Skip to main content
x
የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ኢትዮጵያ የተከተለችውን የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜና የገቢ ስሌት ውድቅ አደረገ
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ወልደማርያም (ዶ/ር)

የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ኢትዮጵያ የተከተለችውን የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜና የገቢ ስሌት ውድቅ አደረገ

ጉብኝት ላይ የነበሩ ቱሪስቶች መስተጓጎልና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሥጋቶችን ደቅነዋል

በዚህ ዓመት የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ መንግሥት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታውቆ ነበር፡፡ ይሁንና ይህ ገቢ የተሰላበትን መንገድ ውድቅ የሚያደርጉ ትንታኔዎች ከዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ብቅ ብለዋል፡፡

ዓመታዊ የቱሪዝምና የጉዞ ትንታኔዎችን በማቅረብ ሪፖርት የሚያዘጋጀው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም፣ የኢትዮጵያን የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ወደ 444 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ የሚያደርግ ትንታኔ ያቀረበው፣ በአገሪቱ የቱሪስቶችን ቆይታ መሠረት ባደረገው የትንታኔ መነሻ ነው፡፡ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸው በአማካይ አንድ ሳምንት ወይም ሰባት ቀናት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በአንፃሩ የኢኮሚክ ፎረሙ በበኩሉ ኢትዮጵያን ከሚጎበኘው አብዛኛው ቱሪስት ውስጥ 87 በመቶው የቢዝነስ ወይም የኮንፈረንስ ቱሪስት በመሆኑ ሰባት ቀናት የሚቆይበት አግባብ የለም በማለት፣ ይልቁንም የኮንፈረንስ ቱሪስቶች አማካይ የቆይታ ጊዜ ከሁለት ቀን እንደማይዘል አስቀመጧል፡፡ ቢበዛ ሦስት ቀናት እንደሚቆዩ ግምቱን አስቀመጧል፡፡

በዚህ መሠረት ሲሰላ የዘንድሮው ስድስት ወራት ገቢ ወደ 440 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከዚህም ዝቅ ሊል የሚችል አኃዝ በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ተጠቅሷል፡፡ በአንፃሩ እንደ ጊዜው ሁኔታ የሚለዋወጠው የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ በአሁኑ ወቅት አማካዩ ሰባት ቀናት መሆኑን መንግሥት አስቀምጧል፡፡ ይልቁንም በእነዚህ የቆይታ ጊዜያቸው ቱሪስቶች ምን ያህል በቀን ወጪ ያደርጋሉ፣ ለሚያስፈልጋቸው አገልግሎት በቀን በአማካይ ያወጣሉ ተብሎ የሚታሰበው ከ250 ዶላር አይበለጥም፡፡ ይህ የመንግሥት ወይም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባለሙያዎች የሚያስቀምጡት ግምታዊ የወጪ መጠን ነው፡፡ በመሆኑም በ2010 ዓ.ም. መጀመርያው መንፈቀ ዓመት ኢትዮጵያን የጎበኙት ቱሪስቶች ቁጥር 465 ሺሕ ሲሆን፣ በሚኒስቴሩ ግምት በቀን 250 ዶላር ወጪ የሚያደርጉና ሰባት ቀናት የሚቆዩ ከሆነ፣ የእነዚህ አኃዞች ብዜት የሚያስገኘው 814 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ነገር ግን በ16 ቀናት ቆይታ ሲሰላ ግን 1.86 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይገኛል ማለት ነው፡፡

የገቢ ሥሌቱ መነሻዎች አነጋጋሪ ቢሆኑም፣ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ባስቀመጠው ሥሌት መሠረት ከ465 ሺሕ ቱሪስቶች ውስጥ 87 በመቶው ወይም ለ404 ሺሕ የሚልቁት የኮንፈረንስ ቱሪዝም ጎብኝዎች በመሆናቸው የቆይታ ጊዜያቸው በአማካይ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት እንደሚገመት አስቀምጧል፡፡ በዚህ መሠረት የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም አንድ ቱሪስት በአንድ ቀን የኢትዮጵያ ቆይታው 450 ዶላር ወጪ ያደርጋል የሚል ስሌት ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም በሁለት ቀናት አማካይ ቆይታ ከተሰላ (465 ሺሕ ቱሪስት ታሳቢ ተደርጎ) ከ420 እስከ 440 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ መገኘቱን ይጠቅሳል፡፡ በሦስት ቀናት ቆይታ ከታየም 628 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝ አስቀምጧል፡፡

የሚኒስቴሩ ሪፖርት አብዛኛውን ማለትም ከ80 በመቶ በላይ ገቢ የሚያመነጨው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፋሪዎች እንደሆነ ከሚኒስቴሩ የሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ አካባቢዎች በተፈጠረው የመንገድ መዝጋትና የሥራ ማቆም አድማ ሳቢያ በጉዞ ላይ የነበሩ ቱሪስቶች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡ ከኢትዮጵያ አስጎብኝዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ያዕቆብ መላኩ ማረጋገጥ እንደተቻለው ባሌ ጎባ አካባቢ በ14 የአስጎብኝ መኪኖች ለጉብኝት መንገድ 33 ቱሪስቶች፣ ዝዋይና ሻሸመኔ አካባቢ የነበሩ እንደዚሁ 33 ቱሪስቶች ለጉብኝት ወደመረጧቸው ቦታዎች በመጓዝ ላይ ሳሉ በነበረው የመንገድ መዝጋት እንቅስቃሴ መስተጓጎላቸው ታውቋል፡፡ በመሆኑም በመከላከያ ሠራዊት አጀብ ከባሌ አካባቢ ወደ ሐዋሳ ጥቁር ውኃ አካባቢ ከተወሰዱ በኋላ፣ ከሐዋሳ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ትብብር ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን አቶ ያዕቆብ ገልጸዋል፡፡ ዝዋይና ሻሸመኔ አካባቢ የነበሩትም ወደ አርባ ምንጭ በመከላከያ አጀብ እንዲሄዱ ተደርጎ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን መጓጓዛቸው ታውቋል፡፡

ከእነዚህ አካባቢዎች በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ወደ ክልሎች ለመጓዝ ያልቻሉ በርካታ ቱሪስቶችም በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት የተዘጉ መንገዶች እስኪከፈቱ ለመጠበቅ መገደዳቸው ተጠቅሷል፡፡ በግርግሩ ወቅት ጉዟቸውን ሰርዘው ወደየመጡበት አገር የተመለሱ እንዳሉ ሁሉ፣ ሌሎች የነበራቸውን የጉብኝት ጊዜ አጠናቀው የሄዱ እንዳሉና ለመምጣት ቀጠሮ ያስያዙ፣ በግርግሩ ምክንያት ግን ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ዕቅዳቸውን ለመሰረዝና ለማራዘም የተገደዱ በርካቶች ስለመሆናቸውም ይገለጻል፡፡

ይህ በሆነበት ወቅት መንግሥት ለስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱም በአገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ሥጋት አሳድሯል፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት የተቀዛቀዘ የቱሪስት ፍሰት የሚታይበት ወቅት መሆኑን አቶ ያዕቆብ ቢጠቅሱም፣ አገሮች የሚያወጧቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች በመስኩ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ወደፊት የሚጠበቅ ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ጉዳዩን በሚመለከት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያለው ነገር የለም፡፡ ሪፖርተር ለማነጋገር ሞክሮም እንዲህ ያሉ ክስተቶች መፈጠራቸው እንደማይቀር የሚጠቁም ምላሽ አግኝቷል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች በበኩላቸው በየአካባቢው ጉብኝት ላይ ሳሉ መንገድ የተዘጋባቸው ቱሪስቶች ስለመኖራቸው ለሚመለከታቸው የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ጠቁመው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ ባለሥልጣኑ ባህር ዳር ከተማ በነበረባቸው ስብሰባ ተወጥረው እንደነበር ተገልጾላቸዋል፡፡