Skip to main content
x

በደርዘን ሸምተን ባዶአችንን ቀረን!

እነሆ ጉዞ!  ከሳሪስ አቦ ወደ ቦሌ ድልድይ ልንጓዝ ተሳፍረናል፡፡ ሰው በሰው ላይ እንደ ጥልፍ ጥለት ተደራርቦ ይተፋፈጋል፡፡ ቅብጥብጡ ወያላ፣ “አንድ ሰው አንድ ሰው. . .” እያለ ሲጮህ ዕቃ እንጂ ሰው የሚጭን አይመስለውም፡፡ “ምናለበት ብንሄድ?” ይሉታል እንደ መከዳ የሚደገፋት ወንበር ላይ ስብር ብለው የተቀመጡ ወይዘሮ፡፡ “እንሄዳለን አንድ ሰው ብቻ?” ይላቸዋል፡፡ “እንዲያው በሁዳዴ እንኳ ብትታዘዙን ምን አለ?” አጉተመተሙ፡፡ ሾፌሩ ሰምቶ ተጠምዞ ዓያቸውና “ምነው እማማ ንክኪ ሲበዛ ማስገደፍ ጀመረ እንዴ?” አላቸው፡፡ “ሥጋ፣ ሥጋ ነው፡፡ ያው በለው፤” አሉት፡፡ “በለው። ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ በዚህ መጣችሁብን፡፡ ኧረ ሠርተን እንብላበት?” ተገላመጠ፡፡ “አንተው አመጣኸው አንተው አሮጥከው፡፡ እንጂ እኔ ምን አልኩህ? ደግሞ ግልምጫህ? አንተ እንዲያው ሌላው ቢቀር ሁለቴ አልወልድህም? ደግሞ ሠርተን እንብላበት ይለኛል፡፡ ሥራችሁማ ይኼው፡፡ የዘመኑ ልጆች በሥራ እያመካኛችሁ ሽቅብ ማንጓጠጥ ነው። ለነገሩ እናንተ ምን ታደርጉ? ድፍረትና ንቀታችሁን በገንዘብ የሚተምንላችሁ ሰው ቢበዛም አይደል?” ሲሉት ምን አጨቃጨቀኝ እያለ አንደኛ ማርሽ አስገባ፡፡

ወያላው፣ “ቆይ እንጂ ይሙላ?” አለው ነገር አንጀቱ ውስጥ እንደተሰነቀረበት ሁሉ ገርጥቶ፡፡ ይኼኔ ከወይዘሮዋ ጎን የተቀመጠ ወጣት አንድ ሁለት ብሎ ሁላችንንም ቆጥሮ ሲያበቃ፣ “17 ሰው ጭነህ ነው ይሙላ? የምትለው?” አለው፡፡ ወያላው አንገቱን ደፍቶ በስድብ እያጉተመተመ ተንሸራታቹን በር ከረቸመው፡፡ “የዘንድሮ ወያላና መራጭ መቼ ወንበር ይቆጥራል ልጄ? ገንዘብ ወዳጅ ሁሉ፡፡ ስግብግብነት እኮ እንኳን ሰው ተራራ ከዓይንህ አያስገባም። የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት የማጣታችን ጫፍ መስሎኝ ወስዶ ወስዶ እኛኑ ራሳችንን እንደ ግዑዝ ዕቃ ያለማስተዋል በጎታ መሥፈርት የሚሰፍረን?” ሲሉት ወይዘሮዋ ወጣቱ አማርኛቸው ቻይነኛ ሆኖበት ለይምሰል አንገቱን ይወዘውዛል። መንገዱ እኮ ባቢሎን ከሆነ ከራርሟል!

ጉዟችን ቀጥሏል፡፡ ጋቢና ከተቀመጡት አንዱ በስልክ ይነታረካል፡፡ “ስማ ስልኩ እኮ የሚሠራው በካርድ ነው ፍሬ፣ ፍሬውን አውራ፤” ይላል። እንኳን ስልኩ ሰውም በካርድ መሥራት ጀምሯል እኮ?” ይላል ከመጨረሻዎቹ በዚያ ጥግ የተቀመጠው። “ታዲያ ካርድ መሙላት ያቃተው አለቀለት በለኛ?” ስትል ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ዘመናይ ከሩቅ ቅርብ ሆና ማይኩን ተቀበለችው። “ለስንቱ ይሆን ከሆዳችን ቀንሰን ካርድ እየሞላን የምንዘልቀው? ያም አምጡ ይኼም አምጡ ባይ ሆኗል፤›› ይላል ከጎኗ የተቀመጠ ቀጠን ያለ ወጣት። ‹‹ሁሉም አጉርሱኝ ባይ ሆነ ብሎ ዝም ምንድነው ልጄ? ንሳ ሁሉም ካልክ ዘንዳ አንተንም ጨምርና ንስሃ ግባ፤›› አሉት ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጡ ቄስ።

“አይ አባት ጣት መቀሳሰሩን ትተን ሸክማችንን በጋራ መሸከም ብናውቅ እስከ ዛሬ እርስ በርስ በዓይነ ቁራኛ ስንተያይ እንኖር ነበር?” ቢላቸው ከሰውነቱ ወይ  ከኑሮ ማንኛው እንደ ከበደው ያላወቅንለት ወጣት መልሰው፣ “እሱስ ልክ ነህ ልጄ። ምን ይደረግ የአንዱን ሥጋ አንዱ መሸከም እያቃተው እኮ ነው?” አሉት። ነገር በፈስቡክ ብቻ የሚገባው ዝም ሲል ሌላው ሳቀ። ሼኩ በፈገግታ ጣልጋ ገብተው፣ “ይኼን ካወቅክ ዘንድ ሆድ አየሁ ማለትን እንደማያውቅ ከተረዳህ ይኼ ሁሉ ስብ ምንድነው? ለሰማዩም ለምዱሩም እኮ አይበጅም። ኧረ ለጤናም ጥሩ አይደለም፤”  ሲሉት ወጣቱ ወዲያው የጨዋታውን መንፈስ ቀየረው። የሰውነቱ ውፍረት አገር እንደ ነቀዝ እየሰረሰረ ከሚያፈርሰው ‘ብቻዬን ጠብድዬ ልሙት’ ብሂል ጋር መነካካቱ አናደደው መሰል ቁጣው ድምፁ ስርቅርቃ መሀል አታሞ እየደለቀ፣ “መሆንን ትተን መምሰል መምሰል ካልን አይቀር ምናለበት እኛስ ስብ ጠናባቸው ብንባል? ቀለን ኖረን ማን አከበረን?” ብሎ አዋዝቶ የልቡን ተናገረ። ስንቱ ነው ግን የልቤን ልናገር እያለ ልቡን የሚያጣው እናንተ?!

ወያላው ሒሳቡን እየተቀበለ፣ “ሳንቲም ካላችሁ ተባበሩኝ?” ሲል ያስተጋባል። ሾፌሩ “ትርፍ ጭነሃል እንዴ?” ብሎ ድንገት በርግጎ ጠየቀው። “አዎ! ሁለት ሰው አለኝ ምነው?” ከማለቱ ሾፌሩ በብስጭት፣ “ስንቴ ትርፍ አትጫን ብዬ ላስጠንቅቅህ ግን? ያው ሁለት ናቸው፤” ብሎ ትራፊኮቹን እየጠቆመ የታክሲዋን ፍጥነት አቀዘቀዘ፡፡ ወያላው፣ “አንተ ደግሞ? ሀቀኝነት ማንን ሲያነሳውና ሲያከብረው ዓይተህ ነው ትርፍ አልጭንም የምትለው? እየተበላንም ቢሆን መሥራት አለብን ፍሬንድ፤” ብሎ ያደፋፍረው ጀመር። ትራፊኮቹ አፍ ለአፍ ገጥመው እያወሩ ሳያዩን አለፍናቸው። “አቤት ሥራና ወሬ?  በዚህ ዓይነት ስንቱ አገር አጥፊ ይሆን ተዝናንቶ የሚኖረው? ኧረ አቋራጩና ተቆራራጩ በዛ?” አለች መጨረሻ የተቀመጠች ወጣት። “ምናልባት ይኼ መከረኛ ኮምፒውተር ከ’ዲስክቶፕ’ በ’ሾርት ከት’ ‘ፕሮግራም’ እየከፈተ ማቋረጥን ክፉኛ አለማምዶን ይሆን?” ብሎ ፈገግ አሰኘን። አውነቱን እኮ ነው! ሰው ካየውና ከሰማው ውጪ መች ይኖርና!

“አስኩ ገበርኩ!” ይላሉ መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ አዛውንት። ግርማ ሞገሳቸው ልዩ ነው። ፀጉራቸው ሪዛቸውን ጨምሮ ቡፍ ብሎ ቆሟል። “ምነው አባት? ምን ሆኑ?” አጠገባቸው የተቀመጠች አጭር ቀይ ኮረዳ ትጠይቀዋለች። “የምሆነው እየጨነቀኝ ነዋ! እንጂ ምንም አልሆንኩ እስካሁን!” መለሱላት በእርጋታ። “ማን የሚሆነውን ያውቃል ብለው ነው?” ለማወጣጣት ነው ነገሩ። “እሱን ብዬ እኮ ነው ልጄ ነጋ ጠባ አሟሟቴን አሳምረው የምለው። ሳይሰለቸው ቀረ ብለሽ ነው?” ፍስስ ይላሉ ደርሰው በተመስጦ፡፡ “ምነው ካልጠፋ ነገር አሟሟትዎ ያስጨንቀዎታል? ልጆች የሉዎትም? ባለቤትዎስ?” የምትለቃቸው አትመስልም ወጣቷ። “ኧረ ሁሉም አሉ። የሁሉም አጠገቤ መኖር ነው አንድም የሚያሳስበኝ፡፡ በዚያ ላይ አንዳንዱ በአሟሟቱ ይበደልና በአቀባበሩ ይካሳል። ለምሳሌ ይኼው እንደምትሰሚው በአሸባሪዎች ሴራ የሞቱት ሰዎች ምንም እንኳ እንደወጡ በዚያ አፈር ቢለብሱም ይኼው ዓለም በየሰዓቱ በየደቂቃው እያሰባቸው ይውላል። ዓለም ይኼው በባንዲራቸው ምሥሉን እስከ መሸፈን ደርሶ የሐዘናቸው ተካፋይ ሆኗል።  ሲኖሩ ተረስቶ ሲሞቱ መታወስ እጅግ የሚገርመኝ የዓለም ፀባይ ነው ልጄ። አየሽ ብዙ ብዙ አለ የሚያሳስበኝ። ወዲያ ደግሞ ወደ ፓሊስቲንና ወደ አፍጋኒስታን ብትሄጂ በቦምብ ሞትሽ፣ ታመሽ ሞትሽ፣ ሮኬት አግኝቶሽ ፍንጣሪው ዓይንሽን አጠፋው ከአበቃልሽ አበቃልሽ ነው። በበኩሌ ታዲያ በሕይወት ስኖር ለመኖሬ ዕውቅና ባይሰጠኝም፣ ስሞት ቀባሪ ካላሳጣኝ አሟሟቴ ‘ክላሲ’ ባይሆንም እንኳ አስታዋሾቼ ‘ክላሲ’ በሆነ መንገድ ካስታወሱኝ ምን እፈልጋለሁ?” ብለው ፈገግ አሉ። ወይ ሰው! መፈለግም አለመፈለግም በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ የሚገኝበት ቀን እንደሚመጣ እያሰበም የሚፈልገውና የማይፈልገውን ሲመርጥ ይኖራል? ‹‹ታዲያ ከሞት በኋላም ምርጫ አማረህ?›› ሲል የሰማነው ወያላ ስንት ቢያጆ ሸቅሎ ይሆን ከነጋ?

መውረጃችን ለመድረስ የቀሩን ጥቂት ደቂቃዎች ናቸው። ከልክ በላይ መኪናዋን የሚጋልባት ሾፌራችን ከምድር ለመጥፋት ያሰበ ይመስላል። “ቀስ በል እንዳንል እንደ ዘንድሮ ሰው አስተያየት፣ ምክር፣ ተግሳጽ የጠላ የለም፤” ይለኛል አጠገቤ ያለው ወጣት። ከኋላችን የተቀመጡት ጎልማሳና ቆንጅዬዋ ወጣት እንዲህ ይጫወታሉ። “እኔ ምለው መንግሥት ለትልልቅ ፕሮጀክቶቹ ሥራ ማስኬጃ ኪስ ሳያጥረው አልቀረም የሚባለው እውነት ነው?” ብላ ጎልማሳውን ስትጠይቀው፣ ‹‹ምን አውቃለሁ ብለሽ ነው? እንዲያ ሲባል መቼም እዚህ አገር የማይባል ነገር የለም እያልኩ ነው እንጂ መስማቱን ሰምቻለሁ። ምናልባት የፕሮጀክቱ መጓተት ይሆናል ሁሉም ገንዘብ አጥሮ የሚነፋረቀው፤›› ይላታል።

ትንሽ እንደ ሄድን ‘ኢርፎን’ ሰክታ አልሰማም አላይም ብላ ከተቀመጠችው ወጣት ሦስተኛ ተደርበው የሚጓዙት አዛውንት፣ “እውነት ሙስና ላይ ከበድ ያለ ዘመቻ ካልተጀመረ ይህች አገር ምን ሊቀራት ነው?” ብላው ሳያስቡት ድምፃቸውን አጉልተው ጠየቁ። “እንዴት?” ስትላቸው ወይዘሮዋ፣ “ከጥበቃ እስከ  ዋና ሥራ አስኪያጅ ያለምንም እጅ መንሻ መግባት፣ መውጣት፣ ጉዳይ ማስጨረስ፣ መከታተል የማይታሰብባት በሆነችው ኢትዮጵያ ማን ሊማር? ሙስና ሥር ሰዷል ያልተዘፈቀበት የለም። በአጠቃላይ አገሪቷ ራሷ ተዘፍቃለች ማለት ይቀላል እኮ? ታዲያ አሁን እኔ እያልኩ ያለሁት ‘የቱ ተወዶ የቱ ሊጠላ?’ ነው?” ሲሉን ‘ህም’ ብለን ‘ዝም’። ምክንያቱም ወያላው በሩን ከፍቶ ‘መጨረሻ’ ብሎ ውረዱልኝ እያለ ነበር። በደርዘን ሸምተን ባዶአችንን ቀረን እኮ ጎበዝ? መልካም ጉዞ!