Skip to main content
x
የዋሽንትና ክራር ፈርጡ መላኩ ገላው (1929 - 2010)
ነፍስ ኄር መላኩ ገላው

የዋሽንትና ክራር ፈርጡ መላኩ ገላው (1929 - 2010)

‹‹እኛም አለን ሙዚቃ . . .

መንፈስ የሚያነቃ . . .

በገናችን . . .

መሰንቋችን . . .

ክራራችን . . .

ዋሽንታችን . . .

እምቢልታችን . . . ››

ይህ ዘመን ተሻጋሪው የቀድሞው የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ አስተዋዋቂ ሥራ ሁሌም ይታወሳል፡፡ በተስፋዬ ለማ የተቀናበረውና በኢትዮጵያ ሬድዮ የባህል ሙዚቃ መሰናዶ ማስተዋወቂያ የነበረውን ድንቅ ሥራ ካቀነቀኑት መካከል ባለዋሽንቱና ባለክራሩ መላኩ ገላው ይገኝበታል፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቤተ ኪነጥበባት ወቴአትር (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል) ሲደራጅ ሙያውን 1960 .. አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ባህልና ኪነ ጥበብን የሚደግፍ የቴአትር ቤት ለማቋቋም ጥረት አድርገው ያልተሳካላቸው ትውልደ ግብፃዊው አሜሪካዊ ሃሊም ኤልዳብ፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ፋኩልቲ እስኪቋቋም ድረስ የሚያገለግሉና የጥንቱን ሙዚቃ የሚያውቁ የአገር ባህል ሙዚቃ ጓድ ሲያቋቁሙ፣ አንዱ ተሳታፊ የነበረው መላኩ ገላው ነበረ፡፡ ክራር፣ ማሲንቆ፣ በገና፣ ዋሽንት፣ እምቢልታ፣ መለከት፣ ከበሮ፣ ቶም የተሰኙ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በያዘው ኦርኬስትራው የመላኩ ድርሻ፣ ለዘለቄታው የተጠበበባት ‹‹ሊቅ›› ያሰኘችው ዋሽንቱ ናት፤ እንዲሁም ክራሩ፡፡

ከመጀመርያው ዳይሬክተር ሃሊም ኤልዳብ በኋላ የተተካው ዳይሬክተር አሜሪካዊው የሰላም ጓድ አባሉ ጆን ሲሆን፣ ሦስተኛው ዳይሬክተር ተስፋዬ ለማ (1959 እስከ 1968 ..) የኦርኬስትራው ፈርጥ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ በዘመነ ተስፋዬ 1960 .. የአሜሪካ ሰላም ጓድ አባል ሆኖ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመጣው የሃርቫርድ ምሩቁ ቻርልስ ሳተን ኦርኬስትራውን በአስተዳዳሪነት እንዲመራ መመደቡ አዲስ አቅጣጫን አስገኘ፡፡

ቻርለስ ሳተን 1958 .. ኢትዮጵያ በደረሰ ጊዜ ቀልቡን የገዛው ባህላዊ ሙዚቃ ነበር፡፡ በሙዚቃው መመሰጥ ብቻ ሳይሆን መሰንቆውን ለመማርና ለመጫወት የቻለው በኦርኬስትራው አባል በጌታመሳይ አበበ አማካይነት ነው፡፡ የጌታመሳይ ዱካን ተከትሎ ማሲንቆውን ያነገተው ሳተን፣ ለመጀመርያ ጊዜ 1959 .. ወርኃ መጋቢት እንደ መምህሩ ማሲንቆውን ይዞና የኦርኬስትራው ጭፍራ ሆኖ በአማርኛ ማቀንቀን ያስጀመረው በአሰፋ አባተ ዜማ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ የመላኩ ዋሽንት አለችበት፡፡

‹‹ሸጊዬ ሸጊዬ ሸጊቱ ወጣቱ

ጠጋ ብለሽ ተኚ ወደ ግድግዳው

ከልቤ ላይ ብትሞች የማነው ዕዳው?

ሆይ ናና የአገሬ ልጅ፣ የወንዜ ልጅ …››

ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በአገር ቤት ትርዒቱን በማቅረብ ከመወሰን ተላቆ፣ ባሕር ማዶ እንዲዘልቅ የማመቻቸቱን ዐቢይ ድርሻ በሚወስደው ቻርልስ ሳተን አማካይነት መላኩና ጓደኞቹገረ አሜሪካ ዘለቁ፡፡ በዩኒቨርሲቲው፣ በአዲስ አበባ ሆቴሎች፣ በአሜሪካ ኤምባሲ፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ተወስኖ የነበረው ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ፣ በቻርልስ ሳተንና በአሜሪካ ሰላም ጓድ ጥረት በ1961ዓ.ም. በዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ በመካከለኛው ምዕራብ ጥግ እስከ ምሥራቅ ‹‹ ብሉ ናይል ግሩፕ›› (የዓባይ ልጆች) በሚል መጠሪያ 20 ከተሞች ማንሃታንስን፣ ታውንሆልንና ኢድ ሱሊቫን ሾውን ጨምሮ ትርዒቱን አቅርቦ አድናቆትን አትርፏል፡፡

አብረው ከዘለቁትና ጥበባዊ ማዕዳቸውን ለታዳሚዎች ካቋደሱትና ባህላዊውን ሙዚቃ ካስተዋወቁት አንዱ መላኩ ነበር፡፡

‹‹እኛም አለን ሙዚቃ

መንፈስ የሚያነቃ

ክራራችን፣

ዋሽንታችን …›› እያለ የባህል መሣሪያዎቹን ሲያስተዋውቅ የዋሽንቱ ጌታ (ማስተር) መላኩ ገላው ነበረበት፡፡

የእነ መላኩ ሥራዎች 1962 እና 1965 ..  ‹‹ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ›› በሚሉ በሁለት አልበሞች ተለቋል፡፡ የመጀመርያ ‹‹ ብሉ ናይል ግሩፕ›› የሚል ንዑስ ርዕስ ነበረው፡፡ የኦርኬስትራው ጉዞም ናሽናል ጂኦግራፊክ ባዘጋጀው ‹‹Ethiopia: The Hidden Empire (1970)›› ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ተካትቷል፡፡

1968 .. ለኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ገዳ (የገድ ዓመት) አልነበረም፡፡ የደርግ ሥርዓት መመሥረቱን ተከትሎ ኦርኬስትራው ታገደ፡፡ በርካቶቹ ሙዚቀኞች ወደ ተለያዩ ቡድኖች አመሩ፡፡ መላኩም አስተማሪነቱን እስከ ዘመነ ጡረታው ቀጥሎበታል፡፡

በኢትዮጵያ ሦስተኛ ሚሊኒየም ዋዜማ፣ የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በሪል ኦዲዮ ቴፕ ተቀርፆ የነበረው ነባር ሥራም ወደ ኦዲዮ ሲዲ በአንድሪው ሎረንስ አማካይነት ተገልብጦ፣ በቡዳ ሙዚክ ኢትዮፒክስ በኩል በአውሮፓና በአሜሪካ 2000 .. መሠራጨቱን የእነ መላኩ ገላው ሥራን ሕያው አድርጎታል፡፡

ዝነኛው ዋሽንተኛ መላኩ መግነን የጀመረው በ1960ዎቹ መጀመርያ በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ጥበባዊ ሥራውን በምልዐት በማከናወን ብቻ አይደለም፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ለ28 ዓመታት በባህላዊ ሙዚቃ በተለይ በክራርና ዋሽንት አስተማሪነት ዘልቋል፡፡ ከተማሪዎቹ መካከል ታዋቂው ስለሺ ደምሴ (‹‹ጋሽ አበራ ሞላ››) ይገኝበታል፡፡  

እነ ጥላሁን ገሠሠ፣ ጌታመሳይ አበበ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ሒሩት በቀለ፣ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እና ሌሎች ስመጥር ድምፃውያንን በዋሽንትና በክራር በማጀብም አሻራ አኑሯል፡፡

በ1988 ዓ.ም. መኖሪያውን በአሜሪካ ሲያደርግ ከሙዚቃው አልተለየም፡፡ ተስፋዬ ለማ  የኢትዮጵያን ባህልና ጥበብ ለማስተዋወቅ ባቋቋማቸው ማዕከልና ሙዚየም ተግባር ውስጥ የመላኩ አስተዋጽዖ ምትክ እንዳልነበረው ይወሳል፡፡  የባህል ሙዚቃ መሣሪያን፣ ክራርና ዋሽንትን ከማስተማር ባሻገር ከቀደምቱ የሙዚቃ አጋሮቹ ቻርልስ ሳተን፣ ተስፋዬ ለማና ጌታመሳይ አበበ ጋር በመሆን ‹‹ዞሮ ገጠም›› የተሰኘውን አልበም ለማሳተም በቅቷል፡፡

‹‹የሽምብራ ጥርጥር የዛፎቹ ፍሬ

የትም የትም ዞሬ ትዝ አለኝ አገሬ›› የሚለውን የሙዚቃ ድርሰት ለባልንጀራው ጌታመሳይ አበበ መስጠቱም ይታወሳል፡፡

ከኦርኬስትራ ኢትዮጵያ የቀድሞ አባላት መካከል ከዓመታት መለያየት በኋላ አራቱ ዳግም በዋሽንግተን የተገናኙት 1998 .. ነበር፡፡ 1950ዎቹ መጨረሻና 1960ዎቹ መጀመርያ የተጫወቷቸውን ዳግም ‹‹ዞሮ ገጠ›› በሚል ርዕስ በናሆም ሪከርድስ አማካይነት ያወጡት መላኩ ገላው፣ ጌታመሳይ አበበና ተስፋዬ ለማና ቻርልስ ሳተን ናቸው፡፡ ከዋሽንግተን ሌላ ከአሥር ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ራስ መኰንን አዳራሽ በሚያዝያ 2000 .. መመረቁ ያኔ ‹‹ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ እንደገና›› መሰኘቱ በሪፖርተር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በተስፋዬ ለማ ዳይሬክተርነት ለታተመው የኢትዮጵያ የባህላዊ ሙዚቃዎች ስብስብ አልበም ዞሮ ገጠም ብለው የሰየሙት፣ ዞረው መገናኘታቸውን ለመዘከር እንደነበረ ከአልበሙ ሽያጭ የተገኘው ገቢም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም እንቅስቃሴ እንዲውል በወቅቱ ማበርከታቸው ይታወሳል፡፡

በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ከአባቱ ከአቶ ገላው ተክሌና ከእናቱ ከወ/ሮ (በኋላ እማሆይ) ትኩነሽ ተሰማ በላስታ ላሊበላ ከተማ የተወለደው መላኩ፣ ባለትዳርና የሰባት ልጆች አባት ሲሆን፣ 12 የልጅ ልጆችንም አይቷል፡፡ 

የዋሽንትና የክራር ፈርጡ መላኩ ባደረበት ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በአርሊንግተን ቨርጂንያ ከተማ የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በ81 ዓመቱ አርፏል፡፡ ሥርዓተ ቀብሩም የካቲት 12 ቀን በአዲስ አበባ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

የዋሽንቱና የክራሩ መላክ መላኩ ተከተተ፡፡ ተስፋዬ ለማን ጨምሮ ቀድሞት በሞት የተለየው የማሲንቆው ጌታ ጌታመሳይ ያቀነቀለለት ሥራውን ‹‹የሽምብራው ጥርጥር የዛፎቹ ፍሬ የትም የትም ዞሬ ትዝ አለኝ ሀገሬ›› እንዲል እሱም በስደት ኖሮና ዞሮ ማረፊያው በአገሩ ሆነ፡፡