Skip to main content
x

ስሜታዊነት የሰላም ጠንቅና የአዕምሮ እንከን ነው

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በዚህ ጽሑፍ ስሜታዊነት የሚለው ቃል ከራሳችን በስተቀር የተለየ አስተሳሰብ፣ አካሄድ፣ ፍልስፍና፣ አስተምህሮት ያላቸውን ባለመቀበል፣ በመጥላት፣ በማጥላላት፣ በዚህም ምክንያት በሚቻል መንገድ ሁሉ ተቀባይነት እንዳያገኙ ተፅዕኖ በማሳደር በአንደበት፣ በገጽታ፣ በድርጊት፣ በጽሑፍ፣ የሚገለጥ ባህርይ ነው፡፡ ይህ ስሜታዊነት በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ሲሆን፣ አንዱ ጠባብነት ነው፡፡ ጠባብነትን ደግሞ ቢገትሪ (Bigotry) ለሚለው ቃል በአማርኛችን ተመሳሳይ ትርጉም ብንሰጠው ጽልመታዊ፣ ዕቡይ፣ አልኩ ባይ፣ ተመፃዳቂ፣ ‹‹ከእኛ በላይ ጎራሽ ማዕድ አበላሽ›› የሚል፣ አዋራጅ፣ ክብርን የሚነካ፣ በራሱ ጠባብ አመለካከት የታጠረ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል የማያውቀውን አውቃለሁ፣ የማያደርገውን አደርጋለሁ የሚል አስመሳይ፣ በተገኘው አጋጣሚ የሚጠቀም ልንለው እንችላለን፡፡ አሜሪካውያን ደግሞ ከነጮች ወይም ከጥቁሮች የዘር ጥላቻ ጋር አጥብቀው ያያይዙታል፡፡ እኛ ደግሞ ከጠባብ ብሔርተኝነት፣ ከጎጠኝነት፣ ከሻጉሬነት (ከእኔ ሌላ ሃይማኖት ለቅስፈት ባይነትና ሃይማኖት አጥባቂነት) ጋር እናያይዘዋለን፡፡ የፕሮፌሰር ሌስላው እንግሊዝኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ፣ ‹የራሱን ያልሆነ ማንኛውንም ዓይነት ሐሳብ የማይቀበል› በማለት ይተረጉመዋል፡፡  በዳንኤል ወርቁ ተዘጋጅቶ በሜጋ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት የታተመው እንግሊዝኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ሥርወ ቃሉን ‹‹አክራሪ (ለሃይማኖት ወይም ለፖለቲካ)፣ ቅንዓተ ቀኖና ይልና አክራሪነት፣ ጠባብነት›› በማለት ይተረጉመዋል፡፡

‹ቢገትሪ› የሚለው ቃል ‹ጠባብነት› ብለን ከወሰድነው ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ ‹በሐሳቡ ግትር የሆነ፣ ወይም የራሱ አመለካከት ከሌላ አመለካከት ጋር አቻችሎ ለማስኬድ ፈቃደኛ ያልሆነ፣ የራሱን እንጂ የሌላውን አመለካከት፣ ሐሳብ ዕውቀት፣ ፍልስፍና፣ ሽምግልና፣ ወዘተ የማይቀበልና አንድን ወገን፣ ቡድን፣ ዘር፣ ሃይማኖትን፣ ወዘተ አጉልቶ ሌላውን የሚጠላና የሚያጥላላ፣ የመቻቻል ስሜት የሌለው፣ የእኔ ነው የሚለው ሐሳብ ትክክል ባይሆንም እንኳን የሌላውን ላለመቀበል ድርቅ ያለ፣ ድርቅና› በሚለውም ይተረጎማል፡፡ እኛ ‹ጠባብነት› ያልነውን ‹ቢገትሪ› ‹አክራሪነት›፣ ‹ጽንፈኝነት› በማለት ስለሚተረጉሙትም ይኼንንም ሐሳብ ያካትታል፡፡ እነዚህ ደግሞ ለሰላም መደፍረስና ለሁከት መከሰት መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የጠባብነት ትርጉም አከራካሪነት

ምንም እንኳን አንዳንድ ሊቃውንት ቀደም ያለውን ፍቺ ቢሰጡትም፣ የቃሉ ትርጉም አከራካሪ ሆኖ የሚገኝበት ሁኔታም ይኖራል፡፡ ይኸውም አንድ ሰው አስተሳሰቡ ልክ ቢሆንም ሌሎች ላይቀበሉት ስለሚችሉ እርሱም የሌሎቹን ሐሳብ መቀበል ይሳነዋል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ሳይንቲስቶች ከኅብረተሰቡ ተገለዋል፣ ሐሳቡን በማይቀበሉት ዘንድ ተነቅፈዋል፣ አቅም ባላቸው ተዋርደዋል፣ ሲበረታ ደግሞ ተገድለዋል፡፡ ለምሳሌ ኢጣሊያዊው ጋሊሊዮ ጋሊሊ (ከ1564-1642) ፀሐይ በመሬት ዙሪያ ትዞራለች በሚባልበት ዘመን ‹‹የለም፣ መሬት በፀሐይ ዙርያ ትዞራለች እንጂ ፀሐይ በመሬት ዙርያ አትዞርም›› አለ፡፡ በዚያን ጊዜ የሃይማኖት አባቶች ተቃወሙት፡፡ ደጋፊዎቻቸው ባለሥልጣናት ‹‹ይኼ ዕቡይ፣ ከሃይማኖት ሊቃውንት በልጦ ነው? ተሳስቶ አሳሳች!›› አሉና ዘብጥያ አወረዱት፡፡ ከዚያም አመለካከቱን በአደባባይ እንዲለውጥ ተደረገ፡፡ እርሱም ወደ መድረክ ወጣና ‹‹መሬት በፀሐይ ዙርያ አትዞርም ካላችሁ አትዞርም›› አለና ከመድረክ ሲወርድ ‹‹ግን ትዞራለች›› የሚል ጨመረበት፡፡ በዚህም ምክንያት ለእስር ተዳረገ፡፡ የምርምር ሥራዎቹንም ተወረሰ፡፡ በቁም እስር እያለም ሞተ፡፡ እንግዲህ ጋሊሊዮ በአሳሪዎቹ ዘንድ ጠባብ አመለካከት ነበረው ማለት ነው፡፡ ሌሎችም ብዙ አሉ፡፡

‹‹አባ ኮስትር›› የሚል የፋኖ ስም የተሰጠው የእኛው ደጃዝማች በላይ ዘለቀ (1904-1938) ጠላትን ካርበደበዱትና ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ተመልሰው ሥልጣን እንዲይዙ ካደረጉት አርበኞች አንዱ ቢሆንም እንኳን፣ በወቅቱ ከነበሩት አርበኞች የተለየ ባህርይ በማሳየቱና ሥልጣን ደፋሪ ሆኖ በመገኘቱ በስቅላት ተገድሏል፡፡ የደርግ መንግሥት ደግሞ፣

የፍየል ወጠጤ ትከሻው ያበጠ ልቡ ያበጠበት፣

እንዋጋ ብሎ ለነብር ላከበት፡፡

እያለ ወደ ሥልጣን ያመጡትን መግደል ከመጀመሩ በፊት የደጃዝማች በላይ ዘለቀን በግፍ መገደል አስመልክቶ ከፍተኛ ሕዝባዊ ንቅናቄን ለመፍጠር ተጠቅሞበት ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ ብዙ ሺሕ ጀግኖች የበቀሉባት ጎጃም ሌላ ጀግና የሌላት አስመስሏት ቀረ፡፡ ስለሆነም ‹‹ጠባብነት›› ስንል አሉታዊ ብቻ ሳይሆን አዎንታዊ ገጽታም እንዳለው እንገነዘባለን፡፡

ጠባብ አመለካከት የአገራችንና የዓለማችን ወቅታዊ ትኩሳት

ቀደም ሲል የቀረበው ሰፋ ያለ ትንታኔ አንባቢያን በተለይም ወጣት አንባቢያን ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ ሲሆን፣ ጸሐፊው ስሜታዊነት፣ ሐሳበ ግትርነት፣ ወይም የራሱ አመለካከት ከሌላ አመለካከት ጋር አቻችሎ ለማሳኬድ ፈቃደኛ ያልሆነ፣ የራሱን እንጂ የሌላውን አመለካከት፣ ሐሳብ፣ ዕውቀት፣ ፍልስፍና፣ ሽምግልና፣ ወዘተ የማይቀበል፤ አንድን ወገን፣ ቡድን ዘር፣ ሃይማኖትን፣ ወዘተ እንጂ ሌላውን የማይቀበልና ሌውን የሚጠላና የመቻቻል ስሜት የሌለው፣ የእኔ ነው የሚለው ሐሳብ ትክክል ባይሆንም እንኳን፣ የሌላውን ላለመቀበል ድርቅ የሚል ድርቅና ከሆነ ያለ ምንም ጥርጥር የአዕምሮ እንከን መሆኑን የአዕምሮ እንከንነቱንም ካገኘው መረጃ በመነሳት ከመግለጹ በፊት ግን ስለጠባብነት አንዳንድ መገለጫዎቹን አስቀድሞ ለማቅረብ ይወዳል፡፡

ለምሳሌ የባሪያ ንግድን ዳግማዊ አፄ ምንሊክ በአዋጅ ቢከለክሉም፣ ከሰማንያ ዓመታት በፊት ኢጣሊያ ብዙ ባሮችን ነፃ ቢያወጣም፣ ሰውን እንደ ከብት መሸጥና መለወጥ ግን እስካለፉት 60 ዓመታት አልቀረም ነበር፡፡ ያኔ ‹‹አልሸጥም፣ አልለወጥም›› ማለትም ሆነ ‹‹በባርነት አላገለግልም›› ማለት አስቸጋሪ እንደነበረው ሁሉ፣ ባሪያ ሻጭንና ገዥን መቃወም ከንቱ ድካም ነበር፡፡ ለመሆኑ ከአምቦ ሰሜን ምሥራቅ የምትገኘው ግንደ በረት የተባለች ሥፍራ ከብዙ የባሪያ መሸጫ ኬላዎች አንዷ መሆኗን እናውቃለን? በዚህና በሌሎች ሥፍራዎች ባሪያ መሸጥና መለወጥ መቼ እንደቀረ ጸሐፊው ባያውቅም እስከ 1950ዎቹ፣ እናርቀው ብንል እስከ 1960ዎቹ ድረስ ባሪያም የባሪያ ጌታም እንደነበር ጸሐፊው ያስታውሳል፡፡ ብቻ ግን ‹‹ባሪያ ማነው? ባሪያ ፈንጋዩስ?›› ስንል ባሪያ የሚሆነው ቀን የጣለው ማንም ሰው፣ ባሪያ ፈንጋዩም ርካሽ ጉልበት ፈላጊና አቅራቢ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ግንደ በረት ፈረንጅም ጭምር ይሸጥ እንደነበር አንድ አዛውንት በ1980ዎቹ መጀመርያ ላይ ለጸሐፊው ነግረውታል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን አቶ መንግሥቱ ለማ ‹‹ባሻ አሸብር በአሜሪካ›› በሚል ርዕስ በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ያሳተሙትን ግጥም እንመልከት፡፡ ባሻ አሸብር ከልካይ፡-

የዛሬ አሥር ዓመት በታላቅ ሹመት፣

አሜሪካ ልኮኝ ነበረ መንግሥት፤

ካሉ በኋላ በነጮች ካፍቴሪያ ለመመገብ ቢሹ በጥቁረታቸው በድብደባ ይባረራሉ፡፡ እርሳቸውም ደብዳቢያቸውን በከዘራቸው በመዠለጣቸው ምክንያት ተገኘና ዘብጥያ ይወርዳሉ፡፡ እናም እንዲህ ይላሉ፡፡

የሞጃው ተወላጅ የጠራሁት መንዜ፣

ምንትስ፣ ምንትስ፣ ተብዬ መያዜ፣

በግፍ እንደሆነ ባሰት በውሸት፣

አቃተኝ ማንንም ከቶ ማስረዳት፤

እናም ባሻ አሸብር መብታቸው የተደፈረው እርሳቸው ሆነው ሳለ፣ መታሰራቸው አግባብ አለመሆኑን ማስረዳት ሳይችሉ ቀርተው ከአንድ ጥቁር አሜሪካዊ ጋር እስር ቤት ይታጎራሉ፡፡ ስለዚህም፣

ሲቸግረኝ ጊዜ አንዱን ተጠግቼ፣

‹ሻንቆን›› እንዲህ አልኩት፣ ነገሬን አስልቼ

‹‹ስማኸኝ ወንድሜ አላሳዝንህም፣

በሰው ጠብ ገብቼ በከንቱ ስደክም?

አውቃለሁ ከጥንትም ነጭና ሻንቅላ፣

በቂም እንደኖረ ሲዋጋ ሲጣላ፡፡

እኔ ግን ሐበሻው ምን ወገን ልለይ፣

በማይነካኝ ነገር ለምን ልሰቃይ፡፡

እንካ ፀጉሬን እየው ምንትስ አይደለሁም፣

ፊቴን ተመልከተው… እንዳንተ አልጠቆርኩም፡፡

ቀይ ዳማ ነኝ..እየኝ..ይሁን ጠይም ልባል፡፡

እኔን መቁጠሪያ ራስ የሚለኝ ሰው አብዷል!

ይላሉ፡፡ አቋማቸውንና የባሪያነት መለኪያውን በጥቁሩ አሜሪካዊ መልስ አማካኝነት በቀልድ፣ በዋዛና በፈዛዛ ሲገልጡም፣

እንዲህ ያል ንግግር ያሰኛል አላቲ፣

ባሻ አሸብር ከልካይ ልጠይቅህ እስቲ፣

ገና አንተ ነህና ኢትዮጵያዊ፣

አይደለሁም ልትል ጥቁር አፍሪካዊ?

በማለት በሰፊው ያስረዳቸዋል፡፡ እርሳቸውም ነገር ዓለሙ ይገባቸውና በመጨረሻ

 ይመስገነው ገባኝ ከጊዜ በኋላ

ምንትስ ምንትስ፣ ምንትስ …ላ

ምንትስ ኪኩዩ ስዋሂሊ ባንቱ፣

ኩኑሉሉ ማሳይ ኔግሮ ባማንጓቱ

ማለት እንደሆነ ስልቻ ቀልቀሎ፣

ቀልቀሎ ስልቻ፣ ስልቻ ቀልቀሎ፣

ስልቻ፣ ስልቻ፣ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ፡፡

 ብለው በሌሎች ስንኞች ይደመድማሉ፡፡ ባሻ አሸብር በ1950ዎቹ ተልከው ከሆነ ጊዜው ከ60 ዓመት በፊት ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው ለባሻ አሸብር ትምክህተኝነቱ፣ ዘረኛነቱ፣ ጠባብነቱ፣ ወዘተ ላይሰማቸው ይችላል፡፡ ምንትስ፣ ምንትስ ለተባለውና ዛሬ ትምክህትና ጠባብነት ይጎዳል ብሎ ለተነሳው ግን ትናንት አሳማሚ ስድብ ነበር፡፡ ስለዚህ «ካያያዝ ይቀደዳል፣ ካነጋገር ይፈረዳል» እንዲሉ የምንናገረው፣ የምንሠራውና የምናቀርበው ሁሉ ሌሎችን የሚያሳምምና የሚጎዳ እንዳይሆን በሚቻል ሁሉ በእጅጉ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡

ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት የነበሩ የአሜሪካ ነጭ ወታደሮች «እኔ ጥቁርን አልጠላም፣ የነፃነት ፍላጎታቸውንም አልቃወምም፣ ነገር ግን የእርምት (ማሰር፣ መግረፍ፣ መግደል) ዕርምጃ የምወስድባቸው በሚከተሉት የተሳሳተ መንገድ ሄደው ራሳቸውንና ኅብረተሰቡን የሚጎዳ ተግባር እንዳያከናውኑ ለመከላከል ነው፤» የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው፡፡ ይኼ አስተሳሰብ በአሜሪካ ገዥ መደቦች ዘንድ ለብዙ ጊዜ ትክክል ነበር፡፡ ዳሩ ግን ራሱን ለመከላከል ያልቻለውን ለመከላከል ከመፈለግና ከመቆርቆር የመነጨ ቢመስልም ለጥቁሮች ደግሞ ለዘመናት ሲጎዳ የነበረ የተለመደ ሐሳብ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣኑን ከደርግ ሲወስድ በአንድ ወገን ድንጋጤ፣ ውስጣዊ ሽብር፣ ቁጭትና ጭንቀት ተፈጠረ፡፡ ለመቶ ዓመታት የተገነባው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድልድይ በደርግ የተሰበረ ይመስል እንደነበረው ሁሉ በተራው በኢሕአዴግ ሥልጣን መያዝ ማግሥትም የተሰበረ መሰለና ‹‹ኢትዮጵያ አለቀላት›› ተባለ፡፡ በአንድ በኩል አሁንም ቢሆን በአንድነት ላይ በተመሠረተ ልዩነት እንጂ፣ በልዩነት ላይ በተመሠረተ ልዩነት የማናምን አለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ ብለን፣ ከተከፋፈልን በኋላ በመከባበርና በመተጋገዝ ካልኖርን፣ አንድነት የሚሉት ሾላ በድፍን ቃል አልተመቸንም›› የሚሉ በመቶ የሚቆጠሩ ጠንካራም፣ ደካማም የፖለቲካ ድርጅቶች ተፈጥረዋል፡፡ በሥራቸውም በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አሰባስበዋል፡፡

በዚህም መሠረት ለብዙ ዓመታት ተቀብሮ፣ ተዳፍኖ፣ ታምቆ የነበረው ስሜት ፈነዳና ተበዳይ ነኝ ባይ መታየት ጀመረ፡፡ የመገናኛ ብዙኃንም ይኼንን አመለካከት አጎኑት፡፡ ለምሳሌ በደርግ ዘመን ስለብሔረሰቦች ጭቆና በሰፊው እየተነተነ ይቀርብ ነበር፡፡ የብሔረሰቦች ኢንስቲትዩትም በሕግ የተቋቋመው በደርግ ዘመን እንደነበር አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ባለፈው ሥርዓት የተደረገው ነገር ሁሉ እንዳልተደረገ ተቆጠረ፡፡

ወቅታዊ ግጭትና ጠባብነት

ዛሬ አገራችን አንድን ብሔር ወይም ብሔረሰብ በስመ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ወንድማማችነት፣ ወዘተ ማጥላላትና ታሪኩን ማጠልሸት፣ ምንም ዓይነት አቅም የሌላቸውን ዜጎች በጠላትነት መፈረጅ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት እንደሆነ በሕገ መንግሥትም በሕግም ተረጋግጧል፡፡ በዚህም መሠረት አገሪቱ በቋንቋ ላይ የተመሠረተ (ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ) የፌዴራል መንግሥት አቋቁማለች፡፡ ይኼም ማለት ሰባት ትውልድና እዚያው አካባቢ መወለዱን የሚቆጥር ሳይሆን፣ በሕገ መንግሥቱ በተጠቀሰው መሠረት በዚያ አካባቢ የኖረና ቋንቋውን የሚናገር ማለት ነው፡፡ እናም የሶማሌን ክልል ሶማሌ፣ የኦሮሚያን ክልል ኦሮሞ፣ የሌላውን ክልል ደግሞ ሌላው ይገዛል እንጂ አንዱ ወደ ሌላው ሄዶ አይገዛም፡፡ ሆኖም ይኼ ዓይነቱ ፌዴራላዊ ሥርዓት የራሱ የሆኑ ችግሮች ስላሉት በተለይ በድንበሮች አካባቢ ውዝግብ መከሰቱ አልቀረም፡፡ ይኼም ችግር ከአስተዳደር በደልና ከጠባብነት ጋር ተያይዞ መታየት ጀመረ፡፡ ‹‹እኛ እንዲህ እንጂ እንዲያ አይደለንም›› የሚሉ አስተሳሰቦች ተከሰቱ፡፡ ገዥው ፓርቲ በወቅቱ እርማት መውሰድ ሲገባው ባለመውሰዱ ምክንያት ጠባብ ብሔርተኝነትን፣ ዘረኝነትን፣ በብሔር ብሔረሰብ የተመሠረተ ፌዴራሊዝምን ሲያወግዙ የነበሩ ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ እርስ በእርስ ግጭት አመሩ፡፡ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተጀመረው ግጭትና ግድያ ወደ ድንበር ግጭት አደገ፡፡ ‹‹ከክልላችን ውጡልን›› መባል ተጀመረ፡፡ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን መሆኗ ማስረዳት ቀላል አልሆን አለ፡፡ ዜጎቿ የትም ሠርተው የመኖር መብታቸው በወቅታዊ ጠባብነት ስሜት ተገሠሠ፡፡ አንዱ ብሔረሰብ የሌላው ጠላት ሆነ፡፡

ነገሩ ‹‹ከክልላችን ውጡልን›› ከማለት አልፎ መኪኖች ወደዚህ ክልል እንዳያልፉ ተባለ፡፡ የተወሰኑ መኪኖችም ተቃጠሉ፡፡ አንድ አካባቢ በተነሳ ግጭት መኪኖች መንገዱን አቋርጠው እንዳይሄዱ በቋጥኝ ቢዘጋ፣ ለዘጊዎቹ ከቁጣ ጋር በማያያዝ ስናየው ልክ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን መንገድ መዝጋት የተዘጋበትን ክፍል ስለሚጎዳ የሚያስከትለው መዘዝ በቀላሉ መታየት አይኖርበትም፡፡ መንገድ ብቻ አይደለም፡፡ ከዕለት ተዕለት የምንጠቀምበት ምርት የሚገኝበት አካባቢ ምርቱን ቢያቋርጥ የተቋረጠበት ክፍል ዝም ብሎ አይመለከትም፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ጨው ከነበራቸው ግዛቶች ጨው ያልነበራቸው በፖለቲካዊ ምክንያት እንዳይገባላቸው በመከልከላቸው ምክንያት ጦርነት እንዳካሄዱ፣ ከአሜሪካ የታሪክ ምዕራፎች የምናገኘው ሀቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ሩቅ ሳንሄድ በቅርቡ ስናደርገው ደግሞ ለምሳሌ በጂቡቲ አንዳንድ ምርቶች በተወሰነ ሰዓት ከኢትዮጵያ መግባት ሲገባቸው ካልገቡ ጉዞ ወደ ኤምባሲ ወይም ወደ ፕሬዚዳንቱ ቢሮ ቢሆን ሊገርመን አይገባም፡፡

የህዳሴ ግድባችን ዓለም አቀፍ ሕጉን ጥሶ ጠቅላላውን ፍሰቱን ቢያቋርጥ ጠቡ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ብቻ ሳይሆን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ስሜትን ተከትሎ መጓዝ፣ ወይም የስሜት ተገዥ በመሆን የሕይወት መሠረት የሆነውን መንገድ በአንዱ ወይም በሌላው ምክንያት መዝጋት፣ በዚህም ምክንያት ሕዝብን መጉዳት በእጅጉ አደገኛ ነው፡፡ ስለሆነም አንዳች ተቃውሞ ታስቦና ታልሞ ካልተደረገ በስሜት ተገፋፍቶ ኅብረተሰብን የሚጎዳ እንዳይሆን፣ ያም የተጎዳ ኅብረተሰብ በጎጂው ላይ ተነስቶ እጅግ የከፋ ጥፋት እንዳያስከትል በጋራ ለጋራ ጥቅም ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

ጠባብነትና ትምክህተኛነት ከሃይማኖት አኳያ

ምንም እንኳን በመለኮታዊ ባህርይው ሃይማኖት፣ በተለይም አብርሃማዊ ሃይማኖት «ፈጣሪ እኔን አምልኩ፣ ለእኔ ስገዱ፣ ካለኔ በቀር ሌላ አታምልኩ» የሚል በመሆኑ የሰውን ልጅ ሁሉ የሚያቅፍ ቢሆንም፣ ሰዎች የየራሳቸውን የእምነት መንገድ ያስበልጣሉ፡፡ ያስቀድማሉ፡፡ ስለዚህም ጠባብነት፣ ትምክህተኛነትና ግለኝነት የሚከሰተው በፖለቲካ ብቻ አይደለም፡፡ በሃይማኖትም በሰፊው ይከሰታል፡፡ አንድ ሃይማኖት «እኔ እንደዚህ የማደርገው ወገኖቼ ሲኦል እንዳይገቡ ነው፡፡ ወይም ከሚታየው ዕብሪታዊ አዝማሚያ ራሴን ከአደጋ ለመከላከል ነው፡፡ ወይም እኔ የቆየሁ እርሱ ግን መጤ ስለሆነ የግዛት ወሰኔን አስከብሬ የመቆየት ታሪካዊ ኃላፊነት ስላለኝ ነው፡፡ ወይም መለኮታዊ ግዴታ ስላለብኝ ነው፡፡ ወዘተ…» ሊል ይችላል፡፡ ይህም አስተሳሰብ ከራሱ አኳያ ሲያራምደው አንዳችም ስህተት ላይታየው ይችላል፡፡ ለሌላው ግን ጠባብነት፣ ትምክህተኛነትና አድሏዊነት ሊሆን ይችላል፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ አንዱን ሃይማኖት የበላይ ሌላው ሃይማኖት የበታች ወይም ከኃይል ሚዛን አኳያ ቀለል አድርጎ ማየት ለጊዜው ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ሃይማኖት ብቻውን አይቆምም፡፡ በውስጡ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ሌሎችም ውስብስብ ጉዳዮች እንዳሉበት ማጤን ይገባል፡፡

ጸሐፊው የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ከአላማጣ ወደ ደሴ ሲሄድ ዞብልን የበለጠ ለማወቅ ይፈልግና ከጎኑ ተቀምጦ የነበረውን ወጣት ስለአካባቢው እንዲነግረው ይጠይቀዋል፡፡ እርሱም እስከ ዋጃ ድረስ (ከአላማጣ ቆቦ ሰባት አሥር ኪሎ ሜትር) ስለታወቁት ገዳማት፣ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት በቅንነት መንገር ይጀምራል፡፡ ጥሙጋ ሲደርሱ አንዲት የጸሐፊው ዘመድ ትደውልና በዓረብኛ ‹‹አሰላሙ ዓለይኩም›› ትለዋለች፡፡ ‹‹ወዓለይኩሙ ሰላም ወረበረካትሁ›› ይላታል፡፡ ትርጉሙም ‹‹ሰላም ላንተ ይሁን›› ላለችው ‹‹እንዲሁም ላንቺ ይሁን የፈጣሪ በረከትም ባንቺ ይወረድ›› እንደ ማለት ነው፡፡ በግዕዝ ‹‹እፉ ወዓልከ፣ ሐደርከ›› ቢባል ‹‹ይሰባህ እግዚአብሔር›› ከሚለው ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ ነገር ግን ዓረብኛውን እስላምኛ በማድረግ ‹‹የማምለክ አሽከር፣ አከከከ እናንተኮ አመጣጣችሁ አይታወቅም፡፡ እንዴት? እንዴት?››፣ ብሎ አንዱ ወጣት ፊቱን አዞረበት፡፡ ‹‹አገሬ እኮ ነው፡፡ እኔና አንተ እኮ ነን ኢትዮጵያውያን የምንባለው፤›› እያለ የአካባቢው ሰው እየሰማ ለማስረዳት ቢሞክርም አልሆነም፡፡ ወጣቱ እንደዚህ ያለውን ቁጣ ያሳየው የራያ ሙስሊም ‹‹ቢስሚላህ፣ አልሐምዱሊላህ›› እያለ ያላንዳች ችግር  የሚኖርበት አካባቢ በመሆኑ ለምን ተቆጣ?  ይህ ተጠራጣሪነት የዚህ ወጣት ችግር ብቻ ነው? ምን እየተነገረው ቢያድግ ነው? ብለን እንድንጠይቅና መልስ እንድንፈልግ ያስገድደናል፡፡

ነገሩን ከሌላ አቅጣጫ እንመልከተው፡፡ የዛሬ 94 ዓመት የታተመ ኢስላሚክ ሪቪው የተሰኘ ህንድ የሚታተም ኢስላማዊ መጽሔት ጠባብነት የተሞላበትን ኢስላም ሲተረጉም፣ ከመካከለኛ (ከዘመንኛ) ኢስላም የተለየ መሆኑን አስመልክቶ ይተነትነዋል፡፡ በኢራንም እ.ኤ.አ. በ1979 ፀረ በሃኢ እንቅስቃሴ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ እ.ኤ.አ.. በ2002 ፓኪስታን ውስጥ ፀረ ክርስትና እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ በዚሁ ዓመት ሙስሊሞች ነን የሚሉ የፓኪስታን ሰዎች ካሽሚር ላይ ባደረሱት ጥፋት ብዙ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በርካታ ጥናቶች በመጽሐፍም፣ በጆርናሎችም፣ በመጽሔቶችም፣ በጋዜጦችም እየታተሙ ወጥተዋል፡፡

ደይሊ ቴሌግራፍ የተሰኘው ዕውቅ ጋዜጣ እ.ኤ.አ. በነሐሴ 2008 ኢስላማዊ ጠባብነት፣ አግላይነት፣ አልቻቻልም ባይነት፣ ትምክህተኛነት ሌላ ስም ሊሰጠው ቢችልም፣ ያው ራሱ መሆኑን ከተለያያ መስጊዶች ስብከት ጋር አያይዞ መጻፉ ይታወሳል፡፡ በአሜሪካ ‹‹ከኢስላም በስተቀር ሌላ ሥጋት የላችሁም›› የሚሉ ያህል ነው ጥላቻው የሚናፈሰው፡፡ ብሪጊት ጋብሪየል (Brigitte Gabriel) ድረ ገጽ ‹‹ከአባቶቻችን የወረስነውን በነፃነት፣ በእኩልነትና በመከባበር የመኖር እሴታችንን ጠብቀን ለመኖር ኢስላማዊ ጠባብነትን፣ ጥላቻን ጠንክረን ልንታገለው ይገባል፣ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ልናደርጋቸው ይገባል፤›› በማለት ሳይወሰን እንዴት ጽንፈኛ ኢስላምን ድል ማድረግ እንደሚቻል ይተነትናል፡፡  (Brigitte Gabriel, Macmillan, 2010, p. 191) 

በመሠረቱ አንድ ሃይማኖት ሲነሳ ስለሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ስለሰዎች እንደሚነሳ መረሳት የለበትም፡፡ ሰው ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስሜቱን ይገልጣል፡፡ ይህን በቀላል ምሳሌ እንመልከተው፡፡ መንግሥት ሥርዓቱን ለማስከበር ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮ መንገድ እየዘጉ የሚሸጡትን በደንብ አስከባሪዎቹ አማካይነት እንዲነሱ ያደርጋል፡፡ አንዳንዱም ዕቃው ይወሰድበታል፡፡ የሚነግደው መነገጃ ተበድሮ ሊሆን ይችላል፡፡ አበዳሪውም መንግሥትም፣ የግል ድርጅትም፣ ግለሰብም፣ ተቃዋሚም… ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ መሠረት በሕገወጥ ንግድ የሚተዳደሩ ይኖራሉ፡፡ «መንገድ ላይ አትነግዱ» ማለት ለመንግሥትም ለሕግ አስከባሪም ስህተት አይደለም፡፡ ነገር ግን አንዳች አነስተኛ ተቃውሞ ከጠባብ አመለካከት፣ ከዘረኝነት፣ ከትምክህተኝነት፣ ከሃይማኖት ነክ ጥያቄ ጋር ታኮ ቢመጣ ያንን አመፅ ምክንያት በማድረግ ታፍኖ የቆየው ችግር መተንፈሻ መንገድ ያገኝና ተቃውሞውን ሊያጎላው ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚወስዱት ኃይሎች ደግሞ በሚገባ በመጠቀም ሊያጋግሉት ይችላሉ፡፡

በጠባብነት፣ በትምክህተኝነትና በራስ ወዳድነት በተመሠረተ ስሜት የሚራመድ ሃይማኖት ነክ ጉዳይ ሁሉ ለጊዜው የታወቀ አደጋ የማያስከትል ቢመስልም፣ ሊያስከትል ይችላል ብሎ በማሰብ አድሏዊ ያልሆነ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በጥላቻ ላይ ተመሥርቶ የሚካሄደውን ስብከት በተጠና ዘዴና በምክክር ማስተካከል ይገባል፡፡

ጠባብነት እንደ አዕምሮ በሽታ

የሥነ ባህርይ ምሁራን ጠባብነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ትምክህተኛነትና ከዚህ ጋር የተያያዘው ጥላቻ የአዕምሮ በሽታ መሆኑን በአደጉት አገሮች እየመሰከሩ ነው፡፡ በዚህም ረገድ ከፍተኛ ጥናቶችና ምርምሮች እየተደረጉ ነው፡፡ በእነዚህ ተመራማሪዎች መሠረት፣ አንጎላችን በብዙ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ኒውሮን በተሰኙ መልዕክት የማስተላለፊያ መስመሮች የታጨቀ ነው፡፡ ቁጥሩን ብዙ ተመራማሪዎች ‹‹የትየለሌ ወይም ለመቁጠር የሚያዳግት ነው›› ይሉታል፡፡ በእነዚህ መልዕክት አስተላላፊ መስመሮች አማካይነት የሚመጣለትን መልዕክት አንጎል ከሰውየው ዕድገት፣ ልምድ፣ ባህል፣ ወዘተ አኳያ ይተረጉማል፡፡ መጥፎና ጥሩ የሚባለው ነገርም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡  ለምሳሌ አንድ ሰው ብሶት፣ ጭንቀት፣ ናፍቆት፣ መከፋት፣ ወዘተ የመሳሰሉ ችግሮች ካሉበት በኒውሮኖች አማካይነት የሚመጣለትን መልዕክት የሚተረጉመው ከዚህ በመነሳት ሊሆን ይችላል፡፡

ለምሳሌ አንድ ወጣት ወደ ጸሐፊው መልዕክት ይልክና ‹‹ዝም ብዬ መጻሕፍትን ከማግበሰብስ ምርጥ የታሪክ መጻሕፍትን ንገረኝ›› በማለት ይጠይቀዋል፡፡ ጸሐፊውም ‹‹ልጄ ሆይ፣ ለመሆኑ ምርጥ ማለት ምን ማለት ነው? የታሪክ መጽሐፍ ዓይነቱ፣ የሚጻፍበት ምክንያቱ፣ ዘመኑ፣ ጸሐፊው፣ ወዘተ… ብዙ ነውና እንዴት ነው እኔ መምረጥ የምችለው? ባይሆን ራስህ የምታገኘውን እየመረጥክ ብታነብ ጥሩ ነው፤›› የሚል መልስ ቢሰጠው አኮረፈ፡፡ ምቀኝነት አድርጎ ወሰደው፡፡ እስቲ አስቡት ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚል ርዕስ ስንት መጽሐፍ ታትሟል? የዓረብ፣ የአሜሪካ፣ የህንድ፣ የዓለም ታሪክ እያልን ስናየውስ? ስለዚህ ጸሐፊው ነው ስህተተኛው ወይስ እርሱ? እርሱ ከሆነ በአዕምሮው የተቀረፀው ነገር ያንን እንዲል እንዳደረገው ሁሉ ጸሐፊውም ያንን እንዲመልስ ያደረገው ይኸው ነው፡፡

ስለሆነም አንጎል አንዳች ቀርፆ ያስቀመጠው ግንዛቤ ከሕይወት ልምድ፣ ከትምህርት ቤት፣ ከተረቶች፣ ከሃይማኖቶች፣ በአካባቢው ከሚነገሩ ተረትና ምሳሌዎች፣ ከታሪካዊ ባህላዊ እሴቶች፣ ወዘተ… ተቀርፀው የተቀመጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህም የተቀረፁ ነገሮች አንዳች ነገር ሲፈጠር አንጎል በቅጽበት ይተረጉምና አንዳች ውሳኔ እንድንወስን ያደርገናል፡፡

አብርሃም ሊንከን (ከ189-1864) የተባሉ አሜሪካዊ መሪ፣ ‹‹ሁለቱም ፓርቲዎች ጦርነት አይፈልጉም፡፡ ነገር ግን ከሁለቱ አንዱ አገሪቱ ባርነትን ከምታስወግድ ባትኖር ይሻላል ብለው ጦርነትን ሲመርጡ፣ ሁለተኛው ደግሞ አገሪቱ ከምትጠፋ ጦርነት ይመርጣሉ፤› በማለት መናገራቸው ይጠቀሳል፡፡ አብርሃም ሊንከን ከዚህም በተጨማሪ፣  ‹‹ሀቅና ሸፍጥ ከመጀመርያው አንስቶ እስካሁን ፊት ለፊት ቆመው እየታገሉ ነው፡፡ ይኼም ትግል እስከ መጨረሻው ይቀጥላል፡፡ አንደኛው (ሀቅ) ሊሆን የሚገባው የሰብዓዊ ፍጡር መብት ሲሆን፣ ሁለተኛው (ሸፍጥ) ግን ንጉሦች ከሰማየ ሰማያት ወረደልን ብለው የሚያምታቱበት ነው፡፡ ሀቅና ሸፍጥ በማንኛውም ቅርፅ ይከሰቱ ‹አንተ ዋተህ ሠርተህ አምጣ እኔ ደግሞ እበላልሃለሁ› ከሚል የተለየ አይሆንም፡፡ ስለሆነም በሕዝቡ ላብ ደልቦ የሚኖር ንጉሥም ሆነ አንዱ ዝርያ ሌላውን ዝርያ ባሪያ አድርጎ ለመኖር የሚፈልግ አይኖርም፤›› ማለታቸው ይዘከራል፡፡

‹‹ይህችን የአንድነት መርከብ ከመስመጥ ካላዳናት በስተቀር ሌሎች ሰዎች በሌላ ጉዞ ይዘዋት ሊሄዱ አይችሉም፡፡ ይህች አገር ከመላው ተቋማቷ ጋር የሚኖርባት ሕዝብ እንጂ የማንም አይደለችም፡፡ ስህተት፣ ስህተት መስሎ ሲሰማኝ ለማረም ጥረት አደርጋለሁ፡፡ አዲስ ሐሳብም ትክክለኛና በተግባር ሊውል የሚችል ሆኖ ሳገኘው እጠቀምበታለሁ፡፡…ሁሉም ሕዝብ ነፃ ይሁን የሚለው አመለካከቴን ግን ምንጊዜም ሊያሻሽለው አይችልም፤›› ያሉት አብርሃም ሊንከን፣ ‹‹የምንጨቃጨቅበት ትክክለኛ ጊዜ መኖር ካለበት ያ ጊዜ ያለ ጥርጥር አሁን አይደለም፡፡ ዛሬ የምናሳልፈው እጅግ አስቸጋሪ ፈተና በሚቀጥለው ትውልድ እንድንከበርም እንዳንከበርም ሊያደርገን ይችላል፡፡ ዛሬ እኛ ለአገሪቱ የግዛት አንድነት ቆመናል ብለናል፤›› በማለታቸውም ይጠቀሳሉ፡፡

ምንም እንኳን አብርሃም ሊንከን በዚህ አመለካከታቸው ዓለም የሚያስታውሳቸውና የሚያደንቃቸው ቢሆንም፣ የሞቱት ግን በጠላቶቻቸው ጥይት ነው፡፡ ስለሆነም ጠላቶቻቸው የባሪያ ንግድ አቀንቃኞች፣ ዘረኞች፣ ጠባቦች፣ አልኩ ባዮች በመሆን ያደረሱት ጥፋት በዓለም ታሪክ ሲዘከር ይኖራል፡፡ የአዕምሮ እንከን የነበራቸው ስብስቦች ምሳሌም ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡

ብሔራዊ ችግራችንን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት?

ችግራችን በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ጽልመታዊ፣ ‹ዕቡይ፣ አልኩ ባይ፣ ተመፃዳቂ፣ ‹‹ከእኛ በላይ ጎራሽ ማድ አበላሽ›› የሚል፣ አዋራጅ፣ ክብርን የሚነካ፣ በራሱ ጠባብ አመለካከት የታጠረ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል የማያውቀውን አውቃለሁ፣ የማያደርገውን አደርጋለሁ የሚል አስመሳይ፣ በተገኘው አጋጣሚ የሚጠቀም ከሚለው ጋር የተያያዘ ከሆነ የኅብረተሰቡን አዕምሮ ያወኩት ነገሮች ተበጥረውና ተለቅመው መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ስሜታቸውን ቀስቅሶ፣ ጤነኛ ሰው የማያደርገውን አስደርጎ ያሳመፃቸውና እርስ በእርስ እንዲጨፋጨፉ ያደረገው የድንበር ችግር ቢሆን፣ ችግሩ በእኛ ተጀምሮ በእኛ የሚያልቅ ሳይሆን በብዙ አገሮች ያለና የኖረ ነውና ሕዝቡን አረጋግቶ በግጭት አፈታት ዘዴ መፍታት ነው፡፡ ችግሩ እንዲፈታ ማድረግም የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ መምህራን፣ ወዘተ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ የሥነ አዕምሮ ሊቃውንት ከጠባብነት ጋር የተያያዘውን የአዕምሮ እንከን ለችግሩ ትኩረት ሰጥተው የመፍትሔ ሐሳብ መሰንዘር ይጠበቅባቸዋል፡፡  የመገናኛ ብዙኃንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ ለጋራ ሰላም፣ ለወንድማማችነት፣ ለመከባበር፣ ለመተባበር፣ ለመቻቻልና ለፍቅር ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ 

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች እየተመካከሩ የሚሠሩበት ተቋም ዕውን አድርጋለች፡፡ ነገር ግን ይኼ ተቋም ህያው እንቅስቃሴ እንዲያደርግና ተሰሚነት ያለው እንዲሆን በመንግሥትም፣ በግል ድርጅቶችም፣ በኅብረተሰቡም ያልተቋረጠ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለመቻቻል፣ ለአንድነትና ለመከባበር ይሠሩ ዘንድ መንግሥት ድጋፍ ማድረግ መቻል ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ አቅም ያላቸው የሃይማኖት ድርጅቶችም ከትምክህተኛነት፣ ከጠባብነት፣ ከግለኛነት፣ ወዘተ ተላቀው ከሌሎች ችግሮች ጋር እየታከኩ የሚመጡትን ችግሮች በጋራ ለመቅረፍ ያስችላል በሚል እምነት ታንፀው የበኩላቸውን ድጋፍ ቢያደርጉ ጥሩ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡