Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ተመልሰው የፓርቲ ስብሰባ ውስጥ ገቡ

ክቡር ሚኒስትሩ ተመልሰው የፓርቲ ስብሰባ ውስጥ ገቡ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • አንተ ምን ዓይነት ሰው ነህ?
 • ምን እያልሽ ነው?
 • በሕይወቴ እንደ አንተ ዓይነት ፈዛዛ ዓይቼ አላውቅም፡፡
 • ምንድነው የምትቀባጥሪው?
 • ለምንድነው ያልነገርከኝ?
 • ስብሰባ እንደምገባ ነው?
 • ስማ የአንተ ስብሰባ ምንም ሲፈይድ አላየንም፡፡
 • ስለምንድነው የምታወሪው?
 • መፈቀዱን ለምን አልነገርከኝም?
 • ሰላማዊ ሠልፍ መቼ ተፈቀደ?
 • እሱንማ ባትፈቅዱም ሕዝቡ እየተሠለፈላችሁ ነው፡፡
 • ስለምን ፈቃድ ነው የምታወሪው?
 • ከቀረጥ ነፃ ዕቃ ማስገባት እንደሚቻል ነዋ፡፡
 • አልሰማሁም እንዳትይኝ?
 • አንተ ካልነገርከኝ ማን ይነግረኛል?
 • ሚዲያ አትከታተይም እንዴ?
 • እንዲህ ዓይነት ነገር በሚዲያ እንደማታወጡማ አውቃለሁ፡፡
 • ለምን አይወጣም?
 • የሚወጣው እኮ የተፈቀደው ሲከለከል ነው፡፡
 • አሁን ማን ይሙት ጓደኞችሽ አልነገሩሽም?
 • እነሱማ ነገሩኝ፡፡
 • ታዲያ ከሰማሽ ለምን እንዲህ ትጨቀጭቂኛለሽ?
 • የከነከነኝ እሱ አይደለም፡፡
 • ምኑ ነው የከነከነሽ?
 • እስካሁን በዕድሉ አለመጠቀሜ ነዋ፡፡
 • ምን እያልሽ ነው?
 • ጓደኞቼ ለሱቃቸው እኮ ዕቃ እያስመጡ ነው፡፡
 • የምን ዕቃ?
 • ይኸው ይህን የቀረጥ ዕድል በመጠቀም አንዴ ከዱባይ አንዴ ከቻይና ዕቃ እያስገቡ አይደል እንዴ?
 • እየቀለድሽ ነው?
 • ምን እቀልዳለሁ፣ ይኸው ጓደኞቼ ከበሩ አይደል እንዴ?
 • ይኼማ ሊሆን አይችልም፡፡
 • ለማንኛውም እኔ ወስኛለሁ፡፡
 • ምንድነው የወሰንሽው?
 • የቀረጥ ነፃ ዕድሉን ተጠቅሜ ላስጭን ነው፡፡
 • ምንድነው የምታስጭኝው?
 • አንድ አርባ ፊት ኮንቴይነር፡፡
 • ምን?
 • እነሱ እንዲያውም የማይረባ ሻንጣ እያስጫኑ ስለተሸወዱ እኔ በአንዴ ኮንቴይነሩን አስጭኜ ብገላገል ይሻለኛል፡፡
 • ሴትዮ ጤነኛ ነሽ?
 • ምን ሆንክ?
 • አንድ ሙሉ ኮንቴይነር ዕቃ አስመጥተሽ አልቀረጥም ልትይ ነው?
 • በመመርያ እኮ ነው የተፈቀደው፡፡
 • ሴትዮ ምንም ሳይገባሽ እኔን ችግር ውስጥ እንዳትከቺኝ?
 • ምን ሆነህ ነው ችግር ውስጥ የምትገባው?
 • ያልሆነ ነገር ለማድረግ ስትሞክሪ መጥፎ ነገር ውስጥ እንዳትገቢ፡፡
 • የተፈቀደ ነገር ነው እኮ ነው የምልህ?
 • ሴትዮ መመርያው በደንብ የገባሽ አልመሰለኝም፡፡
 • በሚገባ ነው የገባኝ፡፡
 • ከገባሽ ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የተፈቀደው ለመንገደኞች ብቻ ነው፡፡
 • እኔም ዕቃውን ከዚህ ሆኜ ሳይሆን የማዘው ሄጄ ነው የምገዛው፡፡
 • ከዚያ ኮንቴይነሩን በአውሮፕላን አንጠልጥለሽ ልታመጪው?
 • እሱንማ ካርጎ ነው የማደርገው፡፡
 • ስለዚህ አንቺ መንገደኛ ሳትሆኚ ነጋዴ ነሽ፡፡
 • አይ መመርያው በደንብ የገባህ አልመሰለኝም፡፡
 • በዚህ የቀረጥ ነፃ መመርያ አንቺም ነፃ መሆንሽን አውቂያለሁ፡፡
 • ከምን?
 • ከዕውቀት!

[ክቡር ሚኒስትሩ መኪናቸው ውስጥ ገብተው ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ምንድነው አንተ ይኼ?
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • መኪናውን ዓይተኸዋል?
 • ምን ሆነ ክቡር ሚኒስትር?
 • ቅድም ምን ብዬህ ነበር?
 • ምን አሉኝ?
 • ቀጠሮ አለኝ ብዬህ አልነበር?
 • ለዚያ እኮ ነው ባሉኝ ሰዓት የመጣሁት፡፡
 • ትልቅ እንግዳ ነው የማገኘው አላልኩህም?
 • ታዲያ ምን አጠፋሁ ክቡር ሚኒስትር?
 • መኪናው ምን እንደሚመስል ዓይተኸዋል?
 • ልጆቹ ኳስ ሲጫወቱ አበላሽተውት ነው፡፡
 • ታዲያ ይኼን እያየህ መኪናውን ይዘህ ትወጣለህ?
 • የቀጠሮው ሰዓት እንዳይረፍድብዎት ብዬ ነው፡፡
 • ከትናንት ጀምሮ ነበር የነገርኩህ፡፡
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዲታጠብ በተደጋጋሚ ነበር የነገርኩህ፡፡
 • እሱማ ታጥቦ መኪና ውስጥ ይዤዋለሁ፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ይኸው ላውንደሪው በአስቸኳይ እንዲያጥበው አድርጌ ይዤዋለሁ እኮ ልብስዎን፡፡
 • ልብሴን መቼ አሳጥብ አልኩህ?
 • ታዲያ ምንድነው ያሉኝ?
 • መኪናዬን አሳጥብ ነው ያልኩህ፡፡
 • ኧረ ልብሴን አሳጥብ ነው ያሉኝ፡፡
 • ከመቼ ጀምሮ ነው አንተ ልብሴን የምታሳጥብልኝ ደግሞ?
 • እኔም ገርሞኝ ነበር፡፡
 • የሚነገርህን ስለማትሰማ እኮ ነው፡፡
 • መስሎኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለመሆኑ አደረስክልኝ?
 • የሚፈልጉት ቦታ አድርሼያቸዋለሁ፡፡
 • ማንን ነው ያደረስከው?
 • ሚስትዎን ነዋ፡፡
 • እኔ የጠየቅኩህ አድርስ ያልኩህን ዶክመንት አደረስክ ወይ?
 • የምን ዶክመንት?
 • ዶክመንት አድርስልኝ አላልኩህም ነበር?
 • አድርስልኝ ሲሉኝ ያው እሳቸውን የሚፈልጉበት ቦታ አድርሻቸዋለሁ፡፡
 • ሰውዬው ማገናዘብ ተስኖሃል እንዴ?
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምትታዘዘውን ነገር አትሰማም ማለት ነው?
 • ኧረ እሰማለሁ፡፡
 • ታዲያ ይኸው ሁለቱንም ያዘዝኩህን አላደረግከውም እኮ?
 • እኔማ የታዘዝኩትን ፈጽሜያለሁ፡፡
 • ያልታዘዝከውን ነው እንጂ የፈጸምከው፡፡
 • ከዚህ በላይ ምን ላድርግ?
 • ትልቅ የኮሙዩኒኬሽን ችግር እንዳለብህ ነው የተረዳሁት፡፡
 • ማን እኔ?
 • እህሳ?
 • የኮሙዩኒኬሽን ችግር ያለበት እኔ ሳልሆን ሌላ ነው፡፡
 • ማን ነው?
 • መንግሥት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ሲወጡ የቀድሞ ወዳጃቸውን አገኟቸው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ጠፉ እኮ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሥራ ወጥሮኝ ነው፡፡
 • ነው የወጠረዎት?
 • ያው የሕዝብ ጥያቄ እየጠጠረ ስለመጣ እኛም ጠጠር ያለ ስብሰባ እያደረግን ነው፡፡
 • ታዲያ አሁን ከየት እየመጡ ነው?
 • ከፓርቲያችን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መውጣቴ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እዚያ ስብሰባ ላይ ነው ስለአገር ጉዳይ ያወራችሁት?
 • በሚገባ እንጂ፡፡
 • እኔ ግን አንድ የማይገባኝ ነገር አለ፡፡
 • ምን?
 • የፓርቲ ስብሰባ ላይ ነው ስለአገር የምትወያዩት?
 • አገሪቷ ምን ዓይነት ችግር ውስጥ እንዳለች ረሳኸው?
 • እሱማ አውቃለሁ፡፡
 • ታዲያ ይኼን ችግር እንኳን ፓርቲዬ ውስጥ ቤተሰቤ ውስጥ ማውራት ይጠበቅብኛል?
 • ክቡር ሚኒስትር የእኔም ነጥብ እሱ ነው፡፡
 • ምንድነው ነጥብህ?
 • እንዴት ነው የፓርቲ ስብሰባ ላይ ስለአገር ጉዳይ የምታወሩት?
 • ምን ችግር አለው?
 • በፓርቲ ስብሰባ እኮ ስለፓርቲውና ስፓርቲው ፕሮግራም ነው መወራት ያለበት፡፡
 • ነገሩ የገባህ አልመሰለኝም?
 • ያልገባዎት እርስዎ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን?
 • ይኸው መቼ ዕለት የፓርቲዎቹ ሊቃነ መናብርት መንግሥት የሚወስነውን ውሳኔ ሲወስኑ ተመለከትን፡፡ 
 • ሰውዬ ተምታቶብሃል ልበል?
 • እናንተ ናችሁ እንጂ የተምታታባችሁ፡፡
 • ምን?
 • ወይ አንደኛችሁን እንደ CPC መሆን ይሻላችኋል?
 • እንደ ምን?
 • እንደ ኮሙዩኒስት ፓርቲ ኦፍ ቻይና፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ያው እነሱ ፓርቲም መንግሥትም አንድ ነው ብለው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡
 • እ. . .
 • አንዴ ዴሞክራሲ፣ ሌላ ጊዜ መድበለ ፓርቲ ምናምን እያላችሁ ሕዝቡን ታምታቱላችሁ፡፡
 • አንተ አንድ ያልገባህ ነገር አለ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ፓርቲና መንግሥት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው፡፡
 • ስለዚህ ለምን አትናገሩም?
 • ምኑን?
 • አንድ መሆናችሁን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ተመልሰው የፓርቲ ስብሰባ ውስጥ ገቡ]

 • ክቡር ሚኒስትር በእርስዎ ጉዳይ ተወያይተናል፡፡
 • ምን ወሰናችሁ?
 • እርስዎ መሰናበት አለብዎት፡፡
 • ምን?
 • በክብር መሸኘት አለብዎት፡፡
 • አልገባኝም?
 • ክቡር ሚኒስትር ከዕለት ወደ ዕለት የሚያጠፉት ጥፋት ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡
 • አሁን ራሳችሁን ከችግር የፀዳ አድርጋችሁ ስታወሩ አታፍሩም?
 • እኛ ንፁህ ነን እያልን ሳይሆን የእርስዎ የባሰ ነው፡፡
 • አሁን እኔን ወህኒ ልታወርዱ?
 • ኧረ በፍፁም፣ እሱማ መዘዝ አለው፡፡
 • ሁላችሁንም ጠራርጎ እንደሚያስገባችሁ ማወቃችሁም ጥሩ ነው፡፡
 • ስለዚህ አይታሰሩም፡፡
 • ምን ልታደርጉ ነው ታዲያ?
 • አገር ስላገለገሉ በክብር ይሸኛሉ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • አገር ላገለገሉበት በደብል ቪ ነው የምንሸኝዎት፡፡
 • ምንድነው ደብል ቪ?
 • ቪ8 እና ቪላ ነዋ፡፡
 • ይህቺን ይወዳል?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ስንቱን ቪ8 ሳገላብጥ አልነበር እንዴ?
 • እ. . .
 • ቪላስ ቢሆን እኔ ጀማሪ ካድሬ አይደለሁ?
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ሥልጣኔን መልቀቅ አልፈልግም፡፡
 • እሱማ አይቀርም፡፡
 • ከለቀቅኩ ደግሞ ባልረባ ነገር ስሜ እንዲነሳ አልፈልግም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • አገራችን እኮ በደብል ዲጂት እያደገች ነው፡፡
 • እናውቃለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ወደፊትም ምናልባት የባህር በር ሊኖረን ይችላል፡፡
 • ምንድነው የሚያወሩት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ የእናንተን ቪ8 እና ቪላ አልፈልግም፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የሚፈልጉት?
 • መርከብ!