Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

በመስከረም 1998 ዓ.ም. የመስቀል በዓል ሲከበር በመስቀል አደባባይ ተገኝተን ነበር፡፡ በዚያን ወቅት የአዲስ አበባ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ኢሕአዴግን በምርጫ ካርድ ያሰናበተበት ጊዜ በመሆኑ፣ በኢሕአዴግና በተቃዋሚዎች ንትርክ የተነሳ አዲስ አበቤዎች አኩርፈን ስለነበር የመስቀል በዓል ሲከበር ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ተቃውሞ አጋጠመ፡፡ በዓሉን ለማክበር ከመጣው ሕዝበ ክርስቲያን መሳ ለመሳ የፌዴራል ፖሊሶችም ተገጥግጠው ስለነበር፣ የሕዝቡን ብስጭትና ተቃውሞ ለመበተን የተጠቀሙበት ሥልት በበዓሉ ላይ ከፓትርያርክ አባ ጳውሎስ አጠገብ የነበሩ በርካታ የውጭ አገር እንግዶችና አምባሳደሮች በትዝብት በዓሉን አቋርጠው መውጣታቸው (መመለሳቸው) ይታወሳል፡፡ በዚያ 1998 ዓ.ም. መስከረም መጨረሻ ላይ ፓርላማው ሲከፈት የቅንጅት ፓርቲ መሥራቾች የነበሩት ዋና ዋናዎቹ ምሁራን ከርቸሌ ወርደው ነበር፡፡ ተጎርዶ የቀረው ቅንጅትም ከኅብረት ፓርቲ ጋር በመሆን ወደ ፓርላማ ለመግባት ተገደዱ፡፡ አገሬ ኢትዮጵያም በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ተቃዋሚዎችና መንግሥት አንድ አዳራሽ ውስጥ ቁጭ ብለው በአገራቸው ጉዳይ ላይ መከራከርና መጨቃጨቅ ያዙ፡፡

ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ ከ120 በላይ የሚሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ከኢሕአዴግ መንግሥት ጋር ፓርላማ ውስጥ ያደርጉት የነበረው የሐሳብ ፍጭት እጅግ አስደሳችና የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ምልክትም ሆኖን ነበር፡፡ ዛሬ በእንግሊዝ ፓርላማ ውስጥም ሆነ በአሜሪካው ምክር ቤት ሪፐብሊካኖችና ዴሞክራቶች የሚያደርጉትን ያህል ክርክርና የፖለቲካ ውይይት፣ እኛም በዚያን ጊዜ ለማየትና ለመስማት በመታደላችን አገሬ ኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ መንግሥት አስተዳደር ምሳሌ በመሆን ለአፍሪካውያን እንደ አርዓያ ለመታየት በቅታ ነበር፡፡ የዛሬን አያድርገውና፡፡

ታዲያ በእነዚህ ወርቃማ የፓርላማ ዓመታት ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ ከ120 በላይ ለሚሆኑት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በፓርላማው ውስጥ መልስ የሚሰጡት፣ የሚሟገቱትና ብቻቸውን የሚጋተሩት ‹‹መልስ በኪሱ›› ይበሉ የነበሩት የኢሕአዴግ ፊታውራሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና መለስ ዜናዊ ከፓርላማ አባላት በተረትና ምሳሌ ጭምርም ሳይቀር ያቀርቧቸው የነበሩት መከራከሪያዎችና ትንተናዎች 547 የፓርላማ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን፣ በቴሌቪዥን መስኮት የፓርላማን ውይይት ለምንከታተል ሁሉ ያስቀንና ያስገርመን ነበር፡፡ ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፓርላማ ብርቅ ነበር፡፡

ታዲያ በተለይም በ1998 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ሕዝብ ከኢሕአዴግ ጋር የጎሪጥ የምንተያይበት ጊዜ እንደመሆኑ በጥር ወር የጥምቀትን በዓል ስናከብር፣ የቃና ዘገሊላ ዕለት የየካውን ቅዱስ ሚካኤል ታቦት ካደረበትና ከባረከን 11 ሜዳ የዛሬው ወረዳ ተገኝተን ታቦቱን አጅበን፣ በሃይማኖታዊ መዝሙርና በተቃውሞም እየተናጥን አድማ በታኝ ባለቆብ ፖሊሶችን በመሀላችን በዳርና በዳር እንዲሁም በኋላችን ይዘን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄድን ነበር፡፡ እኔ በወቅቱ የአሥር ዓመት ታዳጊ ወንድ ልጄን በመያዝ ከጓደኛዬ ጋር ሆነን፣ በየዓመቱ እንዳስለመድነው ታቦቱን ለማስገባት በዚያ ሁሉ ሕዝብ መካከል በሰላም እየተጓዝን እያለ እንግሊዝ ኤምባሲ አልፈን ሾላ ገበያው አካባቢ ደረስን፡፡ ታቦቱ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሊገባ ጥቂት ሜትሮች ያህል እንደቀሩት ከሕዝቡ ይደርስበት የነበረውን ውግዘት፣ ርግማንና ስድብ መቋቋም ያቃተው የፌዴራል ፖሊስ ተኩሱን አንጣጣው፡፡

አቤት የዚያን ጊዜ ምድር ተከፍታ ብትውጠን ምንኛ ዕድለኞች ነበርን? የእግዚአብሔር መገለጫ ታቦቱ (ቅዱስ ሚካኤል) ቀጥ ብሎ ሲቆም፣ እነዚያ ትዕግሥትን ርህራሔንና ዘመናዊ ብተናን የማያውቁት ወታደሮች (ፌዴራል ፖሊሶች) በያዙት ቆመጥ ሕዝቡን ይነርቱት ገቡ፡፡ ጥይቱም ይንጣጣል፣ የቅዱስ ሚካኤል ታቦትም ቀጥ ብሎ ይታዘባል፡፡ እኔም የአሥር ዓመቱን ታዳጊ ልጄን ይዤ፣ ከጓደኛዬ ጋር ታቦቱን እዚያው የቆመበት ጥለን ከበርካታ ምዕመናን  ጋር ሽቅብ ወደ ላይ እግሬ አውጪኝ አልን፡፡ ዳገቱ ላይ ወደ አንድ ግቢ ለመግባት ስንግተለተል የፈሩ ቤተሰቦች በሩን ዘጉብን፡፡ እንደገና እያለከለክን ወደ ላይ ስንሮጥ የተባረኩ ቤተሰቦች አጋጠሙንና በራቸውን ወለል አድርገው ከፍተው ግቢያቸውን ውስጥ ተጠቀጠቅን፡፡

ከዚያ ግቢ ተጠልለን ከተረጋጋ በኋላ፣ ወደ ቤታችን በድንጋጤ ቁና ቁና እየተነፈስን ጉዞ ጀመርን፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ታቦትም ብቻውን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ ሕዝበ ምዕመናንም ተበታትኖ ወደ መጣበት ተመለሰ፡፡ ዛሬ 2010 ዓ.ም. ከ12 ዓመታት በኋላ የጥምቀት በዓልን እንዲሁ እንደ ልማዳችን የየካው ሚካኤልን ሸኝተን በሰላም አስገብተነዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአደባባይ ሃይማኖታዊ በዓል ሲከበር የሚያስተናግዱና ሥርዓት የሚያስይዙ በርካታ ወጣቶችን በማፍራታችን እጅግ ደስ ይላል፡፡ ከታጠቀ ጦር ጥበቃም ተገላግለን በልጆቻችን በማይታክታቸው ወጣቶቻችን እየተስተናገድን በዓላችንን ስናከብር ደስ ይለናል፡፡ ዘንድሮ የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮም ለማስመዝገብ እየተሠራ በመሆኑ፣ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ከታጠቀ ጦር (ወታደር) ነፃ መሆኑ እሰየው ነው ብንልም፣ ከወደ ወልዲያ የተሰማው አሳዛኙ የጥምቀት በዓል የሞት ዜና በጣም በጣም ያሳምማል፡፡

የሚካኤልን ታቦት በመሸኘት ላይ ያሉ ሰባት ያህል ወጣቶች በጥይት መረፍረፋቸው አገሬ ወዴት እያመራች ይሆን? የዛሬ 12 ዓመት እንኳን ያልተሞከረውን እንዴት በወልዲያ ፀጥታ አስከባሪ በሰባት ሕፃናት ላይ ቃታ ለመሳብ ተነሳሳ? ያሳዝናል፡፡ ልጆቻችን ነፍሳችን በገነት ያኑረው ከማለት ሌላ ትዕግሥት የለሹ ወታደር ሕይወታቸውን በመቅጠፉ መቼም ለፍርድ ይቀርባል ማለት አጉል ሞኝነት በመሆኑ አይጠበቅም፡፡

እኔን ግን የደነቀኝ የዛሬ 12 ዓመት ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ እነዚያ ተቃዋሚ የፖለቲካ የሕዝብ ተወካዮች በፓርላማ ውስጥ ሊከራከሩ እነ መረራ ጉዲና፣ በየነ ጴጥሮስ፣ ተመስገን ዘውዴ፣ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ልደቱ አያሌውና ሌሎችም ከኢሕአዴግ ጋር የቃላት ግብግብ ሲገጥሙ ማየት ዛሬ ብርቅ ሆነና ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. አንድ ግርማ ሰይፉ ብቻውን ከኢሕአዴግ 546 ያህል ሰዎች (የፓርላማ አባላት) ጋር ሲጋተርና ሲያንጫጫ ማየትና መስማት እርሱም በነበር ቀረ፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ኢሕአዴግ ሆዬ መቶ በመቶ ፓርላማውን ለብቻው ተቆጣጠረና የምን ተቃዋሚ የሚባልበት ጊዜ ላይ ደረስን፡፡ አገሬ በፖለቲካውና በዴሞክራሲው ነገር ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት እንዘጭ እምቦጭ አለችና አረፈችው፡፡

በኢኮኖሚው ረገድ በተለይም በአዲስ አበባ ባለፉት 12 ዓመታት በሰፋፊ መንገዶቿ፣ በታላላቅ ሆቴሎቿ፣ በኮንዶሚኒየም ቤቶቿ፣ በሕንፃዎችና በሌሎችም ረገድ የሚታይና የሚዳሰስ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ በዴሞክራሲና በፖለቲካው ግን ከ1998 ዓ.ም. ጋር ስናየው ቁልቁል ወርዳለች፡፡ ጭራሹንም ሃይማኖትዊ በዓል ላይ ጭምር ወጣቶቿ ላይ በጥይት የሚገድሉ ወታደሮችን ዛሬ 2010 ዓ.ም. አፍርታለች፣ ያሳዝናል፡፡ እውነትም እንዘጭ እምቦጭ፡፡ አሁን ላይ የሚያሳስበን ነገር አገራችን በኢኮኖሚ እያደገች ያለች ቢሆንም፣ ያለ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ትርጉምና ውጤት የለውምና ኢሕአዴግ ሆይ እባክህን የፖለቲካ ምኅዳሩን አስፋ፡፡ ቀሪዎቹን የታሰሩ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን ፍታ፡፡ ያላግባብ ሕዝብ ላይ የተኮሱና የሰው ሕይወት የቀጠፉ ታጣቂዎችን በአደባባይ ለፍርድ አብቃቸው፡፡

(ተክልዬ ጀማነህ፣ ከአዲስ አበባ)