Skip to main content
x

እየተናጠ ካለው የዓረቡ ዓለም ምን እንማር?

በልዑልሰገድ ግርማ

የመካከለኛው ምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ ቀጣና ከዛሬ ሰባት ዓመት ጀምሮ ነበር በተቃውሞ ሠልፎች፣ አመፆችና በተደራጁ የትጥቅ ትግል ሥልቶች እንደ አዲስ መናጥ የጀመረው፡፡ የእነዚህ እንቅስቃሴዎች ዋና ዓላማ ዜጐች በየአገሮቻቸው ጉዳዮች በባለቤትነት መንፈስ በመሳተፍ አምባገነናዊ ሥርዓቶችን ማስወገድ የነበረ ሲሆን፣ ስኬቱና ውጤቱ ግን አከራካሪ ሆኖ አሁንም ቀጥሎ ይገኛል፡፡

የዓረቡ ዓለም አብዮት እንቅስቃሴ ሲታወስ በፍጥነት ወደ አዕምሮ የሚመጡት አገሮች ቱኒዚያ፣ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ የመንና ሶሪያ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ አገሮች የተነሱባቸውን ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በተለያዩ ዘዴዎች በማዳፈን ለጊዜውም ቢሆን ጋብ እንዲል አድርገዋቸዋል፡፡ መነሻዎቹ በዋነኝነት የአብዛኛው የዓረቡ ዓለም ቤተሰባዊና አምባገነናዊ አገዛዝ፣ የይስሙላ ምርጫዎች፣ የፀጥታ አካላት ጭካኔ፣ ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነትና ሙስና ሲሆኑ፣ ለዘመናት ያለቅጥ በመጠራቀማቸው ፈረንጆቹ ‹‹ጂኒው ከብልቃጡ ውስጥ ወጥቷል›› እንደሚሉት ዓይነት በጣም ሰፊና ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለ ታሪካዊና ሕዝባዊ አመፅ ነው፡፡

ዋነኛው የሕዝብ ጥያቄ የማኅበራዊ ፍትሕ አለመሟላት ቢሆንም፣ አክራሪና ፅንፈኛ እስላማዊ ኃይሎችም ሃይማኖታዊ ሕጐችን ፍፁማዊ በሆነ መንገድ ለመተግበር በሚል ሁኔታውን ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ በተቃዋሚነት ጐራ የተሠለፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መቀናጀትና ለሕዝቡ የሚጠቅሙ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፕሮግራሞችን መንደፍ ተስኗቸው የረባ ውጤት ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡

የዓረቡ ዓለም አብዮት አልተሳካም የሚባለው ለዘመናት የተንሰራፉት አምባገነናዊ መንግሥታት በተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በቀላሉ ይተካሉ ብለው በሚያስቡ አካላት ዘንድ ነው፡፡ የእነዚህ አካላት ዋነኛ ስህተት በሙስና የተጨማለቁ መንግሥታት በወደቁ ማግሥት የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል መጠበቃቸው ነው፡፡ ሆኖም ተጨባጭ ሁኔታው ሲታይ ግን ሥር በሰደደ አለመረጋጋትና የኢኮኖሚ መንገራገጭ የማኅበራዊ ችግሮች መባስ አጋጥሟል፡፡ እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች ውጤታማ የሚሆኑት ከረዥም ጊዜ የለውጥ እንቅስቃሴ በኋላ ሊሆን እንደሚችልም እያመላከቱን ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም የዓረቡ አብዮት የእነዚህ ለውጦችና ግቦች መነሻ እንጂ በራሱ ግብ ሊሆን አይችልም፡፡ የዓረቡ ዓለም አብዮት እንደ ትምህርት ጥሎልን ያለፈው ነገር ቢኖር፣ የዓረቡ ዓለም ሕዝብ ለፖለቲካ ለውጦች ፍላጐት የለውም ተብሎ የሚታሰበውን ማክሸፉና እብሪተኞችና የማይበገሩ ይባሉ የነበሩትን የዓረቡ ዓለም መሪዎች ማነኳኮቱ ናቸው፡፡ ሕዝባዊ ተቃውሞ ባላጋጠማቸው ወይም በዘዴታፈነባቸው አገሮችም ሙያ በልብ በማለት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ጭምር ያደረጉ አሉ፡፡

የዓረቡ ዓለም መሪዎች የሕዝባቸው ቁጥር እጅግ እየጨመረ መምጣቱን፣ ከዚህም ውስጥ ከሁለት ሦስተኛው በላይ ዕድሜው 30 ዓመት በታች መሆኑን በፍፁም አላጤኑትም፡፡ እነርሱ አሳድገነዋል የሚሉት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ልማት ጊዜውን ጠብቆ ከሚፈነዳ ቦምብ አላዳናቸውም፡፡ ሥራቸው አለመረጋጋታቸውንና ጥፋታቸውን የሚያፋጥን ከመሆን አላገዳቸውም፡፡

 

የዓረቡ ዓለም በግራ ዘመም ኃይሎችና በእስላማዊ አክራሪዎች ትግል የሚታወቅ ቢሆንም፣ ሰዶ የቆየውና የሥራ አጥነትና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የፈጠሯቸው ቅሬታዎች ወደ ሕዝባዊመፅነት ተቀይረዋል፡፡ ይህ አመፅ በሥልጣን ላይ የቆዩትን አንጋፋ መሪዎች ሕዝባዊ ቅቡልነት የሌላቸው መሆኑን በግልጽ አሳይቷል፡፡ የዓረቡ ዓለም በዝግታ የቆየው የፀጥታ ተቋማትን ፍራቻና እስላማዊ አክራሪዎች ወደ ሥልጣን እንዳይመጡ ካላቸው ፍራቻ የመነጨ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ የኢኮኖሚ ችግሮች ያስከተሏቸው የሕመም ስሜቶች እኩል ባለመከፋፈላቸውና የተሻለ የወደፊት ሁኔታን ማየት ባለመቻላቸው፣ የዓረቡ ዓለም ሕዝቦች በመሪዎቻቸው ላይ ሊነሱ ችለዋል፡፡ በመንግሥት መር የኢኮኖሚ ልማት ተጠቃሚዎች ጥቂቶች ብቻ ነበሩ፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ወገኖች ጉዳይ አያሳስባቸውም ነበር፡፡

የዓረቡ ዓለም አብዮት የሕዝብ አመፅ መሪ የለሽ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ስኬት የማያስገኝ በመሆኑና የተወሰነ ኃላፊነት የሚወስድ ክፍል ባለመኖሩም ለመንግሥታቱ ጭምር ራስ ምታት ሆና ይቀጥላል፡፡ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ለትግሉ መፋፋም የራሳቸውን አበርክተዋል፡፡ መስጊዶችም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ ዓርብ ዕለት የሚካሄዱ እስላማዊ የስብከትና የፀሎት ሥነ ሥርዓቶች ለትግሉ መነሻ በመሆን አገልግለዋል፡፡ አምባገነኖቹም አሰቃቂ የሆኑ ምላሾችን ሰጥተዋል፡፡ በሊቢያናሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነቶች ተቀስቅስዋል፡፡ ዜጐች እየሞቱ በመጡ ቁጥር አደባባዮች በተቃውሞዎች እየተጥለቀለቁ ሄደዋል፡፡ ከአገር አገር የመስፋፋት ሁኔታው እየተባባሰ መጣ፡፡ እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2011 የቱኒዚያው አምባገነን መሪ መውደቅና በወሩ የግብፅ ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን መውረድ የፍራቻ ግንቡን ከማፍረሱ ባሻገር፣ አሁን የምናየውን የመካከለኛ ምሥራቅ ፖለቲካዊ ሁኔታ ለመፍጠር ችሏል፡፡

የዓረቡ አብዮት መጨረሻ የማይታወቅ ቢሆንም ጥልቅና ያልታሰቡ ውጤቶችን አስከትሏል፡፡ የተጀመረው አብዮት በአጭር ጊዜ ሊቋጭ የማይችል የፖለቲካና ማኅበራዊ ለውጥ ጅማሮ ነው፡፡ ከመጡት ለውጦች አንዱና ዋነኛው መጠየቅ ያልለመዱትን አምባገነናዊ መንግሥታት ዕድሜ ማሳጠሩ የሚጠቀስ ነው፡፡ መንግሥታቱ በወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣ ወይም በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት አልተወገዱም፡፡ የሕዝብ ቁጣ በተለይም በዓረቡ ዓለም የመንግሥታትን የደም ሥር መቁረጥ እንደሚችል አረጋግጧል፡፡ የሕዝብ ኃይል በቱኒዚያ፣ግብፅ፣ሊቢያናየመን አምባገነኖቹን አስወግዷል፡፡ አምባገነን መንግሥታቱ በአብዛኛው አሁንም ሥልጣን ላይ ያሉ ቢሆንም፣ የሕዝብ አመፅ እስከ ምን ሊያደርስ እንደሚችል የተገነዘቡበት ጊዜ ነው፡፡ ሙስና፣ የእኩልነት አለመኖርና የደኅንነትና የፖሊስ ተቋሞቻቸው ጨካኝነት ሕዝብን እንደሚያስነሳ በመገንዘብ ተመጣጣኝ ባይሆንም ለውጦችን እያየን እንገኛለን፡፡ በቅርቡ በሳዑዲ ዓረቢያ እየተከናወነ ያለው ለውጥ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ሁነኛ ምሳሌ ነው፡፡

በመንግሥት በተወገደባቸው አገሮች ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈልፍለዋል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡና የሚዲያ አባላትም በዝተዋል፡፡ ታፍኖ በቆየ ማኅበረሰብ ውስጥ ይኼ መከሰቱ አይገርምም፡፡ የዚሁ ሁሉ ሁኔታ መፈጠር አማራጮችን እንደ አሸን ቢያፈላውም፣ ለመራጮች ግን የራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡ የተቃዋሚዎች መብዛትና የአክራሪዎች ትርምስ ለቀጣናው አለመረጋጋት የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ ነገሩ እስኪረጋጋና አዲስ ፍጥረት የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሳል ደረጃ እስኪደርሱ ምን ያህል ጊዜ ይፈጅ ይሆን?

የመንግሥት አስተዳደር ዓለማዊ ይሁን የሚል ካምፕ እንዳለ ሁሉ፣ በእስላማዊ ሕግ መመራት አለበት የሚሉ ፅንፈኛ አካላትም ከምንጊዜውም በላይ ተጋግሎ ይገኛል፡፡ ይህም ሁኔታ ጥልቅ አለመተማመንን እየፈጠረ ነው፡፡ የመነጋገርና የመደራደር መንፈሶች እየራቁ ይገኛሉ፡፡ አንዱ ወገን ብቻውን አሸናፊ መሆን ይፈልጋል፡፡ ለዜሮ ድምር ፖለቲካ በር ይከፍታል፡፡ ለዚህም ነው የዓረቡ ዓለም አብዮት በአጭሩ የማይቋጭ ነው የሚባለው፡፡ ተቃዋሚዎች ሥልታዊ ትግል ማካሄድ አልቻሉም፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነት በጠነከረባቸው አገሮችም የተራዘመ የእርስ በርስ ጦርነት ተለኩሶ ይገኛል፡፡ ሊቢያ፣ ሶሪያና የመን ወደ ገኃነምነት ተለውጠዋል፡፡

የዓረቡ ዓለም አብዮት በሱኒና በሺዓ ሙስሊሞች መካከል ያለው አለመግባባት ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ አድርጓል፡፡ በሶሪያ ያለው የእርስ በርስ ጦርነትና የውጭ ጣልቃ ገብነት በዚህ አስተሳሰብና አሠላለፍ ተሰድረው ይገኛል፡፡ የአሜሪካ ከቀጣናው የሱኒ ኃይሎች ጋር መሠለፍ፣ እንዲሁም የሱኒ ታጣቂዎችን መርዳት በአንድ በኩልሩሲያ ከሶሪያ መንግሥትና ከኢራን ጋር በማበር የአሳድን መንግሥት ዕድሜ የማራዘም ፕሮጀክት መሳካት፣ በሌላ በኩል የሱኒ ሺዓ ውጥረትን ከፍ ከማድረግ ባሻገር ትርፍ አላስገኘም፡፡ አንዱ የራሱን የበላይነት ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት ቀጣናውን ወደ ባሰ አዙሪት ውስጥ ከትቶታል፡፡

አሁን በቀጣናው ያለው እንቅስቃሴአብዛኛውን ሕዝብ የኢኮኖሚ ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ ላይ አይደለም፡፡ ተቃዎሚዎች በሁለት እግሮቻቸው መቆም ባልቻሉባቸውና የእርስ በርስ ጦርነት እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ፣ ስለኢንቨስትመንትና ስለቱሪዝም ፍሰት ማሰብ አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ክልሉ ተረጋግቶ ለሕዝብ ጥቅም የሚውል የኢኮኖሚ ዕድገት በቅርቡ የሚጠበቅ አይሆንም፡፡

የተጠራቀሙ ብሶቶች ድንገት ሊፈነዱ እንደሚችሉና ለአገርም ጥፋት አስተዋጽኦ ሊያበርክቱ እንደሚችሉ ከዓረቡ ዓለም ትግል እየተማርን እንገኛለን፡፡ ይህ ትግል መሪ የሌለውና ያልተደራጀ በመሆኑ ምክንያት ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ለአክራሪ ቡድኖች መርመስመስ ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር ችሏል፡፡ በመሆኑም ግብታዊ የሆነ ሕዝባዊ አመፅ መቋጫ ለሌለው የእርስ በርስ ጦርነት እንደሚዳርግ ተገንዝበናል፡፡ እነዚህ አገሮች ለዚህ የተዳረጉት የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ዕጦት ስለደረሰባቸው መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ባሉባቸው አገሮች መሠረታዊ አገልግሎቶች የተሟሉ ስለሚሆኑ የተሻለ ኑሮ ማየት ይቻላል፡፡

በተቃራኒው በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ የእነዚህ ተቋማት አለመኖር የዴሞክራሲናሰብዓዊ መብቶች፣ እሴቶችና መርሆዎች እንዳይስፋፉ አድርጓል፡፡ ስለሕገ መንግሥታዊና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማሰብ አይቻልም፡፡ ምርጫዎች በየተወሰነ ጊዜ ቢካሄዱም የይስሙላ ይሆናሉ፡፡ የፍትሕ አካሉ ነፃነት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ የዴሞክራሲ ባህልና ልምድ አይዳብርም፡፡ ውጤታማ የሆኑ አካባቢያዊና አኅጉራዊ ውህደቶችን ማሰብ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሙስናን መዋጋት አይቻልም፡፡ በአጠቃላይም እነዚህ ሁኔታዎች ሥልጣንን ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ መያዝን ስለሚያስመኙ ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ደኅንነት አደጋ ሆኖ ይኖራል፡፡

አፍቅሮተ መሪነት የተጠናወታቸው አገሮችና አክራሪዎች በፈጠሩት ትርምስ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ሥፍራዎች ሳይቀሩ ወደ ዶግ አመድነት ተቀይረዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ አክራሪና እስላማዊ ድርጅቶች እስላማዊ መንግሥታትን ለመመሥረት ሙስሊሞችን ሳይቀር አርደዋል፣ አቃጥለዋል፣ እንዲሰደዱም አድርገዋል፡፡ የሚፈለገው የአስተዳደር ዘይቤም ሰማይ ላይ የተሰቀለ ዳቦ ሆኖባቸዋል፡፡የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች› እንደሚሉት አምባገነኖችን ለማስወገድ በተጀመረው ትግል ሰላም ጠፍቷል፣ ኢኮኖሚም ደቋል፡፡ ሕዝብ በኮሌራ ረግፏል፡፡ በኃያላን አገሮችም ሆነ በቀጣናው አገሮች መካከል ያለው ጥላቻ ከሯል፡፡ እየተሰደዱና እየሞቱ ካሉት የመካከለኛው ምሥራቅ ዜጐች ይልቅ፣ የእነዚህ አገሮች ጂኦፖለቲካ ፍላጐት ሁነኛፍራ አግኝቷል፡፡ የዜጐች የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ወደ ጐን ተትቶ የአገሮቹ ጂኦፖለቲካዊ ፍላጐት አይሎና የመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ማጥፊያናቃይ ማራዘሚያ ሆኖ ይገኛል፡፡ ኃያላኑበርካታ የጦር መሣሪያዎች መሸጫና የአዳዲስ መሣሪያዎች መሞከሪያ መናኸሪያም አድርገውታል፡፡

በቅርቡ አሜሪካ ለሶሪያ ኩርዶች ይፋ ያደረገችው የፖለቲካና የትጥቅ ድጋፍ፣ እንዲሁም ቱርክ ኩርዶችን ለማጥፋት እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ የፀጥታ ማደፍረሱ ማራዘሚያ ሥልቶች ናቸው፡፡ የአሳድ መንግሥት ይወገድና አይወገድ አጀንዳዎች የኃያላኑ አገሮች መፋጠጫ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቀውስ መነሻው ግን የዴሞክራሲ ዕጦትና ብዝኃነትን ያለማስተናገድ የአምባገነኖቹ የመጥፎ አገዛዝ አካሄድ ነው፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ ከረዥም ጊዜያት ጀምረው ተንከባለው የመጡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየሄድንበት ያለው መንገድ አንድነታችንንና ሰላማችንን እየተፈታተነ ነው፡፡ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በሙስና ውስጥ መዘፈቅና የአንዳንድ ተቃዋሚዎች ከ‹‹የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው›› የትግል ሥልት አለመውጣት ለሕዝብ አይጠቅምም፡፡ የእርስ በርስ ጦርነት ድህነትን ከማባባስ ያለፈ ጥቅም እንደሌለው ከእኛ በላይ መስካሪ አይኖርም፡፡ በመሆኑም አሁን ያለንበትን ጊዜ ቆም ብለን በመመካከርና በመደማመጥ መጓዝን ከምንጊዜውም በላይ የተማርንበት ሲሆን፣ በዚህም የዓረቡ ዓለም ከገባበት መያዣና (መጨበጫ ከሌለውና ዜጐችን በከፍተኛ ሁኔታ ለሞትና ለስደት ከሚዳርግ የትግል ሥልት የምንጠበቅበት ጊዜ መሆን አለበት፡፡ እዚህም እዚያም የተጀማመሩና ለአገር ግንባታ የሚጠቅሙ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚችሉት መደማመጥ ሲኖር ብቻ ነው፡፡

በሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ አሁን ላሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጣቱን ወደ ራሱ መቀሰሩ፣ የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ድርድር መጠነኛም ቢሆን ለውጥ እያመጣ መሄዱ፣ መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት የተለያዩ ማሻሻያዎችን ለማድረግና ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ ችሎታው ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ ለማድረግ ቃል መግባቱ ተስፋ ሰጪ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሕዝብም (በተለይም ወጣቱ) በአንድ ጀንበር የሚለወጥ ነገር አለመኖሩ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ የትግል ሥልቶችን ተግባራዊ በማድረግ፣ የዓረቡ ዓለም የደረሰበትን የሰላም ዕጦት እዚህ እንዳይከሰት መጣር አለበት፡፡ የመልካም አስተዳደርም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚመጣው ሁሉም በሰከነ መንፈስ ሰላማዊ ጐዳናን ሲከተል ብቻ ነው፡፡

 ከአዘጋጁ- ጸሐፊው በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ የጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected].  ማግኘት ይቻላል፡፡