Skip to main content
x
አንድ በውጭ የሚኖር ተቃዋሚ ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወለላቸው

አንድ በውጭ የሚኖር ተቃዋሚ ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወለላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተርን ሆቴል ቀጥረው እየጠበቁት ነው]

 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር አረፈድኩኝ አይደል?
 • አሥራ አምስት ደቂቃ እኮ አስቀመጥከኝ፡፡
 • መንገድ ተዘጋግቶብኝ ነው፡፡
 • በሌለኝ ሰዓት ከየት አመጣዋለሁ፡፡
 • በጣም ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፣ ከውጭ እንግዶች መጥተውብኝ ነው፡፡
 • የምን የውጭ እንግዳ?
 • አገራችን ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርጉ ናቸዋ፡፡
 • በዚህ ወቅት አገራችን ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶች አሉ?
 • አይ ያው ለረዥም ጊዜ ስንነጋገርበት የነበረና ሲጠና የነበረ ፕሮጀክት ነው፡፡
 • አሁንም ኢንቨስተሮች በመንግሥታችን ላይ እምነት አላቸው ማለት ነው?
 • በሚገርም ሁኔታ እኛም ይኼንኑ ነበር ስንወያይ የነበረው፡፡
 • እና እዚህ ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ?
 • አሁን አሁን እንኳን እነሱን ማሳመን እየከበደኝ ነው፡፡
 • ምኑ ነው የከበደህ?
 • እዚህ ኢንቨስት ማድረግ አይፈልጉም፡፡
 • ለምን?
 • ይኸው ሦስት ዓመት ሙሉ ብጥብጥ ስለነበር እምነታቸውን አጥተዋል፡፡
 • ለዚህች አገር እኮ ይኼ የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ዋነኛ ችግር እየሆነ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እነዚህ ሰዎች ለአገሪቱ ምን ያህል ጥቅም ያለው ፕሮጀክት ነበር ያሰቡት፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ?
 • ባይገርምዎት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ከሁለት ኢንቨስተሮች ጋር ለመሥራት ተስማምተን እንደዚሁ ፈረሰብኝ፡፡
 • ምን ትቀልዳለህ?
 • በኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ሥራ ሊጀምሩ አስበው በፀጥታው ሁኔታ ተደናግጠው ነው የሄዱት፡፡
 • እነሱ እንኳን አይጠቅሙንም፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛ ቱሪስት ኢንቨስተር አንፈልግም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • በየአገሩ እየዞሩ ይጠቅመኛል አይጠቅመኝም ብለው የሚሠሩትን ሳይሆን የምንፈልገው ከእኛው ጋር ሁሉን ነገር የሚጋፈጡትን ነው፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • እነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንደዚህ ዓይነቶቹ ኢንቨስተሮች በየቀኑ ነው እኔ ጋ ቢመጡም ፊት አልሰጣቸውም፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • እነዚህ ወዲያው በልተው ወዲያው መጥፋት ነው የሚፈልጉት፡፡
 • ታዲያ ምን ዓይነቶቹን ነው እኛ የምንፈልጋቸው?
 • ከእኛ ጋር በችግሩም በደስታውም ጊዜ የሚሆኑትን ነዋ፡፡
 • አሁን እኮ ደስታ የሚባል ነገር ጠፍቶ ይኸው ለሦስት ዓመት ችግር ነው የሰማነው፡፡
 • አየህ ሊነጋ ሲል ይጨልማል ስለሚባል ለዚያ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎን በሚኒስትርነት አውቅዎታለሁ፣ በኢንቨስተርነት አውቅዎታለሁ፣ በነብይነት ግን አላውቅዎትም፡፡
 • ከአንተም ጋር ተደፋፈርን ማለት ነው?
 • ኧረ እኔ ለጨዋታ ነው፣ እኔ ለነገሩ ችግር የለብኝም፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ዛሬ ከኢሕአዴግ ጋር እንደ ሠራሁት፣ ነገም ሌላ ከመጣ ከእሱም ጋር መሥራት አይከብደኝም፡፡
 • ምን አልክ አንተ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት እንደዚህ ልታስብ ትችላለህ?
 • ምን ችግር አለው ክቡር ሚኒስትር፣ እኔ እኮ ነጋዴ ነኝ፡፡
 • በዚህ ሥርዓት አይደለም እንዴ ከአፈር ተነስተህ እዚህ የደረስከው?
 • እሱንማ አልክድም ክቡር ሚኒስትር፣ ብዙ ተጠቅሜያለሁ፡፡
 • ታዲያ እንዴት ከሌላ መንግሥትም ጋር ቢሆን መሥራት እችላለሁ ትላለህ?
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ዝግጁ ነኝ ስላሉ እሱንም ማሰቡ አይከፋም ብዬ ነዋ፡፡
 • እኔማ መቼ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን ተቃወምኩ?
 • እና ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ዝግጁ ነዎት?
 • በሚገባ እንጂ፣ እኔን ያስፈራኝ ሌላኛው ሽግግር አይኖርም ብዬ ነው፡፡
 • ሌላኛው ሽግግር ምንድነው?
 • ሰላማዊ የሀብት ሽግግር!

[አንድ በውጭ የሚኖር ተቃዋሚ ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወለላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የእኛ ኪራይ ሰብሳቢ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በቃ አበቃላችሁ እኮ፡፡
 • ምኑ ነው ያበቃው?
 • ተበላችሁ እኮ፡፡
 • ምኑን ነው የተበላነው?
 • ቁማሩን ተበላችሁ፡፡
 • ምን እያወራህ እንደሆነ አልገባኝም?
 • ይኸው ሕዝቡ እስረኛ አስፈታችሁ፣ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሊያስቀይራችሁ ነው፡፡
 • እናንተ ለዚህ ነው ይህችን አገር ለመምራት ብቃቱም፣ አቅሙም የላችሁም የምንለው፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛ እኮ እስረኞቹንም ለመፍታት ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲወርዱ ከተስማማን ቆየን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እጃችሁን ተጠምዝዛችሁ እንጂ ተስማምታችሁ አይደለም፡፡
 • ስነግርህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን መልቀቅ ከፈለጉ ቆይተዋል፤ እኛ እስክንተካቸው ነበር የቆዩት፡፡
 • እናንተማ መቼም እንደማታምኑ አውቃለሁ፡፡
 • ስማ ምንም ይፈጠራል ብለህ እንዳታስብ፡፡
 • እሱንስ እንኳን ይተውት፡፡
 • ማለት?
 • እኔ አሁን ጮቤ እየረገጥኩ ነው፡፡
 • ለምኑ?
 • በቃ ክቡር ሚኒስትር አብቅቶላችኋል፣ እኔም ሻንጣዬን እያዘጋጀሁ ነው፡፡
 • ምን ለማድረግ?
 • አገሬ ለመግባት ነዋ፡፡
 • እስቲ አታስቀኝ?
 • ይኸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይኖራል እያሉ አይደል እንዴ?
 • ዶሮ ብታልም ጥሬዋን አሉ፡፡
 • አገሬ መግባቴ አይቀርም ስልዎት፡፡
 • ለነገሩ ይኼንን ማሰቡ አይከፋም፡፡
 • እንዴት?
 • አንድ ቀን አገራችሁ ትገቡ ይሆናል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ውስጥዎት ያውቀዋል በቅርቡ መሆኑ አይቀርም፡፡
 • በነገራችን ላይ አሜሪካ ጥሩ ቤት አለህ አሉ፡፡
 • እሱንም ትቼው እምጣለሁ፡፡
 • እኔም እዚህ ጥሩ ቤት ስላለኝ አንድ ነገር አስቤ ነበር፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ብንቀያየር ብዬ ነዋ፡፡
 • ምኑን?
 • ቤታችንን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ይደውልላቸዋል]

 • ክቡር ሚኒስትር ተቸገርን እኮ፡፡
 • ምንድነው የተቸገርከው?
 • ምንም ሥራ መሥራት አልተቻለም፡፡
 • ምን ሆንክ ደግሞ?
 • አንዴ መንገድ ተዘግቶ አገር ይታመሳል፡፡
 • ምን ይኼ አዲስ ነገር ነው?
 • ሰላም ነው ብለን ደግሞ ሥራ ስንጀምር በድጋሚ ይታመሳል፡፡
 • ታዲያ ምን ይጠበስ?
 • መንግሥት ምን እየሠራ ነው?
 • ሥራውን እየሠራ ነዋ፡፡
 • ይኸው ንግዱም ቆሟል፣ ሁሉም እንቅስቃሴ ቆሟል፡፡
 • ስማ እኔም ንግዱ ውስጥ ስላለሁ ሁሉን ነገር ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡
 • ታዲያ ትንሽ አይቆጭዎትም?
 • ለዚያ አይደል እንዴ መፍትሔ ለማምጣት ጠብ እርግፍ እያልን ያለነው፡፡
 • ግን ምንም ዓይነት መሻሻል እያየን አይደለም፡፡
 • እንቅልፍ አጥተን ነው እየሠራን ያለነው፡፡
 • የሚመስለው ግን አውቃችሁ የተኛችሁ ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ብትቀሰቀሱ አልሰማም አላችኋ?
 • ሰውዬ ልትጨቀጭቀኝ ነው የደወልከው?
 • እሱማ አንድ ጉዳይ ነበረኝ፡፡
 • የምን ጉዳይ?
 • በአካል ተገናኝተን ነው ማውራት ያለብን፡፡
 • ጫፉን ንገረኛ?
 • መሬት የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ፡፡
 • በዚህ ጊዜም መሬት እየደለልክልኝ ነው?
 • እንዲያውም ማጧጧፍ ያለብን በዚህ ወቅት ነው፡፡
 • ለምን?
 • ነገ ምን እንደሚፈጠር አይታወቅማ፡፡
 • በቃ ይኸው ነው ጉዳይህ?
 • በዚያውም እንኳን አደረሰዎት ለማለት ነው?
 • ፋሲካ ገና አይደል እንዴ?
 • ኧረ ለዓመታዊው በዓላችን ነው፡፡
 • ለምኑ?
 • ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ!

[ክቡር ሚኒስትሩ የፓርቲ ስብሰባ ውስጥ ናቸው]

 • ክቡር ሚኒስትር በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቅ ምን ያስባሉ?
 • የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ትክክል ነው ባይ ነኝ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሌሎቻችንም እንደ አርዓያ ልንከተለው የሚገባ ነዋ፡፡
 • ይኼ ነው ሐሳብዎ?
 • ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ሌላ ነው፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • የሚተካቸው ሰው ማን መሆን አለበት የሚለው ነዋ፡፡
 • እርስዎ ማን ይተካቸው ይላሉ?
 • ሕዝቡ እውነተኛ ለውጥ ነው የሚፈልገው፡፡
 • እሱማ ትክክል ነው፡፡
 • ስለዚህ በእኔ አስተያየት ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከእሳቸው የሚያጥር መሆን አለበት፡፡
 • ምን?
 • ከዚያም ባለፈ መነጽር የማያደርግ ቢሆን ይሻላል፡፡
 • አበዱ ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሕዝቡ እውነተኛ ለውጥ ነው የሚፈልገው ስላችሁ?
 • እና ይኼ ነው እውነተኛ ለውጥ ለእርስዎ?
 • ከቁመናው ባሻገር ራሰ በረሃ ሆኖ የደም ግባት ቢኖረው ይሻላል ባይ ነኝ፡፡
 • ቀጥለው እኔን ምረጡኝ እንዳይሉ?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • የሚመረጠው ሰው እኮ ለቁንጅና ውድድር አይደለም የሚፈለገው?
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • የሚመረጠው ሰው አገሪቷን ከገባችበት ቀውስ ሊያወጣት የሚችል መሪ መሆን አለበት፡፡
 • ለዚያ ነው እኮ ሰውየው እነዚህን ነገሮች ማሟላት ያለበት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ስለጤነኝነትዎ እየተጠራጠርን ነው፡፡
 • እንግዲህ መስማማት ካልቻልን አንድ አስታራቂ ሐሳብ ላቅርብ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • የሚፈለገው መሪ ኢትዮጵያን ወደ አንድነት የሚያመጣ መሆን አለበት፡፡
 • ለዚያ አይደል እንዴ እየተወያየን ያለነው፡፡
 • ስለዚህ በጋዜጣ ማውጣት ነዋ፡፡
 • ምንድነው የምናወጣው
 • የሥራ ማስታወቂያ!