Skip to main content
x
ለክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

ለክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ምንድነው አንተ ይኼ?
 • አዲሱ መኪና ነዋ፡፡
 • የሰው መኪና አትያዝ አላልኩህም?
 • ይኼ የሰው መኪና አይደለም፡፡
 • አንተ የእኔ ሾፌር ብቻ ነህ፡፡
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • ታዲያ ይኼ የማን መኪና ነው?
 • የእርስዎ መኪና ነዋ፡፡
 • ሰውዬ በጠዋቱ ጠጥተህ ነው እንዴ የመጣኸው?
 • በዚህ በጠዋት ምን እጠጣለሁ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ታዲያ እንደዚህ ዓይነት መኪና የእርስዎ ነው ስትለኝ ትንሽ አታፍርም?
 • ስለሆነ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለሆነ ነው ማለት ምን ማለት ነው?
 • ባለፈው የወጣውን መመርያ ረሱት እንዴ?
 • እኔ እያንዳንዱን የሚወጣውን መመርያ እንዴት ላስታውስ እችላለሁ?
 • የመንግሥት ባለሥልጣናት ቪ8 መኪናቸውን ለፊልድ ብቻ ይጠቀሙበት የሚለውን መመርያ ነዋ፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው ታዲያ?
 • በመመርያው መሠረት ከተማው ውስጥ የሚያንቀሳቅስዎት መኪና አገር ውስጥ የተገጣጠመ ነዋ፡፡
 • ምን?
 • እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እየቀለድክ ነው እንጂ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይቺን አገር እያጠፋት ያለው ቀልድና ቀልደኞች ናቸው፡፡
 • አሁን የማታውቀውን ፖለቲካ ለመፈትፈት ባትሞክር ጥሩ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ፖለቲከኛ ባልሆንም ከፖለቲካ ግን ማምለጥ እንደማልችል አውቃለሁ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • በቃ የሁሉም ሰው ሕይወት ከፖለቲካ ጋር የተገናኘ ነው፡፡
 • እሺ የእኛ የፖለቲካ ፈላስፋ?
 • እየተፈላሰፍኩ ሳይሆን እውነታውን ነው የነገርኩዎት፡፡
 • አሁን እሱን ተወውና ቪ8ቴን በአስቸኳይ አምጣልኝ፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው?
 • እሱ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ ሲባል አልሰሙም?
 • ምን እያልክ ነው?
 • ቪ8 ቀርቶ ሌላ ከቻይና መጥቷል ተብሏል፡፡
 • ሰውዬ ቅኔ ዝረፍልኝ አላልኩህም እኮ?
 • ያው ለጨዋታ ብዬ ነው፡፡
 • አሁን ቪ8ቴን አምጣልኝ፡፡
 • ቪ8ቱማ ከፊልድ ውጪ አይቻልም ስልዎት፡፡
 • ማነው የከለከለው?
 • መመርያው ነዋ፡፡
 • እኔ አይደለሁ እንዴ አለቃህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ከመመርያ ውጪ ብሠራ ስለምጠየቅ፣ ከፈለጉ ራስዎ ቪ8ቱን መያዝ ይችላሉ፡፡
 • ይቺን ይወዳል ሰውዬው?
 • ክቡር ሚኒስትር ለከተማ ይቺ ናት መኪናዎ፡፡
 • ይኼማ ሊሆን አይችልም፡፡
 • ቪ8 ለፊልድ ብቻ ነው፡፡
 • በቃ ፊልድ እንውጣ?
 • እሱንም ማድረግ አንችልም፡፡
 • ለምን?
 • ከአዲስ አበባ ውጪ መንገዶች ስለተዘጋጉ መውጣት አንችልም፡፡
 • አሁን ምን እንደማደርግ አውቃለሁ፡፡
 • ምን ሊያደርጉ ነው?
 • የሥራ ባልደረቦቼ ጋ ደውዬ አስተባብራለሁ፡፡
 • ምንድነው የሚያስተባብሩት?
 • መውጣት አለብን ብዬ ነዋ የማስተባብረው፡፡
 • ምን?
 • ሰላማዊ ሠልፍ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰላም ነኝ አንተ እንዴት ነህ?
 • አገሪቷ ውስጥ ምንድነው የምሰማው?
 • ምን ሰማህ ደግሞ?
 • አገር ሰላም ነው?
 • ሁሉ ነገር ሰላም ነው፡፡
 • ኧረ እኔ የሰማሁት ነገር ደግሞ ሌላ ነው፡፡
 • ምን ሰማህ ደግሞ?
 • አሁን አንድ ወዳጄ ከአገር ቤት ደውሎልኝ ነበር፡፡
 • ምን አለህ?
 • ተቃውሞው እንደ አዲስ አገርሽቶ ነገሩ ያስፈራል እያለኝ ነው፡፡
 • ይኼ የፀረ ሰላም ኃይሎች ወሬ ነው፡፡
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ይኼንን ነገር ይተው፡፡
 • ምኑን?
 • ሕዝብን ፀረ ሰላም የምትሉት ነገር ነዋ፡፡
 • እንዴት?
 • ሕዝብን እንዴት ፀረ ሰላም ትላላችሁ?
 • አሁን ምክር ልትመክረኝ ነው የደወልከው?
 • ኧረ እንደው የአገሪቷ ሁኔታም ሲያሳስበኝ ነው የደወልኩት፡፡
 • ምንም አያሳስብህ ስልህ?
 • በነገራችን ላይ ሰሞኑን በሶሻል ሚዲያ ያየሁት ነገር አስገርሞኛል፡፡
 • ምን ዓይተህ ነው?
 • አንዳንዴ መንግሥት የሚሠራው ሥራ ያስቃል፡፡
 • ምኑ ነው የሚያስቀው?
 • ባለፈው የጉለሌ ኮሙዩኒኬሽን የለጠፈውን መረጃ ዓይተውታል?
 • ምን ላይ?
 • ፌስቡክ ላይ ነዋ፡፡
 • ፌስቡክ የወሬኞችና የውሸታሞች ቦታ ስለሆነ አልጠቀምበትም፡፡
 • በአሁን ጊዜማ ፌስቡክን መጠቀም አለብዎት፡፡
 • ለምን?
 • በርካታ መረጃዎች ያገኙበታላ፡፡
 • እኔ መረጃ የሚሰጠኝ መቼ ጠፋ?
 • ለማንኛውም የጉለሌ ኮሙዩኒኬሽን የለጠፈው ግን በሳቅ ነው ያፈነዳኝ፡፡
 • ምን ብሎ ለጥፎ ነው?
 • በጉለሌ ክፍለ ከተማ ላሉ ነዋሪዎች ሥልጠና መስጠቱን ነዋ የለጠፈው፡፡
 • ሥልጠና መስጠት ምን ችግር አለው?
 • እሱ አይደለም ቁም ነገሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው ቁም ነገሩ ታዲያ?
 • ሥልጠናው ስለኒዮሊብራሊዝም መሆኑ ነዋ፡፡
 • ታዲያ ምን ችግር አለው?
 • የሥልጠናው ርዕሰ ‹‹ኒዮሊብራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?›› የሚል ነበር፡፡
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን እነትዬ ብርቄና እትዬ አስካለ ኒዮሊብራሊዝም ቢሸሽ ወይም ቢያፈገፍግ አይደለም ፈርጥጦ ቢጠፋ ምን አገባቸው?
 • አንተ ራስህ የኒዮሊብራሊዝም አመለካከት ነው ያለህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን እትዬ ስርጉት ስለኒዮሊብራሊዝም ያውቃሉ ብለው ይገምታሉ?
 • አንተ ሕዝባችንን ስለምትንቀው ነው፡፡
 • እንዲያው ሕዝቡን የምትንቁትማ እናንተ ናችሁ፡፡
 • እንዴት?
 • ሕዝቡ የሚጠይቀው ሌላ እናንተ የምታወሩት ሌላ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • አሁን ፋብሪካ የሚቃጠለውና መንገድ የሚዘጋው ኒዮሊበራሊዝም በመሸሹ ወይስ በማፈግፈጉ ነው?
 • ምን?
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ ሕዝብ በጣም እየታዘባችሁ ነው፡፡
 • አንተ ውጭ ስለምትኖር የዚህን አገር ሕዝብ ብዙም አታውቀውም፡፡
 • ለነገሩ እኔ ፎቶዎቹንም ሳይ የሥልጠናው ዋናው ነገር ኒዮሊብራሊዝም አለመሆኑ ገብቶኛል፡፡
 • የሥልጠናው ዋናው ነገር ምንድነው ታዲያ?
 • አበሉ!

[የክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ወዳጅ ይደውሉላቸዋል]

 • ክቡር ሚኒስትር እዚህ አገር ላይ ምንድነው እየተካሄደ ነው ያለው?
 • ሰው ያለዚህ ጥያቄ የለውም እንዴ?
 • በዚህ ወቅት ሌላ ጥያቄ እንዴት ይጠየቃል?
 • ምን እያልክ ነው?
 • ሰላም ናፈቀን እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኛም እንደ ሕዝብ ሰላም ፈላጊዎች ነን፡፡
 • እውነት ክቡር ሚኒስትር?
 • የሚሠራው እኮ አገር ሰላም ሲሆን ነው፡፡
 • የሚሰረቀው ማለትዎ ነው?
 • ብንከባበር አይሻልም?
 • መከባበር ያለብዎትማ ከሕዝቡ ጋር ነው፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • የሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ ይመለስ፡፡
 • መቼ ነው እኛ የሕዝብ ጥያቄ አንመልስም ያልነው?
 • ከ27 ዓመት በላይ ሊሆናችሁ ነው፡፡
 • ከዚህ በላይ እንዴት ይመለስ?
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እስረኛ እየለቀቅን ነው፡፡
 • የሕዝቡ ጥያቄ እሱ ብቻ አይደለም፡፡
 • እኔ የሕዝቡ ጥያቄ ምንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ፍላጎት ስለሌላችሁ እንጂ ጠፍቷችሁ አይመስለኝም፡፡
 • ሰውዬ ምን እያልክ ነው?
 • እናንተ ራስ ወዳድ ሆናችሁ ኪሳችሁን ማደለብ ስለምትፈልጉ እንጂ የሕዝቡ ጥያቄ ቀላል ነው፡፡
 • ከዚህ በላይ ምን እንደሚደረግ አይገባኝም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ከእኔ በላይ የሚያውቅልህ የለም የሚለው አካሄድ አያዋጣችሁም፡፡
 • አሁን ምንድነው ጥፋታችን?
 • ያለአዋቂ ሳሚ ምን ይለቀልቃል ሲባል አልሰሙም?
 • ልትሞልጨኝ ነው እንዴ የደወልከው?
 • እኔማ የአገሪቷ ሁኔታ አስጨንቆኝ ነው፡፡
 • ምንም አትጨነቅ፡፡
 • ለነገሩ እኔ ከድሮም ጀምሮ አውቅዎታለሁ፡፡
 • አውቅዎታለሁ ስትል?
 • ያው በልጅነታችን ካርታ ስንጫወት ያስታውሳሉ፡፡
 • ሁሌም እኔ እንደ በላሁዋችሁ ነበር፡፡
 • አሁንም እየተጫወቱ ያሉ ነው የመሰለኝ፡፡
 • ምን?
 • ቁማር!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር የፓርቲ ስብሰባ አድርገው ሊጨርሱ ነው]

 •  ክቡር ሚኒስትር በማጠቃለያው ምን ይላሉ?
 • አሁን ባፋጠኝ የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ አለብን፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ከበርካታ ሰዎች ጋር አውርቼ የነገሩኝ አንድ ዓይነት ነገር ነው፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • እስረኛ መፍታት ችግሩን አይፈታም፡፡
 • ታዲያ ሌላ ምን ይደረግ?
 • ሌላው የሕዝቡ ጥያቄ ይሰማ፡፡

[ሌላኛው ባለሥልጣን መናገር ጀመሩ]

 • እኔም ክቡር ሚኒስትሩ ያሉትን ሐሳብ እደግፋለሁ፡፡
 • የትኛውን?
 • የሕዝቡ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡
 • እሱማ ትክክል ነው፡፡
 • ስለዚህ እስከ ታች ድረስ ያለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡
 • ሁላችንም ተስማምተናል፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የስብሰባው መጠናቀቅን አስመልክቶ ምን መደረግ እንዳለበት ሐሳብ ማሰባሰብ ጀመሩ]

 • እንግዲህ ስብሰባችንን ጨርሰናል፡፡
 • ምን ይደረግ ይላሉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ትንሽ ብንዝናና ጥሩ ነው፡፡
 • እንግዲያው እኔ አንድ ሐሳብ አለኝ፡፡
 • ምድነው እሱ?
 • አንድ ብላክ ሌብል አወርዳለሁ፡፡

[ሌላኛው ባለሥልጣን ማውራት ጀመሩ]

 • እኔ ጎልድ ሌብል አወርዳለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በጣም ደስ ይላል፡፡

[ሌላኛው ባለሥልጣን በተራቸው ተናገሩ]

 • እኔ ብሉ ሌብል አወርዳለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼ ደግሞ ጫን ያለ ነው፡፡
 • እርስዎ ምን ያወርዳሉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ራሴን፡፡
 • ከምን?
 • ከሥልጣን!