Skip to main content
x
ሕጋዊ  አመራር በሌለው ተቋም ስለፍትሕ ማውራት ለማን?
በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ገጽታ

ሕጋዊ  አመራር በሌለው ተቋም ስለፍትሕ ማውራት ለማን?

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበላይነት ከሚመራቸው ሊጎች መካከል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፤ ከፍተኛ (ሱፐር) ሊግ  እና ብሔራዊ ሊግ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በሁሉም ሊጎች  በጨዋታ ዳኞች ሊሆን ይችላል፣ በሚከሰቱ ስህተቶች ምክንያት የሚደመጡ አስተያየቶችና ትችቶች ከሙያ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ እየሆኑ ቀላል የማይባል ጥፋት እያስከተለ ይገኛል፡፡ የክለብ አመራሮችና አሠልጣኞች በተለይ ውጤት ሲርቃቸው ከሙያ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ ከፋፋይ አስተያየቶችን ጊዜያዊ መሸሸጊያ ካደረጉት ሰነባብተዋል፡፡ 

ለእግር ኳሱ ትልቁ የሥልጣን አካል ተብሎ በሚታመነው ጠቅላላ ጉባዔ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ላለፉት አራት ዓመታት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ሲያስተዳድር የቆየው ሕጋዊው አመራር የአገልግሎት ጊዜውን ካጠናቀቀ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን ያለው አመራር ፌዴሬሽኑን እንዲያስተዳድር ሥልጣኑ የተሰጠው ከማን እንደሆነ እስካሁን በውል አይታወቅም፤ እንዲታወቅ ጥያቄ ማቅረብ የቻለ፣ ይመለከተኛል የሚል አካልም የለም፡፡ ይሁንና ጨዋታዎች በተከናወኑባቸው መድረኮች ሁሉ ውድድሮች ያለውዝግብ፣ ያለአቤቱታ፣ ያለክስና ግርግር ሲጠናቀቁ አይታይም፡፡ የለምም፡፡ ይህንኑ ተከትሎ እየተፈጠረ ያለው ውዝግብና እሰጣ ገባ መልክና ይዘቱ መለወጥ የጀመረበት አጋጣሚም እየተስተዋለ ይገኛል፡፡

የእግር ኳሱ ትልቁ የሥልጣን አካል ተብሎ በሚታመነው ጠቅላላ ጉባዔ ታኅሣሥ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ምርጫ ተደርጎ፣ ሕጋዊ የኃላፊነት ሥልጣኑን መረከብ የነበረበት የፌዴሬሽኑ ምርጫ፣ ወደ ጥር ከዚያም ወደ የካቲት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲሽጋገር ተደርጓል፡፡ ምርጫው አሁንም በተባለው ጊዜና ቦታ ስለመከናወኑ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል የበርካቶች ሥጋት እንደሆነ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የምርጫ አካሄድ ሥርዓትን በመጥቀስ ግለሰቦች “አገር ትቀጣለች” በሚል ሽፋን የራስን ጥቅም በማስቀደም በሚፈጥሩት ሰበባ ሰበብ  እንደሆነም ይታመናል፡፡

በዚህና መሰል ክፍተቶች የክለብ አመራሮችና አሠልጣኞች ከጨዋታ ሽንፈት በኋላ የሚሰጧቸው መግለጫዎች የጎንዮሽ ጉዳቱ በብዙ መልኩ አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸው ከሰሞኑ የሚደመጡ የዘገባ ውጤቶች ያሳያሉ፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ለሪፖርተር የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች ከውጤት ጋር ተያይዞ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለሚስተዋሉ አለመግባባቶችና ግጭቶች አንዱና መሠረታዊ ክፍተት ተብሎ አየቀረበ ያለው የእግር ኳስ ዳኞች የብቃት ጉዳይ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ከዳኝነቱ ባልተናነሰ የጨዋታ ታዛቢ ዳኞችና በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚቋቋሙ በየደረጃው የሚገኙ የፍትሕ አካላትና በአመራር ደረጃ ያሉ ግለሰቦች የሙያ ጣልቃ ገብነት ችግሩ ይበልጥ እንዲወሳሰብም እያደረገው ይገኛል፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከሆነ፣ የእግር ኳስ ዳኞች በተለይም የአንዳንዶቹ ወቅታዊ ብቃት መፍትሔ የማይገኝለት ከሆነ በመንግሥታዊም ይሁን በግል ድርጅት የሚተዳደሩ ክለቦች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ጭምር ይነገራል፡፡ “በእንቅርት ላይ… እንዲሉ፣ እንዲህም ሆኖ አንዳንዶቹ ክለቦች እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ለኅብረተሰቡ በሚሰጡት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እየታየና ስትራቴጂክ ዕቅድ ተቀምጦላቸው ሳይሆን፤ ተቋማቱን በሚመሩ ሥራ አስኪያጆች መልካም ፈቃደኝነት ጭምር እንደሆነ እንዲበተኑ የተደረጉ ክለቦች ተሞክሮ ያሳያል፡፡ ስለሆነም በዳኞች የብቃት ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ሥራ በመሥራት ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርጉ እንደሚገባ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

የጨዋታ ታዛቢ ዳኞችን አስመልክቶ አስተያየት ሰጪዎች፤ እንደ ጨዋታ ዳኞች ሁሉ የጨዋታ ታዛቢ ዳኞችም ከዕድሜ መግፋት ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የብቃት ችግር እንደሚስተዋልባቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ለእነሱ አካሄድ የማይመቹ የክለብ አመራሮችን ወይም አሠልጣኞችን ለመጉዳት አጋጣሚዎችን ፈልገው በጨዋታው አጠቃላይ ሪፖርት ላይ በጨዋታ ወቅት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ምክንያት በማድረግ በይቅርታ የሚታለፉ ወይም የታለፉ ክስተቶችን በማካተት ጭምር ለዲሲፕሊን እንዲቀርቡ በማድረግ የቅጣት ዕርምጃ እንዲጣል የሚያስደርጉ እንዳሉ ይነገራል፡፡ በዚህም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከወዲሁ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን የሚያደርጉ አካላትን በመለየት ተቋሙና ውድድሮች በሥርዓት እንዲመሩ በማድረግ ረገድ የአመራር ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስተያየት ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ውጤት ሲጠፋና ሽንፈት ሲከሰት የችግሩን መንስዔ ሙያዊ በሆነ አካሄድ በመተንተንና ጥናት በማድረግ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ፤ ‹‹ዳኛው የዚያና የዚህ ብሔር በመሆኑ ተበድለናል፡፡ እንዲያውም ለቡድኖች ሽንፈት ብቻ ሳይሆን፣ ለአገሪቱ እግር ኳስ ውድቀትም ተጠያቂዎቹ ዳኞች ናቸው፤›› በሚል በዜጎች መካከል መከፋፈልና ልዩነት እንዲፈጠር የሚያደርጉ የክለብ አመራሮችም ሆነ አሠልጣኞች ካሉ ሕጋዊነቱ እያነጋገረ የሚገኘው አመራርም ቢሆን፣ ለእግር ኳሱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ሲል ጠበቅ ያለ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም የሚያምኑ አሉ፡፡