Skip to main content
x
ሆሄ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ጸሐፊዎችን ያወዳድራል
አቶ ዘለዓለም ምሕረቱ

ሆሄ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ጸሐፊዎችን ያወዳድራል

ሆሄ ዓመታዊ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም ግጥምና ወግ የሚያስነብቡ ጀማሪ ጸሐፊዎችን አወዳድሮ እንደሚሸልም አስታውቋል፡፡ ዓምና የመጀመሪያው ዙር ውድድር የተካሄደው በረዥም ልቦለድ፣ በልጆች መጻሕፍትና በግጥም ዘርፍ ሲሆን፣ ዘንድሮ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ታክሎበታል፡፡ በ2009 ዓ.ም. በማኅበራዊ ድረ ገጽ (በዋነኛነት በፌስቡክ) ከቀረቡ ግጥሞችና ወጎች በተጨማሪ ታትመው ለንባብ የቀረቡ የወግ መጻሕፍትም በውድድሩ ይካፈላሉ፡፡

የሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዘለዓለም ምሕረቱ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በርካታ ጀማሪ ጸሐፍት ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም በሚያስነብቡዋቸው ሥራዎች ይታወቃሉ፡፡ ‹‹ብዙ ጸሐፊዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም እየመጡ ስለሆነ ዕውቅና ለመስጠት ዘርፉን በሽልማት አካተናል፤›› ይላል፡፡

በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ አማተር ጸሐፊዎች በ2009 ዓ.ም. በፌስቡክ ፖስት ካደረጓቸው ግጥሞች ወይም ወጎች መካከል አንዱን መርጠው ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ከዚህ ቀደም ሥራዎቻቸውን ያላሳተሙ መሆን ያለባቸው ሲሆን፣ በውድድሩ ካሸነፉ ጽሑፎቻቸው ታትመው ለሕዝብ እንዲደርሱ ይደረጋል፡፡

‹‹አቅም ያላቸው ጸሐፊዎች ሥራዎቻቸው ታትመው ሰዎች እንዲያውቋቸው ለማድረግ ይረዳል፡፡ ጽሑፎቹ በሥነ ጽሑፋዊ መስፈርቶች በዳኞች የሚመዘኑ ይሆናል፤›› ሲል ገልጿል፡፡ ውድድሩ በግንባር ቀደምትነትን የልጆችንና በአጠቃላይ የማኅበረሰቡን የንባብ ባህል ለማዳበር ያለመ እንደመሆኑ ጽሑፎቹ እንዲታተሙ ማድረግ የጎላ ሚና እንዳለው ያክላል፡፡

በ2009 ዓ.ም. በተካሄደው ውድድር በረዥም ልቦለድ ዘርፍ አዳም ረታ በ‹‹የስንብት ቀለማት››፣ በልጆች መጻሕፍት ዘርፍ አስረስ በቀለ በ‹‹የቤዛ ቡችላ›› እና አበረ አያሌው በ‹‹ፍርድና እርድ›› አሸንፈዋል፡፡ ዘለዓለም እንደሚለው፣ ለሽልማት የበቁት መጻሕፍት ተነባቢነት መጨመሩን አስተውለዋል፡፡ ከመጻሕፍት ሻጮችና ከደራስያኑ በሰበሰቡት መረጃ መሠረት የመጻሕፍቱ ሽያጭ ከፍ ብሏል፡፡

የመጻሕፍት ሽያጭን ከፍ የማድረግ ባለፈ የልጆችን የንባብ ባህል የማዳበር ሥራዎችን መሥራታቸውን ይናገራሉ፡፡ ልጆች የሚገኙባቸው ቦታዎች የሕፃናት መጻሕፍትን በማስነበብና ስለ ንባብ ጠቀሜታ በማስተማር እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ‹‹የንባብ ባህል ከልጅነት የሚጀምር በመሆኑ የልጆችና የመጻሕፍትን ቁርኝት በማጥበቅ ላይ እናተኩራለን፤›› ይላል፡፡

በየዓመቱ የሚታተሙ መጻሕፍትን በየዓመቱ መጨረሻ በመሸለም ብቻ በንባብ ባህል ላይ ጉልህ ለውጥ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ስለዚህም የተለያዩ መርሐ ግብሮች እንደሚያዘጋጁ ይናገራል፡፡ ከነዚህ መካከል ከሴት ደራስያን ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት የሚሠሩት ይገኝበታል፡፡ ከተቋሞቹ ጋር በጋራ የመጻሕፍት ውይይትና ንባብ ተኮር ወርክሾፖች ይዘጋጃሉ፡፡

‹‹መርሐ ግብሩ አንዴ ደምቆ መጥፋት የለበትም፡፡ ተከታታይነት እንዲኖረው፣ የውይይት መድረኮችና ወርክሾፖችን እናካሂዳለን፤›› ይላል፡፡ በዘርፉ ዘላቂነት ያለው ለውጥ ለማምጣት ዓምና ውድድሩን ያሸነፉ መጻሕፍት በድጋሚ እንዲታተሙ ከቡክላይት አሳታሚ ድርጅት ጋር ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ደራስያኑ ከመጻሕፍት ሽያጭ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሚያግዝም ያስረዳል፡፡

ደራስያን ቀጣይ ሥራዎቻቸውን የሚያግዝ ገንዘብ ከመጽሐፋቸው ሽያጭ እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር፣ ሥራዎቻቸውን በሚዲያ የማስተዋወቅ እንቅስቃሴም ያደርጋሉ፡፡ በተጨማሪም አዳዲስ አንባቢዎችን በማፍራት ላይ እንደሚያተኩሩም ይናገራል፡፡ ‹‹የሚያነበውን ሰው ታሳቢ ከማድረግ ባሻገር የማያነቡ ሰዎች ላይ በማተኮር የንባብ ፍላጎት እንዲያድርባቸው እንሠራለን፤›› ሲልም ያስረዳል፡፡