Skip to main content
x
ሥጋት የተደቀነበት ጃንሜዳና 35ኛው ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ

ሥጋት የተደቀነበት ጃንሜዳና 35ኛው ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ

ከአዲስ አበባ ስፖርት ማዘውተሪያዎች ከቀደምቱ አንዱ የሆነው ጃንሜዳ በበዓል ማክበሪያነትም ይታወቃል፡፡ ‹‹ትልቅና ሰፊ ሜዳ›› የሚል ፍች ያለው ጃንሜዳ በመዝገበ ቃላት እንደተገለጸው የንጉሥ ሜዳ፣ ንጉሡ የጦር ሠራዊት ሰልፍ የሚያይበት ከባለሟሎቹ ጋር ጉግስ የሚጫወትበት ሜዳ ነው፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በ25 ሺ ካሬ ሜትር የተቀየሰው ጃንሜዳ፣ በተለይ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ሩጫ ውድድሮችና የገና እና እግር ኳስ ጨዋታዎችን እንዲሁም የሙዚቃ ድግሶች እየተካሄዱበት እስከዚህ ዘመን ድረስ ዘልቋል፡፡ እንደ ስሙ ትልቅና ሰፊ ሜዳነቱን የሚገዳደር ነገር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አጋጥሞታል፡፡

በስፖርትና በሃይማኖታዊ ክንውኖች መናገሻነቱ የሚታወቀው ጃንሜዳ ዙሪያውን በግንባታ መታጠር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከዚህ በመነሳትም እንደ ሌሎቹ የአዲስ አበባ ሜዳዎች ጃንሜዳም በስም ብቻ የሚታወስበት ጊዜ እንዳይመጣ ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡

ጃንሜዳ ከታሪካዊነቱና ካለው ማዕከላዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ወሳኝ ድርሻ አኳያ በዙሪያው የሚካሄዱት ግንባታዎች መንግሥት በአግባቡ ሊከታተለው የጃንሜዳና ሕልውናንም እንዲያስጠብቅ ዘመናዊነትን አላብሶ ለትውልድ እንዲያቆየው የሚጠይቁ ድምፆች እየተደመጡ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዘንድሮ ለ35ኛ ጊዜ በዚሁ ሥፍራ እሑድ የካቲት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ዓለም አቀፍ የጃንሜዳ አገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር ይደረጋል፡፡ በስያሜው መሠረት በውድድሩ የሚሳተፉ ከተለያዩ አገሮች የመጡ አትሌቶች ባይኖሩም ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ ከክለቦችና ከማሠልጠኛ ማዕከላት፣ በግል ጭምር በአጠቃላይ 966 ተወዳዳሪዎች ታድመውበታል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሐሙስ የካቲት 15 ቀን በኢትዮጵያ ሆቴል በሰጠው መግለጫ 35ኛው የጃንሜዳ ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ውድድር በወጣት ሴቶች ስድስት ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ወንዶች ስምንት ኪሎ ሜትር በአዋቂ ሴቶችና ወንዶች አሥር ኪሎ ሜትር እንዲሁም በድብልቅ ጾታ ስምንት ኪሎ ሜትር ይደረጋል፡፡

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ለሚወጡ አትሌቶች ለአዋቂ ሴቶችና ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር ከ40ሺ እስከ 8ሺ ብር በድምሩ 13ሺ፣ ለወጣት ወንዶች ስምንትና ሴቶች ስድስት ኪሎ ሜትር ከ20ሺ እስከ 4ሺ ብር በድምሩ 66ሺ ብር ለድብልቅ ሪሌ ከ10,ሺ እስከ 3ሺ ብር በድምሩ 36ሺ ብር፣ ከ50 ዓመት በላይ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለሚወጡ በድምሩ 1ሺ በአጠቃላይ ለውድድሮቹ 323ሺ ብር ፌዴሬሽኑ አዘጋጅቷል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች እንዳብራሩት፣ የዘንድሮው የጃንሜዳ ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ከወትሮው የተለየ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ታዋቂና ስመጥር አትሌቶች ማለትም በወንዶች ሙክታር እድሪስ፣ ጌታነህ ሞላ፣ ሁነኛው መስፍን፣ ሙሰነት ገረመው፣ በሴቶች የብርጓል መለሰ፣ ሽቶ ሰዴሳ፣ በላይነሽ ኦልጅራ፣ ለተሰንበት ግደይ፣ ፎቴንና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡