Skip to main content
x
ዶናልድ ትራምፕንና ሪፐብሊካን ፓርቲን ጥያቄ ያስነሳባቸው አወዛጋቢው ማስታወሻ
ሚስጥራዊው ማስታወሻ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ግፊት ሲያደርጉ የነበሩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያሰቡት ተሳክቷል

ዶናልድ ትራምፕንና ሪፐብሊካን ፓርቲን ጥያቄ ያስነሳባቸው አወዛጋቢው ማስታወሻ

ከምርጫ ክርክር ጊዜያቸው ጀምሮ ውዝግብ ሳይለያቸው እስከ መንበረ ሥልጣናቸው የዘለቁት ዶናልድ ትራምፕ ከራሳቸው አልፎ ፓርቲያቸውን ያስወቀሱባቸው ጊዜያት እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ይኼም ዓርብ ጥር 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይና የኢንተለጀንስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዴቪን ኑንስ ተጽፎ፣ በፕሬዚዳንቱ ይሁንታ ይፋ በተደረገው አወዛጋቢ ማስታወሻ ይበልጥ ጎልቶ ታይቷል፡፡

ዴቪን ኑንስ በኤፍቢአይና በፍትሕ መምርያው የተፈጸሙ የውጭ አገር የመረጃ ማሰባሰብ ሥነ ሥርዓት አሠራር ጥሰቶችን የተመለከተ እንደሆነ፣ ‹‹እጅግ ሚስጥራዊ›› ተብሎ የማስታወሻ ግርጌ ላይ ተሰርዞ ‹‹ይፋ›› የሚል የተጻፈበት ማስታወሻ ያስረዳል፡፡

እንዲህ ዓይነት ሚስጥራዊ ማስታወሻዎች ይፋ ከመደረጋቸው በፊት ለፕሬዚዳንቱ ተልከው መገምገም የሚኖርባቸው ሲሆን፣ ይኼንንም የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከማስታወሻው ጋር ተያይዞ ይፋ ተደርጓል፡፡ የኢንተለጀንስ ኮሚቴ ሰብሳቢው ኑንስ ማስታወሻ በሁለት ዋና ነጥቦች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በዋናነትም በዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ፉክክር ወቅት አማካሪ በነበሩት ካርተር ፔጅ ላይ፣ በውጭ አገር የደኅንነት መረጃ  ማሰባሰብ ሥነ ሥርዓት ፍርድ ቤት የወጣውን በድብቅ መረጃ የማሰባሰብ ማዘዣ አጠያያቅ ላይ ታይተዋል የተባሉ ክፍተቶችን ማሳየት ዓላማው ነው፡፡ የመጀመርያው ማዘዣውን ለማግኘት በሚል የቀረቡ ማስረጃዎች ሆን ተብለው የተወገዱ ይዘቶች ያሏቸው መሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ማስረጃዎቹ ተዓማኒ ባልሆኑ ምንጮች ላይ የተመረኮዙ ናቸው የሚል ነው፡፡

ዶናልድ ትራምፕንና ሪፐብሊካን ፓርቲን ጥያቄ ያስነሳባቸው አወዛጋቢው ማስታወሻ

የምክር ቤቱ የኢንተለጀንስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሪፐብሊካኑ ዴቪን ኑንስ ለሚስጥራዊው ማስታወሻ ዝግጅት ጉልህ ተፅዕኖ ነበራቸው ተብሏል

 

በፔጅ ላይ ምርመራ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ለማሸነፍ በሚያደርጉት ፍልሚያ፣ የእርሳቸው የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ከሩሲያ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማጣራት ሲባል ነበር፡፡ ካርተር ፔጅ ከሩሲያ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ግንኙነት እንደነበረው ለሚዲያ ተናግሯል፡፡

በፔጅ ላይ መረጃዎችን ለማሰባሰብ የሚረዳ አንድ የመጀመርያ ማዘዣ ለኤፍቢአይና ለፍትሕ መምሪያው መሰጠቱንና ሦስት ጊዜ ማዘዣው እንደ ታደሰ ይፋ ያደረገው ማስታወሻው፣ እነዚህን ማዘዣዎች ለመስጠት ለፍርድ ቤቱ የቀረቡ ጥያቄዎችና ማስረጃዎች የተሰበሰቡት ክሪስቶፈር ስቲሊ በተባለ የቀድሞ የእንግሊዝ የደኅንነት ሠራተኛ ነው ይላል፡፡ ለዚህ ሥራውም ግለሰቡ ክፍያ ያገኘው ከቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተፎካካሪ ከነበሩት ዕጩ ተወዳዳሪ ሒላሪ ክሊንተንና ከዴሞክራቶች ብሔራዊ ምክር ቤት እንደነበረ ማስታወሻው ያትታል፡፡ ይሁንና የማዘዣ ጥያቄው ለፍርድ ቤቱ ሲቀርብ ይህ የክፍያ ሁኔታ እንዳልተገለጸና ሆን ተብሎም ፍርድ ቤቱን በማሳሳት ማዘዣ ለማውጣት የተደረገ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

በስቲሊ የተሠራውና ‹‹የስቲሊ ዶሴ›› በሚል የሚታወቀው ሰነድ ሲዘጋጅ፣ በዴሞክራቶች ብሔራዊ ምክር ቤትና በሒላሪ ክሊንተን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን እንደተከፈለበት ምንም መግለጫ አልተሰጠም ይላል ማስታወሻው፡፡ የማዘዣ ጥያቄው ሲቀርብ በስቲሊ የተዘጋጀ እንደሆነ ቢገለጽም፣ ከታወቀ አካል ጋር ተዋውሎ ሥራውን እንዳከናወነው ከመግለጽ በዘለለ ከርሱ ጋር ውል ፈጽመው እያሠሩ ያሉ አካላት እነማን እንደሆኑ ምንም ዓይነት መረጃ አይሰጥም ይላል ማስታወሻው፡፡

ዶናልድ ትራምፕንና ሪፐብሊካን ፓርቲን ጥያቄ ያስነሳባቸው አወዛጋቢው ማስታወሻ
የሩሲያን በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ መግባትን በመመርመር ላይ ያሉት ሮበርት ሙለር የዋይት ሐውስ ሚስጥራዊ ማስታወሻ መውጣትን ተቃውመዋል

 

ከዚህ በተጨማሪ ስቲሊ ለኤፍቢአይ እየሠራ እንደሆነ ለሚዲያ በመናገሩ፣ መረጃዎችን እያሾለከ እንዳለ ተደርሶበት ከኤፍቢአይ እንደታገደና ከሥራውም እንደተሰናበተ የሚያትተው ማስታወሻው፣ ስቲሊ ካሁን ቀደም ለኤፍቢአይ መዋሸቱን በመግለጽ ‹‹የስቲሊ ዶሴ›› ተዓማኒነት የሌለው ሆኖ ሳለ ፍርድ ቤቱን በማሳሳት ማዘዣ እንዲወጣበት ተደርጓል ይላል፡፡

ስቲሊ ከታገደ በኋላ በተደረጉ መረጃዎችን የማመሳከር ሥራ ሲከናወን ከስቲሊ የቀረበው መረጃ ልክ እንዳልነበረ በኤፍቢአይ ተረጋግጧል ይላል፡፡ ከዚህ ባለፈም ስቲሊ ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንት እንዳይሆኑ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ሲናገር እንደነበር፣ ይህም በእርሱ የቀረበው መረጃ ቅቡልነት እጅግ አናሳ እንደሆነ ያመላክታል ተብሏል፡፡

ይሁንና የኑንስ አወዛጋቢ ማስታወሻ አሁን በዶናልድ ትራምፕ ላይ በልዩ መርማሪ ሮበርት ሙለር በሚመራው ቡድን እየተካሄደ ያለውን ምርመራ ለማስተጓጎል ተብሎ የወጣ ነው እየተባለ ይተቻል፡፡ ዴሞክራት የምክር ቤት አባላትም ማስታወሻው መውጣቱን በእጅጉ የተቃወሙ ሲሆን፣ የእነርሱን ማስታወሻም ፕሬዚዳንቱ ይፋ እንዲያደርጉላቸው ግፊት እያደረጉ ነው፡፡

ካርተር ፔጅ ለሩሲያ መንግሥት ይሠራ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም የሚሉት ዴሞክራቶች፣ ኑንስ ያቀረቡት ማስታወሻ ውስጥ የተካተቱ ነጥቦች አሳሳችና ውሸት የታከለባቸው ናቸው ይላሉ፡፡

እንደ ማሳያም ዶናልድ ትራምፕና ሩሲያ ስለነበራቸው ግንኙነት የሚደረገው ምርመራ ማዘዣው ከመውጣቱ እጅግ ቀደም ብሎ እየተካሄደ የነበረ መሆኑን፣ የኤፍቢአይንና የፍትሕ መምሪያውን ስም ለማጠልሸት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ፍርድ ቤቱም ማዘዣውን የሰጠው አሳማኝ ምክንያቶችን ስላገኘ እንደነበረና ከዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ሁለት ሰዎች ጥፋተኛ መባላቸው፣ ሁለት ሰዎች ደግሞ ፍርደኞች መሆናቸው የውሳኔውን ትክክለኛነት ያሳያል ብለው ይከራከራሉ፡፡

ከማስታወሻው መውጣት በኋላ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ‹‹የኑንስ ማስታወሻ እኔ ከሩሲያ ጋር እንደነበርኩ ተብሎ እየተደረገ ካለው ምርመራ ሙሉ በሙሉ ነፃ ያደርገኛል፤›› ሲሉ በትዊተር ገጻቸው የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ባለ ወኔውና ከፍተኛ ጥንካሬ ያላቸው የሪፐብሊካን ተወካዩ ዴቪን ኑንስ፣ ባጋለጡት ጉዳይና ተከትሎ በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት አንድ ቀን የአሜሪካ ጀግና ተብለው የሚወደሱበት ቀን ይመጣል፤›› በማለት አወድሰዋቸዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕንና ሪፐብሊካን ፓርቲን ጥያቄ ያስነሳባቸው አወዛጋቢው ማስታወሻ
የምክር ቤቱ የኢንተለጀንስ ኮሚቴ አባል ዴሞክራቱ አዳም ሺፍ ሚስጥራዊው ማስታወሻ ያልተሟሉ መረጃዎችን ያጨቀ ነው ብለዋል

 

አወዛጋቢውን ማስታወሻ የጻፉት ኑንስ ለፍርድ ቤቱ ቀረቡ የተባሉትን መረጃዎች እንላዩ መናገራቸውም ዶናልድ ትራምፕን ለመደገፍ ሲሉ ያደረጉት ነው የሚል ትችትም አስከትሏል፡፡ ይህም ሊባል የቻለው ኑንስ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሽግግር ኮሚቴ አባል ስለነበሩ ነው፡፡

ከዴሞክራቶች ወገን የማስታወሻውን መውጣት እጅጉን ከተቃወሙት አንዱ አዳም ሺፍ ሲሆኑ፣ ኮሚቴው ይፋ ሊያደርገው ያልወሰነበትን ማስታወሻ ለፕሬዚዳንቱ ልኮ ማስገምገሙና ይሁንታን መጠየቁ አስገራሚ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱን ለመጥቀም ካልሆነም በስተቀር ኤፍቢአይንና የፍትሕ መምሪያውን በሚሳደቡት ፕሬዚዳንት ማስታወሻውን ማስገምገም ልክ እንዳልነበረ ሺፍ አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም ሺፍ የተጻፈውና ለሁሉም ሕዝብ ተወካዮች ይፋ የተደረገው የዴሞክራቶች ማስታወሻ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ግፊት እያደረጉ ነበር፡፡

ይሁንና የኑንስ ማስታወሻ ይፋ መደረጉ በፍትሕ አካላቱ ላይ የተቃጣ ጥቃት እንደሆነ የሚያሳዩት ክርክሮች በስፋት እየተሰሙ ነው፡፡ ምንጮች በዚህ አወዛጋቢ ማስታወሻ ምክንያት ለኤፍቢአይ መረጃ ላይሰጡ ይችላሉም እየተባለ ነው፡፡ 

ዶናልድ ትራምፕንና ሪፐብሊካን ፓርቲን ጥያቄ ያስነሳባቸው አወዛጋቢው ማስታወሻ
የምክር ቤቱ የኢንተለጀንስ ኮሚቴ አባላት ሩሲያ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አድርጋዋለች የተባለውን ጣልቃ ገብነት ላይ ምርመራ ሲያደርጉ