Skip to main content
x

ትውልዱን የጨው ምድር እንዳናወርሰው

ከጂንካ ግርጌ የሚነሳውን የማጎ ብሔራዊ ፓርክ ጫፍ ይዞ በአገሪቱ ደቡባዊ አቅጣጫ የሚጓዝ ሰው፣ ታማ የዱር እንስሳት ‘ጥብቅ’ ሥፍራን ያገኛል፡፡ ባለ ግርማ፣ እርጋታ የረበበት ጥቁሩን የኦሞ ወንዝ ድልድይ እንደተሻገሩ፣ ስንዝር እንኳ ሳይጓዙ ድሮ ድሮ የሚቀበልዎት የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ግዛት ነበር፡፡ አሁን ግዛቱ የኦሞ ስኳር ፋብሪካ በመሆኑ ድልድዩን ሲሻገሩ ፋብሪካውም ከዚያ ጀምራል፡፡

እርግጥ በየትም አገር ቢሆን ድሮ የነበረ ነገር ሁሉ ዛሬም ይኑር ማለት ያስቸግራል፡፡ በእኛ አገር ግን ችግሩ ይሰፋል፡፡ ሁሉንም ነገር ከዛሬ የማስጀመር፣ የትናንቱን የመቀየር አባዜ አለብን፡፡ ተፈጥሮን ከዛሬ ማስጀመር ግን አይቻልም፡፡

ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት የዱር እንስሳቱንና መኖሪያ አካባቢያቸውን ለመጠበቅ ሲባል የኦሞ ፓርክ ተመሠረተ፡፡ ኖረ ኖረና የሆነ ዘመን ላይ ደረሰ፡፡ አቶ ለይኩን አቡኔ፣ የተባሉ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን የቀድሞ ባልደረባ  በቅጽ 7 ቁጥር 1 የመሥሪያ ቤቱ የ‹‹ዱር ለዱር መጽሔት›› ላይ እንግዳ ሆነው ቀርበው ነበር፡፡ በተደረገው ቃለ ምልልስም ትውስታቸውን ገልጸው ነበር፡፡

‹‹ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከባለሟሎቻቸው ጋር በሥፍራው ደረሱ፡፡ ጊዜው 1977 ዓ.ም. ገደማ ነበር፡፡ ሰውየው ጠየቁ፡፡ ‹አገራችን ላይ ድርቅና ረሃብ ተከስቶ እናንተ ይህን ያህል መሬት መያዛችሁ አግባብ ነው?››› ማለታቸውን ያስታውሳሉ፡፡  የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ቺፍ ዋርደን የነበሩት አቶ ለይኩን አቡኔ፣ አጭርና ቅልብጭ ያለ ንግግር ብቻ እንደተናገሩም ይናገራሉ፡፡ ‹‹አገሪቱ የመሬት ችግር የለባትም፡፡ የአስተዳደር ችግር እንጂ፤›› ይህ አጭር ንግግር የፕሬዚዳንቱን ሐሳብ ፈታው፡፡ የኦሞ ፓርክም ልትቆም የነበረችው የልብ ምቱ እንደገና መምታቷን ቀጠለች፡፡ ሰውየው ይህን ለእርሻ የተመኙትን በተፈጥሮ የታደለና የብዝኃ ሕይወት ስብጥር ገነት የሆነውን ምድር በአየር ላይ እየተሽከረከሩ ተመለከቱት፡፡ ምን እንዳሉ ልገምት? ‘ምን ዓይነት ምትኃታዊ አገር ነች? ከቋንቋ በላይ፣ ከጥበብ የላቀ ጥበብ፣ እንዴት ወንዝ ነፍስ ይኖረዋል?

ይኸው በዚህ መንገድ የተጠበቀው ኦሞ ኖረ ኖረና ዛሬ ላይ ደረሰ፡፡ ዛሬን መሻገር ግን ለኦሞ ፈተና ሆኗል፡፡ ኦሞ ቋንቋው ረቂቅ ቢሆንም፣ እንዲህ እንደሚል እገምታለሁ፤ ‹‹መኖር ማለት እንደ አዋሽ ከሆነ ይቅርብኝ. . . ሞት በስንት ጣዕሙ፤›› ማለቱ ይቀራል?

የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ አንዱ የልማትና የጥበቃ አካል መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአንፃሩ ግን ምድር ሁሉ ታርሶ ካልተዘራበት፣ የሚበላው እንስሳ ሁሉ ታድኖ ካልተበላ፣ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ ካልተማገደ ማለት ግን አደጋ አለው፡፡ አግባብም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በመገንባት ላይ ላለው የስኳር ፕሮጀክት እስካሁን ድረስ 1,750 ስኴር ኪሎ ሜትር (ተራራማና ረባዳ ቦታዎችን ሳይጨምር) የሚታረስ ቦታ ለቆለታል፡፡ ወዶና ፈቅዶ፡፡ 80 ኪሎ ሜትር ገደማ ፓርኩን አቋርጦ የሚያልፍ የውኃ ካናል ወይም ቦይ እንዲገነባም መግባባት ላይ ተደርሶ ሥራው እየተሳለጠ ይገኛል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡

ካናሉ የሚገነባው በፌዴራል ውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅትና በደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን አማካይነት ሲሆን፣ ሁለቱም የየራሳቸውን የግንባታ ሒደት ተከትለው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ 80 ኪሎ ሜትር በፓርክ ውስጥ የሚያቋርጠው ይህ ካናል፣ 60 ሜትር ስፋትና ከሁለት እስከ 19 ሜትር አማካይ ጥልቀት አለው፡፡ ከዚህ ካናል እየተቆፈረ የሚወጣው አፈር በፓርኩ ውስጥ በሳራማ ገላጣ ቦታ ላይ ይደፋል፡፡ እስካሁን የተደፋው አፈር ከካናሉ ሁለት መቶ ሜትር ርቀት ካናሉን ተከትሎ በአማካይ በአራት መቶ ሜትር ቦታ ላይ ተከምሯል፡፡ (በተለይም በደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን በመገንባት ላይ ያለው)፡፡ በጨዋ ዓይን ሲታይ ክፋት የሌለው ጉዳይ ቢመስልም ከጥፋት የላቀ ጥፋት መሆኑን ግን መረዳት ይገባል፡፡ የፓርኩ መገለጫ የሆኑት የሳይና እልል ባይ ሳራማና ቁጥቋጣማ ሜዳዎች ሥነ ምኅዳራዊ ለውጥ እንዲያመጡ በማድረግ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ያዛባል፡፡ ቀድሞ የተደፋው አፈር በአፋጣኝ እንዲነሳ በማድረግና ወደፊት የሚካሄዱት ቁፋሮዎች ከፓርኩ ቀጣና ውጭ ባሉ ቦታዎች እንዲደፉ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ካናሉ በሚያልፍበት የፓርኩ ክፍል ካናሉን ሳይጨምር ግራና ቀኝ እስከ ሁለት መቶ ሜትር ቦታ ተመንጥሯል፤ ይኼ ምንጣሮ ለአሠራር እንዲያመች ተብሎ የተሠራ ከፍተኛ ጥፋት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም ከካናሉ ውጭ የሚጠረግ ቦታን አስመልክቶ የቀረበ አንዳችም ስምምነት ባለመኖሩ፡፡ ሕጋዊ ወሰን ባለው ፓርክ ውስጥ ማንኛውም ዓይነት ቁፋሮ ማካሄድ ሕገወጥ ተግባር ቢሆንም እንዳስፈላጊነቱ ለልማቱ ሲባል ጉዳት በማያስከትል መልኩ ቁፋሮ የተፈቀደባቸው ቦታዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከዚህ አልፎ የፓርኩ አስተዳደር ሳያውቀው ቁፋሮ ማካሄድ ይቅር የማያስብል ሥራ ነው፡፡ ይህ ተግባር በፓርኩ በተለያዩ ቦታዎች እየተካሄደ ይገኛል፡፡ 

ካናሉን ለመሥራት ሲባል በፓርኩ ውስጥ የሠፈሩ መንደሮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የካናሉ ሥራ ሲጠናቀቅ እነዚህ መንደሮች ህልውናቸው ያበቃል፡፡ በዚህ ሥፍራ ቋሚ የሆኑ ግንባታዎችን ማካሄድ እንደ ሕጉ ተገቢ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ መንደሮች የቆይታ ሥርዓት ያልተነደፈላቸው በመሆናቸው ከጊዜያዊ መንደርነት ወደ ቋሚ ከተማነት ለማደግ እየታተሩ ይገኛሉ፡፡ በፓርኩ ውስጥ በሚገኙ እነዚህን መሰል መንደሮች ክልሉ የሥራ ዕድል ከፈጠረላቸው ሰዎች ግብር ይሰበስባል፡፡ ሥራ ፈጠራውም ሆነ አግባብ ያለው ግብር መሰብሰቡ ክፋት ባይሆንም እንደ አሠራር ግን ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው፡፡ ፓርኩ የሚተዳደረው በፌዴራል መንግሥት እስከሆነ ድረስ ሥራ ፈጠራው መካሄድ ያለበት በፓርኩ አስተዳደር ሥር ነው፡፡ መንደሮቹ የቆሻሻ አያያዝ ሥርዓት የላቸውም፡፡ በተለይም ለሥነ ምኅዳሩ አደጋ ያላቸው እንደ ፕላስቲክና ኬሚካል ዓይነት ቆሻሻዎች እንዴት እንደሚወገዱ የሚያስረዳ ምንም ዓይነት ደንብ የለም፡፡ ስለሆነም በርካታ ቆሻሻዎች በየቦታው ተወግደው ይታያሉ፡፡ መንደሮቹም ሆኑ ሌሎች በፓርኩ ውስጥ የሚሠሩ ማንኛውም ሥነ ምኅዳራዊ ለውጥ የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች አገልግሎታቸው ሲጠናቀቅ መስተካከል በሚገባቸው ልክ መታከም አለባቸው፡፡ ቀደም ሲል መንገድ ሥራ ሲሠሩ የነበሩ ድርጅቶች ሥራቸውን አጠናቀው ሲወጡ በሥርዓት የተመራ አካሄድ ሳይከተሉ መውጣታቸው ይታወቃል፡፡   

እርግጥ ነው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አምስት የሚደርሱ 60 ሜትር ስፋት ያላቸው የዱር እንስሳት የሚሻገሩባቸው ድልድዮች በካናሉ ላይ ይገነባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው የካናሉ ክፍል ለዱር እንስሳቱ አደጋ እንዳይሆን በምን መልኩ ሊከለል እንደሚገባ የሚያስረዳ አሠራር የለም፡፡ ይህ የአሠራር ክፍተት ፓርኩን ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክቱ ላይም እክል መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ፓርኩና የሸንኮራ እርሻው በቀጥታ የሚገናኙ ሲሆን፣ ወደፊት የዱር እንስሳቱ በእርሻው ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የማይጠረጠር ሀቅ ሆኖ እያለ ይህንን ወደ ፊት ሊከሰት የሚችል ችግር እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል ከመነጋገር የዘለለ ተግባራዊ ዕቅድ አልተቀመጠም፡፡ በፓርኩ ውስጥ በስምምነት በተፈቀደ ቦታና ቅርብ ርቀት ላይ አራት አዳዲስ መንደር ምሥረታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ በክልሉ አርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ የሚሰባሰቡት ነዋሪዎችና የዱር እንስሳቱ በምን መልኩ ጤናማ መስተጋብር ሊኖራቸው እንደሚችል ቆም ብሎ ያሰበ አካል አለመኖሩ አሁንም ልብ ሊባል የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ አንበሳ፣ ነብርና ጎሽ ያሉ የዱር እንስሳት ከእርሻ ሠራተኞችና መንደር ሠፋሪዎቹ ጋር ግጭት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ አሁን ዕቅድ ያልተነደፈለት ይህ ሁኔታ ሲከሰት እንስሳዎቻችሁን ያዙልን እርሻችንን አጠፉ ልንባባል ነው?

ፕሮጀክቱ በሚገነባበት በዚህ ጊዜ የሚታዩ ችግሮች አልታጡም፡፡ በርካታ ማሽኖችና የተለያዩ መኪኖች በፓርኩ ውስጥ በፍጥነት እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉ የዱር እንስሳት ግጭት ተከስቷል፡፡ ይህ ሒደት እንዲታረም አንዳንድ ውሳኔዎች የተላለፉ ቢሆንም፣ ተግባራዊ ባለመደረጉ ችግሩን መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ አይደለም በፓርክ ውስጥ በከተሞች ውስጥ እንኳ የተሽከርካሪዎች የፍጥነት ወሰን የተገደበ ነው፡፡ በፓርኩ ውስጥ የሚኖረው እንቅስቃሴ የፍጥነት ወሰንና የሰዓት ገደብ ሊበጅለት ይገባል፡፡

የተፈጥሮ ምኅዳር ቀጣና መጠበቅን ከወቅታዊ ችግሮች ጋር በማወዳደር ፋይዳ ቢስ አድርጎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋን መጠበቅ ከጀመረች ከመቶ ዓመት በላይ ሆኗታል፡፡ ዘመናዊው የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ደግሞ ግማሽ ምዕተ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ እስካሁን ድረስ ግን ‹‹ከባልሽ ባሌ ይበልጣል›› ዓይነት ነገር ሆኖ ዘርፉ ትኩረት እንደተነፈገ ይገኛል፡፡  ኢትዮጵያ ኦሞ ብሔራዊ ፓርክን የመጠበቅና የማልማት ሥራ ለመሥራት የማንም አካል ግፊትና ማስፈራሪያ አያስፈልጋትም፡፡ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ለአገሪቱ ከሀብት በላይ ነው፡፡ የአምስቱ ትላልቅ አጥቢዎች አንበሳ፣ ነብር፣ ጎሽ፣ ዝሆንና ቀጭኔ መገኛ ነው፡፡ በዓለማችን ህልውናው አደጋ ላይ የወደቀው ተኩላ በዚህ ፓርክ በብዛት ይገኛል፡፡ መጋላ ቆርኬ፣ ውድንቢ፣ የሜዳ አህያ፣ የሜዳ ፍየል፣ ዝሆንና ሌሎች በርካታ እንስሳት ዝርያዎች በከፍተኛ ቁጥር ይገኛሉ፡፡ ማራኪ የብዝኃ ሕይወት ስብጥርም ይዟል፡፡ ከአምስት በላይ በጣም ሰፋፊ ሳራማ ሜዳዎች፣ ቁጥቋጧማና ጥቅጥቅ ደኖች የተሸፈነ ነው፡፡ አስደናቂ ሥነ ምኅዳር የያዘው ይህ ፓርክ ሲመሠረት 4,068 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት የነበረው ሲሆን፣ ኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክትና የመንደር ማሰባሰብ ሥራውን የወሰዱ መሬት ሲቀነስ 2,318 ካሬ ኪሎ ሜትር እንደሚቀር ይገመታል፡፡ የማኅበረሰቡ ልማት ተጠቃሚ መሆን ለፓርኩም አወንታዊ ፋይዳ እንዳለው ይጠበቃል፡፡ ቀሪው የፓርክ ቀጣና በአግባቡ ክለላ ተደርጎለት ሌሎች መጋፋቶች የማይመጡበት ከሆነ ተስፋ ይኖረዋል፡፡ የተነሱት ነጥቦች ከግምት ውስጥ ገብተው፡፡

ኦሞ ብሔራዊ ፓርክን ለመጠበቅ ባለፉት 50 ዓመታት እጅግ የሚባል መስዋዕት ተከፍሏል፡፡ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሰው ሕይወትም ጠፍቷል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት የአንድ ወገን ድርሻ ወይም ችሮታ አይደለም፡፡ አንዱ የሚበለጽግበት ሌላው የሚሞትለት ጉዳይም ሊሆን አይገባም፡፡ በጋራ የምንቆምለት ሀብት እንጂ፡፡ ስለሆነም መተንፈስ እስካላቆምን ድረስ በየትኛውም ቦታ ስለምትቆረጥ እያንዳንዷ ዛፍ ሁላችንንም ሊመለከተን ይገባል፡፡

(ዳንዮት ዓለምሰገድ፣ ከአዲስ አበባ)