Skip to main content
x

የአገሪቱ ምሁራን በኦሜርታና በሰጎን ፖለቲካ ጥላ ሥር

 በቶፊቅ ተማም

''ምንም የማይሰማ፣ የማያይ፣ እንዲሁም የማይናገር ሰው መቶ ዓመታትን በሰላም መኖር ይችላል፡፡'' ይህ አባባል ‹ኦሜርታ› ተብሎ የሚጠራውን የዝምታ ሕግ (Code of Silence) አስፈላጊነት ለመግለጽ በተለይ በጣሊያን ሲሲሊዎች ዘንድ የሚነገር የዘወትር ቃል ነው፡፡

ዛሬም ድረስ ታዲያ በአንዲት አገርና ሕዝብ ላይ የፍርኃት ድባብ ሲነግሥና የፍርኃቱም ምክንያት ከቡድን ወይም ከመንግሥት አስተዳደር ጋር ሲገናኝ በውጤቱም ሕዝብ፣ እንዲሁም ምሁራን አላየሁም፣ አልሰማሁም፣ አልናገርም የሚል ዝምታ ሲፈጠር ክስተቱ ኦሜርታ ይባላል፡፡

በእርግጥ በዚህ ጽሑፍ ከምሁራን ባላውቅም በዋነኛነት በአጭሩም ቢሆን ለመዳሰስ የምሞክረው ጉዳይ ቢኖር፣ በአገሪቱ ምሁራን ዘንድ እየተስተዋለ የሚገኘውን ኦሜርታ ይሆናል፡፡ በአንድ አገር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ምሁራን ለልማት፣ እንዲሁም ለዘላቂ ልማትና ሰላም የሚጠቅሙ ሐሳቦችን በማመንጨት የሚጫወቱት ሚና የላቀ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን በአጥጋቢ ሁኔታ እየተተገበረ አይደለም፡፡ ለዚህም አንዱና መነሻ ምክንያት የሚሆነው የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓትን ለመተቸትና ያልተገቡ አካሄዶችን ነቅሶ ለማውጣት አመቺ በሆነ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ባለመኖራቸው ምክንያት፣ የአገሪቱ ምሁራን ከትችትና ከአስተያየት ተቆጥበው ዝምታን መርጠው እየኖሩ ነው፡፡

በማንኛውም አገር ምሁራን ትውልድን በዕውቀት መቅረፅ ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ጉዳይ ላይ የተሻለ አመራር እንዲመጣ የዕውቀታቸውን ያህል ማበርከት ድርሻቸው ነው፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደ ተሞከረው ምሁራንን አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር ባለመኖሩ፣ በአገር ጉዳይ ተሳትፎ ለማድረግ ምን ቸገረኝ የሚል እሳቤ እያመጣ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ምሁራን ራሳቸውን ለመደበቅና ለዝምታ የተዳረጉ ሲሆን፣ ከሰጎን ፖለቲካ (Ostrich Politics) ሊያልፉ አልቻሉም፡፡ በዚህ የሰጎን ፖለቲካ የምሁራን ዝምታ ለአገርና ለወገን የማይበጅ በመሆኑ ሊቆም የሚገባበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡

በአንድ አገር የፖለቲካ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ምሁራን ለልማት የሚጠቁሙ ሐሳቦችን በማመንጨት ረገድ የላቀ ሚና የሚኖራቸው ሲሆን፣ በተለይ ከሌላው ኅብረተሰብ በላቀ ደረጃ እውነት በመናገር ሐሰትን ሊያጋልጡ፣ ዕውቀትን አክብረው ሊያስከብሩና ለምሁርነታቸው ታማኝ ሊሆኑ፣ ራሳቸውን ለውይይትና ጥያቄ ክፍት ሊያደርጉ ይገባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በርከት ያሉ ፖለቲካው የፈጠራቸው ችግሮች እንዳሉ የሚታወቅ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ትግበራው ችግር ያለበት ከመሆኑም በላይ፣  የመልካም አስተዳደር ጉድለትና የመንግሥት ባለሥልጣናት ግልጽነትና ተጠያቂነት ገና ተገቢ መፍትሔ ያላገኙ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ምሁራን ፖለቲካዊ ሚና ሊሆን የሚችለው ችግሮችን በጥልቀት መርምሮ በመረዳት እውነትና ዕውቀትን መሠረት በማድረግ የመፍትሔ ሐሳብ ማመንጨትና ሐሳቦች ወደ ኅብረተሰቡ እንዲደርሱ ለማድረግ የሚረዳ ሥልት መቅረፅ፣ ከአገሪቱ ምሁራን የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

አገሪቱ ያሉባት ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምሁሩ ሊያቀርባቸው በሚችሉ የዕድገት ሐሳቦች ሊታገዙ ይገባል፡፡ አገሪቱ በርካታ የኢኮኖሚና ሌሎች ተዛማጅ መስኮች ባለሙያዎችን ያፈራች ሲሆን፣ አገሪቱ አማራጭ የዕድገትና የልማት ሐሳቦችን ታገኝ ዘንድ ምሁራንም ኃላፊነታቸውን ለመውጣት የተለየ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

ከኢኮኖሚያዊ ችግሮች ባልተናነሰ የአገሪቱ ማኅበራዊ ችግሮች በርካታ መሆናቸው ዕሙን ሲሆን፣ እጅግ የባሱት ለአብነት ያህል የትምህርት ጥራት ጉድለት፣ ሥራ አጥነትና ሌሎችንም ችግሮች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምሁራን ማኅበራዊ ችግሮችን በማጥናት የመፍትሔ ሐሳቦችን ማመንጨት፣ እንዲሁም ማሠራጨት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከላይ የጠቀስናቸውን ተግባራት ምሁራን በአግባቡ መፈጸም ያስችላቸው ዘንድ፣ መደማመጥና በልዩነታቸው ተከባብረው ለመሥራት ቅን መንፈስ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ምሁራን በአገር ቤት ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ዓለም ተሠራጭተው የሚገኙ በመሆናቸው በቦታ በርቀት ሳይገደቡ በብዙ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ሊፈጥሩ ይገባል፡፡

በአገሪቱ ያሉትን ችግሮች ከመፍታት አንፃር አገሪቱ የሚታዩ ችግሮች ነቅሰው የሚያወጡ፣ ለዚህም መፍትሔ አቅጣጫ የሚጠቁሙ ብዙ የአደባባይ ምሁራን (Public Intellectual) በአገሪቱ ሊፈሩ ግድ የሚል ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በሚኖሩበት አገር ውስጥ ካለ ፍርኃት፣ እንዲሁም መሸማቀቅ ስለሚኖሩበት ኅብረተሰብ ካላቸው ጥልቅና የበለፀገ ዕውቀት በመነሳት የሚታዩ ክፍተቶችን የሚሄሱ፣ እንዲሁም አገር በቀጥተኛ ጎዳና ትሄድ ዘንድ ህፀፆችን የሚጠቁሙ ሐያሲ ምሁራን ቁጥር የበለጠ ሊያሻቅብ ይገባል፡፡

በእርግጥ ስለምሁራን ሲወራ ብዙ ምሁራን በአገር ቤት እንዳሉት ሁሉ፣ በውጭ አገር ያሉ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ዳያስፖራ ምሁራን (Intellectual Diaspora) አሉ፡፡ ከፊሎቹ በሙያና በገንዘባቸው ለአገራቸው የሚችሉትን እያደረጉ ሲሆን፣ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ዳያስፖራ ምሁራን አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ለአገሪቱ መስጠት ያለባቸውን ያህል እየሰጡ አለመሆኑ፣ ዳያስፖራውም በአገሪቱ ጉዳይ ዙሪያ ኦሜርታን የመረጡ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያደርገው ተሳትፎ አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ያዘነበለ መሆኑ፣ የሚከተሉት የፖለቲካ ሥልት ከሰጎን ፖለቲካ የወጣ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡

ከላይ በጥቂቱም ቢሆን የአገሪቱ ምሁራን በአገሪቱ ልማት ዙሪያ ሊጫወቱ የሚገባቸውን ሚና በተመለከተ የተገለጸ ሲሆን፣ የምሁራን እንቅስቃሴ ብቻውን በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ የሚቆጠር ነው፡፡ ምሁራን በአገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች በንቃት ይሳተፉ ዘንድ የመንግሥት ድርሻ ወሳኝ ነው፡፡

በምሁራን የሚቀርቡ ሐሳቦች በነፃነት በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲንሸራሸሩ የሚረዳ ፖለቲካዊ ሁኔታ ማመቻቸት የወቅቱ መንግሥት ኃላፊነት ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለኅብረተሰቡ ከሚጠበቁ አገልግሎቶች ዋነኛው ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ልዩ ልዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት እንዲሆን አለማድረግ አማራጭ ማስቀረት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

መንግሥት ምሁራንን የበለጠ አሳታፊ የሚያደርግ የፖለቲካ ሥርዓት በመዘርጋት ምሁራን በራሳቸው አማራጭ የፖለቲካ ኃይል ሆነው እንዲወጡ በማድረግና መልካም ፈቃድን በማሳየት፣ ምሁራን ለአገራቸው ልማት የበኩላቸውን ይወጡ ዘንድ ሁኔታዎች ሊያመቻች ይገባል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኅብረተሰቡ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የተለያዩ አግባብ ያልሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙት ቆሞ በምን ቸገረኝነት ችግሮችን እንዳላየና እንዳልሰማ ባለማለፍ ከኦሜርታ ሲያፈገፍግ የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች በአግባቡ መንግሥት ዘንድ በማድረስ፣ እንዲሁም ይህን ተከትሎ የሚከሰቱ ቀውሶችን በመከላከል ረገድ የምሁራን ሚና ለአፍታም ቸል የማይባል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ይህ ጽሑፍ በሚዘጋጅበት ወቅት የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፣ የኦሮሞ ምሁራን በሁሉም የታሪክ ምዕራፍ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ባለፈበት የትግል ሒደት ውስጥ መስዋዕትነት መክፈላቸውን፣ እንዲሁም አሁንም ከኦሕዴድ ጋር በመሆን ዋነኛ ሥራቸው የሆነውን ሐሳብ የማፍለቅ፣ ጥናትና ምርምርን እንዲቀጥሉ በማሳሰብና ከምሁራን ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም  በአዎንታዊ መልኩ የሚታይና በአፋጣኝ ወደ ተግባር ሊገባበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አልፎ አልፎ ለሚከሰቱ ችግሮች አንዱ ምክንያት የሚሆነው በመንግሥት በኩል ለምሁራን ተገቢው የፖለቲካ ምኅዳር አለመመቻቸቱ ሲሆን፣ መንግሥት በኦሜርታ ጥላ ሥር የሚገኙ ምሁራንን ካሉበት ጥላ በማውጣት ከምሁራን ጋር ተባብሮ የመሥራት ባህልን ሊያዳብር የሚገባበት ወቅት መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡

በመንግሥት በኩል እስካሁን ያልተሠሩና መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው በምሁራን በኩል በስሜት የማይነዱ፣ በአገሪቱ ለሚታዩ አዎንታዊና አሉታዊ ጉዳዮች ሚዛናዊ የሆነ ዕይታ ያላቸው፣ እንዲሁም በውይይት የሚያምኑ ሆነው ሊገኙ የሚገባቸው ሲሆን እነኚህን ምሁራን አገሪቱ አጥብቃ የምትፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡   

በመጨረሻም አገሪቷ ያሏትን ምሁራን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻል የወላድ መሃን ከመሆን ትድን ዘንድ፣ ምሁራንን በየተዋረዱ የሚያሳትፍ የፖለቲካ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ተሰብሮ ያለውን በመንግሥትና በምሁራን መካከል ያለውን ድልድይ በአግባቡ በመሥራት፣ ምሁራን በአሁኑ ወቅት ከሚገኙበት ጥልቅ ዝምታና አሁን ካሉበት የሰጎን ፖለቲካ ይወጡ ዘንድ በመንግሥት በኩል አሳታፊና አካታች ሥርዓት በየተዋረዱ መዘርጋትና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ለአፍታም ቢሆን ቸል ሊባል አይገባውም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]ማግኘት ይቻላል፡፡