Skip to main content
x

የመንግሥትና የጋራ ቤቶችን ማን ይቆጣጠራቸው?

በሒሩት ደበበ

ብዙ ጊዜ የመንግሥት የሚባሉ ነገሮች ሁሉ የጋራ ንብረት ስለሆኑ እንደ ግል ይዞታ ባለቤት ያላቸውና የሚጠበቁ አይደሉም፡፡ እኛን በመሰሉ አገሮች ደግሞ ከሕዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ባህሉ ለጋነትና የእኔነት ስሜት አለመዳበር በመነሳት፣ እንዲሁም የሕዝቡ ንቅተ ህሊናም ስለሚገድብ የዜጎች የባለቤትነት መንፈስ ተዳክሞ መታየቱ አይቀርም፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን እየመጣ ያለው መሻሻል መኖሩ እንጂ በነባሩ አስተሳሰብማ የጋራ ሀብት (የሕዝብ መጠቀሚያም ቢሆን) እንደ ባላንጣ ይዞታ የመቁጠሩ ችግር የከፋና የገነገነ ሆኖ መቆየቱ የታመነ ነው፡፡

በአገራችን በተለይም አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት ቤቶችም እንደ ጋራ ሀብት እየተቆጠሩ ናቸው ለማለት አዳጋች ነው፡፡ በእርግጥ  ጥቂቶች (ቀድመው የያዙዋቸው) እንዳሻቸው ሲጠቀሙባቸው፣ ለብዙኃኑ ግን ባለቤት አልባ ቤቶች ሆነው መታየታቸው ላይገርም ይችላል፡፡ አንዳንዶች ዘመናዊ የመንግሥት ቤት ተከራይተው ዝቅተኛ ኪራይ መክፈላቸው፣ ደፋሩም ከመንግሥት የተከራየውን ቤት በብዙ ዕጥፍ ለሌላ አከራይቶ ሲነግድ ወይም እየተመሳጠረ ቁልፉን ሲሸጥ ለተመለከተ ሕዝባዊ ተቆርቆሪነት መቀነሱ ብቻ ሳይሆን፣ በአንድ አገር ሁለት መንግሥት ያለ ያህል  መሰማቱ አይቀርም፡፡

በተለይ ደግሞ በአንዳንድ ስግብግብ ቤት አከራይ ግለሰቦች እየተፈጠረ ያለው የቤት ኪራይ ጣሪያ መናር ጀርባውን ከሚያጎብጠው ዜጋ አንፃር ድርጊቱ በእጅጉ ያሳምማል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የቀበሌ በሚባሉት የመንግሥት ቤቶች አስተዳዳርና አጠቃቀም ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥት በጀት ተሠርተው ለሕዝብ እየተላለፉ ባሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አስተዳዳርና አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ጉልህ ክፍተቶችን ለመጠቃቀስ ይሞከራል፡፡

ነባሮቹ የኪራይ ቤቶች

‹‹የመንግሥት ቤት›› የሚባለው በአዋጅ ቁጥር 47/1967 ዓ.ም. (በደርግ አዋጅ) የተወረሰና ከ100 ብር በላይ ሊከራይ የሚችል የከተማ ቤት ወይም የፌዴራል መንግሥት ያሠራው፣ ወይም በማንኛውም መንገድ የመንግሥት ንብረት የሆነ በኪራይ ለመኖሪያ፣ ለንግድ ሥራ ወይም ለሌላ አገልግሎት የሚውል ቤት ነው፡፡ አሁን አሁን አብዛኛውን መኖሪያ ይህ ዓይነቱ ቤት የመልሶ ማልማት መርሐ ግብሩ እየደረማመሰው እንጂ ከፍተኛ ችግር ያለበት ዘርፍ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡

አዋጅ 47/1967 በወጣበት ዘመን ከ100 ብር በታች የሚከራይ ቤት በቀበሌ ቤትነት ተመዝግቦ በዚያው መሠረት የሚተዳደር ነበር፡፡ ለነገሩ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም በመንግሥት በተሠሩ ቤቶች የመኖር ዕድል ያጋጠማቸው ዜጎች (በመንግሥት ኃላፊነታቸውም ሆነ በውጭ አገር እንግድነታቸው) እንዳሉም ይታወቃል፡፡ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ዜጎች አንድ ቤት ይዘው መኖራቸው የዜግነት መብታቸው ቢሆንም፣ ከአንድም ሁለትና ሦስት የሕዝብ ሀብት ይዘው ያላግባብ የሚጠቀሙት ግን፣ ሃይ ባይ ሳያገኙ እነሆ እስካሁንም ዘልቀዋል፡፡ ጉዳዩን ማንሳት የሚፈልግ መንግሥታዊ አካል ስለመኖሩ ምልክት አለመታየቱም አስገራሚ ነው፡፡

በአገሪቱ በየከተሞች የመንግሥት ቤቶች የመኖራቸው ዓላማ፣ መንግሥት በሚያወጣው ፖሊሲ መሠረት ፍትሐዊ የመኖሪያም ሆነ የንግድ ቤቶችን በሥራ ላይ ለማዋልና የቤት ችግርን ለማቃለል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የመንግሥት መኖሪያ ቤቶችን ጥቅም ላይ ማዋል አንዱና ዋናው ዓላማና ቀዳሚው ተልዕኮም የዜጎች ተጠቃሚነት መሆኑን መጠራጠር አዳጋች ነው፡፡ ይሁንና የመንግሥት ቤቶችን ኢኮኖሚያዊ ውጤታማነትና ብቃት ባለው መንገድ ለማስተዳደር  ዘመናዊ የሥራ አመራር ሥርዓትን በሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ቤቶችን ለጥቂቶች መጠቀሚያና አፍትሐዊነትን ለማንሰራፋት ማዋል፣ ብሎም ኪራይ የመሰብሰቢያ ዋና መሣሪያ ማድረግ ግን መንግሥትን ከሕዝብ የሚነጥል ተግባር ብቻ ሳይሆን በታሪክም ከመጠየቅ የማያድን ሥራ ነው፡፡

በመሠረቱ መንግሥት እኮ እንኳን በአንድ ወቅት የተወረሱ ቤቶችን በአግባቡ ማስተዳዳር አይደለም፣ አስፈላጊነቱ ሲታመንበት ለመንግሥታዊ አገልግሎት በሚፈለግ መጠን የቤት እጥረትን ለማቃለል በቤቶች ልማት (Real State) ወይም አሁን እንዳለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ግንባታ ሥራ የመሳተፍ ድርሻ አለው፡፡ የመንግሥት ቤቶች በፍትሐዊነት፣ በሕጋዊ ሥርዓትና ቅልጥፍና ባለው መንገድ በሽያጭ እንዲተላለፉ የማድረግ ሥራም ከዚሁ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡

የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ‹‹ለመንግሥታዊ አገልግሎት በሚፈለግ መጠን የቤት እጥረትን ለማቃለል›› ሲባል፣ የሚመለከተው ተቋም በቤት ልማት ሥራ ላይ ይሳተፋል ሲባል፣ ለራሱም ቢሮ ሲያስፈልገው ወይም ለሌላ የመንግሥት አገልግሎት ቤት ሲያስፈልግ፣ ወይም ለተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች (ባለሥልጣናት) መኖሪያ ሲያስፈልግ፣ በሰበብ አስባቡ በቤቱ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎችን በማፈናቀል የሚሠራ ብቻ ሳይሆን፣ ተጨማሪ የቤቶች ልማት ሥራዎችን በማከናወን ችግሩን የማቃለል ዘዴን የመከተል አግባብ ሊኖረው እንደሚገባ ያሳያል፡፡ አሁን አሁን ግን ይህ ዓላማ በምን ያህል የግልጽነትና የተጠያቂነት አግባብ በሥራ ላይ እየዋለ ነው የሚለው ጥያቄ ነው መመለስ ያለበት፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት የሚያስተዳድራቸውን የመንግሥት ቤቶች የማከራየትና ኪራይ የመሰብሰብ ሥልጣን ያለው የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በዚያ ገቢ የመንግሥት ቤቶችን አስፈላጊውን ጥገናና ዕድሳት በማድረግ መጠበቅና መንከባከብ እንዳለበት የሚታወቅ ቢሆንም፣ ምን ያህል እየተሠራበት ነው ብሎ መጠየቅም አስፈላጊ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ግን ስንት ጉድ እንዳለ ነዋሪዎች በምሬት እንደሚያነሱት የሚታወቅ ነው፡፡ በመመርያው መሠረት ቤቱ የሚጠገንለት፣ ውኃው የሚበጅለት፣ ፍሳሽ ማስወገጃው የሚሠራለት፣ የሻገተ ግድግዳው ቀለም የሚቀባለት ስንቱ ነው? ያለ ሙስና ወይም ያለ ከፍተኛ አመራር ምልጃና ተፅዕኖ አገልግሎት ለማግኘት የሚታደለው ምን ያህሉ ነው? የሚለው አብሰክሳኪ ጥያቄ በአግባቡ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

የመንግሥት ቤትን በኪራይ ለማግኘትማ ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡ እንኳንስ ዛሬ ቤት እንዲህ ተወድዶ፣ እንዲሁም ዛሬ መንግሥት ለዘርፈ ብዙ ሥራዎቹ በርካታ ቤቶችና የከተማ ቦታዎች እያስፈለጉት ባለበት ሁኔታ ይቅርና ድሮም ቢሆን የመንግሥት ቤት ለማግኘት በቀላሉ የሚሆን እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ጉዳዩ የፖለቲካ መሣሪያ ሆኖ መቆየቱም ይታወቃል፡፡ ቢያንስ አሁን በጥቂቶች ውሳኔ ሳይሆን፣ የመንግሥት ቤት ለማን? እንዴትና በምን አግባብ ይሰጣል? የሚለውን መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም በግልጽ ማወቅ ነበረበት፡፡

ቀደም ብሎ ስያሜ ቀይሮ የተቋቋመው ‹‹የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ›› እየተባለ ይጠራ የነበረው መሥሪያ ቤት (አሁን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተብሏል) ለዜጐች የሚያስገኘው ጥቅም ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም፣ የተያዙ ቤቶችን በማስለቀቅ ሥራ ላይ የተጠመደ መሆኑን የሚያሳዩ ጠቋሚ ነገሮች አሉ፡፡ የ‹‹ልቀቁልኝ›› ደብዳቤ እየጻፈ ይለጥፋል፡፡ ለእነማን እንደሚሰጥ ግን አይታወቅም፡፡ ይህ ደግሞ ያለጥርጥር የሕዝብ ቅሬታን መቀስቀሱ አይቀርም፡፡

ከተቋሙ ሥልጣንና ተግባር አንዱ በገቡት ውል መሠረት ግዴታቸውን የማይወጡ ተከራዮችንና ምንም ውል ሳይኖራቸው የመንግሥት ቤት የያዙትን በራሱ ውሳኔ የማስለቀቅ፣ እንዳስፈላጊነቱ በመንግሥት ቤቶችና ይዞታዎች ላይ የሚከናወኑ ሕገወጥ ግንባታዎችን የማስፈረስ ሥልጣን ነው፡፡ በመንግሥት ቤቶች ግድግዳዎች ላይ እየተቀጠሉ (እየተጨመሩ) የተሠሩ ስንት ቤቶች አሉ? ተቆጣጣሪዎች የሉም? መጥተው አላዩም? እንዳላየ ዓይተው ወይም በሆነ ብልሹ አሠራር ተግባብተው ትተው አላለፉም? በእጅ ያልሄደውን አላስፈረሱም? ከተቋሙ ምንም ዓይነት ዕውቅና ሳይኖራቸው ውል ሳይዋዋሉና አንዳችም የስምምነት ሰነድ ሳይኖራቸው በመንግሥት ቤቶች ውስጥ የሚኖሩስ አልነበሩም? የሉም? ምን ተደረጉ? ምናቸው ተነካ? እውነት እሱ ሳያውቅ ነው? ይህን ካላወቀስ ሥራው ምን ሊሆን ነው? ቢያንስ በአዋጁ ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባር አንዱን (አንቀጽ 6/3) አልተወጣም ማለት አይደለምን? የሚሉ ጥያቄዎች በዚህ ወሳኝ ወቅት እንኳን ካልተመረመረ መቼ ሊስተካካል ይሆን ያስብላል፡፡

ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው በመንግሥት ቤቶች ዙሪያ መታየት ያለባቸው ብዙ ጉዳዮች መኖራቸውን ለመጠቋቆም እንጂ፣ ሕዝብ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ተቋሙ በዋናነት ለመንግሥት አገልግሎት ሲፈለግ በየሰበቡ ነዋሪዎችን ከየቤቱ ከማፈናቀል ተቆጥቦ ወይም ያቺኑ በፊት የነበረችውን የመንግሥት ቤት ወዲያ ወዲህ እያደረገ ሲያቀራምት ከሚኖር፣ ኮርፖሬሽን ሆኖ ሲቋቋም በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣንና በተመደበለት በጀት በሚፈለገው መጠን እያጠና የቤት እጥረትን ለማቃለል በቤቶች ልማት ሥራ የሚሳተፍበትን መስመር መከተል እንዲችል መጎትጎትም ያስፈለግ ይመስለናል፡፡ በየፎቁ ላይ ‹‹ወደፊት ሊያስፈልጉ ይችላሉ›› በሚል እሳቤ ተዘግተው ያለ አገልግሎት የሚገኙ ቤቶችንም በግልጽነትና በፍትሐዊነት አገልግሎት ላይ ማዋል አለበት፡፡ ይጠበቅበታልም፡፡

አዳዲሶቹ የጋራ መኖሪያ ቤቶች

መንግሥት በተለይ ከ13 ዓመታት ወዲህ ከ170 ሺሕ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ከ800 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ይበል የሚያሰኝ ትልቅ ተግባር ነው፡፡ በእነዚህ ሕንፃዎች ሥር የሚገኙ ከ12 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የንግድ ቤቶችም በጨረታ መሸጣቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ አዳዲስ ከተማ የመመሥረቱ ጉዳይም በሰዎች መካከል ያለው አካላዊ ቅርርብ እያደገና አዕምሯዊ ግንኙነታቸው እየተራራቀ እንዲመጣ እያደረገ ነው፡፡ ከተሜነት የፈጠረውን ይህን አካላዊ ቅርበትና አዕምሯዊ ርቀት ፈረንጆቹ ''Physical Proximity, Mental Disparity'' ይሉታል፡፡ የኮንዶሚኒየም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለከተሞች ዕድገትና ሕዝብን እርስ በርስ በማቀራረብ ረገድ ወሳኝ ሚና መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከተማ ውስጥ መሬት እንደ ልብ  ስለማይገኝ ለመኖሪያ፣ ለእርሻ ሥራ፣ ለከብት ማርቢያ፣ . . . ወዘተ የሚሆን ቦታ ለአንድ ሰው ወይም ቤተሰብ የሚገኝበት ሁኔታም ስለሌለ የፕሮጀክቱ መቀጠል  አስፈላጊ ነው፡፡

እስካሁንም በአዲስ አበባ መንግሥት እየገነባ የቤት ባለቤት ያደረጋቸው ወገኖች  በመንደርም በመሰባሰባቸው፣ አካላዊ ቅርርባቸው (Proximity) ከፍተኛ ነው፡፡ የአንዱ ቤት ከሌላኛው ቤት አይርቅም፡፡ በአንድ ሕንፃ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በአንድ ፎቅ  ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በአንድ የመወጣጫ ደረጃ ወይም አሳንሰር የሚመላለሱ፣ ሲወጡና ሲገቡ የሚገናኙ ናቸው፡፡ የአንድ ቤተሰብ ያህል ናቸው፡፡ ግን ከነባሩ ኢትዮጵያዊ ባህል አንፃር ሕዝቡ ምን ያህል ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቱን በጋራ እየገነባ ነው? የሚለው ጥያቄ በራሱ በሕዝቡና በምሁራንም መፈተሽ አለበት፡፡

በእኔ እምነት ከተሜነት በጋራ መኖሪያ ቤቶች አማካይነት የመቀራረብን ፀጋ ይዞ መምጣቱ እልል ቢያሰኝም፣ በተቀራረቡት ነዋሪዎች መካከል ያለው የሐሳብ ወይም አዕምሯዊ ርቀት (Mental Disparity) ግን የሚያነጋግርና መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም የየራሱን በር ዘግቶ ስለሚቀመጥ እርስ በርሱ አይተዋወቅም፡፡ በሰላም ስለመዋሉና ማደሩ ወይም መክረሙ አይጠያየቅም፡፡ በጋራ ችግሮቹ ላይ አይነጋገርም፡፡ በሐዘንም ሆነ በደስታ አይደራረስም፡፡ አንዱ ስለሌለው ቤተሰብ ምንም ነገር አያውቅም፡፡ ስምና ሥራውን እንኳ አያውቅም፡፡ ለማወቅም አይተጋም፡፡ ይህም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርን የሚጎዳ ለደኅንነትና ለአብሮነት የሚያሠጋ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ሠፈር ውስጥ ባሉት ነዋሪዎች መካከል ያለውን ይህን ሥነ ልቡናዊ የግንኙነት ርቀት ግን ሌቦች አሳምረው ያውቁታል፡፡ በዚህ የተነሳ የተቆለፈውን በር እየፈለቀቁ ነዋሪውን ይዘርፉታል፡፡ የአሁኑ ወቅት የሌብነት ስትራቴጂ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ያነጣጠረውም ያለምክንያት አይደለም፡፡ ስንት ቲቪ፣ ኮምፒዩተር፣ ወርቅ፣ ገንዘብ፣ የኤሌትሮኒክስ ዕቃዎች፣ አልባሳት፣ . . . ከኮንዶሚኒየም እንደተሰረቁ ያልሰማ ሰው ይኖራል ተበሎ አይገመትም፡፡ ስለዚህ እዚህም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡

የገጠሩ ሕዝብ እንኳንስ በአንድ መንደር የሚኖረው ቀርቶ በመንገድ ሲተላለፍ ክንብንቡን ከራሱ ገልጦ፣ ከአንገቱ ጐንበስ ብሎ ለማያውቀው ሰው ጭምር ሰላምታ በመስጠት ይታወቃል፡፡ በሳምንት አንድ ቀን የገበያ ዕለት ሲገናኝም ስለየራሱ ቤተሰብ  ከተጠያየቀ በኋላ ስለሚያውቃቸው ሌሎች ሰዎች ተጠያይቆ፣ ስለከብቱና ስለአዝመራው ተጨዋውቶ፣ ስለአገሩ ጉዳይ የሚያውቀውን ያህል አውርቶ ይለያያል፡፡ ዝም ተባብሎ አይተላለፍም ለማለት ነው፡፡ በቂ መረጃ አለው፡፡ የገጠሩ ሁኔታ የከተሜው ተቃራኒ ነው፡፡ ይህም በተለይ ወደ ፊት እንደ አገር ሊገጥሙን ለሚችሉ የሽብርና ፀረ ሰላም ድርጊቶች በቀላሉ እንዳያጋልጠን ማስተዋል ከሁላችንም የሚጠበቅ ይመስለኛል፡፡

በሌላ በኩል ከተማና ከተሜነት የዘመናዊነት ይዘት ቢኖራቸውም፣ የጋራ መኖርያ ቤቶች አቀራርቦ የማገናኘት የላቀ ሚና ቢኖራቸውም፣ ነዋሪዎቹ ግን በጋራ የመኖርን ዘይቤ ተግባራዊ ለማድረግ ተግዳሮት ሆኖባቸዋል፡፡ አንዱ ስለሌላው የማይጨነቅበት ሁኔታም ብዙ ነው፡፡ የጋራ የሆነውን መተላለፊያ ሥፍራ በቆርቆሮ ግጥም አድርጐ አጥሮ ሲያበቃ መፈናፈኛ የሚያሳጣ ነዋሪ አለ፡፡ የራሱን የቆሻሻ ጥራጊ ከቤቱ አውጥቶ ሌላው ሰው ደጃፍ የሚጥልም እንዲሁ፡፡ ከጣሪያ በላይ ሙዚቃ  እያስጮኸና እሱም አብሮ እየጮኸ የጐረቤቱን ሰላም የሚፈታተንም አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ የለውጥ መዘውርን ይሻሉ፡፡

በአንዳንድ የጋራ ሕንፃዎች ፎቅ ላይ ሆኖ ቡና የሚወቅጥም አለ፡፡ ሕግና ሥርዓት የሌለ ይመስል ሕንፃውን ለኑሮ አመቺ የማያደርጉ ሁኔታዎች ይከሰታሉ፡፡ ለምን? መጀመርያ ነገር አይተዋወቁም፣ ሁለተኛ ነገር በጋራ የሚያሰባስባቸው መድረክ የለም፡፡ እውነት ለመናገር ብዙዎቹ መኖሪያ መንደሮች ጠንካራ ማኅበር የላቸው፣ ዕድር የላቸው፣ ዕቁብ የላቸው፣ ማን የማን ልጅ እንደሆነ አለመተዋወቁ ደግሞ የራሱ ችግር አለው፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርስ ትንኮሳና ጉንተላ አንዱ ነው፡፡  ስድና ልቅ የሆነ ጠባይ ጐልቶ የሚታየው ለዚህ ነው፡፡ ማንም ማንንም ስለማይቆጣጠር ወይም ስለማይመክር፣ ወጣቱ እንደ ልቡ ሆኗል የሚሉ ወገኖች እንደ ሕዝብ ቅሬታ መፈተሽ አለበት ይላሉ፡፡ በተለይ በታችኛው መንግሥታዊ መዋቅር በኩል፡፡

በብዙዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶችና መንደሮች የጫትና የሲጋራ ተጠቃሚነት የሚፈጸመው በግልጽ በአደባባይ ነው፡፡ ከትምህርት ቤት መቅረትና በዩኒፎርም አልባሌ ቦታ መታየት ገሀድ እየሆነ ነው፡፡ ‹‹አንተ የእገሌ ልጅ አይደለህም ወይ? ቆይ ለአባትህ ባልነግርልህ!››፣ ወይም ‹‹ተው ታረም!›› የሚል የለም፡፡ ከያለበት የመሰባሰቡና ያለመተዋወቁ ሁኔታ የፈጠረውን ችግር በየቦታው ዞር ዞር ብሎ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንፃዎች በመቀራረባቸው ቀደም ሲል ብዙም  የማይታወቁ መጥፎ ተግባራት እየተዛመቱ መሆኑን ሁኔታ መኖሩን ተገንዝቦ በጋራ መፍትሔ መሻት ግድ ይለናል፡፡

አነሳሳችን በኮንዶሚኒየም የጋራ መኖሪያ ቤቶች አማካይነት ያገኘነው ተቀራርቦ የመኖር ፀጋ ባለመተዋወቃችን፣ ባለመነጋገራችን፣ የየራሳችንን በር ዘግተን በመቀመጣችን የተነሳ ጉዳት ሊያስከትልብን አይገባም ለማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሚደርስብንን ጉዳት ለመቀነስ፣ ለማስወገድና ችግሩን ለመፍታት ጠንካራ ግን ቀላል ሥራ መሥራት አለብን፡፡ የመጀመርያው ዕርምጃ በችግሩ ላይ ጥልቀት ያለው ጥናትና ምርምር ማድረግ ነው፡፡ በፊት ይኖሩበት በነበረው ሠፈራቸው የነበሩዋቸው ማኅበራዊ ግንኙነቶች ምንድን ናቸው? አሁን የት ደረሱ? ለምን? መታወቅ አለበት፡፡ ይህን ማስተካካል የሚቻለው ደግሞ በመንግሥት፣ በምሁራንና በሕዝቡ የተቀናጀ ጥረትም መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም አዳዲስ ከተማ የመሰሉ መንደሮችንና በርካታ ሕንፃዎችን ከመገንባት ጎን ለጎን፣ በማኅበረሰቡ አዕምሮና በትውልዱ ሞራል ላይም የግንባታ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

በአጠቃላይ ቤት ወሳኝ የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ በመሆኑም በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ የመንግሥትና የሕዝብ የጋራ ቤቶች በፍሐዊነትና በግልጽነት ለዜጎች ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በሥነ ምግባርና በሞራል የታነፀ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት የሚታይባቸው የመኖሪያ መንደሮች እንዲሆኑ በጋራ መትጋት ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡