Skip to main content
x

ለደሃ አገሮች ቃል የተገባላቸው ድጋፍ ካልተተገበረ የኑሮ ልዩነት እንደሚባባስ ተመድ አስጠነቀቀ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ትንታኔ መሠረት፣ አብዛኞቹ በድህነት ውስጥ የሚገኙ 47 በኢኮኖሚ ኋላ የቀሩ አገሮችን ከኢኮኖሚ ለመደገፍ የበለፀጉ አገሮች ቃል ቢገቡም፣ በዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት መዳከም ሳቢያ ለመስጠት የገቡትን ቃል ከማክበር ሲያፈገፍጉ ይታያሉ፡፡ በዚህ ሳቢያም ልዩ ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባቸው ድሆቹ አገሮች እ.ኤ.አ. በ2030 መጨረሻ ዕውን እንዲሆኑ የተቀመጡትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ያወጣቸውን ዘላቂ የልማት ግቦች የማሳካት ዕድላቸው የመነመነ ስለመሆኑ አስጠንቅቋል፡፡

የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ (UNCTAD) ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው አዲስ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ፣ በአብዛኛው ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች የተካተቱበት 47ቱ የዓለም ደሃ አገሮች ወይም በኢኮኖሚ ደረጃ ኋላ የቀሩ አገሮች፣ ቃል የተገባላቸው ድጋፍ ከተመድ የዘላቂ ግቦች አኳያ በሚጣመር መልኩ ‹‹ማንም ወደኋላ መተው የለበትም፤›› በሚለው ግብ መሠረት፣ ያደጉ አገሮች ድጋፋቸውን ከመስጠት እንዳያቋርጡ አሳስቧል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት የሚታይበት አዝጋሚ የማንሰራራት ሒደት ታክሎበት፣ ለጋሽ ተቋማትን የልማት አጋሮች ለድሆች አገሮች የሚሰጡት ድጋፍ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን የጠቀሱት የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገሮችና የልዩ ፕሮግራሞች የአፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር ፓውል አኪዉሚ ናቸው፡፡ በድሆቹና በሀብታሞቹ አገሮች መካከል ለወትሮው የሚታየው የኢኮኖሚ ደረጃ ልዩነቱ እየሰፋ፣ የኑሮ ልዩነቱም እያየለ እንደሚገኝና ይህም ለወደፊቱ አደጋ እንደሚደቅን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ አማካይነት የተሠራው ትንተናዊ ጥናት እንደሚያስቃኘው፣ በኢኮኖሚ ያላደጉ አገሮች ዓምና ያስመዘገቡት አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት በአምስት በመቶ የተገደበ ነበር፡፡ ሆኖም በኢኮኖሚ ወደ ኋላ የቀሩት አገሮች እንዲያስመዘግቡ ይጠበቅ የነበረው ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሰባት በመቶ በላይ ነበር፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በየዓመቱ መመዝገብ ያለበት የኢኮኖሚ ዕድገት ሰባት በመቶና ከዚያ በላይ እንዲሆን በመወሰኑ ነው፡፡ የዘላቂ ልማት ግብ ቁጥር ስምንት በሚያስቀምጠው መሠረት ዘላቂና አካታች የኢኮኖሚ ዕድገት በመላው ዓለም ማስመዝገብ የሚል ቢሆንም፣ በጥቂት አገሮች ውስጥ ካልሆነ በቀር ይህ ሲሆን አልታየም፡፡

ይሁንና አብዛኞቹ ደሃ አገሮች በዚህ ዓመት ያስመዘግባሉ ተብሎ የሚጠበቀው የኢኮኖሚ ዕድገት የ5.4 በመቶ እንደሚሆን ከወዲሁ ግምት ተቀምጧል፡፡ አብዛኞቹ ያላደጉት አገሮች ላስመዘገቡት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያት ከተደረጉ ነጥቦች መካከል በግብርና ሸቀጦች ላይ የተመረኮዘ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ስለሚከተሉ ነው፡፡ የግብርና ምርቶች ደግሞ በዓለም ገበያ ከፍተኛ መቀዛቀዝ በማስመዝገብ ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የታየባቸው የዋጋ ቅናሽ ደሃ አገሮችን ተጎጂ አድርጓቸዋል፡፡

ከ47 አገሮች ውስጥ መረጃ ማግኘት በተቻለባቸው 45 አገሮች መካከል ሰባት በመቶና ከዚያም በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገቡት አምስት አገሮች ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህም ኢትዮጵያ የ8.3 በመቶ፣ ኔፓል የ7.5 በመቶ፣ ማይናማር የ7.2 በመቶ፣ ባንግላዴሽ የ7.1 በመቶ፣ እንዲሁም ጂቡቲ የሰባት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በተመድ የተቀመጠውን ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት መስፈርት በማሟላት ረገድ የሚጠቀሱ አገሮች ሆነዋል፡፡

በዚህ ዓመት እንደሚኖር የሚጠበቀው የእነዚህ አገሮች ዝቅተኛ አፈጻጸም በዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ካላቸው ዝቅተኛ ተሳትፎ አኳያ፣ አነስተኛ ምርት ወደ ውጭ በመላክ በምትኩ ከፍተኛ መጠን ያለው ሸቀጥና ሌላውንም ዕቃ ከውጭ የሚያስገቡ በመሆናቸው ሳቢያ፣ ደሃ አገሮች የሚያስመዘግቡት የንግድ ሚዛን ጉድለትና የተዛባ የክፍያ ሚዛን ይበልጥ እየጨመረ በመምጣት በእጅጉ እንደሚዳከም ሥጋት ተፈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ አገሮች በዚህ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ችግር እየተመቱ ይገኛሉ ያለው ተመድ፣ እንደ አፍጋኒስታንና ደቡብ ሱዳን ያሉ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ የሚያገኙ አገሮችን ጨምሮ፣ ኤርትራና ጊኒ ቢሳው ከተዛባ የክፍያ ሚዛን ነፃ እንደሚሆኑ ተስፋ የተደረጉ አገሮች ናቸው፡፡

ለድሆቹ አገሮች የሚሰጠው ልዩ የውጭ ዕርዳታ ከ43 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ቢገመትም፣ ከዚህ ውስጥ 27 በመቶው ለታዳጊ አገሮች የሚቀርብላቸው ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ለድሆች አገሮች የሚደርሰው መጠንና በየዓመቱ ያሳየው ጭማሪ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚጠበቀው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እየተዳከመና በሕዝቦቻቸው የኑሮ ደረጃ ላይ ሊታይ የሚገባው ለውጥ ወደ ታች እንዳያዘግም ተመድ ሥጋቱን አስተጋብቷል፡፡