Skip to main content
x
ኦሕዴድ አራት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን አገደ
ከግራ ወደ ቀኝ የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የኦሕዴድ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ እንዲሁም የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ኦሕዴድ አራት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን አገደ

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአሥር ቀናት በአዳማ ከተማ ያካሄደውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ፣ አራት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ማገዱን አስታወቀ፡፡

ማክሰኞ ጥር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ላይ ማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ፣ ስማቸው ያልተገለጸ አራት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሚቀጥለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ ታግደው እንዲቆዩ ውሳኔ መተላለፉን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ደግሞ በማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን አመልክቷል፡፡

የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባል የሆኑ 14 አባላቱን በአዲስ ጠንካራ አመራሮች እንዲተኩ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ መወሰኑ ተገልጿል፡፡ ለኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት አዳዲስ አመራሮች እንዲሰየሙ የተወሰነውም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ በተሻለ አቅምና ብቃት ትግል ለማድረግና ድርጅቱ ጥንካሬውን እንዲያጎለብት መሆኑም በመግለጫው ተገልጿል፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአሥር ቀናት ቆይታው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት መወያየቱን መግለጫው ያስረዳል፡፡

አሥር ቀናት በፈጀው ዝርዝር ግምገማው የአገሪቱን ሕዝብ ሰላምና አብሮነት በምንም ሁኔታ አደጋ ውስጥ እንዳይገባ ኦሕዴድና የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ በቅንጅት በመሥራት የአገሪቱን ህልውና እንደሚታደግ፣ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደሆነ በአፅንኦት መወያየቱን አስታውቋል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን በሳይንሳዊ መንገድ በመለየት አፋጣኝ ዕርምጃዎች በመውሰድ፣ የሕዝቡን ፍላጎት ማሳካት ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን በዝርዝር መመልከቱን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲሰፍን፣ አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር፣ ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን በጥብቅ ዲሲፕሊን በመሥራት የሕዝብ እርካታን ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው መሠረታዊ አጀንዳ መሆኑን መምከሩን የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመተባበር የአገሪቱን ቀጣይ ጉዞ የማቅናት ሚናውን ዛሬም እንደ ትናንቱ መጫወት እንደሚገባው ውይይት መደረጉ ተመልክቷል፡፡

በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በዴሞክራሲ አግባብ በማጠናከር የጋራ ዓላማን ለማሳካት ርብርብ ማድረግ፣ የፓርቲዎቹ ግንኙነትም ሕግን ብቻ የተከተለ እንዲሆን፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ የወሰናቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ፣ የአገሪቱንም ህልውና ከአደጋ መከላከል እንደሚገባ በዝርዝር በመምከር አቅጣጫ ማስቀመጡንም አክሏል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣሉ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን፣ ሕዝቡ በመሪ ድርጅቱ ላይ እንዲያመፅ ያደረጉ የመልካም አስተዳደር ዕጦቶችን፣ ሥልጣን ሕዝብን ማገልገያ መሣሪያ መሆኑን በመዘንጋት በርስትነት ይዞ ለግል ምቾትና ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን በነፃነት ተዘዋውሮ የመሥራት መብትን ነፍጎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦችን እስከማፈናቀል የደረሰ ድርጊትን፣ በኢንቨስትመንት ስም የመንግሥትና የሕዝብ መሬት መመዝበሩን፣ እንዲሁም የሕዝቦች ሰላምና ፀጥታ መደፍረስና የመሳሰሉ እየተፈጸሙ ያሉ አደገኛ ድርጊቶችን ሕዝቡን በማሳተፍ አምርሮ በመታገል የአገር ህልውናን መታደግ ልዩ ትኩረት የሚሹ ዓበይት ጉዳዮች እንደተመከረባቸው ተገልጿል፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ጋር ከወቅቱ ፈታኝ ሁኔታ አንፃር ከስሜታዊነት በመውጣት ተቀራርቦና ተደማምጦ አብሮ መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ፣ ኦሕዴድ ለዚህ ዓላማ ቁርጠኛ መሆኑን ማስታወቁ በመግለጫው ተሰምሮበታል፡፡

በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር ውይይት መደረጉን ያወሳው የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ለኦሮሞ ሕዝብ፣ ለኦሮሞ ምሁራን፣ ለኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች፣ ለኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት፣ ለኦሕዴድ አባላት፣ በውጭ አገር ለሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች፣ ለኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በመሥራት የታሰበውን ዓላማ ለማሳካት እንዲቻል ጥሪውን አቅርቧል፡፡