Skip to main content
x

ታማሚዋ ኢትዮጵያ አገራችን የሚታደጋት ባለመድኃኒት ትሻለች

በሰይፈ ሥላሴ አያሌው (ዶ/ር)

አንድ የኦሮሚፋ ተረት ከሞላ ጎደል እንዲህ ይነገራል፡፡ አንድ ፈሪ ሰው ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ሆነው መንገድ ይጓዛሉ፡፡ በመንገድ ላይ መሽቶባቸው ካሰቡበት ቦታ ሳይደርሱ ጫካ ውስጥ ለማደር ይገደዳሉ፡፡ ጫካ ደግሞ አውሬ አያጣውምና ፈሪው ከአውሬ ራሱን ለመደበቅ እኔ የምተኛው ከመሀላችሁ ነው በማለት ጓደኞቹን ከግራና ከቀኝ አድርጎ እንቅልፍ ይወስዳቸዋል፡፡ ሌሊት ላይ የተፈራው ደርሶ ጅብ ይመጣና በግርጌ በኩል መሀል የተኛውን ፈሪውን ከእግሩ ይጀምረዋል፡፡ ፈሪው እየተበላና እየሞተም ዘራፍ አስጥሉኝ ብሎ ጮክ ብሎ መናገሩንም ይፈራና ጥርሱን ነክሶ መበላቱን ይቀጥላል፡፡ በዚህን ወቅት ጓደኞቹ የሆነ ድምፅ ይሰሙና ምንድነው ይባባላሉ፡፡ ፈሪው እየተበላም ድምፁን ጮክ ላለማድረግ በለሆሳስ በኦሮሚፋ ‹‹Dhiisa Na Dhonka›› አለ፡፡ ትርጓሜው ‹ዝም በሉ እኔን እየበላ ነው› እያለ ተበልቶ ሞተ ይባላል፡፡

ይህ የአገሬ ተረትና አባባል ዛሬ አገሬ ከምትገኝበት ሁኔታ ጋር ተመሳሰለብኝ፡፡ አገር ማለት የአገሩ ነዋሪና ምድሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገሬ ዛሬ የምትገኝበት ሁኔታ እንደ ፈሪው ሰውዬ ተውኝ ወይም ዝም በሉ የምንልበት አይደለም፡፡ አገሬ ከምሥራቅ ጫፍ እስከ ምዕራብ ጫፍ ከሰሜን ጫፍ፣ እስከ ደቡብ ጫፍ ታማለች፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች፣ በአማራ ክልልና በደቡብ ክልል በተለያዩ ሥፍራዎች የተካሄዱ እንቅስቃሴዎችና ያንን ተከትሎ የጠፋው የንፁኃን የአገሬ ልጆች  ሕይወት፣ የወደመው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ንብረት ነው፡፡ በመጨረሻ በእሬቻ በዓል አከባበር ወቅት የደረሰው ዕልቂት የተከሰተውን ሁኔታ ወደ መጨረሻ ጥግ በማምጣት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አንደበት ‹‹በተለመደው ሁኔታ በመቀጠል ይኼንን ነገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስተካከል አስቸጋሪ ስለሚሆን  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፤›› ተብሎ አገሬ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ሥር ቆይታለች፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ወቅት ችግሩ ሳይፈታ ተዳፍኖ ለአንድ ዓመት ያህል መቆየቱን እናስታውሳለን፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ በመላ አገሪቱ እየታየ ያለው ከቀደመው ጊዜ ጠንከር ብሎና መጠነ ሰፊ ሆኖ የመጣው ችግር፣ አገሬ ኢትዮጵያን የያዛት ሕመም ከዕለት ዕለት እንደፀናባት አመላካች ነው፡፡

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪና በኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪ የአንድ እናት የአገሬ የአትዮጵያ ልጆች መካከል ተነስቶ ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለመፈናቀል ወዳርገዋል፡፡ ይኸው ችግር ወደ ደቡባዊ ጫፍ ተዛምቶ ያስከተለው የንፁኃን ኢትዮጵያውያን ሕልፈተ ሕይወት በምዕራብ ኢትዮጵያ በነቀምት ከተማ የእሬቻ በዓል ወቅትና በሻምቡ ከተማ፣ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሕይወታቸው ያለፈው የነገዋ የአገሬ ተረካቢ ልጆች ናቸው፡፡ በጨለንቆ፣ በወልዲያ፣ በቆቦ፣ በሐማሬሳ፣ በመደ ወላቡና በሌሎች የተለያዩ ሥፍራዎች ሕይወታቸው ያለፈው የአገሬ ልጆች፣ የአገሬን የኢትዮጵያን ሕመም ከምንም በላይ ገላጮች ናቸው፡፡ የአገሬ ልጆች በቋንቋ ተለያይተው ጥቂት በጥቂት እርስ በርስ ይተላለቃሉ፡፡ የአገሬ ልጆች በፀጥታ ኃይሎች ጥይት እየተመቱ ያልቃሉ፡፡ አገር ማለት መሬቱ፣ መልክዓ ምድሩና ጋራው ሸንተረሩ ብቻ አይደለም ካልንና አገር ማለት የዚህ ስብስብ ሲደመር ሕዝብ ነው ብለን ካልን፣ አገርንም አገር ብሎ የጠራውና ካለሱም አገር ተብላ የምትጠራ ልትሆን የማትችል ሕዝብ ነው ካልን፣ የልጆቿ ደም በየቦታው እየፈሰሰና ምድሬም የልጆቿን ደም ዕለት ዕለት እየጠጣች የአገሬ ኢትዮጵያ ምድር በደም ጨቅይታለች፣ አገሬ ኢትዮጵያም በፅኑ ታምማለች፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ ለመታመሟ ከዚህ ይበልጥ ምልክት የለም፡፡ የሕመሟና የስቃይዋ የመጨረሻ ጥግ ላይ ትገኛለች፡፡ አገሬ ኢትዮጵያን የያዛት ሕመም የሚገድላት አይደለም፡፡ ምክንያቱም አገሬ ኢትዮጵያ የመቶ ሚሊዮኖች እናት ነች፡፡ የመቶ ሚሊዮኖች እናት አትሞትም እንድትሞትም፣ አይፈቀድላትም፡፡ አገሬን የያዛት በሽታ ግን ከዛሬ ነገ ይበልጥ ከጠናባት ከሰውነት ተራ ያወጣታል፣ ያከሳታል፣ ያመነምናታል፣ መዳኛ መድኃኒቱን ያርቅባታል፣ ሕክምናዋን ያወሳስብባታል፣ የሕክምናዋን ወጪ ያስወድድባታል፡፡ 

አዎን አገሬ ኢትዮጵያ ታምማለች ‹‹ከልጆቼ ባለመድኃኒት አጣሁ›› ትላለች፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ ሕመሟን ሕመሜ፣ ስቃይዋን ስቃዬ ብሎ ሕመሟን በአግባቡ ተረድቶ መድኃኒት የሚያበጅላት ባለመድኃኒት ትሻለች፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ ሕክምናዋን ለዕለት እንጀራ ማግኛ ሳይሆን፣ ለሙያው ታማኝ ሆኖ ሕመሟን መርምሮና አውቆ ፍቱን መድኃኒት የሚጽፍላት፣ የጻፈላትን መድኃኒትም ተከታትሎ አስውጦ ከሕመሟ የሚያድናት ባለመድኃኒት ትሻለች፡፡

በእኔ ዕይታ በአንድ አገር ላይ በሥልጣን ወንበር ላይ ተቀምጦ ያን የሚመራውን አገርና የተቀመጠበትን ወንበር ሆን ብሎ ወደ ጥፋት መንገድ የሚገፋ ገዥ የለም፡፡ ምክንያቱም የአገር ጥፋትና የወንበሩ መነቃነቅ እሱንም ጭምር የሚጎዳውና ይልቁንም በስተመጨረሻ ከሁሉ በበለጠ የሚጎዳው መልሶ ራሱን ስለሚሆን ነው፡፡ እዚህ ላይ ልንስማማ ከቻልን ማንም የሥልጣን ወንበር ላይ የተቀመጠ ራሱ በመሰለውና ለአገርም ይበጃል፣ የኔንም ሥልጣን ያራዝማል ብሎ ባመነበት መንገድ አገርን ለመምራት ጥረት ያደርጋል፡፡ ያም መንገድ ወደ ልማት ወይም ወደ ጥፋት ሊወስድ ይችላል፡፡ ከሁለቱ ውጪ ሊሆን አይችልምና፡፡ የሥልጣን ኮርቻን የተቆናጠጠ አካል የሚከተለው ጎዳና ግን ሁሌም የሕዝብን ፍላጎት ያንፀባርቃል ማለት አይደለም፡፡ የሕዝብን ወቅታዊ ፍላጎት ባያንፀባርቅም በሥልጣን ላይ ያሉ ፍላጎቱን እንደሚያንፀባርቅ ለሚመሩት/ለሚያስተዳድሩት/ለሚገዙት ሕዝብ በአንድም በሌላም መንገድ ይነግሩታል፡፡ ከተቀበለ እሰየው ካልተቀበለም እንደ ቀንበር በላዩ ላይ ይጭኑበታል፡፡ ሕዝብም እስከ ተወሰነ ደረጃ የተጫነበትን ቀንበር ተሸክሞ ይኖራል፡፡ ይህ በአብዛኛው ታዳጊ አገሮች የሚንፀባረቅ እውነታ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የሕዝብን ፍላጎት ያንፀባረቀ ቢሆን እንኳ፣ ሕዝብ ለውጥ ፈላጊ ስለሆነ ፖለቲካውና አካሄዱ ሲገባውና ሲረዳ ወይም ደግሞ ለውጥ ሲሻ ሆ ብሎ ደግፎ ከሥልጣን ኮርቻ ላይ ያቆናጠጠውን እንኳ ሳይቀር ዓይንህን ለአፈር ሊለው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የለውጥ ሒደት ውጤት ነው፡፡  

አገሬ ኢትዮጵያ ከዚህ ውጪ አይደለችም፡፡ በሌሎች አገሮች የሚታየው መልኩንና አካሄዱን ቢለውጥም ያው የሌሎች ታዳጊ አገሮች ዕጣ ፈንታ የእሷም ዕጣ ፈንታ ሆኖ የወደደችውንም፣ ያልወደደችውንም በጫንቃዋ ተሸክማ ላለመውደቅ ትውተረተራለች፡፡

ደፍረን በግልጽ ባንናገረውም በመግቢያዬ እንደጠቀስኩት ተረት እየተበላን መሆናችንን ልንሸፋፍን ጥረት ብናደርግም፣ ኢትዮጵያ አገሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ በጤናማ ሁኔታ ውስጥ አይደለችም፡፡ ስለችግራችን ባንናገር፣ ችግራችንን ሌላ ገጽታ ቀብተን ልናቀርበው ጥረት ብናደርግ፣ የችግራችንን ትክክለኛውን ምክንያት በልባችን እያወቅን ዙሪያ ዙሪያውን ስንሽከረከር ብንውል፣ ችግራችን በራሱ ቆሞ ያለ ከሆነ ለችግሩ አፈታት ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ አያደርግም፡፡ ችግራችንን ለይተን ፊት ለፊት ልንጋፈጠው ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ የሁሉንም ወገን ጥረት ብቻ ሳይሆን ቅንነት የተሞላበት ጥረት ይጠይቃል፡፡ አገራችን የገባችበትን ችግር መፍታት ሙሉ በሙሉ አካሄዳችንንና የምንከተለውን ርዕዮተ ዓለም እስከመቀየር ድረስ የሚጠይቅ ከሆነ ይህን ለማድረግ ድፍረት ሊኖረን ይገባል፡፡ አገራችን የገባችበት ችግር ሥልጣንን እስከመልቀቅ ድረስ የሚጠይቅ ከሆነ በጋራ መክሮ አገርን ለመታደግ ሲባል እስከዚያ ጥግ ድረስ የመሄድን ድፍረት ይጠይቃል፡፡ ያን ማድረግ አለመቻል ዛሬን ቢያሳድር ነገ ከታሪክ ተጠያቂነት በምንም ዓይነት አያድንም፡፡

ችግራችን ሲነገረን እንደኖረውና እንደሚነገረን ፀረ ሰላም ኃይሎች ያመጡትና የጫኑብን አይደለም፡፡ ችግራችን እነዚሁ ፀረ ሰላም ኃይሎች የሚባሉት የመገናኛ ብዙኃንና ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቅመው የዘሩብን አይደለም፡፡ ይህ ማለት የአገሬን ሕዝብ መናቅና ዝቅ ማድረግ ይሆናልና፡፡ የአገሬ ሕዝብ አልተማረም፣ የአገሬ ሕዝብ  ጠግቦ ላያድር ይችላል፣ የአገሬ ሕዝብ  አዳፋ ልብስ ለባሽ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን አስተዋይና ለእሱ የሚበጀውን የሚያውቅ በኃይል ካልሆነ ማንም ወዳሻው ጎዳና የማይነዳው፣ በትምህርት ቋንቋ መሀይም ነገር ግን ሕይወት ያስተማረችው አዋቂና አስተዋይ ሕዝብ ነው፡፡ እናም የአገሬ ችግር ቴሌቪዥን ከመስማትና ሬዲዮ ከማዳመጥ የመነጨ አይደለም፡፡ የአገሬ ችግር በኢንተርኔትና በማኅበራዊ ሚዲያ ከመነጋገራችን የመነጨ አይደለም፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር በአገሬ በእጅጉ የተንሰራፋ ቢሆንም፣ የአገሬን ችግር ዛሬ ላይ ሆኜ ሳየው የችግሩ አልፋና ኦሜጋ እሱ ነው ብል የተወሳሰበውን ችግር አሳንሶ ማስቀመጥ ይሆንብኛል፡፡

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ወደ ውጭ ጣት ከመቀሰርና ችግሩን ውጫዊ ለማድረግ (Externalize) ከመጣር ትክክለኛውን ችግር ማየትና የችግሩን ምንጭ በመፈተሽ፣ ለተጋረጠብን ችግር ሥር ነቀል አገርኛ መፍትሔ መሻት ይገባል፡፡ ይህን የምለው መንግሥት ከየትኛውም አካል የበለጠ ኃላፊነት ስላለበትና ኳሱም በሜዳው ውስጥ ስላለ ነው፡፡ ችግራችንን ከምናራምደው ፖሊሲና ከምንከተለው ጎዳና ጋር መመልከት ይኖርብናል፡፡

በኢትዮጵያ አገሬ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ምርጫዎች ተጭበረበሩ የተባለባቸው ጊዜያት እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ በዚህ ረገድ በ1997 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ዋነኛውና ምናልባትም ብቸኛው ምርጫ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ ወዲህ የተደረጉ ምርጫዎች ተጭበረበሩ የሚባሉ ሳይሆን፣ እዚህ ግባ የሚባል የተቃዋሚዎች ተሳትፎ ያልታየባቸውና ገዥው ፓርቲ ብቻውን ሮጦ ያሸነፈበት ማለት ይቀላል፡፡ በ2007 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ገዥው ፓርቲና አጋር ድርጅቶቹ መቶ በመቶ ያሸነፉበት እንደነበር ተነግሮን ዓመት ባልሞላ ጊዜ እንዴት አድርጎ ሕዝብ እንደዚያ አምኖ ድምፁን በመቸር ውክልና በሰጠው ሥርዓት ላይ ሊነሳ ይችላል? መልሱ ወይ ሕዝቡ እንደተባለው ድምፁን ሰጥቶ ውክልናውን አልሰጠም፣ ወይም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት አንድ መቶ ሰማንያ ዲግሪ አቅጣጫ የሚያስቀይር ተዓምራዊ ነገር ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ ተዓምራዊ ነገር ተፈጥሯል የሚለውን መላምት የሚደግፍና ምርጫው በተከናወነበትና አለመረጋጋቱ በተጀመረበት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተለወጠ ጎልቶ የወጣ ነገር አለመታየቱ ጉዳዩን ወደ ምርጫችንና ውጤቱ ያመጣዋል፡፡ የትናንት ምርጫችንን ዛሬ ላይ ሆነን ብንኮንነው ግን ላለንበት ችግር የሚሰጠው ፋይዳ አይታይም፡፡ ‹‹ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራለትም›› እንደሚባለው ምርጫው በዚህ በኩል እንደዚህ ሆኖ ውጤቱ እንደዚያ ሆነ ብለን ዛሬ ብናወራ ለቀጣይ የአገሬ የምርጫ ሥርዓት አስተማሪ በመሆን የቀደሙትን ስህተቶች እንዳንደግም ካልረዳን በስተቀር፣ የተፈጠረውን ስህተት ከማረም አኳያ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ስለዚህ ምርጫዎቻችን ያለፉበት ሒደት ላይ የምንነጋገረው ከማስተማሪያነቱና ለወደፊት ምርጫዎች ከእነዚህ ስህተቶች የፀዳ አሠራር ለመዘርጋት ከሚሰጠው ፋይዳ አኳያ ብቻ ይሆናል፡፡

ዛሬ የምንገኘው በሁለት የምርጫ ዘመኖች አጋማሽ ላይ ነው፡፡ አገሬን የያዛት በሽታ ሕዝቡን እሳት ላይ ተቀምጦ እንደተከደነ ድስት ከዳር እስከ ዳር እያንተከተከ ይገኛል፡፡ ይህንን እውነታ እንደ እውነታ መቀበል የግድ ይላል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ቀደም ሲል የጠቀስኩትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያውጅ ‹‹በተለመደው ሁኔታ በመቀጠል ይኼንን ነገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስተካከል አስቸጋሪ ስለሚሆን፤››  የሚለው አባባል የእነ ቭላድሚር ኢሊች ኡልያኖቭ ሌኒንን አንድ ቲዎሪ አስታወሰኝ፡፡ ዛሬ ወደ መቃብር ተሸኝቶ የሚገኘው የኮሙዩኒስት ሥርዓት ፈጣሪ ቭላዲሚር ሌኒን ለአብዮት መካሄድ ቅድመ ሁኔታዎችን ሲተነትን፣ ‹‹የበላዮቹ አይችሉም የታችኞቹ አይፈልጉም›› ነው ያለው፡፡ ዘርዘር ስናደርገው ሕዝብ በዚያ ሥርዓት ለመተዳደር መቀጠልን አይፈልግም፡፡ መሪዎች/ገዥዎች ደግሞ በቀደመው መንገድ መምራት/መግዛት አይችሉም ይላል፡፡ ኢትዮጵያ አገሬ ከምትችለው አቅም በላይ የሆነና ለብዙ መተኪያ የሌላቸው ብርቅዬ ልጆቿ ሕልፈት ምክንያት የሆነ አብዮት በ1966 ዓ.ም. አካሂዳ በተራማጅና አድሃሪ፣ በጨቋኝና ተጨቋኝ፣ በዝባዥና ተበዝባዥ፣ አብዮተኛና ፀረ አብዮተኛ፣ በቀይና በነጭ፣ ወዘተ. ተከፋፍላ ልጆቿም ጎራ ለይተው 17 ረዥም ዓመታት የደም ምድር ሆና አሳልፋለች፡፡ የአብዮቱ አካሄድ ያልተዋጠላቸውና ትግራይን ነፃ ማውጣትን ዓላማ አድርገው (ቢያንስ ከድርጅቱ ስም እንደምንረዳው) ነፍጥ አንግበው የተነሱ የትግራይ ወጣቶች፣ የአብዮቱን ዘመን ያህል ዕድሜ ያስቆጠረ ውጊያ ተዋግተውና ቁጥሩ ቀላል የማይባል የአገሬን ልጅ ሕይወት በሁለቱም በኩል ገብረው አብዮታዊውን መንግሥት በኃይል ገርስሰው፣ በሌላ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ስም ሥልጣን ተቆናጥጠውና አገሬን በቋንቋ ከፋፍለው ማስተዳደር ከጀመሩ ሦስት አሥርት ዓመታት ለመድፈን ጥቂት ዓመታት ብቻ ይቀራሉ፡፡

ቀደም ሲል በጠቀስኩት የሌኒን ፍልስፍና መሠረት ኢትዮጵያ አገሬ በአብዮት ደጃፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ይሁን እንጂ አገሬ ኢትዮጵያ ከፍልስፍናው ባለቤት ከሌኒን ከራሱ ይበልጥ የአብዮትን ምንነትና መራራ ፅዋ በተግባር ተጎንጭታ አልፋለች፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አገሬ ኢትዮጵያ በጠብመንጃ አፈሙዝ ሥልጣን መያዝ የሚለውንም በእኩል  አይታዋለች፣ አልፋበታለችም፡፡ በጠመንጃ አፈሙዝ የተያዘ ሥልጣን ሕዝቦችዋን ያስከፈለውንና እስከዛሬ እያስከፈለ ያለውን ዋጋ ከማንም ይልቅ ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ይህ ሁሉ የሥርዓት ለውጥ አስከፊ ገጽታ እንዳለ ቢሆንም፣ ሁሉም የአገሬ ሰውም ሆነ ታዛቢ እንደሚረዳው ኢትዮጵያ አገሬ በቀደመው አካሄድ የተጋረጠባትን አደጋ ልትሻገር እንደማትችል ዕውን ነው፡፡ እናም አገር ዘመኑን የዋጀ የጊዜውን ጥያቄ የመለሰ አካሄድ ትሻለች፡፡ ለውጥ ያስፈልጋታል፡፡ ለውጡ ግን ጥገናዊ ሳይሆን መሠረታዊ ሊሆን እንደሚገባው ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ አዲስ ነገርና አዲስ አካሄድ አገሬን ያስፈልጋታል፡፡ ይህን አዲስ ነገር ሊሸከም የሚችል ሥርዓትም ያሻታል፡፡ ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማረበትና በቅዱስ ማቴዎስ፣ በቅዱስ ማርቆስና በቅዱስ ሉቃስ ወንጌሎች እንደተጻፈው በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ማኖር አይቻልም፡፡ አቁማዳውም ይፈነዳል የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ ይልቁንም አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ይደረግና ሁለቱም ይጠባበቃሉ፤›› በማለት አስተምሯል፡፡ እንደዚሁ ዛሬ አገሬን ቀስፎ የያዛት ሕመም እዚህና እዚያ በሚደረግ ጥገናዊ ለውጥ የሚድን አይደለም፡፡ ይልቁንም ከመሠረቱ ችግሮችን ማየትንና ለችግሩ የሚመጥን መሠረታዊ መፍትሔ በማበጀት ለውጥ ማምጣትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ አገሬን ለያዛት በሽታ መድኃኒት ያላቸውን ወገኖች ሁሉ ዕገዛ ይሻል፡፡

በእንግሊዝ አገር ለንደን በ1983 ዓ.ም. የተደረገውን የቀድሞውን የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካንንና የሕወሓት መሪዎችን ያደራደሩት አሜሪካዊ ዲፕሎማት ኸርማን ኮኸን፣ ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚገኝበት ሁኔታ አንፃር የአሜሪካንን አደራዳሪነት ሊጠይቅ እንደሚገባ ገለጹ የሚል ወሬ ከድረ ገጻቸው ባላነብም ሰምቻለሁ፡፡ ሰውዬው የአገሬን ጉዳይ እንደሚከታተሉ ቀደምት ዲፕሎማት ይህን ማለታቸው አይገርምም፡፡ ወዳጆቻችን ችግራችንን ከመፍታት አኳያ ሊያደራድሩን መሻታቸው ምሥጋና የሚቸረው ቢሆንም፣ ባለመድኃኒቶቹ የአገሬ ሰዎች መድኃኒቱም በእጃቸው መሆኑ አገሬን ላገኛት በሽታ መድኃኒቱ አገራዊ መሆን ይገባዋል፡፡ አንድ ከእሳቸው ያሰመርኩት ነጥብ ግን የትም ይሁን መነጋገር፣ መደራደርና የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ብቻ አገሬን ከያዛት በሽታ ማገገሚያ እንደሚሰጣት ነው፡፡ መሸማገልን አስመልክቶ የአገሬ ሽማግሌዎች እንኳን ለአገሬ ኢትዮጵያ ለሌላም ሊተርፉ እንደሚችሉ ጥርጥር የለኝም፡፡ የሽምግልና ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ረዥም ዘመናት ያስቆጠረና ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፡፡ ይህንን የሽምግልና ሥርዓት ከፍ አድርገን ወደ አገር ደረጃ በማምጣት አገሬን ኢትዮጵያን ቀስፎ ከያዛት በሽታ የመታደግ ሥራ ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ እኛ እርስ በርስ ለመሸመጋገል የግድ የፈረንጆችን ድጋፍና ዕገዛ ወይም የእነሱን ይሁንታ መጠበቅም መፈለግም የለብንም፡፡ ታማሚዎቹ እኛ ነን፡፡ ለበሽታችን መፍትሔው ከባዕዳን እጅ ሳይሆን በእኛው እጅ ነው፡፡

ዛሬ አገሬ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት አደገኛ ሁኔታ እንድትወጣ  ብቸኛው አማራጭ ባለመድኃኒቶቹ (የፖለቲካ ድርጅቶች) በነፃነት ተቀራርበው መወያየትና የጋራ መግባባት የተደረሰበት መፍትሔ ማበጀት ብቻ ነው፡፡ ተቀራርበው መወያየት ሲባል አንዱ ጋባዥ ሌላው ተጋባዥ፣ አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ፣ አንዱ ጠንካራ ድምፅ ያለው ሌላው ደካማ፣ አንዱ ተናጋሪ ሌላው ሰሚ የሚሆንበት ሳይሆን  በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀስ በውጭ አገር የሚንቀሳቀስ ነፍጥ ያነገበ፣ ያላነገበና የመሳሰሉት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይኖሩ ሁሉን አቀፍ የሆነ በገለልተኛ ምድር በዴሞክራሲ ሥርዓታቸው በአንፃራዊነት ጥሩ ዕርምጃ እየተራመዱ ነው ከሚባሉት የአፍሪካ አገሮች በአንዱ ላይ የተደረገና አገሬን እየገባችበት ካለው አዘቅጥ በድል ሊያወጣና ለመላው አፍሪካና ለሌሎችም ታዳጊ አገሮች አርዓያና አስተማሪ የሆነ የባለ መድኃኒቶች ጥልቅ ምክክርና መግባባት ያስፈልጋታል፡፡

ኢትዮጵያ አገሬ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በጠና ታማ በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ከራሱና እሱ ካመነበት ርዕዮተ ዓለም በላይ የሆነን መድኃኒት ሊቀምምላት የሚችል ባለመድኃኒት ትሻለች፡፡ ኢትዮጵያ አገሬ ‹‹የማንም ሥልጣን ከአገር በላይ አይደለም›› ብለው በድፍረት የሚናገሩ መሪዎች ማፍራት መቻሏ ትልቅ ዕርምጃ ሲሆን፣ ይህን ማለት ብቻ ሳይሆን ያሉትን በትክክል በተግባር የሚያሳዩ ባለመድኃኒቶች ትሻለች፡፡

ኢትየጵያ አገሬ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ናት፡፡ ዛሬ ደግሞ ቀስፎ ለያዛት በሽታ በራሷ ለራሷ የሚሆን አገራዊ፣ ባህላዊና ኢትዮጵያዊ  የሆነ  ፍቱን መድኃኒት በመቀመም መድኃኒቱንም አስውጦ በመዳንና የዓለምን ሕዝብ በማስደመም በወርቅ ቀለም ስማቸውን የምትጽፍላቸው ባለመድኃኒቶች ትሻለች፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ ይህን ስታደርግ ተሸናፊ ሳይኖር ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን መንገድ ልታይና የልጆቿ እንባ ሊታበስ፣ ልጆቿ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ጫፍ ከሰሜን እስከ ደቡብ ጫፍ በነፃነት እንዲወጡና እንዲገቡ ቋንቋቸው መግባቢያቸው እንጂ መለያያቸው እንዳይሆን፣ ይህንንም በማድረግ ወደ ላቀ የልማትና ዕድገት ደረጃ ተሸጋግራ ራሱን ቀና አድርጎ የሚሄድ ኩሩ ሕዝብ አገር ሆና ልትታይ ትሻለች፡፡ የዛሬ 25 ዓመት አካባቢ በየመኪናው ተለጥፎ ይታይ በነበረ አንድ ግጥም፣

የደስታ የሐዘን የክብር ቤታችን

በአንድነት ኑሪልን እናት ኢትዮጵያችን

የደስታ የሐዘን የክብር ጌጣችን

ከፍ እንዳልሽ ኑሪልን ሰንደቅ ዓላማችን

ይል ነበር፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ ልጆች በአንድነት ሆነን ድምፃችንን ጮክ አድርገን ይህን ግጥም ከዳር እስከ ዳር እናስተጋባለን፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!

 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡