Skip to main content
x

ትውልዱ የሥነ ምግባር ትጥቁን ጨርሶ እንዳይፈታ!

በንጉሥ ወዳጅነው 

    በተለያዩ ጊዜያት በሥነምግባራችንና ሞራላችን አማካይነት በሰብዕናችን ላይ የታዩ ችግሮች ምንድን ናቸው? አገራዊ ጉዳታቸውስ ምን ያህል ነው? የችግሮቹ ምንጮችስ ምን ምን ናቸው? መፍትሄያቸውስ? በሚሉ ዐበይት ምዕራፎች ዙሪያ ሰፊ ጊዜ የወሰደ  አገራዊ ውይይት ስለመደረጉ አላውቅም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስለ ሞራልና ሥነምግባር  ችግር አለብን ብሎ የሚያምንና ከዚህ በመነሳትም ለውጥን ለመፈለግ የሚሞክር አገር ወዳድ ዜጋ ወይም መንግሥታዊ አካል ቁጥሩ ሲመነምን ማየት ደግሞ በጉዳዩ ላይ የሚታየውን ሥጋት ያንረዋል፡፡

   በዚህ መነሻ ርዕሰ ጉዳዩ አንገብጋቢና ወቅታዊ መሆኑን ከመገንዘብ ባሻገር  መነጋጋሪያ እንዲሆን ለዛሬ ተመርጧል፡፡ እንደ አገር በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ  ተባብሶ እንደሚታየው ሁኔታ ትውልዳዊ የሥነምግባርና ሞራል ጉድለት (ምንም  እንኳን ሐሳቡ ሰፋፊ ነጥቦች ሊነሱበት የሚችል መሆኑ ቢታመንም) እየነገሠ እንደመጣ መናገር ይቻላል፡፡ በዚህ ጸሐፊ ዕይታ ክፍተት ከሚመስሉት መካካል ጥቂቱን መጠቃቀስም  ተፈልጎል፡፡

በአገራዊ የጋራ እሴት አለመኩራትና አፍራሽነት

     አገራዊ የጋራ እሴትን፣ ትውፊትና አኩሪ ልማድን ጠብቆና አስፋፍቶ መገኘት ከሥነምግባርና ሞራል እሴት (Ethics and Moral Value) መመደብ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በእርግጥ አሁን ባለው ዓለም የማይካደው እውነት በአንዱ አገር የተከሰተ ደግሞ ሆነ መጥፎ ድርጊት በንፋስ ፍጥነት ወደ ሌላው አገር የመሸጋገርና በአጭር ጊዜ የመወረሱ አደገኝነት በተለይ ለወጣቱ ፈታኝ መሆኑ  ነው፡፡ ለዚህም ነው በብዙ አገሮች የሚነሱ የሽብርተኝነት አስተሳሰብና ድርጊቶች፣ የዘረኝነትና አድሎ ፍላጎቶች፣ አመፀኛ የለውጥ እንቅስቃሴዎችና አለመረጋጋቶች ከአፅናፍ አጥናፍ እየተስተጋቡ የሚስፋፉት፡፡ ሕገወጥ ስደት፣ ሕገወጥ የዕፅ ዝውውር፣ የጦር መሣሪያ ዝውውርና ሕገወጥ ንግድ እንዲሁም የባሕር ላይ ውንብድናና ሌሎችም ተግዳሮቶች  የብዙ አገሮች መንግሥታትና ሕዝቦች ሥጋት የመሆናቸው እውነትም ከዚሁ ይመነጫል፡፡ ያም ሆኖ በየአገሮቹ እንደየ ሕዝቡ ሞራልና ሥነምግባር ወይም እንደ መንግሥታቱ ድክመትና ጥንካሬ የችግሮቹ የጉዳት መጠን ተመሳሳይ የመሆን ዕድል እንደሌላቸው የሚታወቅ ነው፡፡

  ለውጥ ደግሞ የማይቀር የማኅበረሰብ ተፈጥሮዊ ባህሪ እንደመሆኑ እነዚህ ሁኔታዎች በየአገሮቹ ያለውን የኖረ አስተሳሰብ እየለወጡና እየሸረሸሩ መሄዳቸው አይቀርም፡፡ በአገራችን እየታየ ያለው ነበራዊ ሀቅም ከዚሁ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል አገር ጥሎ መሰደድ (ያውም ጎረቤት አገርና መካካለኛው ምሥራቅ) በከፋው የድህነት ዘመናችን እንኳን ፈፅሞ ከማይታሰብበት ሁኔታ ተነስተን ዛሬ አውሮፓና አሜሪካ አይሉት  የትም እግር የመራው አገር ያውም በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሰደድ የሐበሻ መገለጫ ሆኖል፡፡ አሳዛኙ ነገር ደግሞ ቀድሞ በሕገወጥ መንገድ በተሰደደው ወገን ላይ ከፍተኛ ስቃይና መከራ እየደረሰም የቀጠለ ድርጊት መሆኑ የችግሩ መነሻ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን የሞራል ውድቀትና በእናት ምድር ሠርቼ እቀየራለሁ የሚል ተስፋ መመናመን የወለደው ችግር ጭምር እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡

    በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን በቀደመው ጊዜ የነበራቸው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የጠነከረ እንደ ነበር በብዙ መገለጫዎች ሊጠቀስ የሚችል ሀቅ ነው፡፡ በተለይ በመቼውም ጊዜ (በፀረ ዴሞክራሲ ሥርዓቶች ውስጥም) አገር ስትወረርና የጋራ ጠላት ሲደፍረን  ሕዝቡ በአንድነት ቆሞ ጠላትን ሲያሳፍር የኖረበት መንገድ በኩራት የሚወሳ ነው፡፡ ይኼን የሚያደርገው ደግሞ ቋንቋ፣ ዘርና ቀለም ሳይለየው በፈጣሪም ሆነ በባንዲራው ስም በሚደረግለት ጥሪ ብቻ እየተመሠረተ ደምና አጥንቱን በመገበር፤ በአንድ ጉድጓድ እስከመቀበር እየደረሰ ነበር፡፡ ያም ሆነ እንደ የፖለቲካ ሥርዓቱ ችግር (በተለይ በትምክህትና በጠባብነት አመለካካቶች ቆስቋሽነት) ሁሉ እንደ ሕዝብ  የተለያዩ ልዩነቶች መንፀባረቃቸውና የእርስ በርስ ግጭቶች (በየትኛውም ዓለም እንደሚያጋጥመው) ይከሰቱ እንደነበር መካድ አስቸጋሪ ነው፡፡

      ከዚያ አልፎ ግን አሁን እየሆነ እንደሚታየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአንድነቱ በላይ ልዩነትን እያስበለጠ፤ ሕዝብ ለሕዝብ እየተጋጨና እየተጠፋፋ፤ አንዱ ሌላውን አሳዳጅ እየመሰለ በሌሎች አገሮች የምንፈራው ድርጊት ውስጥ ሲገባ አልታየም፡፡ ከሁሉ በላይ በጎሳና በዘር እየተቧደኑ ለርካሹ የፖለቲካ ትርፍ የሚተጋተጉ ጥገኞችን አፍርቶና አልምቶ በዩኒቨርሲቲና በየሥልጠና ተቋሙ ሳይቀር የሚታመስ ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ድረ ገጽም በማይበጀው የጥፋት መንገድ ሲላጋ የሚውል፣ የሚያድረው ወጣት መብዛቱ ሲታይ ችግሩ ከፖለቲካው ብቻ ሳይሆን ከነባሩ የሞራልና ሥነምግባር አገራዊ ዋጋ እንደመውጣት የሚቆጠር ነው፡፡

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ አገራዊ የጋራ እሴትን እየጣሉ በመንደርና በቡድን አስተሳሰብ ታጥሮ መንጎድ የኋላቀርነት መንገድ መሆኑን ተገንዝቦ ከራስ፣ ከሕዝብና ከአገር መታረቅ ብሎም ትልቁን ሥዕል ማየትና ነገን ማሰብ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ ተግባሩ የሞራልና የሥነምግባር መኮሰስ የወለደው ጭምር መሆኑን አጢኖ ወደ ሕሊና መመለስም ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥትም ቀዳሚና ወሳኝ ተግባር ሊሆን ይገባዋል የሚል የፀና እምነት በሁሉም ወገን መያዝ ይኖርበታል፡፡

ሙስናና የሌብነቱ መገንገን

     በአገራችን ስርቆት ሌላውና ዋናው የሥነምግባር ጉድለት ገጽታ እየሆነ መምጣቱም የሚያሳስበን ፀያፍ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ዙሪያችንን መታዘብ እንደምንችለው ችግሩ ድሮም ያለ ቢሆንም፣ በተባባሰ ደረጃ ሙሰኛ አመራርና ባለሙያ፣ ደላላና ጉዳይ ገዳይ፣ ከዚያም አልፎ ቄስና ሼሕ፣ እንዲሁም በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚቋምጥ ባለሀበት ተብየ (ጥገኛ) እንዴት ለመበራከት  ቻሉ  ብሎ መጠየቅ የችግሩን ሥረ መሠረት ለመመርመር ይረዳ ይሆናል፡፡

   አንዳንዶቻችን በመንግሥት ቤት ወይም በግል ድርጅት ለምነን እንዳልተቀጠርን ወይም በውድድር ተቀጥረን (ተሾመን)ም ገና ፊርማችን ሳይደርቅ በትናንሽ ስርቆት (Larceny) ውስጥ ተዘፍቀን መገኘታችን ከምን የመጣ ውርደት ይሆን ያስብላል፡፡ በሕዝብና መንግሥት ሀብት ዘረፋ፣ የሀብት ተራራ ላይ ወጥቶ መፏነንስ እንዴት የቀለለ ተግባር ሊሆን ቻለ? የሚለው ከፍ ያለ ተጠየቅ የሚነሳበት አንገብጋቢ ወቅት አሁን ይመስለኛል፡፡

    በብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች  የሚታየው ቀዳሚውና ትንሽ መሰል ሕዝብ አማራሪ ችግር (እየተሻሻለ መልሶ እያገረሸ) የሥራ ሰዓት ስርቆት ነው፡፡ አርፍዶ መግባት፣ ቀድሞ መውጣት የብዙ መሥሪያ ቤቶች ሀሁ ሆኗል፡፡ ለሥራ የተሰጡ  አላቂ ቁሳቁሶች ወረቀት፣ አግራፍ፣ እስክሪብቶ፣ ካኪ ፖስታ ቢጠቅምም ባይጠቅመም በቦርሳ ከትቶ መሄድ ጤነኛ ተግባር መስሏል፡፡ 

   ከሙስና ባልተናነስ የሚታየው ጥፋትም ምንቸገረኝነት ነው፡፡ በብዙ ቦታዎች  የመንግሥት ንብረት የሆነን ነገር ሁሉ መውሰድ፣ አልያም ማበላሸት ‹‹ደግ አደረክ›› የሚያሰኝ መጥፎ ልምድ ጥርሱ ሳይነቀል የቀጠለ መስሏል፡፡ በመንግሥት ግዥ ሽያጭና የአገልግሎት ኪራይ ላይ የሚካሄድ ዘረፋና መሞዳሞድም ተያይዞ የሚመጣ የሥነምግባር ጥሰት ነው፡፡

    በድሃ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ሲል ተበድሮና አብቃቅቶ ሳይቀር ለኤሌክትሪክ ማስተላለፊያና ቴሌኮም አገልግሎት  የሚያስተክላቸው  ብረቶችንና የተወጠሩ ሽቦዎችን ያለ ርህራሄ እየቆራረጡ መውሰድ የተለመደ አሳዛኝ ተግባር እየሆነ ነው፡፡ በከፍተኛ ድካም የሚገነቡ መሠረታዊና ማኅበራዊ ልማቶችን በሕጋዊ ጥያቄ ስም ማውደም የሕዝብን ውድ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፤ ‹‹ባሏን ጎዳሁ ብላ… ወጋች›› እንዲሉ፡፡

     ለዚህ ዓይነቱ ሕገወጥ ተግባር መባባስ የሚነገር አንድ አባባልም አለ፡፡ የቻይና ሰዎች ቢገርማቸው  እነዚህ ሰዎች (እኛንኮ ነው!) ‹‹ሌላ አገር አላቸው እንዴ?›› እስከማለት ደርሰዋል የሚል፡፡  በወጉ ከተመረመረ ነገራችን ሁሉ ግራ አጋቢ ሆኗል፡፡ በአንድ ወገን ከድህነት ለመውጣት ለመሮጥ እንዳክራለን፣ በሌላ በኩል ዘረፋ፣ አባካኝነትና ማውደምን አውግዘን በጽናት መቆም አልቻልንም፡፡ ይኼን ተመካክረንና ተማምነን ማስቀረት ትውልዳዊ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን አደራም ጭምር ነው መባሉም ከዚሁ ሥጋት በመነሳት ነው፡፡

      ባጠቃላይ አጋጣሚውን ካገኘሁ ለወል ሀብት ግድ ማጣት ብቻ ሳይሆን ቀላል ቁጥር ሌለው የመንግሥት ሠራተኛ ወይም የግል አገልግሎት ሰጪና ነጋዴ ሙሰኛ የመሆን የስግብግብነት ዝንባሌ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ብሎ ለራስና ለማኅበረሰብ ጥያቄ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ችግሩ በእምነት ተቋማት እንኳን አለመወገዱ ሲታይ  እርምትን የሚሻ አገራዊ ውድቀት መሆኑን ያመላክታል፡፡

     እውነት ለመናገር ከድህነታችንም ይመንጭ የሞራልና ሥነምግባር ውድቀት ያምጣው በጥናት ባይረጋገጥም በአብዛኛው እንደ አገር የሚታይብን አዝማሚያ ሁሉ የማይገባንን ጥቅም የመሻማት፣ ያልደከምንበትን ገንዘብ የማጋበስና ላብ ሳያወጡና ሳይደክሙ የመበልፀግ አካሄድና አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ምንቸገረኝነትና ለወል ሀብትና ለአገራዊ ጥቅም ያለመቆርቆር በብርቱ ትግል ሊሰበር የሚገባው ውዳቂ አመለካከት ነው፡፡

ከመዝናናት  ያለፈ ሴሰኝነትና መፋዘዝ

    በዚህ ነጥብ በርከት ያሉ ማኅበራዊ ድክመቶቻችን ሊነሱበት የሚችል ነው፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ እንኳን ኅብረተሰቡ ብዙ ጉድ ተሸክሞ ያለ ሕዝብ ነው፡፡ በተለይ በከተሞች የማስተማር ኃላፊነቱን እንዲወጣ በሥራው አጋጣሚ ያገኛትን ትንሽ ልጅ (ተማሪ) የሚያማግጥ መምህር የሚታይበት  ጊዜ  ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ለተማሪው የፈተና መልስ የሚነግር፣ እንዲኮራረጁ የሚፈቅድ (እያየ ዝም የሚል) ከተማሪዎቹ ጋር አብሮ ጫት የሚያላምጥና ሲጃራ የሚቀባበል…. አስተማሪ ባለበት ሁኔታ ምን ዓይነት ሥነምግባር ሊኖር ይችላል? ምን ዓይነት ሰብዕና እየተገነባ ነው ብሎ አለመጠየቁ ነው እንደነውር መቆጠር ያለበት፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የተቀረፀ ትውልድ ለልማት ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ መሠረታዊ ህልውና ሊጫወት የሚችለው ሚናስ  ምንድን ነው? ብሎ አለመፈተሽም ጉዳቱ የትየለሌ ነው፡፡

     በማኅበረሰቡ ውስጥም ነውርና ብልግና እንደ ሥልጣኔና ቅንጦት እየተቆጠሩ የመምጣታቸው ነገር አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ጢማቸውን ላጭተውና ጠጉራቸውን በቀለም አጥቁረው መኪና ይዘው የልጅ ልጅ የሚሆኗቸውን ሕፃናት ሴቶች ሲያሳድዱ የሚውሉ ወጣት መሳይ ሽማግሌዎች (ወመሽ) በሚርመሰመሱበት ከተማ ውስጥ እንዳለንም  መዘንጋት የለበትም፡፡ ወጣት አጥማጅ ሴቶችም በባለገንዘቦቹ ሽማግሌዎች  ንዋየ  ፍቅር  (የስኳር ጨዋታ)  እየተሞላቀቁ  ሲማግጡ  ማየት እንደ ቀልድ ተቆጥሯል፡፡

       በየአካባቢው የቀን ዳንስ ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶችና በማሳጅ ስም የፍትወት መነገጃ ቤቶች … ዓይነት ያልተለመዱ ሥፍራዎች የተስፋፉበት፣ አዛውንቶችና ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ተማሪዎች ዩኒፎርማቸውን ለብሰው ገብተው ውስጥ ቀያይረው  የሚማግጡባቸው ቤቶች መበራከታቸው አገርን ካላስደነገጠ ትውልዳዊ ኪሳራው መቆሚያ ሊኖረው አይችልም የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ኤችአይቪ ኤድስ ዳግም አንሰራርቶ የማጥቃት  ዕድል እንዲያገኝስ ማን አደረገው!

    በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባና ዋና ዋና ከተሞቻችን ጫት ማስቃሚያና ሺሻ ማጨሻ ቤቶች እንደ አሸን እየፈሉ ናቸው፡፡ እነዚህ የማኅበረሰብ ቀውስ አመንጪ ሥፍራዎችን እንደ ሕዝብ በጋራ ታግለን መቀነስና ማስቀረት ሲገባ ለነገሮች ሁሉ ውጫዊ ምክንያት እየፈለግን ጣታችንን መንግሥት ላይ መቀሰር ብቻ ዋጋ  ሊኖረው አይችልም፡፡ ነገሩን ወደ ራስ ካመጣነው ሕዝቡስ በየአደረጃጃቱና ቤተ እምነቱ ድርጊቱን ማውገዝ የሚሳነው ለምን ይሆን ያስብላል፡፡ ከዚህ አንፃር ትውልድ መታደግ የሚያስፈልገው ከሴሰኝነትና ያለፈ ሱሰኝነት ጋር ተያይዞ በተጀመረው ዘመቻ ላይ ሊሆን ይገባዋል፡፡

የትውልዱ ገሳጭ ማጣት አሳሳቢነት 

  በአንዳንድ አካባቢዎች  ከከተሞች መስፋት አንፃር የነዋሪው ሕዝብ ቁጥር በየጊዜው ሲጨምር ማን የማን ልጅ እንደሆነ ለመለየት አይቻልም፡፡ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር ሕገመንግሥታዊ መብት መከበር በፈጠረው አመቺ ሁኔታ በሁሉም ክልሎችና ከተሞች መጤው እየበዛ ነው፡፡ በሕዝቦች መካከል መተዋወቅና መግባባቱም እየላላ ነው  የሚሉ ወገኖች ተበራክተዋል፡፡ ‹‹የእከሌ ልጅ (ዘመድ) አይደለህም ወይ… ቆይ ለአባትህ ባልነግርልህ…›› ማለት ድሮ ቀርቷል ቢባል ሐሰት የለውም፡፡ ለነገሩ እንደ ድሮው ተቆጭና ተፈሪ ሽማግሌዎች በተሞላ ሞራል አሉን ወይ ብሎ ማለትም ተገቢ ነው፡፡

    በተለይ አዲስ አበባን በመሰለው ከተማ የትም ውሎም ሆነ አምሽቶ፣ ሠርቶም ሆነ ቀምቶ ትንሽ ሳንቲም ይዞ ከመጣ ስለሌላው ጉዳይ የሚቸገር ቤተሰብ እየቀነሰ የመጣ ይመስላል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ብዙ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን መቆጣጠር አለባቸው ሲባል እንሰማለን፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ሁሉም ማለት ቢከብድም በአብዛኛው ወላጆች ልጆቻቸውን የሚቆጣጠሩበት ዕድል ግን እየጠበበ ነው ለማለት ይቻል ይመሰለኛል፡፡

       ከድሃው ኅብረተሰብ አንፃር በኑሮ ውድነቱ የተነሳ ወላጆች ለቤተሰባቸው ኑሮ የሚሆን ገቢ ለማስገኘት ባልተቋረጠና አድካሚ በሆነ የሕይወት ሩጫ ላይ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ወላጆች ምናልባት ሕፃናት ልጆቻቸውን ካልሆነ በቀር ከፍ ከፍ ያሉ ልጆቻቸውን መቆጣጠር ከአቅማቸው በላይ እየሆነ ነው፡፡ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያለው ወጣትም በአብዛኛው በቤተሰብ ሀብትና ከውጭ በሚገኝ ገንዘብ እላፊ ከመዝናናትና ከመሳነፍ አንፃር የሚታሙ በርካታ ችግሮች የሚንፀባረቁበት ነው፡፡

     አንዳንድ ጊዜ በመዲናችን በየመንገዱ ላይ የሚካሄደው የሞባይልና የቦርሳ ንጥቂያ፣ ለጆሮ የሚቀፍ ስድብና የቡድን ጠብ በሕግ አስከባሪው አቅም እንኳ የሚቻል አይመስልም፡፡ ፖሊሱም እየተሰላቸ መጥቶ ሁሉም ነገር ዓይኑ ሥር ሲደረግ ዝም ብሎ የሚያይበት ሁኔታ አንዳንዴም እግሬ አውጪኝ እያለ ሲሸሽ ማየት እየተለመደ ነው፡፡ ከጥፋተኞች ጋር የሚተባበሩ ሥነምግባር የለሽ አንዳንድ ፖሊስ ተብየዎችም አሉ፡፡ ያልተገባ ጥቅም ለማስገኘት ብልሹ ፖሊሶች  የወንጀል  ሥራ ውስጥ (ከወንጀለኛ ጋር እስከመደራደር የሚደርሱ) የሚገቡ እንዳሉ የሚናገሩ ዜጎችም በዝተዋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች  ወጣቱን ገሳጭ አልባ አካሄድ እንዲሄድ እያደረጉት ነው፡፡

    ሕግና ሥርዓት ለማስከበር የሚቋቋመው የደንብ አስከባሪ መዋቅርም በጥብቅ መፈተሽ ያለበት ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደሚታየው የደንብ መዋቅሩ ሕግና ሥርዓት እያስከበረ መሆኑ ሊካድ ባይችልም በአብዛኛው ግን ድሃ በማሳደድ የሚያምን፣ ከትንሽ ከትልቁ ቅንጥብጣቢ ሙስና በመለቃቀም የሚታማ፣ አስተዳዳሩም ሕገወጥነት እንዲቆም ሳይሆን መደራደር እንዲበዛ ያቋቋመው እንደሚመመስል አጥብቀው የሚወቅሱ ብዙዎች ናቸው፡፡

       ይኼን በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረ አሉታዊ አስተሳሰብ መቅረፍና በሕግ የበላይነት ላይ የሚያምንና ሕዝቡም የሚያከብረውና የሚያምነው የፀጥታ ኃይልና የሕግና ደንብ አስከባሪ አካል ለመገንባት ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ራሱ ሕዝቡ ያለበት የመኮትኮት፣ የመታገልና የመገንባት ሚና ቀላ እንዳልሆነ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ለትውልዱ ቀጭና ገሳጭ የመገንባት ሚና እንዳለውም ታሳቢ ሊደረግ ይገባዋል፡፡ 

   ለነገሩ ለማኅበረሰቡ  የሞራል፣ የእምነትና ሥነምግባር መጠናከርና አሉታዊ ድርጊቶች መገታት የእምነት ተቋማት ያላቸው ድርሻም በቀላሉ ሊገመት የሚችል አልነበረም፡፡ በኖረው የአገራችን ልማድ ፈሪሃ ፈጣሪ፣ መከባባርና መተዛዘን ያለው ማኅበረሰብ (በጨቋኝ ሥርዓቶችም ጭምር) የበዛ እንደነበር ማስተባበል አዳጋች ነው፡፡ ከዚህ በመነጨ እንኳንስ ለሕጋዊ (ለተቀባ) መንግሥታዊ አካልና ሕግ ይቅርና ለአገር ሽማግሌ፣ ለመምህራን፣ ለሃይማኖት አባቶችና በዕድሜም ከፍ ለሚሉ ታላላቆች የሚሰጠው አክብሮትና ተግሳፅን የመስማት አኩሪ ባህል ተረት እየሆነ የመጣ መስሏል፡፡ ይኼ ሁኔታም በሥልጣኔ፣ በዕውቀትና ማደግ ስም የአዲሱ ትውልድ የሞራልና ሥነምግባር ትጥቁ እንዲላላ አሉታዊ አስተዋፅኦ አላደረገም ማለት ያስቸግራል፡፡

ማጠቃለያ

   ‹‹ትውልዱ የሥነ ምግባርና ሞራል ትጥቁን ጨርሶ እንዳይፈታ›› በሚል ለጊዜው እንደ አንድ ዜጋ በራሳችን በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን እንደመጣልኝ  ለመጠቃቀስ  ሞክሪያለሁ፡፡ በዚህ ማኅበራዊ ሒስ ውስጥ ራስን ከኃጢአቱ በማንፃት ለመመልከት ወይም የመንግሥት ድርሻና ኃላፊነት በመዘንጋት ሳይሆን፤ አንባቢ ሁሉ ራሱን እንዲፈትሽን እንዲወያይበት፣ የቻለም ተጨማሪ ሐሳቦችን እንዲሰነዝርበት ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት ነው የሞከርኩት፡፡ የመልእክቴ ማጠንጠኛም ሁላችንም ችግሩን ወደ ውስጥ በማየት ትውልድና አገርን የመታደግ ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን የሚልም  ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡