Skip to main content
x

ትራንስፖርት ባለሥልጣን በስድስት ወራት ከ4.5 ሚሊዮን ሜትሪክ በላይ ጭነት መጓጓዙን አስታወቀ

  • የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ማኅበራት ባለሥልጣኑን ወቅሰዋል

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በአገሪቱ ትራንስፖርት ዘርፍ ስለነበሩ አፈጻጸሞች ባስደመጠው ሪፖርት መሠረት ከጂቡቲ ወደ አገር ውስጥ ተጓጉዘው የገቡ ጭነቶች ብዛት ከ4.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ እንደነበሩ አስታውቋል፡፡

ባለሥልጣኑ ዓርብ የካቲት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ሌሎች ክንውኖቹን በማስመልከትም ባስደመጠው ሪፖርቱ መሠረት፣ ከዚህ ቀደም ስድስት ወራት ይፈጅ የነበረው የዕጩ አሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃድ ለማውጣት የሚወስዱት ፈተና እና ውጤቱን ለማወቅ ይጠብቁ የነበረውን ጊዜ ወደ 10 ቀናት ዝቅ ማድረጉ ከዋና ዋና ክንውኖች መካከል ተጠቅሷል፡፡

አደጋን በሚመለከት 12,340 የሲኖትራክና 3,883 ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች የአደጋ መንስዔ መሆናቸው ሲገለጽ፣ በትራፊክ አደጋ ሳቢያ በስድስት ወራት ውስጥ በሰዎች ሕይወትና አካል ላይ የደረሰው ጉዳትም ከዓምናው ይልቅ ተባብሶ መታየቱን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም 2,315 ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ፣ 269 ሰዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት፣ 553 ሰዎች ላይ መካከለኛ እንዲሁም 718 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. 2,046 ሰዎች ለሞት የተዳረጉ በመሆናቸው ዘንድሮ ከዓምናው ይልቅ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሞት አደጋ መመዝገቡን ባለሥልጣኑ የፌደራል ፖሊስ መረጃን ዋቢ አድርጓል፡፡ በንብረት ረገድም ዘንድሮ ከ266 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት ማጋጠሙን፣ በአንፃሩ በ2009 ዓ.ም. ከተዘገበው የ460 ሚሊዮን ብር ጉዳት አኳያ ሲታይ የዚህ ዓመት የንብረት ጉዳትና ኪሳራ ሊያሻቅብ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ በኦሮሚያ ክልል ከ25 ሺሕ በላይና በደቡብ ክልል ከ15 ሺሕ በላይ የኮንትሮባንድ ሥራ የሚከናወንባቸው ሞተር ብስክሌቶች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና እንዲህ ያለውን ሕገወጥነት ለመከላከል ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

ከስድስት ወራት ክንውኑ ባሻገር በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ስለተባሉ ሥራዎችና በሕዝቡ ዘንድ ችግር ሆነው በመታየታቸው ፖለቲካዊ መፍትሔ ጭምር እንደተቀመጠላቸው የተጠቀሱ ዕቅዶችም እንደሚተገበሩ፣ በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም በተመራው ስብሰባ ወቅት ሲገለጽ ተደምጧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ስብሰባውን በማስመልከት የዕለቱ አጀንዳ በስድስት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርትና በመጪዎቹ ወራት ስለሚሠሩ ሥራዎች ለመወያየት የተጠራ ስለመሆኑ አቶ ካሳሁን ለተሰብሳቢው በገለጹበት ወቅት ከታዳሚው ወቀሳ ቀርቦባቸዋል፡፡ የጭነት ትራንስፖርት ማኅበራትን ወይም የሕዝብ ክንፍ የሚባሉትን አካላት በመወከል እንደተገኙ የገለጹ ታዳሚ፣ ለስብሰባው የተገኙት ስለደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ችግሮችና የዘርፉ ተዋናዮች የሚያቀርቧቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች ላይ ለመነጋገር እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም በተደረገ ስብሰባ በሁሉም የሕዝብ ክንፍና ባለድርሻ አካላት በሚነሱ ችግሮች ላይ ለመነጋገር እንጂ የስድስት ወራት ሪፖርት ግምገማ እንደሚኖር አልተነገረንም፡፡ ስለአጀንዳውም የሰማነው አሁን ነው፤›› በማለት ቅሬታ ያሰሙ ተሰብሳቢ፣ ‹‹ሪፖርት ለማድመጥ አልመጣንም፤›› በማለት ባለሥልጣኑን ወቅሰዋል፡፡

በዚህ ያልተወሰኑት ቅሬታ አቅራቢ ‹‹ቆጥራችሁ ባልሰጣችሁን ሥራ ለምን ሪፖርት ስሙ ትሉናላችሁ?›› በማለት ጠይቀው፣ ‹‹እዚህ ያለው ኮርፖሬት ሲቲዝን ነው፡፡ እንደ ድሮው አይደለንም፡፡ እንሞግታችኋለን፡፡ የሥራ ክፍፍል ቢኖርም ይህ አገር የሁላችንም ነው፤›› በማለት የከረረ ቅሬታና ወቀሳቸውን አሰምተዋል፡፡

አቶ ካሳሁን በበኩላቸው የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት የሚቀርብበት መድረክ እንዲጠራ የተደረገው የጭነት ትራንስፖርት ማኅበራት ያቀረቡት ጥያቄ ቸል ተብሎ ሳይሆን፣ የደረቅ ጭነት ዘርፉን የሚመሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በስብሰባ ምክንያት መገኘት ስላልቻሉና የእሳቸው መገኘትም ግዴታ በመሆኑ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንደተያዘ አስረድተዋል፡፡

ከሳምንት በፊት በተጠራ ስብሰባ የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ማኅበራት በዘርፉ ስለሚገጥሟቸው ችግሮች መወያየታቸውን ያስታወሱት አቶ ካሳሁን፣ ከባለሥልጣኑ ጋር ስለችግሮቻቸው ለመነጋገር መፈለጋቸውንና ለዚህም ቀጠሮ እንዲያዝላቸው ስለመጠየቃቸው ሪፖርት እንደደረሳቸው ጠቅሰዋል፡፡

በአገሪቱ ከ140 በላይ የጭነት ትራንስፖርት ላይ የተሠማሩ ባለሀብቶችን የሚወክሉ ማኅበራትና 18 አገር አቋራጭ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለንብረቶች የመሠረቷቸው ማኅበራት እንዳሉ አቶ ካሳሁን ጠቅሰዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የትራንስፖርት አገልግሎትን በማኅበር የመምራት ሥራን በማስቀረት ባለሀብቶች በኩባንያ ደረጃ እንዲደራጁ የማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል በቀረበለት ትልመ ሐሳብ መሠረት ይህንን አሠራር ለመተግበር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡