Skip to main content
x
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ

ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም. ለአሥር ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዜጎች ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ፣ የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት የሚያውኩ ጽሑፎችን የማተም፣ የማባዛት፣ የማሠራጨትና ሌሎች ክልከላዎች እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ደግሞ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴሪያት ኃላፊ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ለአሥር ወራት ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳም የመከላከያ ሚኒስትርና የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ ወደ ቀድሞ ገጽታው እንደተመለሰ፣ በውስን አካባቢዎች የሚቀሩ ጥቂት ጉዳዮች እንዳሉና ይህንን ችግር ደግሞ በመደበኛው የሕግ ማስከበር መፍታት እንደሚቻል ጠቁመው፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ በአገሪቱ ሌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ታውጇል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዓርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ለስድስት ወራት የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአገሪቱ ተጥሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በራሳቸው ፈቃድ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ ከኢሕአዴግና ከደኢሕዴን ሊቀመንበርነት ለመውረድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ባስታወቁ ማግሥት በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአደባባይ ሠልፍ ማድረግ፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስና ሌሎች ክልከላዎችን ይዟል፡፡ ወንጀሎችን የጠነሰሰ፣ የመራ፣ ያስተባበረ፣ የጣሰ ወይም በማንኛውም መንገድ በወንጀል መንገድ የተሳተፈ ወይም ተሳትፏል ተብሎ የሚጠረጠርን ማንኛውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ያውላል፡፡ ወንጀል የተፈጸመባቸውና ሊፈጸምባቸው የሚችሉ ዕቃዎችን ለመያዝ ሲባል ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ማናቸውንም ቤት፣ ቦታ፣ መጓጓ ሊበረብር፣ እንዲሁም ማናቸውም ሰው ማንነቱን መጠየቅና መፈተሽ እንደሚቻል መደንገጉን ይታወቃል፡፡ በዚህ አዋጅ እነዚህና ሌሎች ክልከላዎች የተካተቱ ሲሆን፣ አቶ ሲራጅ ቅዳሜ የካቲት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ ሲባል መርማሪ ቦርድ ይቋቋማል፡፡

በአገሪቱ በተለይም ከ2010 ዓ.ም. መግቢያ ጀምሮ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ቀውስ ተከስቷል፡፡ በአገሪቱ ታሪክ በተለይም ባለፉት 26 ዓመታት ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት የበርካታ ዜጎች ሕይወት ከማለፉም በላይ፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ደርሷል፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችም ከሁለቱም ክልሎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች እንዲኖሩ ተገደዋል፡፡

ችግሮችን በመደበኛው የሕግ ማስከበር መፍታት እንዳልተቻለ አቶ ሲራጅ በጋዜጣዊ መግለጫው መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ አቶ ሲራጅ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሥርዓት አልበኝነት ተፈጥሮ የዜጎች ሕይወት እየጠፋና ንብረታቸው በቀላሉ እየወደመ ነው፡፡ የሕዝቦችን አብሮ የመኖር ባህል የሚሸረሽሩ ቅስቀሳዎች፣ አልፎ አልፎም ብሔርና እምነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ማጋጠማቸውን አውስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ባስገቡ ማግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን አለመረጋጋት ለመፍታት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጅ ይልቅ መንግሥት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከወጣቶችና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመነጋገር መፍታት ይችል እንደነበር የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነና በቀላሉ መፍታት እንደማይቻል የሚከራከሩ፣ ይህን ችግር ለመፍታትም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ተገቢ ነው ብለው የሚያምኑ አሉ፡፡

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው መንግሥት አገሪቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ማስተዳደር ስላልቻ መሆኑን ተናግረው፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሁን ለተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሔ ይሆናል ብለው አይገምቱም፡፡ ምክንያታቸውን ሲናገሩም በአገሪቱ የተከሰተውን ችግር መፍታት የሚቻለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይሆን፣ ፖለቲካዊ መፍትሔ በመስጠት እንደሆነ ነው፡፡ ‹‹ችግሩ ፖለቲካዊ ነው፣ መፍትሔውም ፖለቲካዊ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የዶክትሬት ተማሪውና የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ አበበ ዓይነቴ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተገቢነት ከመናገር በፊት ኢትዮጵያ ያለችበትን የውስጥና የውጭ ሁኔታ መረዳት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አገሪቱ ምርጫ ማካሄድ መቻሏ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት እየጎለበተና የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እየተከበሩ እንደሄዱ ገልጸዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጣና ሁከትና ትርምስ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ አገሪቱ ለዚህ ችግር ተጋላጭ እንዳትሆን የውስጥ ችግርን በተገቢው መንገድ መፍታት እንደሚገባ አቶ አበበ አሳስበዋል፡፡ አገሪቱ በውስጣዊ ችግሮች በምትታመስበት ጊዜ ለውጭ ወረራ ስትጋለጥ መቆየቷን አስታውሰው፣ ይህ ችግር ዳግመኛ በአገሪቱ እንዳይከሰት የውስጥ ችግርን መፍታት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ይህን ለማድረግም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ ንጋት አስፋው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ የለበትም ይላሉ፡፡ አገሪቱ ለዚህ የሚያበቃ ሁኔታ ላይ እንዳልሆነች የሚናገሩት ዶ/ር ንጋት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጊዜ ሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡

አቶ ልደቱ በ2009 ዓ.ም. ለአሥር ወራት ተጥሎ የነበረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውጤታማ እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያመጣውን አንፃራዊ መረጋጋት እንደ ዘላቂ መረጋጋት ተቆጥሮ ነው እንዲነሳ የተደረገው፤›› ብለዋል፡፡ የአሁኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ውጤታማ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ለምን ከተባለ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚፈታ ችግር የለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ስለዚህ መንግሥት ለማስተዳደር ተቸግሬአለሁ ካለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መቃወም ሊያስቸግር ይችል ይሆናል፡፡ ይህን ጊዜ የፖለቲካ መፍትሔ ለመስጠት ሊጠቀምበት ይችል ይሆናል፡፡ ይህን በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል፡፡ ወደ ፖለቲካው መፍትሔ የማይሄድ ከሆነ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነገሮችን ከማወሳሰብ ባለፈ ጥቅም አይኖረውም፤›› በማለት አቶ ልደቱ አብራርተዋል፡፡

አቶ አበበ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ምርጫ ማካሄድ ችላለች፡፡ የዴሞክራሲ መብቶችን ማዳበር ተጀምሯል፡፡ ልማት ማየት ተችሏል፡፡ በዓለም ደረጃ የነበረንን ስምና ታሪክ በአዲስ ጽፈናል፡፡ ይህንን ወደፊት ነው ማስቀጠል ያለብን? ወይስ ወደኋላ ነው መመለስ ያለብን? የሚለው መታየት አለበት፤›› ሲሉ ሞግተዋል፡፡ ‹‹አሁን እዚህም እዚያም የሚነሳው ነውጥ አገሪቱን ወደኋላ ነው የሚመልሳት፡፡ ከውጭ ብዙ ጠላቶች አሉብን፡፡ ውስጣችን በተከፋፈለ ቁጥር ለውጭ ጠላቶች በር እየከፈትን ነው፡፡ ስለዚህ ችግራችንን በሰከነ መንገድና በጥሞና መፍታት አለብን፡፡ አሁን ካለንበት ችግር ለመውጣት ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ ይህ አሁንም ችግሮችን እንድንፈታ ዕድል የሚሰጥ ነው፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

አቶ አበበ፣ ‹‹መንግሥት በመደበኛው የሕግ አግባብ አገር መምራት አልቻልኩም ሲል ዴሞክራሲው መጠበቅ አለበት፡፡ የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ ሀብት የማፍራት፣ ወጥቶ የመግባት መብቶች መረጋገጥ አለባቸው፡፡ እነዚህን ለማረጋገጥና ወደ ቀድሞ መልካቸው ለመመለስ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ተገቢ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአንድ አገር በሚታወጅበት ወቅት የአገር ኢኮኖሚ፣ ገጽታ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝምን ክፉኛ እንደሚጎዳ ጠቁመው፣ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ከግምት መግባት ይገባቸው እንደነበር አቶ ልደቱ ተናግረዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ሞላ ዘገዬ አሁን አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምታውጅበት ጊዜ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደ መብት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በአገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ሁኔታዎች ተሟልተዋል ወይ?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡

አቶ ሞላ ዜጎች ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንደሆነ ጠቁመው ይህ በሚሆንበት ወቅት በሰው ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ግን ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጅ ይልቅ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ኃላፊነት የተሰጠው ፖሊስ በመደበኛው መንገድ ችግሩን መቅረፍ ይችል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ከፖሊስ አቅም በላይ የታጠቀና የተደራጀ ኃይል የለም፡፡ አላየሁም፡፡ መንግሥትም ይህን ሲናገር አልሰማሁም፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ተገቢነቱ አይታየኝም፤›› ብለዋል፡፡

አገሪቱ ወደዚህ ቀውስ ልትገባ የቻለችው በመልካም አስተዳደር በአቅም፣ በችሎታ፣ በፈቃደኝነትና ውሳኔ በመስጠት ዕጦት መሆናቸውን አቶ ሞላ ጠቁመዋል፡፡ ዜጎችን እያግባባ፣ እያስተባበረ፣ ጥያቄያቸውን በየደረጃው መልስ እየሰጠ ከእሱ አቅም በላይ የሚሆነውን ደግሞ ሰንሰለቱን ጠብቆ የሚፈታ የፖለቲካ አስተዳደር የለም ብለው እንደሚያምኑም አስረድተዋል፡፡ በዚህ ወቅት በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ መፍትሔ ይሆናል ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል፡፡

አሁን ያለውን የአገሪቱን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም የተለያዩ የመፍትሔ ዕርምጃዎች መውሰድ እንዳለባቸው ተንታኞች አስረድተዋል፡፡ አቶ ልደቱ አሁን የሚታየውን የአገሪቱን ሁለንታዊ ችግር ፈትቶ ዜጎችን በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ ለማድረግ መላ የአገሪቱን ሕዝብ ያሳተፈ ውይይት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የአገሪቱን ችግር በገዥው ፓርቲ ብቻ መፍታት እንደማይቻል አቶ ልደቱ ጠቁመው፣ ሕዝቡን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በማድረግ አገራዊ ውይይት ማካሄድ ተገቢ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ሁለተኛው የመፍትሔ አካል ብለው የጠቆሙት ጉዳይ፣ የችግሮችን ምንጭ በጥልቀት መዳሰስና አምኖ መቀበል እንደሚገባ ነው፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ የፌዴራል አደረጃጀቱና የፕሮፓጋንዳ ሥልቱ መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

አቶ ልደቱ በአገሪቱ የተከሰተውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም ገለልተኛ የሆነ የሪፎርም ኮሚሽን መቋቋም አለበት ይላሉ፡፡ ‹‹ይህ ኮሚሽን በሕጋዊ መንገድ በአዋጅ መቋቋም አለበት፡፡ ሁላችንም የሚወክል መሆን አለበት፡፡ ኮሚሽኑ ሁለት ኃላፊነቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ የፖለቲካ ቀውሱን ሊያስታርቅ የሚችል ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ የመፍጠር ተልዕኮ ሊኖረው ይችላል፡፡ ሁለተኛው አሁን ያሉትን የዴሞክራሲ ተቋማትንና ሕጎችን መፈተሽና ማሻሻል፣ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ የሆነ የፖለቲካ ምኅዳር በመፍጠር ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ፣ ኮሚሽኑም ዕድሜው በሕግ የተወሰነና የሚሠራቸው ተግባራት በሕግ ተዘርዝረው የተሰጡት መሆን ይችላል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

አቶ አበበ ደግሞ የውይይትና የድርድር ፕሮግራሞችን አስፍቶ መቀጠል ተገቢ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡ ኢሕአዴግ በአስቸኳይ የድርጅቱን ሊቀመንበርና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር መሰየም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የተጀመሩትን የዴሞክራሲ ተቋማት በአቅም እንዲጎለብቱ ማድረግም ሌላኛው የመፍትሔ አካል ተደርጎ መውሰድ እንዳለበት አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ሞላ በበኩላቸው በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እመርታ ለማምጣትና የአገሪቱን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ መውሰድ ያለባቸውን መፍትሔዎች ዘርዝረዋል፡፡ አቶ ሞላ የመጀመርያ ዕርምጃ ሊሆን ይገባል ብለው የጠቆሙት ጉዳይ መንግሥት አሁን የጀመረውን እስረኞችን መፍታት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው፡፡ ሁለተኛው መፍትሔ ብለው የገለጹት በአገሪቱ በጠቅላላ ምሕረት ማድረግ ተገቢነት ላይ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩት መንግሥታትም ሆነ በዚህ መንግሥት በተቃራኒ ጎራ ተሠልፈው ለነበሩ ወገኖች ምሕረት ማድረግና አገራዊ ዕርቅ መፍጠር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ሦስተኛው መፍትሔ ብለው የገለጹት ጉዳይ ከመላ የአገሪቱ ሕዝብ ጋር ውይይት ማድረግ ነው፡፡