Skip to main content
x

በአመለካከት ስብከት ሳይሆን በጽንሰ ሐሳብ አሳምኑን

በጌታቸው አስፋው

እያንዳንዱ ሰው የራሱ አመለካከት አለው፡፡ ሰዎች ለጋራ ጉዳይ በቡድን ሲደራጁ የጋራ አመለካከት ይይዛሉ፡፡ አመለካከት በሊቃውንት ተተንትኖ የአካሄድና የተግባር ሕግና መመርያ የያዘ ወጥ መርህ ሲሆንና በብዙ ሰዎች ተቀባይነትን ሲያገኝ ጽንሰ ሐሳብ ይሆናል፡፡ ጽንሰ ሐሳቦች ሰዎች የግልና የጋራ አመለካከታቸውን ወደ ጥበብ የሚገሩበት የሐሳብ ንድፎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ብዙ የተማሩና ብዙ ያወቁ ሰዎች አመለካከት ከሊቃውንት አመለካከትና ጽንሰ ሐሳብ የተቀዳ ይሆናል፡፡ ምሁርነት ማለትም ከግልና ከቡድን አመለካከት ወጥቶ ሐሳብን በሊቃውንት ጽንሰ ሐሳብ መግራት ማለት ነው፡፡

ያልተማሩና ብዙ ያላወቁ ሰዎች አመለካከት ግን በግልና በጋራ አመለካከቶች የተገደበ ነው፡፡ ስለጽንሰ ሐሳብ ጠንቅቀው ስለማያውቁ የራሳቸውን ወይም የቡድኑን አመለካከት ይሰብካሉ ለማሳመን ይሞክራሉ፡፡ ስለጽንሰ ሐሳብ ምንም ግድ የላቸውም፡፡ የአገሮች መሪዎችም በሊቃውንት በተተነተኑ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ ተመርኩዘው ራዕይአቸውንና ፖሊሲያቸውን ይቀርፃሉ፡፡ የመሪዎች የሥራ ድርሻ በመረጡት ጽንሰ ሐሳብ ላይ ተመርኩዞ ፖሊሲ ከመቅረፅ ወይም ስትራቴጂ ከመንደፍ ጀምሮ ወደ ታች ያሉትን ዕቅድ የማዘጋጀትና ዕቅዱን መተግበር፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ማከናወንና እንዲከናወኑ ማድረግ ነው፡፡

የታዳጊ አገሮች መሪዎችና ባለሥልጣናት በተለይም የኢትዮጵያ መሪዎችና ባለሥልጣናት በምርምር ያልተረጋገጡ፣ የግልና የቡድን አመለካከታቸውን ጽንሰ ሐሳብ አድርገው በመውሰድ የሙከራ ፖሊሲ ይቀርፃሉ፣ ስትራቴጂ ይነድፋሉ፣ ዕቅድ ያዘጋጃሉ፣ ዕቅዶቻቸውን ለመተግበርም ይነቀሳቀሳሉ፡፡ አመለካከታቸውን በሕዝብ ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ከሕዝብ ጋር ይጋጫሉ፡፡ የኢሕአዴግ መሪዎች በረሃ ሳሉ በማርክሲዝም ጽንሰ ሐሳብ ይመሩ ነበር፡፡ ከተማ ሲገቡ ግን ጽንሰ ሐሳቡ ፎርሾ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከሰዎች ጭንቅላት ውስጥ እየተፋቀ ስለነበር፣ የግልና የቡድን አመለካከታቸውን በተለይም የአቶ መለስ የግል አመለካከትን ሲሰብኩን ኖሩ፡፡ የአቶ መለስ አመለካከት ተተንትኖ ወደ ጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ስላላደገ፣ ደጋፊዎቻቸው የቱንም ያህል ቢደክሙም ሕዝብ ሊቀበለው አልቻለም፡፡

በሌላ በኩል ከኢሕአዴግ አመለካከት ውጪ ያሉ ሰዎችን በዓላማ  ለማመሳሰልና አንድ ለማድረግ የጋራ አመለካከት ለመያዝ ያልቻሉ፣ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ያልተነሱና በልሂቃን በጽንሰ ሐሳብ መልክ ያልተነደፉ አመለካከቶችን በሳይንሳዊ መንገድ ተንትኖ የሚያስረዳ ተፅዕኖ አድራጊ ሰው ጠፍቶ፣ የየራሳቸውን በምርምር ያልተፈተሸ ሐሳብ ብቻ የሚጽፉና የሚናገሩ ሰዎች ተከታይ ሊያገኙ ይቅርና የሚጽፉትን የሚያነብና የሚናገሩትን የሚሰማ ሰው ታጣ፡፡ በኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ጎራ መቶ ሰዎች ሲሰበሰሰቡ መቶ ሐሳብ ይዘው ይመጣሉ፡፡ መቶዎቹም ሐሳቦች ነጥረው ወደ ተመሳሳይ የጋራ አመለካከት ሳይቀየሩ ዋና ተፅዕኖ ፈጣሪ ገዢ አመለካትም ሳይፈጠር፣ እያንዳንዱ የየራሱን ሐሳብ ብቻ እያደነቀ ስብሰባው ይበተናል፡፡ ቡድኖች ከተሰባበሰቡ በኋላ በሐሳብ ተለያይተው ለመበታተን ጊዜ እንደማይወስድባቸው ከታሪካቸው አየን፡፡ ትልቁ ችግራቸውም የማንበብ ልምድ ስላዳበሩ በሊቃውንት የተተነተኑ ጽንሰ ሐሳቦችን በውል አለማወቃቸው፣ አመለካከታቸው ከሊቃውንት አመለካከትና ጽንሰ ሐሳብ ያልተቀዳ መሆኑ ነው፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ከአንድ በፌዴራሊዝም ፖለቲካ የዶክተሬት ዲግሪ ካላቸው ረዳት ፕሮፌሰር ጋር እኔ ልማታዊ መንግሥትና የብሔረሰብ ፌዴራሊዝም ይጋጫሉ የሚል አቋም ይዤ፣ እሳቸው ይደጋገፋሉ የሚል አቋም ይዘው በግል አመለካከታችን ክርክር ገጥመን ነበር፡፡ በክርክሩ ሊገፉበት ስላልቻሉ ተቋረጠ፡፡ ለሌሎች ምሁራን በተለይም ለሥነ ልቦናና ለሥነ ማኅበረሰብ ምሁራን ውይይቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አስተላልፌ ነበር፣ የመጣ ግን የለም፡፡ አሁንም ቢሆን ምሁራን አትደበቁ፡፡ አንድ ጥይት በተተኮሰች ቁጥር አልጋ ሥር ከመግባት የምታምኑበትን አመለካከት ወርውራችሁ በጽንሰ ሐሳብ መልክ ሊተነተን ከቻለና ሕዝብ ከተቀበለው ለመሪዎች የፖሊሲ መሠረት ሊሆን ይችላል፡፡

በጊዜውም እንደተናገርኩት ኢሕአዴግ የብሔር ፌዴራሊዝሙንና ልማታዊ መንግሥትነቱን ተቃርኖ ለማለዘብ ሚዛን እየጠበቀ ለማራመድ ሃያ ሰባት ዓመት ዳክሮ ዛሬ ክንዱ ዝሏል፡፡ ሚዛን ለመጠበቅ የሄደበት መንገድም ሐሳብን በማንሸራሸር ሳይሆን፣ ሐሳብን በማፈን ስለነበረ የታፈነው ገንፍሎ ሁከት ፈጠረ፡፡  ድህነት ሰውን ሁሉ ስስታም ባደረገበት የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ ሆነን ፌዴራሊዝም ሰውን መጤና ተወላጅ ብሎ በከፋፈለበት ልማታዊ መንግሥት የሀብት አከፋፋይ በሆነበት ፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ፣ ገበያውንና ልማቱን አቀናጅቶ ፖሊሲ ለመቅረፅ የሚረዳ ገዥ ጽንሰ ሐሳብ በሊቃውንት አልተተነተነም

የኢሕአዴግን አመለካከትና ከአመለካከቱ ተነስቶ የቀረፃቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና የፖለቲካ አስተዳደር ችግር በሁለት ፈርጆች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንዱ ችግር በልማታዊ መንግሥት ውስጥ የገበያ ኢኮኖሚውንና የልማት ኢኮኖሚውን ማመጣጠን አልቻለም፡፡ የፌዴራል ፖለቲካዊ ሥርዓቱ ሳይጨመርበትም በልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና ከገበያውና ከልማቱ ምን ዓይነትና ምን ያህል ቅንብር የሚለው አልተፈታም፡፡ የእስያውያንን ልማታዊ መንግሥት ምሳሌ ይጥቀሱ እንጂ፣ ሲንጋፖርና ደቡብ ኮሪያ ወይም ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ሌሎቹም በየራሳቸው የልማታዊ መንግሥት መንገድ ቢጓዙም ወጥ የሆነ የመንግሥትን የሥራ ድርሻና የግሉን የሥራ ድርሻ ለይቶ ያስቀመጠ መንገድና የጉዞ ካርታ የለውም፡፡

ቢከፋም ቢለማም ላለው ይጨምርለታል፣ ከሌለው ያለውንም ይነጥቀዋል ቢባልም ግን ገበያ በቲፎዞነት ሳይሆን በውድድር የሀብት ክፍፍል በማድረግ ሰዎችን በእኩልነት እንደሚያስተናግድ ጽንሰ ሐሳቡ ይናገራል፡፡ ስለዚህም ግለሰቦች በገበያ ተሳትፏቸው እንጂ በአፍ ደጋፊነታቸው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ አይሆኑም የሚለው የሊበራል ኢኮኖሚ አመለካከት፣ ከቀረቡት አማራጮች የተሻለ የማኅበረሰብ አደረጃጀት ገዥ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ሁለተኛው ችግር በልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚ ውስጥ የማዕከላዊ መንግሥትንና የክልል መንግሥታትን ሚና መለየት አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ አንድነትን ደጋፊ የሆኑትም የብሔረሰብ መብት ደጋፊዎችም የኢሕአዴግ ጠላት ሆነዋል፡፡ የብሔረሰቦችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት በሚያቀነቅነው የብሔር ፌዴራሊዝምና በልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ አስተዳደር መካከል የማይታረቅ ቅራኔ አለ፡፡

በጆሀንስበርግ ብዙ ሺሕ ኢትዮጵያውን ሠርተው ይኖራሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ምን ያህል ደቡብ አፍሪካውያን ሠርተው ይኖራሉ? ናይሮቢ ብዙ ሺሕ ኢትዮጵያውያን ሠርተው ይኖራሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ምን ያህል ኬንያውያን ሠርተው ይኖራሉ? ጂቡቲ ውስጥ ብዙ ሺሕ ኢትዮጵያውያን ሠርተው ይኖራሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ምን ያህል ጂቡቲያውያን ሠርተው ይኖራሉ? የዓረብ አገሩንና የፈረንጅ አገሩን ቆጥሬ አልዘልቅም፡፡ ቀድሞ የውጭ አገር ሰው ዝር የማይልባቸው የእስያ ከተሞች ዛሬ የእኛን ሰዎች ጨምሮ በውጭ አገር ሰዎች ተጨናንቀዋል፡፡ እዚህ ግን ሀዲያው ዝዋይ ሄዶ ሠርቶ መኖር አልቻለም፡፡ ምሥራቅ ሐረርጌው ጂግጂጋ ሄዶ ሠርቶ መኖር አልቻልም፣ ጎጃሜው ደምቢዶሎ ሄዶ ሠርቶ መኖር አልቻለም፡፡ የአዲግራቱ ወልዲያ ሄዶ ሠርቶ መኖር አልቻለም፡፡ ሌሎች በአኅጉርና በአገር ደረጃ ሳይጠቡ እኛ በብሔረሰብ ደረጃ መጥበብ አምሮናል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን፣ ዶ/ር መረራ ጉዲናን የመሳሰሉ የአገሪቱ ምሁራን የፖለቲካ ሰዎች የብሔረሰብ ፌዴራሊዝሙ ችግር የለበትም፣ ችግሩ የአፈጻጸም ነው በማለት አመለካታቸውን አስፋፍተው ባይጽፉም ያመኑበትን በመናገር ቂሊንጦን ፈርተው ከተደበቁት ይሻላሉ፡፡ እነዚህ ምሁራን ኢሕአዴግ አልቻለበትም እንጂ እኛ ብንሆን እንችል ነበር ይላሉ፡፡ የግልና የቡድን አመለካለትም በጽንሰ ሐሳብ ካልተረጋገጠ፣ የኢሕአዴግን ዕድል አግኝተው ሥልጣን ቢይዙ ከኢሕአዴግ የተሻለ ለመሥራታቸው ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጽንሰ ሐሳብ ባልተገራ የግልና የቡድን አመለካከት ቤተሙከራ ሊሆን አይገባም፡፡ ስለሆነም የመብትም ሆነ የነፃነት ታጋዮች ነን የምትሉ ሰዎች አመለካከታችሁን በየትኛው ጽንሰ ሐሳብ እንደ ገራችሁ ልታሳዩ ይገባል፡፡

በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመርኩዞ የሚነደፍ ጽንሰ ሐሳብ ከተግባርም፣ ከዕቅድም፣ ከፖሊሲም ሊቀድም ስለሚገባና የፖሊሲ የዕቅድና የተግባር መመርያ ሊሆን ስለሚገባው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እነኚህን ታላላቅ ምሁራን የመንግሥት ሥልጣን ብትይዙ አመለካከታችሁን በየትኛው የሊቃውንት ጽንሰ ሐሳብ ገርታችሁ ነው ፖሊሲ የምትቀርፁት ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ራሳችሁ የነደፋችሁት ጽንሰ ሐሳብ ካላችሁም ፍልስፍናውን ብቻ ሳይሆን የአፈጻጸም ቴክኒኩንም ተንትናችሁ አብራሩልንና በሕዝብ ተቀባይነት ያግኝ ብሎ እንደሚጠይቃቸው አምናለሁ፡፡ እኔም ከጠያቂዎቹ አንዱ እሆናለሁ፡፡

የእኛ አገር ፖለቲከኞች የሚወዛገቡት በሰውና በሰው አመለካከት ወይም በቡድንና በቡድን አመለካከት እንጂ፣ በሊቃውንት በተተነተነ ጽንሰ ሐሳብ አይደለም፡፡ ሰውና ሰው በአመለካከት ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም በሰውና ሰው ክርክር የሐሳብ መሸናነፍ ብቻ አገር ለመምራት የሚያስችል በተግባር የተፈተነና በሊቃውንት የተነደፈ ጽንሰ ሐሳብ ሊሆን አይችልም፡፡ ካፒታሊዝም፣ ኢምፔሪያሊዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ወዘተ የማኅበረሰብ አኗኗር ሥርዓቶች የሰው ከሰው ወይም የቡድን ከቡድን ክርክሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ ከአመለካከት ልዩነቶች ተነስተው በሊቃውንት የተነደፉና በሕዝብ ተቀባይነት ያገኙ ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፡፡ የዓለም አቀፋዊነት፣ የብሔር፣ የብሔረሰብ አመለካከቶችም በሊቃውንት በተነደፉ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ የተመሠረቱ በቂ ምክንያታዊነት ያላቸው ሐሳቦች ናቸው፡፡

አንድ ሰው በተመሳሳይ ጊዜ ካፒታሊስትም ሶሻሊስትም ሊሆን አይችልም፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም የብሔረሰብ መብት ታጋይና የአገር አንድነት ታጋይ መሆንም አይችልም፣ ይህን ቢያደርግ በሁለት ቢላ አንደሚበላ ሰው ነው የሚመሰለው፡፡ በግማሽ ልብ ኬኩን ለሁላችንም እንዲበቃ ትልቅ አድርገን እንከፋፈለው ብሎ፣ ወዲያው በሌላው ግማሽ ልቡ የእኔን ኬክ አትንኩብኝ ማለት አይቻልም፡፡ የሚጋጩ ነገሮች አሉባቸው፡፡ ከሁለቱ አንዱን የመረጡ ሰዎችም የመረጡበትን ምክንያት ለሕዝብ ማስረዳትና ማሳመን  ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁለቱ አይጋጩም እንዲያውም ይደጋገፋሉ የሚሉ ከሆነም የማይጋጩበትን ሁኔታ ማስረዳትና ማሳመን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከዶ/ር ነጋሶ በስተቀርም ሌሎቹ ሁለቱ የፌዴራሊዝም ደጋፊዎች የፖለቲካ ትግል እያደረጉ ነው፡፡ ስለዚህም የልማታዊ መንግሥትና በቋንቋና በብሔረሰብ ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝም ቅራኔዎች በጽንሰ ሐሳብ ትንታኔ እንዴት እንደሚያስታርቁ ቢገልጹልን መልካም ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ወይ ልማታዊ መንግሥትን ወይ የፌዴራል መንግሥትን አንዱን ብቻ ምረጡ፣ ሁለቱ አንድ ላይ አይሄዱም ይባላሉ፡፡ እኔ በበኩሌ በሁለቱ መካከል ያለውን ቅራኔ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

የብሔረሰብ ፌዴራሊዝሙን ለብቻ ወስዶ ማየት ወይም ልማታዊ መንግሥትን ለብቻ ወስዶ ማየት በሁለቱ ጥምረት ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ችግር አያሳይም፡፡ ልማታዊ መንግሥትም ለብቻው ሲያዩት የሚያጓጓ ነገር አለው፡፡ ፌዴራሊዝሙም ለብቻው ሲያዩት የሚያጓጓ ነገር አለው፡፡ ሁለቱን አጣምሮ ሲያዩዋቸው ግን የሚያጓጋው ነገር ወደ የሚያሠጋ ነገርነት ይለወጣል፡፡ ሁለቱን አጣምሮ በአንድ ላይ በማየት ኢትዮጵያ የምትከተለው ልማታዊ ፌዴራላዊ መንግሥት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምን ችግር እንዳለበት ለመረዳት ይጠቅማል፡፡

የልማታዊ መንግሥት ቅድመ ሁኔታ የሆነው የቢሮክራሲው ችሎታና የፌዴራሊዝም ቅድመ ሁኔታ የሆነው የብሔረሰብ ተዋጽኦ ይጋጫሉ፡፡ ይህን መሰል ብዙ ያልተፈቱ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ ለጊዜው ከዚህ ቀጥሎ ልማታዊ መንግሥትነቱ ለፌዴራሊዝም የማይፈቅደውንና ፌዴራሊዝሙ ለልማታዊ መንግሥትነት የማይፈቅደውን አንድ ሁኔታ ብቻ እንመልከት፡፡ በልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚ ውስጥ የረጅም ዘመን አገራዊ የልማት ዕቅድ ስለሚታቀድ ያንን ለማስፈጸም ከአምስት ዓመት የምርጫ ዘመን የበለጠ ጊዜ በሥልጣን መቆየት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ልማታዊ መንግሥት ሥልጣኑን በአምስት ዓመት ውስጥ  በምርጫ የሚለቅ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሊሆን አይችልም፡፡

የልማታዊ መንግሥትነት የኢኮኖሚ ሥርዓት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊነቱን የፖለቲካ ሥርዓት አይደግፍም፡፡ ኢሕአዴግ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ በአውራ ፓርቲ ስምና በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሸፋፍኖ ተቃዋሚዎችን እየኮረከመና እያቀጨጨ የቆየበት ሚስጥርም ይኸው ነው፡፡ በሌላም በኩል በፌዴራል መንግሥት የፖለቲካ አስተዳደር ውስጥ የክልል መንግሥታት የእርሻ መሬት ይቅርና ቋጥኛቸውን እንኳን ለልጆቻችን ሥራ እንፈጥርበታለን በማለት፣ ከደርባንና ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ጋር የገጠሙት አታካራ የሚነግረን ክልሎች ከብሔራዊ ወይም አገራዊ ልማት ዕቅድ የሚቃረን የክልል ልማት አጀንዳና መብት ሊኖራቸው እንደሚችል ነው፡፡ ስለሆነም በብሔራዊ አጀንዳ ዙሪያ ሁሉንም ኅብረተሰብ ያሰባሰበ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የሚለውን የልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚ ቅድመ ሁኔታን፣ የፌዴራል መንግሥት የፖለቲካ ሥርዓቱ አይፈቅድም፡፡

ፊት ለፊት ወጥቶ ባይነገርም በፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ በሕዝቡ ዘንድ የአመለካከት ልዩነትን የፈጠረው ብሔር ተኮር ግጭቶችንም ያስከተለው፣ አቶ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ልማታዊ ፌዴራላዊ መንግሥት እንዴት ተግባራዊ እንደሚደረግ በጽንሰ ሐሳብ መልክ ተንትነው ያላቀረቡት የግል ወይም የቡድን አመለካከታቸውን ፍልስፍና ለሕዝብ በበቂ ሁኔታ ስላላስረዱ በጭፍን በመደገፍና በጭፍን በመቃወም ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በተለይም ምሁራን መፋጨት ያለባቸው ምንም እንኳ ጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ደርሶ እንደ ገዥ ሐሳብ በብዙዎች ተቀባይነትን ያገኘ ባይሆንም መሪ ስለነበሩና ባልደረቦቻቸው አጡዘው ስላቀረቡት የሰዎችን ቀልብ ለሁለት በከፈለው በዚህ የአቶ መለስ የግል አመለካከት ሐሳብ ዙሪያ ነው፡፡

በተለይም ብዙ ሰዎች በኢሕአዴግ መንግሥት የትግራይ ሰዎች በሥልጣንና በሀብት ተጠቃሚዎች ናቸው ብለው ከሚያምኑት መላምትም ይሁን እውነት ባሻገር፣ እስከ አሁንም ድረስ የትግራይ ሕዝብ የአቶ መለስን የግል አመለካከት በጭፍን ይደግፋል ብሎ ያስባል፡፡

የአቶ መለስን አመለካከት ደጋፊ የሆኑ የትግራይ ምሁራን ከዘጠና በመቶ በላይ የሆነው የትግራይ ሕዝብ በማያውቀው ጉዳይ የግጭት ሰለባ እንዳይሆን ለተቃዋሚዎች የአቶ መለስን አመለካከት ትክክለኛነት ማስረዳትና ማሳመን፣ አለበለዚያም ደግሞ ለትግራይ ሕዝብ የአቶ መለስ አመለካከት በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እንደማይሠራ በማስረዳትና በማሳመን ቀዳሚ ሚና እንዲጫወቱ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይህን እንቆቅልሽ አቶ መለስ ራሳቸው በሕይወት ኖረው ቢፈቱት ጥሩ ነበር፡፡ እሳቸው ስለሌሉ ግን በጭፍን በማመን ከሚታሙት የትግራይ ምሁራን በተጨማሪ ደጋፊ ነን የሚሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ላላመኑት አቅርበው መከራከር አለባቸው፡፡ ያላመኑትም እንደዚሁ ያላመኑበትን ምክንያት በጽንሰ ሐሳብ አስደግፈው በመተንተን ማቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ የሐሳብ ፍጭት ብሔረሰብን ማዕከል አድርጎ ከተነሳው ካለማወቅ የመጣ ያለመግባባት ግጭት ሊያወጣን የሚችል ብቸኛ መንገድ ነው፡፡

ዛሬ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቀባይነትን ያጣው በልማታዊ ፌዴራሊዝም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት የአውራ ፓርቲና ዴሞክራያዊ ማዕከላዊነት የአቶ መለስ ዜናዊ የግል አመለካከት፣ ነገ በሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥመው የትግራይ ምሁራን ሊፈጥኑ ይገባል፡፡ ከሁሉም በፊት የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ማወቅ ስለሚገባ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሕዝቦቿ በተፈጥሮ ሀብት በተለይም በመሬት ላይ ጥገኛ የሆኑ በድህነት የሚኖሩ ናቸው፡፡ ከድህነቱ የተነሳ ሰሜኑ አድሎ ሳይደረግበት ወደ ደቡብ ሄዶ ሠርቶ መኖር ይፈልጋል፡፡ ደቡቡም አድሎ ሳይደረግበት ወደ ሰሜን ሄዶ ሠርቶ መኖር ይፈልጋል፡፡ አንድነትና ኅብረት ስለጠፋ ግን ሰዎች በፍርኃት ወደ ብሔረሰባቸው እንዲጠቃለሉ አድርጓል፡፡

ይህን ለዘመናት የቆየ አብሮ የመኖር ጥቅምና መብት ፌዴራሊዝሙ እንቅፋት እንደሆነበት ከትውልድ ቀዬአቸው ውጪ ያሉ የትግራይ ተወላጆችና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተገንዝቧል፡፡ የብዙኃን አስተዳደርና የአናሳዎች መብት መጠበቅ የሚባለው ዴሞክራሲ ለሃያ ሰባት ዓመታት አናሳዎችን ሀብት የማፍራት ዕድል ነፍጓል፡፡ በብሔረሰብ አከላለል ብዙኃን ሆነው በመደራጀት የአስተዳደር መብት ያገኙትም በጣልቃ ገብነት መብታችንን ሙሉ በሙሉ አልተጠቀምንም እያሉ ነው፡፡ ስለሆነም ኢሕአዴግ አገር የሁላችንም የጋራ ናት በሚሉት የአንድነት ደጋፊዎችም ፌዴራሊዝሙ የፈቀደልንን አካባቢያችንን ለራሳችን በራሳችን አላስተዳደርንም በሚሉትም አልተወደደም፡፡ ይህን ሁኔታ ያስከተለው ምድንነው ብሎ መመርመር አገሪቱ የገባችበትን አጣብቂኝ ለመፍታት እንድ ዕርምጃ ወደ ፊት ያስኬዳል፡፡

ግብፆች በዓባይ ውኃ ለረጅም ጊዜ እየተጠቀምን ስለሆነ ጠብታም እንኳ አታጉድሉብን፣ አትንኩብን እያሉ እንደ መብት ሲያነሱ ከብዙ ዘመን በፊት ያገኘውን የአብሮ መኖር ተጠቃሚነት መብት የጋራ አገሬነት ሥነ ልቦና የአንተ መቼ ሆነና ብሎ ልንጠቅህ የሚል ከመጣ፣ አሻፈረኝ የሚል ኢትዮጵያዊ መነሳቱ አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር አብሮ የመኖር ተጠቃሚነት መብቱንም ከውስጡ በበቀሉ ሰዎች ደባ ለኤርትራውያኑ ብቻ ድምፀ ሕዝብ ተሰጥቶ መቋጨቱን ፍትሐዊ እንዳልሆነ ውሳኔ ነው የሚቆጥረው፡፡ ለብዙ ሺሕ ዓመታት አብሮ ከመኖር ያገኘውን በጋብቻ የመተሳሰር ዝምድና በማኅበራዊ ኑሮ የፈጠረውን ግንኙነት፣ በኢኮኖሚያዊ ኑሮ የፈጠረውን የገበያ ስፋት ተጠቃሚነት፣ የባለ አገርነት ሥነ ልቦና፣ በይህ አካባቢ የእኔ ብቻ ነው ባይ ስግብግቦች እንደ ቀልድ ተወስዶ በራሱ መንግሥት አያገባህም ተብሎ ተነጠቀ፡፡ ይህ እንዲደገምበት አይፈቅድም፡፡

እንደ በለፀጉት አገሮች በየትም ቦታ ተዘዋውሮ ለመሥራት አስፈላጊው እጅና የእጅ ሙያ ቢሆን ኖሮ፣ አገራችን በኢንዱስትሪ አድጋ ቢሆን ኖሮ ሰዎች ቢያንስ በኢኮኖሚው ባልተጋጩም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ሠርቶ ለመኖር ዋናው አስፈላጊ ነገር መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በፌዴራሊዝሙ ሥርዓት የእኔ አካባቢ የእኔ ብቻ ነው የሚል ስሜት ፈጠረ፡፡ የሀብት አከፋፋይ ገበያው ቢሆን ኖሮ ጠንካራውና ታታሪው ያገኛል፣ ደካማውና አልምጡ ያጣል፡፡ ነገር ግን በልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት ጠንካራውና ታታሪው ሠራተኛ አጥቶ፣ ደካማውና መንግሥትን የተጠጋው ከእጅ ሥራ የአፍ ልፍለፋ የሚቀድመው እንዲያገኝ ተደረገ፡፡ ፌዴራሊዝሙም ለዚህ የተመቻቸ ሆነ፡፡

ስለፖለቲካው ብዙ ባላውቅም ላለፉት ሁለት ዓመታት ከአርባ በላይ ጽሑፎችን በሪፖርተር ጋዜጣ በማውጣት የኢሕአዴግን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስቃወም ኖሬአለሁ፡፡ ይሁንና ዛሬ በሐሳብና በአመለካከት ደረጃ ተፋጭተን ከመግባባታችን በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሕዝቡን አውላላ ሜዳ ላይ ጥለው ሥልጣን ለመልቀቅ ያቀረቡትን ጥያቄ በበኩሌ አልደገፍኩትም፡፡ የታሪክ ተጠያቂ እንዳይሆኑም እፈራለሁ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ሕግና ሥርዓትን ጠብቆ በሐሳብ ተፋጭቶ መግባባት ሲቻል፣ የተቆጣውንም ያመፀውንም ና እንነጋገር ማለት ሲቻል፣ የውይይትና የመግባባት ምኅዳሩን ማስፋት ሲቻል፣ በፖለቲካ ላይ ላለ ሰው የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሕይወትና ሰላም በእጁ ላለ ሰው ማኩረፍም ሆነ ጥሎ መሸሽም አዋቂነት አይደለም፡፡ ከእሳቸው የተሻለ ገለልተኛ ሰው ይመጣል ብዬም አልገምትም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡