Skip to main content
x
በአዳማ ከፕላስቲክ የውኃ ጠርሙሶች ቪላ ቤት ተገነባ

በአዳማ ከፕላስቲክ የውኃ ጠርሙሶች ቪላ ቤት ተገነባ

ሲምኮን ቴክኖሎጂስ የተባለ አገር በቀል ኩባንያ፣ አገልግሎታቸውን የጨረሱ  የውኃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙሶችን በመጠቀም ያስገነባውን ዘመናዊ ቪላ ቤት ለአገልግሎት አበቃ፡፡

ኩባንያው ለአገሪቱ እንግዳ የሆነውንና ለአካባቢ ጥበቃ ፋይዳ ያለውን አሠራር በመጠቀም፣ ከተጣሉ የውኃ መያዣ ፕላስቲክ ጠርሙሶች የተሠራው ሞዴል ቪላ ቤት የተገነባው በአዳማ ከተማ ነው፡፡ የፕላስቲክ ጠርሙስ ቪላ ቤቱ ሐሙስ፣ የካቲት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሕዝብ ዕይታ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በመቶ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ቪላ ቤት፣ ለግንባታው ከ53 ሺሕ በላይ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ጠይቋል፡፡ የቪላ ቤቱን ግንባታ ለማጠናቀቅ የጠየቀው አጠቃላይ ወጪ 345 ሺሕ ብር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ግንባታውን ለማጠናቀቅም ሦስት ሳምንታት ብቻ እንደፈጀ ኩባንያው አስታውቋል፡፡

በሲምኮን ቴክኖሎጂስ የተሠራው ቪላ ቤት በብሎኬት ቢገነባ ኖሮ ከ1.2  ሚሊዮን ብር በላይ ያስወጣ እንደነበር የስማርት ማኔጅመንት ሰርቪስስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዲል አብደላ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል፡፡ ሦስት መኝታ ቤቶች፣ አንድ ሳሎን፣ ሁለት መፀዳጃ ክፍሎችና አንድ የማዕድ ቤት ያሉት ይህ ቪላ በ345 ሺሕ ብር ብቻ መጠናቀቁ ከዋጋ ባሻገር ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተብራርቷል፡፡

በዚህ የግንባታ ዘዴ ዓለም አቀፍ ጥናቶችን አጣቅሰው፣ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን አፈር በመሙላት የሚሠራ ቤት የጥንካሬ ደረጃው ከመደበኛው የሸክላ ቤት አንፃር በ20 እጥፍ እንደሚልቅ የሚያብራሩ መረጃዎች እንዳሉ የኩባንያው መግለጫ ያስረዳል፡፡ የጥንካሬ ደረጃው በጥናት እንደተጠቀሰው፣ በአንድ ካሬ ሜትር 438,977 ኪሎ ግራም መሸከም እንደሚችል የሚያብራሩት አዲል፣ ቤቱ የተገነባው በአፈር ከተሞላ ፕላስቲክ ከመሆኑ አንፃር በጥይት የማይበሳ፣ እሳት ቢነሳም በራሱ ጊዜ የማጥፋት አቅም እንዳለው ተጠቅሷል፡፡

የፕላስቲክ ጠርሙሶችን አፈር በመሙላት የሚሠራ ቤት በተፈጥሮ የቤት ሙቀትን የሚያመጣጥን፣ በሞቃት አካባቢዎች የቤት ውስጥ የሙቀት መጠንን ለመቆጣጠር ሁነኛ አማራጭ ስለመሆኑም ተነግሮለታል፡፡ እንዲሁም የቤት ውስጥ የሙቀት መጠኑም ከ18 ዲግሪ ሴሊሺየስ የማይበልጥ በመሆኑና እስከ 1.5 ሜትር ድረስ ባለው ከፍታ ጎርፍ የማያስገባ መሆኑ፣ በኃይለኛ ነፋስ ወቅት ማለትም እስከ 200 ኪሎ ሜትር በሰዓት የሚጓዝ ጉልበተኛ ነፋስን የመቋቋም አቅም እንዳለው ተብራርቷል፡፡

በአዳማ ከተማ የተገነባው የፕላስቲክ ጠርሙስ ቪላ ቤት ዕውን ለማድረግ፣ ከመሠረት ግንባታ ጀምሮ ቁራጭ ብረትም ሆነ ድንጋይ ጥቅም ላይ ያልዋለ ሲሆን፣ በማንኛውም መደበኛ ቤቶች ውስጥ መገኘት የሚገባቸውን ነገሮችን ሁሉ ያካተተ ነው፡፡

የኩባንያው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ይህ ዓይነቱ የቤት ግንባታ ዘዴ፣ በላቲን አሜሪካና በህንድ ሲሠራበት የቆየ ነው፡፡ ከአገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዋሃድ የግንባታ ዘዴውን በኢትዮጵያ ለማስለመድ፣ ለቤት ገንቢዎች አማራጭ በማቅረብ በዚህ መንገድ የሚገነቡ ቤቶችን ከአስገንቢዎች ጋር በመሆን እንደሚገነባም አስታውቋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ ከመጣው የአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ አገልግሎታቸውን ጨርሰው የሚጣሉ የፕላስቲክ ውጤቶች ተጠቃሽ በመሆናቸው በተለይ ከውኃ አምራቾች መበራከት ጋር በተያያዘ ለበርካታ መቶ ዓመታት የማይበሰብሱትን የፕላስቲክ ጠርሙሶች ለዚህ ዓይነቱ ዓላማ ማዋሉ ጠቀሜታውን የጎላ ያደርገዋል ተብሏል፡፡

ሥራው ከመጀመሩ በፊት የቤቱን ዲዛይን ከመደበኛ ጠቅላላ ወጪው ጭምር በባለሙያ የተሠራው የቪላ ዲዛይን፣ በፕላስቲክ ጠርሙሶች ለማከናወን የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥመው እንደነበርም ተገልጿል፡፡ ሐሳቡን ዕውን ከማድረግ አንፃር በግንባታ መሐንዲሶች ጭምር ተቀባይነት ለማግኘት ጊዜ ወስዶ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ሲምኮን ቴክኖሎጂስ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት (ፓተንት) ለማግኘት ለኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ማመልከቻ አቅርቦ የአዕምሮ ንብረት ጥበቃ ለማግኘት በሒደት ላይ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ፈቃዱም በዚህ ቴክኖሎጂ የሚገነቡ ግንባታዎችን በባለቤትነት ለማስተዳደር እንደሚያስችለው አዲል ገልጸዋል፡፡

በኢንጂነሪንግ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ዓላማ በመያዝ 2008 ዓ.ም. የተመሠረተው ሲምኮን ቴክኖሎጂስ፣ ቀደም ሲል የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት ያገኘበትን አሸዋን ከአፈር በመደባለቅ አዲስ የእምነበረድ ምርት ቃሊቲ አካባቢ በሚገኘው ፋብሪካው እያመረተ ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

በስማርት ማኔጅመንት ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥር ከሚገኙ 12 ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ኩባንያ፣ ከአሥር ዓመታት በላይ በሥራ ላይ ከሚገኙ ኩባንያዎች ውስጥ በትምህርት፣ በግብርናና አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በሆቴል፣ በፈጣን ምግብ ማዕከላት፣ በአምራችና መስኮችና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ የተሠማሩ ኩባንያዎችን የሚያስተዳድር ነው፡፡