‹‹ጉድ ፉድ አዋርድ›› ውድድር ላይ አብዛኞቹ ቡና ቆዪዎች፣ እንደ ወትሯቸው በኢትዮጵያ ቡና በመወዳደር ዘንድሮም ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ ሪፖርተር ስለዚሁ ውድድር ዝግጅት ከጥቂት ወራት በፊት ባስነበበው ዘገባ መሠረት፣ ከ27 በላይ ኩባንያዎች ለውድድሩ በኢትዮጵያ ቡና እንደሚሳተፉ ዘግቦ ነበር፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ይፋ በተደረገው ውጤት መሠረትም በኢትዮጵያ ቡና ተወዳድረው አሸናፊ የሆኑት ኩባንያዎች ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ ቡና የተወዳደሩት መሆናቸው ይፋ ተደርጓል፡፡

በአሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ መገኛውን ያደረገው ጉድ ፉድ ፋውንዴሽን፣ በየዓመቱ በምግብና ምግብ ነክ በሆኑ ምርቶች መስክ ውድድር ያዘጋጃል፡፡ ከሚያዘጋጃቸው ልዩ ልዩ ውድድሮች መካከል፣ ‹‹ጉድ ፉድ አዋርድስ፤›› የተባለውና በምግብና በመጠጦች ዙሪያ የሚሰናዳው ይገኝበታል፡፡ በምርጥ ጣዕማቸው የታወቁ፣ በዓይነትና በዝግጅታቸው የተመሰረከረላቸው የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች ለውድድር ይቀርባሉ፡፡ በታወቁ ዳኞች ይፎካከራሉ፡፡ አሸናፊዎችም ለሜዳልያ ይበቃሉ፡፡ በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡና በዚህ ውድድር በኩል ትልቅ ስምና ሞገስ እያገኘ ሰፊ ተቀባይነትና የዘገባ ሽፋን እያገኘ መምጣቱን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

ለውድድሩ የሚቀርቡ ቡና ቆዪዎች በብዛት በኢትዮጵያ ቡና አማካይት በጅምላ ለአሸናፊነት ሲበቁ መታየቻውን ድረ ገጾች አስነብበዋል፡፡ ሮስት ሜጋዚን የተሰኘው የድረ ገጽ አውታር፣ በዚህ ዓመት የኢትዮጵያን ቡናዎች ለመወዳደሪያነት ይዘው ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች መካከል አብዛኞቹ ለመጨረሻው ዙር ማለፋቸውን አስነብቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ ጥር ወር በተካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ከተሳተፉ የተለያዩ ተወዳዳሪዎች መካከል 27 የአሜሪካ ቡና አዘጋጆች በኢትዮጵያ ቡናዎች ተወዳድረዋል፡፡

ስምንተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ይህ የሽልማት ሥነ ሥርዓት፣ ከምግብ ጥራት ባሻገር በዘላቂ አቅርቦት፣ እንዲሁም በማኅበራዊ መስክ መልካም ተግባራትን በመወጣት ረገድም አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ ኩባንያዎች ዕውቅና የሚሰጥበት ነው፡፡ ይሁንና አብዛኞቹ ለውድድር የሚቀርቡት የምግብና የመጠጥ ምርቶች ከዚያው ከአሜሪካ የሚቀርቡ ቢሆኑም፣ ቡና ግን ከሌሎች በተለየ ከተለያዩ አገሮች ለአሜሪካ ገበያ የሚቀርብ ብሎም ለውድድር የሚያበቃው ደረጃ ላይ የሚገኝ ምርት ነው፡፡ ምንም እንኳ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ቡናዎች የሚቀርቡበት ይህ ውድድር፣ ዘንድሮ ግን በተለየ መልኩ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ተወዳዳሪዎች በኢትዮጵያ ቡና ለውድድር ቀርበው አሸንፈውበታል፡፡

ኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን የተወከለችበት ውድድር መነሻው ምን ሊሆን እንደሚችል መላምታቸውን ያስቀመጡት የድረ ገጹ ጸሐፊ፣ ካስቀመጧቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይጎላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከሌላው ቡና አምራች አካባቢ የተለየ ከፍተኛ ጣዕምና ቃና ያለው ቡና አምራች መሆኗ አንደኛው መነሻ ነው፡፡ ከተቆላ በኋላ ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ መቆየት እንደሚችል የተመሰከረለት የኢትዮጵያ ቡና፣ ለውድድሩ ብቁ ካደረጉት መሥፈርቶች መካከል አንዱ መለኪያ በመሆኑ ተመራጭ እንደሚያደርገውም ይታመናል፡፡

በሽልማት ድርጅቱ መሥፈርት መሠረት፣ ኢትዮጵያ የቡና ደረጃዎችን በመመደብና የጥራት ማረጋገጫ በመስጠት ረገድም ቀዳሚነቷ መረጋገጡን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ ደግሞ ለዘለቄታው አስተማማኝ የቡና ምንጭ ስለመሆኗ መተማመኛ የሚሰጥ ሆኖ መገኘቱን አብዛኞቹ ተወዳዳሪዎች የአገሪቱን ቡና ለውድድር መጠቀማቸው ሌላኛው ማሳያ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡

አሜሪካውያኑ ተወዳዳሪዎች ያቀረቧቸው ቡናዎች በተፈጥሮ ሒደት የሚዘጋጁ ምንም ዓይነት የኬሚካልም ሆነ የፋብሪካ ንክኪ የማይታይባቸው ሆነው መገኛታቸውም ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ቡናዎች ለአሸናፊነት ያገኙት ቅድመ ግምት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በተፎካካሪነት የቀረቡ የሌሎች ተፈጥሯዊ ያልሆኑ የቡና ዓይነት እምብዛም አለመሆናቸው፣ የተፈጥሮ ቡናዎችም ሆነው ከሌሎች አገሮች ለውድድር የቀረቡ አለመኖራቸው ግርምትን አጭሯል፡፡

ባለፈው ዓመት በተካሄደ ውድድር የኢትዮጵያን ቡና የተጠቀሙ ቡና ቆዪዎች አብዛኞቹ ማሸነፋቸው፣ በዚህ ዓመት ለቀረቡት 27 የአሜሪካ ተወዳዳሪዎች መነሻ እንደሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም በፍፃሜ ውድድሩ ወቅት ከቀረቡት 27 ኩባንያዎች መካከል የኢዶዶ፣ የይርጋጨፌ፣ የገደብ፣ የሐምቤላ፣ የሐምቤላ አለቃ፣ የሐምቤላ ቅርጤ፣ የአማሮ ጋዮ፣ የሊሙ፣ የጉጂ፣ የሻኪሶና የሌሎችም አካባቢዎች ቡናዎች በኩባንያዎቹ ለውድድር የተመረጡ ቡናዎች ነበሩ፡፡ ባለፈው ዓመት በተደረገው ውድድር ወቅትም ለውድድር ከቀረቡ 25 የመጨረሻ ዙር ተወዳዳሪዎች ውስጥ 19ኙ የተወከሉት በኢትዮጵያ ቡናዎች እንደነበር ሲታወቅ፣ አብዛኞቹም ለአሸናፊነት እንደበቁ ተዘግቧል፡፡ ካቻምናም በተመሳሳዩ አብዛኛውን የቡና ቆዪዎች ቀልብ ከኢትዮጵያ የሚላኩ ቡናዎች ለመግዛት ቢችሉም፣ ኬንያ ዋና ተፎካካሪ እንደነበረች ተጠቅሷል፡፡

የማስጠንቀቂያ ደወል

ምንም እንኳ በዘንድሮውም የቡና ጣዕም ውድድር የኢትዮጵያ ቡናዎች ለአሜሪካ ኩባንያዎች አሸናፊነትና የበላይነት መነሾ ቢሆኑም፣ ይህ ሊቀጥል እንደማይገባው አምርረው የጻፉ የቡና ባለሙያ አስተያየት ሥጋት ያጭራል፡፡

ጸሐፊው ጆን ፈርጉሰን የተባሉ፣ ፈቃድ ያላቸው የቡና ደረጃ አውጭና የታወቁ የቡና ጥራት ስፔሺያሊስት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ቡና ደጋግሞ የማሸነፍ ጉዳይ ላይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ለምን? ብለዋል፡፡ የሰላው የሚስተር ፈርጉሰን ምልከታ በመላው ዓለም ከ70 በላይ ቡና አምራች አገሮች እያሉ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ማለትም እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2017 ድረስ በተካሄዱ የቡና ጥራትና ውድድሮች እንደምን የኢትዮጵያ ቡናዎች አሸናፊነቱን ሊቆጣጠሩት ቻሉ? በማለት ሞጋች ትንታኔ አቅርበዋል፡፡

ጥራት ላይ በጉድ ፉድስ አዋርድ አማካይነት ከተካሄዱና ካሸነፉ 86 የቡና ዓይነቶች ውስጥ 50ዎቹ የኢትዮጵያ ቡናዎች ናቸው፡፡ 14 የኬንያ ቡናዎች የኢትዮጵያን ቡናዎች በአሸናፊነት ሲከተሉ፣ ዘጠኝ የፓናማ፣ አምስት የኮሎምቢያ፣ ሦስት የጓቲማላ፣ አንድ የኒካራጓዋ እንዲሁም አንድ የኤልሳልቫዶር ቡናዎች በአሸናፊነት ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም በቅይጥ ምድብ ውስጥ ከሌሎች ቡናዎች ጋር ተደባልቀው በመወዳደርም ሦስት የቡና ዓይነቶች አሸናፈነቱን አግኝተዋል፡፡

የውድድሩ ተሳታፊዎች ቀድሞውንም በኢትዮጵያ ቡና መወዳደርን የሚመርጡት በጥራቱና በጣዕሙ የተመረጠ በመሆኑ ነው፡፡ በተለይም ድኅረ ምርት ሒደት ላይ ቡናው የሚደርቅበት መንገድ የቡናውን ጣዕምና ቃና የሚቃኝ በመሆ፣ኑ በኢትዮጵያ ቡና መወዳደር ለአሸናፊነት እንደሚያበቃ ያለ ጥርጥር ስለሚታመንበት የአብዛኞቹ ቡና ቆዪዎች ምርጫ እንደሆነ መገንዘባቸውን የጻፉት ሚስተር ፈርጉሰን፣ ይህ አካሔድ አልተዋጠላቸውም፡፡ ሌሎች አገሮች ሊያቀርቧቸው የሚችሉ ጥራት ያላቸው ቡናዎች ላይ ተፅዕኖ የሚያደርግ አካሔድ ነው፣ ያልታዩና ያልታወቁ ቡናዎችን የማግኘት ሒደትን የሚያደናቅፍ ነው ሲሉም ተችተዋል፡፡

የውድድሩ ዳኞች አንድ ዓይነት የቡና ዝርያዎች እንዲያሸንፉ መፍቀዳቸውን ጥያቄ ውስጥ የከተቱት ጸሐፊው፣ ለቡና አፍቃሪዎች ከታሰበ ልዩ ልዩ ጣዕም ያላቸውን ቡናዎች ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ለውድድር እንዲበቁ ማድረግ እንደሚገባቸው፣ በኢትዮጵያ ቡና ብቻ መወሰን አግባብ እንዳልሆነ በዝርዝር በመተንተን ወቀሳቸውን አቅርበዋል፡፡ በመሆኑም በፕሮፌሽናል የቡና ቀማሾች የሚደረገው የቡና ጥራት ምዘና፣ በቡና ጠጪዎችም እንዲመዘን ቢደረግ ውጤቱ ተመሳሳይ ይዘት ይኖረው ይሆን ወይ? የሚሉት ሚስተር ፈርጉሰን፣ የኢትዮጵያ ቡና በምርት አምስት በመቶ ቢሸፍንም በጥራት ውጤት ግን ከመቶ 88 ነጥብ ማስመዝገብ ስለመቻሉ ጠቅሰዋል፡፡ በአንፃሩ ሌሎች የኢትዮጵያ ቡና ተፎካካሪዎች በምርት መጠን 95 በመቶ ቢወክሉም፣ በጥራት ግን ከመቶ 83 ነጥብ የሚያገኙ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ለሌሎች የቡና ዓይነቶች የአሸናፊነት ዕድሉ ይሰጥ፣ ቀማሾችና ቡና ቆዪዎች በኢትዮጵያ ቡና ላይ ያላቸው ሚዛኑን የሳተ የጥራት ዕይታ ይስተካከል የሚል አንድምታ ያለው ትችት አቅርበዋል፡፡

ስለዚህ ውድድር በኢትዮጵያውያን በኩል ያለው ግንዛቤ እጅግም መሆኑ የሚታመን ነው፡፡ ለውጭ ከሚቀርበው ቡና ባሻገር አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቡና ጠጭ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ በአማካይ 60 በመቶው የአገሪቱ የቡና ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚውል የቆዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከገጠር አካባቢ ባሻገር በከተሞች የሚታየው የቡና ፍጆታ ከፍተኛ ነው፡፡

የ‹‹ጀበና ቡና›› ከሚጠጣው ባሻገር እንደ ፈር ቀዳጁ ቶሞካ፣ ካልዲስ፣ አቢሲኒያ ኮፊ፣ ያሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሞዬ፣ ጋርደን ኦፍ ኮፊ የተባሉና ሌሎችም የተቆላና የፈተጨ ቡና የሚሸጡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ስማቸው ይጎላል፡፡ በመሆኑም የቡና ጥራት ውድድር በአገር ውስጥ በቋሚነት የማካሔድ ፕሮግራም ቢጀምሩ፣ በተጠቃሚው ዘንድ ስለቡና ጥራት ብቻም ሳይሆን ቡና ስለሚቆላበት ትክክለኛ ሒደት፣ ስለአያያዙ፣ ስለአፈላሉና ስለልዩ ልዩ ቡና ጣዕም ዓይነቶች ትልቅ ግንዛቤ መፍጠር በቻሉ ነበር፡፡ የቡና ጥራት ደረጃ የሚወጣባቸው መሥፈርቶች በአብዛኛው የሚታወቁት በጥቂት ቡና ቀማሾች ዘንድ ነው፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ቡና በደረጃ ተለይቶ፣ የታጠበ፣ ያልታጠበ፣ ቅሽር ወዘተ እየተባለ በርካታ መሥፈርቶች ይደረደሩለታል፡፡

ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርበው ቡና ግን ከጥራት መሥፈርቶች በታች መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የሐረር፣ የሲዳማ፣ የይርጋጨፌ ወዘተ. የሚሉ መለያዎች አይሰጡትም፡፡ በደፈናው ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት እየተባለ ይቀርባል፡፡ ከውጭም ባነሰ የጥራት ደረጃ ደግሞ ከውጭው በላቀ ከፍተኛ ዋጋ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርበው ቡና ከውጭው ያልተናነሰ ሚና ለቡና ኢንዱስትሪው እንደሚጫወት የታወቀ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡

እንኳን በምርት ገበያ በኩል የሚያልፈው ቡና ቀርቶ፣ ስብርባሪውና ብጣሪው ቡና ሳይቀር ትልቅ ዋጋ ያወጣል፡፡ ለዚህ ምስክሩ ደግሞ ከሳሪስ ወደ ቦሌ ቡልቡላ በሚወስደው መንገድ አካባቢ ከየቡና መጋዘኑ የሚደፋው የቡና ገለፈት ምስክር ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ለማገዶነት የሚጠቀሙበት የቡና ገለፈት በውስጡ ከፍተኛ ጥራት ያለው የቡና ስብርባሪ ይገኝበታል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት ሪፖርተር በቦሌ ቡልቡላ አካባቢ በቡና ገለባ ስለሚተዳደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ባቀረበው ዘገባ፣ በኪሎ እስከ 60 ብር የሚሸጥ ስብረባሪ ቡና ያገኙ ነበር፡፡ በወቅቱ እንደተዘገበው፣ አንድ ኩንታል ወይም አንድ ጆንያ ሙሉ የቡና ገለባ በ35 ብር ከቡና ማበጠሪያ መጋዘኖች የሚገዙ ተጠቃሚዎች፣ ገለባውን አበጥረው ስብርባሪውን ቡና ለቅመው በማውጣት በኪሎ በመሸጥ ይተዳደራሉ፡፡ ቡና በኢትዮጵያ ኑሮ ውስጥ የዚህን ያህል ዋጋ ቢኖረውም፣ ለጥራት ደረጃውና አያያዙ የሚሰጠው ትኩረት ግን እጅጉን ኋላ የቀረ ነው፡፡ 

ይሁንና በ2009 ዓ.ም. ቡና 882 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይዘነጋም፡፡ በጥቅምት ወር በተደረገው የምንዛሪ ለውጥ ሳቢያም የቡና የወጪ ንግድ መጠን ጭማሪ እንዳሳየ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዳሳለኝ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አኃዞች እንደሚያሳዩትም፣ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ380 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡