Skip to main content
x
ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ተቃውሞና እያስከተለ ያለው ጉዳት
በኦሮሚያ ክልል ከተካሄዱ ተቃውሞዎች መካከል በአንደኛው የተቃውሞ ሠልፍ ሲካሄድ

ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ተቃውሞና እያስከተለ ያለው ጉዳት

ወጣት ሌንሳ ገመቹ ተወልዳ ያደገችው በኦሮሚያ ክልል ፊኒፊኔ ልዩ ዞን ሱሉልታ ከተማ ሲሆን፣ ወላጆቿ ሁለት ልጆች ብቻ መውለዳቸውንና እሷ የመጨረሻ ልጅ እንደሆነች ትናገራለች፡፡፡ በ1994 ዓ.ም. የአሥረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ብትወስድም ውጤት እንዳልመጣላት ታስታውሳለች፡፡ የቤተሰቧ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ከመሆኑም በላይ አባቷ በ1995 ዓ.ም. በሞት እንደተለዩ ትናገራለች፡፡ የአባቷ መሞት በግል ኮሌጅ እንዳትማርና ራሷን እንዳታሻሽል ከማድረጉም በላይ፣ በሕይወቷ ተስፋ እንድትቆርጥ እንዳደረጋት ታስረዳለች፡፡ አባቷ በሞት ከተለዩ በኋላ በተለያዩ ፋብሪካዎች የጉልበት ሥራ ለመሥራት የመቀጠር ዕድል ብታገኝም፣ ሕይወቷን በዘላቂነት ሊለውጥ እንዳልቻለ ታስታውሳለች፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታትም ተቀጥራ ትሠራ የነበረውን የፋብሪካ ሥራ በመተው ስሙን መናገር በማትፈልገው ሆቴል በረንዳ ላይ የጀበና ቡና በማፍላት መተዳደር እንደጀመረች ታስረዳለች፡፡ በሆቴሉ የጀበና ቡና መሸጥ ከጀመረች ወዲህም ሕይወቷ በተወሰነ ደረጃ መለወጡን አክላ ትገልጻለች፡፡ የጀበና ቡና በመሸጥ የምታገኘውን ገንዘብ በመሰብሰብ ከ30 ሺሕ ብር በላይ መቆጠቧን፣ በሳምንት ደግሞ አምስት መቶ ብር ዕቁብ እንደምትጥል ትገልጻለች፡፡ ባለፉት ወራት በሱልልታ ከተማ ሲደረጉ በነበሩ ተቃውሞዎች ሳቢያም በቀን ታገኝ የነበረውን ገንዘብ ስታጣ እንደነበርና ለዕቁቧም ካጠራቀመችው ስትከፍል እንደነበር ትገልጻለች፡፡

‹‹ቄሮ›› እየተባሉ በሚጠሩት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ከሰኞ የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተጠራው ቤት የመዋልና የንግድ ተቋማትን የመዝጋት አድማ ሳቢያም እናቷ ወዳሉበት አዲስ አበባ በተለምዶ ዘነብ ወርቅ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደመጣች ታስረድታለች፡፡ ሥራዋን ጥላ በመምጣቷም በየሳምንቱ ለምትከፍለው የዕቁብ ገንዘብ ካጠራቀመችው ለመክፈል እንደምትገደድ ጠቁማለች፡፡ በሳምንት ዕቁብ ከመክፈሏም በተጨማሪ፣ ለእናቷ የቤት ኪራይና የቤት ወጪ አብዛኛውን ጊዜ እንደምትሸፍን ትገልጻለች፡፡ በዚህ ሳምንት በተጠራው ተቃውሞ ሳቢያም ብዙ ችግር ሊገጥማት እንደሚችል እምነቷን ታስረዳለች፡፡

በኦሮሚያ ክልል ‹‹ቄሮ›› እየተባሉ በሚጠሩት ወጣቶች ለሦስት ቀናት የሚቆይ አድማ እንደተጠራ የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በክልሉ አብዛኛው ከተሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ሪፖርተር ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ በክልሉ አብዛኛው ከተሞችም የንግድ ተቋማት ተዘግተውና የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችም በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡

በክልሉ በተጠራው የሦስት ቀናት አድማ በተለይም ሪፖርተር ማተሚያ ቤት እስከገባበት ማክሰኞ የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ድረስ በክልሉ በሁሉም አካባቢ በሚያስብል ደረጃ መንገዶችን በድንጋይ የመዝጋትና ጎማ የማቃጠል፣ እንዲሁም የንግድ ተቋሞቻቸውን በከፈቱ ግለሰቦች ላይ የተለያዩ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በጅማ፣ በነቀምቴ፣ በአሰላ፣ በወሊሶ፣ በአምቦ፣ በሻሸመኔ፣ በቢሾፍቱ፣ በሱሉልታ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች በጣፎና በሌሎች የክልሉ ከተሞች የነበረው አድማ ወደ ተቃውሞ ሠልፍ ተቀይሮ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር ለማረጋገጥ እንደቻለው በጅማ ከተማ እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት ድረስ  ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ከረፋዱ አምስት ሰዓት በኃላ ግን ቤት የመቀመጥና የንግድ ተቋማትን የመዝጋት አድማ ወደ ሁከት ተቀይሮ ድንጋይ ከየአቅጣጫው ሲወረወር እንደነበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚህም ሳቢያ የክልሉ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መተኮሱን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በተለይም በጅማና በወሊሶ ከተሞች ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ መተኮሱን ታማኝ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በነበረው ግርግርም የተወሰኑ ሆቴሎች ላይ መለስተኛ ጉዳት እንደ ደረሰ ጠቁመዋል፡፡ ከሰዓት በኋላ ግን በከተማዋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልነበረና አስረድተዋል፡፡  

በጅማ፣ በአሰላ፣ በሻሸመኔ፣ በወሊሶ፣ በቢሾፍቱና በሌሎች የክልሉ ከተሞች በነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴም ‹ኦሮሚያ የእኛ ናት፣ የታሰሩ ግለሰቦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ፣ አገር በተመረጠ መንግሥት ነው መተዳደር ያለባት፣ መንግሥት ሥልጣኑን ይልቀቅ፣ መፋናቀል ይቁም፣ የዜጎች መብት ይከበር . . . › የሚሉና ሌሎች መፈክሮች ሲያሰሙ እንደነበር በተለያዩ ከተሞች ከሚኖሩ ግለሰቦች የተሰባሰበው መረጃ ያመለክታል፡፡

በከተሞች በተለያዩ አቅጣጫዎች ወጣቶች ጎማ እያቃጠሉና መንገዶችን በድንጋይ እየዘጉ እንደነበርም ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በክልሉ አብዛኛው ከተሞች የንግድ ተቋማት ሲዘጉ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ ነበር፡፡ በተለያዩ ከተሞች የተጠራው አድማ ወደ ሁከትና ረብሻ ተቀይሮ በንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ለማወቅ ቢቻልም፣ የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች የደረሰውን ጉዳትና የአድማው ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲነግሩ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

በክልሉ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲደረግ ይህ የመጀመርያው እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው እንቅስቃሴ የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ የክልሉ ወጣቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ 2010 ዓ.ም. ከገባ ጀምሮ የተከሰተው ግጭትና የደረሰው አደጋ ግን የከፋ ነበር፡፡ በተለይም በ2010 ዓ.ም. መግቢያ ላይ በክልሉና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ግጭትና ከደረሰው ጉዳት ጋር በተያያዘ የክልሉ ወጣቶች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንግበው በተለያዩ ቦታዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ወጣቶቹ ከዚህ በፊት ያነሷቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል ‹የታሰሩት ይፈቱ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶችን በመፍጠር ሰዎችን ማፈናቀል ይቁም፣ ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ተገቢውን ጥቅም ታግኝ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይፈቱ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ይስፋ፣› ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችንና መፈክሮችን ሲያስተጋቡ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በክልሉና በአገሪቱ የተከሰተው ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደሆነ የሚናገሩ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ወር ለ17 ቀናት አድርጎት የነበረውን ዝግ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ፣ በአገሪቱ ለተከሰቱ ችግሮች ኃላፊነት እወስዳለሁ ማለቱ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችንም ለመፍታት ዝግጁ እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል፡፡

የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅት ከሆኑት መካከል የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአሥር ቀናት አድርጎት የነበረውን ዝግ ስብሰባ ጥር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲያጠናቅቅ ባወጣው የአቋም መግለጫ፣ የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት ከመቼውም በተሻለ ደረጃ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የክልሉ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ፣ በተለይም ከዚህ በፊት በክልሉ ወጣቶች ይነሱ የነበሩትን  ጥያቄዎች ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህም በክልሉ ሕዝብና በሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች ሲሞካሽ ቢሰማም በክልሉ ያለውን የወጣቶች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ማስቆም እንዳልተቻለ የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአመራሮች ላይ ዕርምጃ ከመውሰዱ ባሻገር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከሚኖሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት ዝግጁ እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል፡፡ አፋን ኦሮሞ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ጥረት እንደሚያደርግና በክልሉ ያለውን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁ እንደሆነ መግለጹ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

ኢሕአዴግም ሆነ ኦሕዴድ በአገሪቱ ያሉ ግጭቶችንና ችግሮችን እንደሚፈቱ ሲናገሩ ቢሰማም፣ በአገሪቱ ግጭትና ተቃውሞ ማቆም አልተቻለም፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ሐማሬሳ መጠለያ ካምፕ ተጠልለው በሚኖሩ ግለሰቦችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል፣ የካቲት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በተፈጠረ ግጭት የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጠቁሟል፡፡ የግጭቱ መነሻ ምን እንደሆነ እስካሁን ባይገለጽም በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት በአገሪቱ የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን እየተናገሩ ባለበት ጊዜ፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች አሁንም መቆም አለመቻላቸው ጉዳዩ ከባድ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራር አቶ ጥሩነህ ገምታ፣ መንግሥት የችግሮችን ምንጭ ለይቼ በማወቅ ለመፍታት ቆርጫለሁ እያለ ባለበት ወቅት ተቃውሞዎች መቀጠላቸው ዋነኛ ምክንያቱ ምንድነው? በትክክልስ የሕዝቡ ጥያቄ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ የሕዝቡ ዋነኛ ጥያቄ ባልመረጥናቸው መሪዎች ወይም ገዥዎች አንተዳደርም የሚል ነው ብለዋል፡፡ በአገሪቱ በተደጋጋሚ ጊዜ በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ሕዝቡ ቅሬታ እንደነበረው አስታውሰው፣ የክልሉ ብሎም የአገሪቱ ሕዝብ ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫ እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

በአንድ አገር ውስጥ አንድ ፓርቲ መቶ በመቶ የሚያሸንፍበት አጋጣሚ እንደሌለ ጠቁመው፣ ‹‹ኢሕአዴግ ከዚህ በፊት በሚደረጉ አገራዊ ምርጫዎች ኮረጆ ሲገለብጥ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የአገሪቱ ሕዝብ ክፉኛ መቆጣቱን አስታውሰው፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫ እስካልተካሄደ ድረስ የአገሪቱ ቀውስ ይቆማል ብለው እንደማያስቡ አስረድተዋል፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን በበኩላቸው፣ ግጭቶችና ተቃውሞዎች አሁንም መቆም ያልቻሉበት ምክንያት መንግሥት እየወሰደ ያለው የመፍትሔ ዕርምጃ በመዘግየቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ ንጋት አስፋው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአቶ ጥሩነህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ የአገሪቱ ወጣቶች ከዚህ በፊት በተካሄዱ አገራዊ ምርጫዎች ላይ ጥያቄ ሲያነሱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህ ድርጊት አሁንም ድረስ ለወጣቶች ጥያቄ ሆኖ እንደቀጠለ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ጥሩነህ ከምርጫ ቦርድ ገለልተኛነት ጋር በተያያዘ አሁንም ሕዝቡ ቅሬታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛው የሕዝቡ ጥያቄ ነው ብለው የጠቀሱት ጉዳይ ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ ሥር የሰደደ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሌሎች ችግሮች አሁንም ሊቀረፉ ያልቻሉ እንደሆኑና የአገሪቱን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ክፉኛ እየጎዱት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ንጋት በበኩላቸው፣ የሕዝቡ ቁጣ ሊበርድ ያልቻለው የአመራር ቀውስ በመፈጠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አገሪቱን በሚመራት የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል አለመግባባት እንዳለና ችግሩ አሁንም መፈታት ባለመቻሉ ሳቢያ ግጭቶችን ማቆም እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአሥራ ሰባት ቀናት አድርጎት በነበረው ስብሰባ በአባል ድርጅቶች መካከል ያለው የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ልል እንደነበር መገምገሙንና ችግሩን ለመፍታትም መወሰኑን ቢገልጽም፣ በተግባር የታየ ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የመዘግየት አዝማሚያ ቢታይበትም፣ ዕድሎች ሙሉ በሙሉ ተሟጠዋል ማለት እንዳልሆነና ያን ያህል አገሪቱ ቀውስ ላይ ናት ብሎ ለመናገር የሚያስችል ደረጃ ላይ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ አሁንም በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተቀመጡ የውሳኔ ሐሳቦችና የትኩረት አቅጣጫዎችን ወደ መሬት በማውረድ፣ የአገሪቱን ሕዝብ በተለይም የወጣቱን ጥያቄ ለመፍታት የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአሥራ ሰባት ቀናት ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ እንደገለጸው፣ በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባልም እስረኞችን ለመፍታት መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት በፌዴራልና በክልል ደረጃ ከአሥር ሺሕ በላይ እስረኞች መፈታታቸውን የሚታወስ ሲሆን፣ አሁንም በፀረ ሽብር አዋጁ ተከሰው የተፈረደባቸውን ግለሰቦች ለመፍታት በዝግጅት ላይ መሆኑን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

አቶ ጥሩነህ ኢሕአዴግ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የታሰሩ ሰዎችን እፈታለሁ ቢልም፣ በአስቸኳይ ተግባራዊ ባለማድረጉና የተለያዩ ሰበቦችን በመፈለግ መፍታት ባለመቻሉ ሕዝቡ ቅር መሰኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ምንም እንኳ ኢሕአዴግም ሆነ ኦሕዴድ ያወጡትን መግለጫና ያስተላለፉትን ውሳኔ በጥንቃቄ እንደሚቀበሉትና እንደሚስማሙበት ቢገልጹም፣ በአስቸኳይ ተግባራዊ ካልተደረገ ትርጉም ሊኖረው እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ 

ዶ/ር ንጋት በበኩላቸው ኢሕአዴግም ሆነ ኦሕዴድ ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ እንደሆኑ ቢገልጹም፣ አሁንም ድረስ በአገሪቱ አክራሪ የሆነ የፖለቲካ አዝማሚያ እንዳለ፣ ሚዲያዎች የሕዝብ ድምፅ መሆን ባለመቻላቸው ሳቢያ ተቃውሞዎችንና ግጭቶችን ማስቆም እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

አቶ ጥሩነህ በአገሪቱ ያለውን ሥር የሰደደ ችግር ለመፍታትና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር አገራዊ ውይይት ማድረግ ተገቢ እንደሆ ጠቁመው፣ ሕዝቡ በሚያስቀምጠው ውሳኔ መሠረት አገሪቱ መመራት እንዳለባት ገልጸዋል፡፡ ሕዝብ ሁልጊዜም ትክክል ነው የሚሉት አቶ ጥሩነህ፣ ሕዝብ ከተሳሳተ እንኳ ሕዝባዊ ውይይት በማድረግ የተሳሳተበትን መንገድ መንግሥት በትክክል ማሳየትና ማስረዳት ይገባው ነበር ብለዋል፡፡

በዚህ ሐሳብ ዶ/ር ንጋት ይስማማሉ፡፡ እየታየ ያለውን ችግር በአገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚኖረው ሕዝብ ጋር በመወያየት መፍታት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ ሕዝብን በማወያየት ችግሩን መፍታት ይቻላል ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተለይም በአምቦ፣ በወሊሶ፣ በአሰላ፣ በጅማ፣ በሻሸመኔና እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የክልሉ ከተሞች ያለው ተቃውሞ ሪፖርተር ማተሚያ ቤት እስከገባበት ማክሰኞ የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ መቀጠሉን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በክልሉ ብሎም በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ እንደሚያስከትል ተንታኞች ጠቁመዋል፡፡ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ከዚህ የከፋ እንዳይሆንና በአገሪቱ የከፋ ቀውስ እንዳያስከትል አፋጣኝ መፍትሔ መፈለግ እንዳለበትም አክለው ተናግረዋል፡፡  

የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ኡሚ አባጆማል አባጆርጋ ማክሰኞ የካቲት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ በተለያዩ ሥፍራዎች የንግድ ሥራ ማቆም፣ መንገድ መዝጋትና ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚያመሩ አዝማሚያዎች መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሁከቱ በዝዋይ፣ በለገጣፎና በጅማ ስምንት ሰዎች ላይ ጉዳት፣ በግልና በመንግሥት ድርጅቶችና ተሽከርካሪዎች ላይ ጥፋት ደርሷል ብለዋል፡፡ መንግሥት የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ባለበት ወቅት ይህንን መሰል ክስተት መፈጠሩ አግባብ እንዳልሆነ አስታውቀው፣ ጥፋት ያደረሱ አካላትን በማጣራት ተገቢው ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡም በሕዝብና በመንግሥት መካከል የተጀመረውን መደማመጥ ከሚያደናቅፍ አፍራሽ ድርጊት እንዲታቀብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡