Skip to main content
x
በማዕድን ማውጫ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታወቀ
የማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

በማዕድን ማውጫ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታወቀ

በአገሪቱ በተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት በአንዳንድ የማዕድን ማውጫዎች የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ እንደሆነ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በተለይ በኦሮሚያ ክልል የታንታለምና ካኦሊን ማዕድናት ማምረቻዎች ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከአስተዳዳሪዎች ጋር በተፈጠሩ አለመግባባቶች ተዘግተዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን ሰባቦሩ ወረዳ ቀንጢቻ በተባለ ሥፍራ ለ30 ዓመታት ያህል የታንታለም ኮንሰንትሬት ማዕድን ሲመረትበት የቆየው የማዕድን ማውጫ መዘጋቱን የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡ የማዕድን ማውጫው ሊዘጋ የቻለው የአካባቢው ማኅበረሰብ ከማምረቻው የሚወጣው ኬሚካል አካባቢያችንን እየበከለ ነው በማለት ባቀረበው አቤቱታ ነው፡፡ ከቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውና 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ንብረትነቱ የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን የሆነ የካኦሊን ማዕድን ማምረቻ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ተዘግቷል፡፡

የማዕድን ማውጫ ኃላፊዎች ታስረው የተፈቱ ሲሆን፣ ሌሎቹም ሸሽተው ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡ በከፍተኛ የወርቅ ምርት ከተሰማራ ኩባንያ የሚወጣ ኬሚካል ዝቃጭ በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ የሚገልጽ ዘገባ ከተሠራጨ በኋላ፣ በኩባንያውና በነዋሪዎች መካከል ውጥረት እንደሰፈነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሌሎችም በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ አነስተኛ የማዕድን ማምረቻና ካባ ባለቤቶች በጭንቅ ላይ ናቸው፡፡ ሥራ አጥ ወጣቶች ባነሱት የተጠቃሚነት ጥያቄ በተነሱ ግጭቶች ሥራ ያቆሙ በርካቶች ናቸው፡፡ የወጣቶቹን ጥያቄ ለማስታገስ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በርካታ ካባዎችን ከግለሰቦች ነጥቆ ለተደራጁ ወጣቶች ሰጥቷል፡፡

የሲሚንቶ ፋብሪካዎችም የተወሰኑ ሥራዎችን ለተደራጁ ወጣቶች እንዲሰጡ ተገደዋል፡፡ ለሚያመርቷቸው ጥሬ ዕቃዎች ማዕድናት በቶን እየተተመነ ለወጣት ማኅበራት ክፍያ እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ከወጣቶች ጋር በተፈጠሩ አለመግባባቶች ሳቢያ ምርት ያቋረጡ የሲሚንቶና ጂፕሰም ፋብሪካዎች አሉ፡፡ በሒደት ላይ የነበሩ አዲስ ኢንቨስትመንቶችና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በአገሪቱ በተከሰተው አለመረጋጋትና ከወጣቶች ጋር በተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት ተቋርጠዋል፡፡ በ700 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ግንባታው ሊጀመር የነበረው የዳንጎቴ ሁለተኛ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከተቋረጡ ፕሮጀክቶች በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በማዕድን ኩባንያዎች ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና ኩባንያዎች ጋር ተባብሮ በመሥራት ላይ ነው፡፡ ችግሩ በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰተ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሞቱማ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከአካባቢው ማኅበረሰብ  ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የታንታለም ማምረቻው ሊዘጋ የቻለው በኬሚካል ብክለት ሳይሆን ከዝቃጭና ውኃ ግድቡን መሙላት ጋር በተያያዘ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ግድቡ መያዝ ካለበት በላይ ውኃ በመያዙ ሰብሮ ከወጣ ያጠቃናል ከሚል ሥጋት የመነጨ ነው፡፡ የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን በጀት ይዞ አዲስ ግድብ ለመሥራት በመንቀሳቀስ ላይ ሳለ በመሀል የአካባቢው ወጣቶች ጥያቄ አቀረቡ፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ መፍትሔው የማዕድን ማውጫዎቹን መዝጋት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ግንኙነት የሌለው ከቀንጢቻ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የካኦሊን ማምረቻ በመዘጋቱ የውኃ ማጣሪያ ኬሚካል የሚያመርተው የአዋሽ መልካሳ አሉሚኒየም ሰልፌትና ሰልፋሪክ አሲድ ፋብሪካ በጥሬ ዕቃ አቅርቦት እንደተቸገረ አስታውቋል፡፡

‹‹የማዕድን ማውጫዎቹን መዝጋት መፍትሔ አይሆንም፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ ወደ ሥራ ሊመለሱ በሚችሉበት ሁኔታ ሚኒስቴሩ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ ከወረዳ አስተዳዳሪዎችና ከኩባንያዎቹ ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከኬሚካል ብክለት ጋር ተያይዞ የተነሱን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ሚኒስቴሩ ሰፊ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የውስጥ አቅም ጥናት እያደረግን ነው፡፡ ሁለተኛ ከሚመለከታቸው ኩባንያዎች ጋር ሆነን ጉዳዩን ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲጠና እያደረግን ነው፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ ችግር የፈጠረው የትኛው ኬሚካል እንደሆነ ጥናት በመካሄድ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እውነት እንደተባለው ይኼ ኬሚካል ችግር ፈጥሯል ወይ? የሚለውን ለማረጋገጥ ከኩባንያው ጋር ተነጋግረን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እያስጠናን ነው፡፡ በላቦራቶሪ የተለያዩ ምርመራዎች እየተካሄዱ ነው፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናቱን አጠናቆ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በትክልል የተባለው ብክለት ተከስቶ ከሆነ ወንጀል ነው፤›› ብለዋል፡፡

በማዕድን ሀብት ክምችት የሚታወቀው የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች የተጠቃሚነት ጥያቄን አንስተዋል፡፡ ‹‹ኅብረተሰቡ ከማዕድን ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን መሠራት አለበት፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ ይህን ለማስፈጸም ሚኒስቴሩ በሕግ የተደገፉ አቅጣጫዎች ማስቀመጡን ገልጸዋል፡፡

ወደ ምርት የሚገባ ማንኛውም ኩባንያ ከሚያገኘው ትርፉ ላይ ሁለት በመቶ ለአካባቢ ማኅበረሰብ ልማት እንዲያውል የሚያስገድድ ሕግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደንግጓል፡፡ ይህ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ኩባንያዎች ለማኅበረሰብ ልማት የሚመድቡት ወጪ በፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንደነበር አቶ ሞቱማ አስረድተዋል፡፡

‹‹አንዱ ሁለት ሚሊዮን ብር ሌላው 200,000 ብር አንዳንዱ ደግሞ ላይሰጥ ይችላል፡፡ አሁን ግን ለአካባቢ ማኅበረሰብ ልማት ከኩባንያዎች የሚሰበሰብ ገንዘብ መጠን በሕግ በግልጽ ተቀምጧል፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ ከወረዳ አስተዳዳሪዎችና ከኩባንያዎች ጋር በመምከር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ወጣቱ ከማዕድን ልማቱ እንዴት ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል? የሚለውን እያየን ነው፡፡ ዕውቀት ያላቸው ተቀጥረው የሚሠሩበት፣ ሌሎቹ ተደራጅተው የሚሠሩበት ሁኔታን ለማመቻቸት ከክልልና ከኩባንያ ኃላፊዎች ጋር እየተነጋገርን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ የማዕድን ግልጽነት ኢኒሺየቲቭ ሁለተኛ ሪፖርቱን ይፋ አደርጓል፡፡ የማዕድን ግልጽነት ኢንሺየቲቭ በማዕድን ዘርፍ ግልጽነት ለማስፈን በማሰብ እ.ኤ.አ. 2009 የተመሠረተ ሲሆን፣ መንግሥት ከማዕድን ኩባንያዎች የሰበሰበውን ገቢና ኩባንያዎች ለመንግሥት የፈጸሙትን የተለያዩ ክፍያዎች የሚያሳይ ሪፖርት አጠናክሮ ያቀርባል፡፡ ሪፖርቱ የሚዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ በሚቀጠር አማካሪ ኩባንያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የማዕድን ግልጽነት ኢኒሺየቲቭ የመጀመርያ ሪፖርቱን በ2007 ዓ.ም. ያቀረበ ሲሆን፣ ሁለተኛ ሪፖርቱን ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡

ሪፖርቱ እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2015 በጀት ዓመት የሚሸፍን ሲሆን፣ 28 የማዕድን ኩባንያዎችና ሦስት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተካተዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ መንግሥት ከማዕድን ኩባንያዎች 1.4 ቢሊዮን ብር ገቢ ማሰባሰቡንና 343.5 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ማዕድናት ለውጭ ገበያ መቅረቡን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ባህላዊ ማዕድን አምራቾች 4.3 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ወርቅ አምርተው ለብሔራዊ ባንክ ማቅረባቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

በሪፖርቱ ከተካተቱ በማዕድን ልማት ዘርፍ ከተሰማሩ 28 ኩባንያዎች መካከል ስድስቱ መረጃ ለመስጠት አለመቻላቸው ተገልጿል፡፡ ፓቶኒር ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን ሥሪኤም እብነ በረድና ቴራዞ ማምረቻ፣ ሳማካ ስቶን፣ ኢትኖ ማይኒንግና ታርጌት ኢንዱስትሪ የተሰኙት ኩባንያዎች የተጠየቁትን መረጃ ሳያቀርቡ ቀርተዋል፡፡

የሪፖርቱን መውጣት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳና የኢትዮጵያ የማዕድን ግልጽነት ኢንሺየቲቭ ማስፈጸሚያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መርጋ ቀንዓ ኩባንያዎቹ መረጃ ያልሰጡት ፍላጎት ከማጣት ሳይሆን የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ስለሌላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ማዕከላዊ የመረጃ ሥርዓት እንዲያደራጁ ዕገዛ እንደሚደረግላቸው ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የማዕድን ግልጽነት ኢንሺየቲቭ በማዕድን ዘርፍ በኩባንያዎችና በመንግሥታት የሚፈጸሙ ሙስናና ሌሎች ብልሹ አሠራሮችን በማስወገድ ግልጽ ያለ አሠራር ለማስፈን፣ በቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር አነሳሽነት እ.ኤ.አ. በ2003 እንደተመሠረተ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2014 የዓለም አቀፍ የማዕድን ግልጽነት ኢንሺየቲቭ ዕጩ አባል መሆኗ ይታወሳል፡፡ የማዕድን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ፣ በአግባቡ ካልተያዘ ደግሞ በተቃራኒው የግጭቶች መንስዔ በመሆን ለአገር ጥፋት ሊውል እንደሚችል በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡