Skip to main content
x
የተምች ወረርሽኝ በዚህ ዓመት ከፍተኛ አደጋ መደቀኑ ተገለጸ

የተምች ወረርሽኝ በዚህ ዓመት ከፍተኛ አደጋ መደቀኑ ተገለጸ

  • ከእንግዲህም በቀላሉ ከኢትዮጵያ እንደማይወጣ ባለሙያዎች አስታውቀዋል

ምንጩ ከወደ ፓስፊክ አገሮች፣ ማዕከላዊ አሜሪካ ከመሆኑም በላይ የአሜሪካ የፀደይ ወራት ስያሜ በመያዝና በዩኤስ አሜሪካም ተንሰራፍቶ እንደሚገኝ የሚጠቀስለትና ‹‹ፎል አርሚዎርም›› በመባል የሚጠራው የተምች ወረርሽኝ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮችን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አዳርሶ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም  ካለፈው ዓመት የበለጠ ጥፋት በኢትዮጵያ ሊያስከትል እንደሚችል ተገምቷል፡፡

በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስአይዲ) አማካይነት በሚመራው ፊድ ዘ ፊውቸር የኢትዮጵያ እሴት ሰንሰለት ፕሮግራም ቺፍ ኦፍ ስታፍ ኢያን ቼስተርማን ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት እንዳስታወቁት፣ የተምች ወረርሽኙ የአገሪቱን ሰብሎች በመላመዱና የአየሩ ጠባይ ለመራባት ምቹ ስለሆነለት በዚህ ዓመት ሊያደርስ የሚችለው ጥፋት ካለፈው ዓመት ይልቅ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

በአገሪቱ በተለይም በበቆሎ ሰብል ምርት በሚታወቁ አካባቢዎች እየተዛመተ የሚገኘው የተምች ወረርኝ፣ በበቆሎ እርሻ የሚተዳደሩ አሥር ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ህልውና የመፈታተን አቅም ላይ ደርሷል ያሉት ቼስተርማን፣ በዚህ ዓመት ሊደርስ የሚችለው የሰብል ጥፋት በገበሬዎች ከሚመረተው ግማሽ ያህል ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

በአገሪቱ የተንሰራፋው ተምች፣ በመጀመሪያ የታወቀው በደቡብ ክልል ሲሆን፣ በወቅቱ 30 በመቶ ሰብል ማጥፋቱን፣ በኦሮሚያ 25 በመቶ፣ በአማራ ክልል 20 በመቶ እንዲሁም በትግራይ ክልል 12 በመቶ የሰብል ምርት በተምች መረርሽኝ መጠቃቱን መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ቼስተርማን ገልጸዋል፡፡ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላም በተምቹ የተጠቁ አካባቢዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት 150 ሺሕ ሔክታር ገደማ የሚጠጋ የበቆሎ ማሳ በተምች ተጠቅቷል፡፡ ይህም በአገሪቱ በበቆሎ ሰብል ከተሸፈነው 1.1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ እንደሆነ የሚኒስቴሩ መረጃዎች አመላክተው ነበር፡፡ ይሁንና የመረጃ ክፍተቶች እንዳሉ ሆነውም በዚህ ዓመት ከዚህም የከፋ ጉዳት ሊከሰት እንደሚችል ሥጋት ፈጥሯል፡፡

ባለፈው ዓመት የወረርሽኙ መምጣትን ተከትሎ በአብዛኛው የግብርና ዘርፍ ተዋናዮች ዘንድ ተምቹ ለአጭር ቆይታ እንደመጣ ይታሰብ ነበር ያሉት ቼስተርማን፣ ‹‹ተምቹ የመጣው በቱሪስትነት አይደለም፡፡ ለብዙ ጊዜ ለመቆየት ነው የመጣው፡፡ አሁን ዜግነቱን አግኝቷል፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

በዚህ ሳቢያ መወሰድ ያለባቸው የመከላከል ዕርምጃዎች እንዲጠናከሩ፣ አርሶ አደሮችም የግብርና ዘዴዎቻቸውን በማሻሻል የተምች ወረርሽኙን መከላከል ወይም ሊያስከትል የሚችላቸውን አደጋዎች መቀነስ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ጠቅሰዋል፡፡ በመከላከል ረገድ በተለይ አርሶ አደሮች በአግባቡ ያልታረሱ የእርሻ መሬቶቻቸውን በአግባቡ እንዲያርሱ፣ ተገቢውን የአፈር ክብካቤና አያያዝ እንዲተገብሩ፣ ማዳበሪያ በአግባቡ እንዲጠቀሙና ተስማሚና ጥራት ያላቸውን ዘሮች እንዲጠቀሙ  መክረዋል፡፡ ይህ ሳይደረግ እየቀረ ተምች በራሱ ጥፋት እንዳደረሰ በማሰብ የሚደመጠው እሮሮ ሊጤን ይገባዋል በማለትም ቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ ትኩረት መስጠት የመፍትሔው መጀመሪያ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በአገሪቱ የተምች ወረርሽኙን ለመከላከል ከተወሰዱት ዕርምጃዎች መካከል በእጅ መልቀምና የመድኃኒት ርጭት የተወሰነ ውጤት ማስገኘታቸውን ያስታወሱት ቼስተርማን፣ ከዚህ ባሻገር ግን ተገቢውን የተቀናጀ የተባይ ቁጥጥር ሥርዓት መተግበርም ከመፍትሔዎች መካከል እንደሚመደብ አስታውቀዋል፡፡ በተፈጥሮ ከአሜሪካዎቹ አካባቢ የመጣው ተምች በዝናብ አማካይነት መከላከል እንደሚቻል ሲያብራሩም፣ አርሶ አደሮች ዝናብ በሚጥልበት ወቅት የፀረ ተባይ ርጭት ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ እዚሁ አፍሪካ መገኛው የሆነው ተምች የአሜሪካውያኑ ተምች ዋነኛ ጠላት በመሆኑም በዚህም ረገድ የወረርሽኙን መንሰራፋት መከላከል የሚቻልበት ዕድል እንዳለ አስታውሰው፣ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ዘንድሮ ከዓምናው የበለጠ ወረርሽኝ ሊከሰት ስለሚችል ተገቢው ቅድመ ጥንቃቄ፣ የመረጃ ልውውጥና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባለፉት 12 ወራት ብቻ በአፍሪካ በርካታ አገሮችን ለማዳረስ የበቃው የተምች ወረርሽኝ ተገቢውን የመከላከል ዕርምጃ ካልተወሰደበት ከሦስት እስከ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የሰብል ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል ሰሞኑን የአሜሪካ ኤምባሲ ያሰራጨው መረጃ አመላክቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ 12 ዋና ዋና የበቆሎ አምራች አገሮች በተምች ወረርሽኝ ተጠቅተዋል፡፡ በአፍሪካ በበቆሎ ምርት የሚተዳደሩ የ300 ሚሊዮን ሰዎች የወደፊት የምግብ ዋስትና ጉዳይ በተምች ወረርሽኝ አደጋ እንዳንዣበበበት መረጃዎች እያመላከቱ ይገኛሉ፡፡

በፍጥነት የሚራባውና የሚስፋፋው ይህ ተምች፣ ጥሩ የአየር ፀባይ ካጋጠመው በቀን እስከ 150 ኪሎ ሜትር የመብረር ብቃት ሲኖረው፣ በአንድ ጊዜ በብዙ ሔክታር ላይ መሬት ላይ የሚገኝ ሰብል ያለ ችግር የመመገብ አቅም ያለው ነው፡፡