Skip to main content
x

ኢትዮጵያዊ አገር ወዳድነት በምክንያታዊ አስተሳሰብ

በአብዱል መሐመድ

ጠቅላይ ሚኒትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከራስ በላይ የአገርን ጉዳይ ባስቀደመ መንፈስ፣ ለወደፊቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጥረታችን ከፍተኛ የአርዓያነት ፋይዳ ባለው መንገድ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ወስነዋል፡፡ ይህ የአገር ወዳድነት ዕርምጃ ወደ በጎ አቅጣጫ የመሸጋገር ተስፋችን ከፍተኛ ስለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ውድ ሕይወታችንን ሳይቀር ለአገር ጥቅምና ህልውና መስዋዕት የማድረግ የጎላ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ እርግጥ ነው ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲሉ የግል ፍላጎትና እምነታቸውን መስዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ፖለቲከኞችን ለማየት ግን አልታደልንም፡፡ ዛሬ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ግላዊና ቡድናዊ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ገትተው ከገባንበት የፖለቲካ ቀውስ ሊያወጡን የሚችሉ ሆደ ሰፊና አገር ወዳድ ፖለቲከኞች ያስፈልጉናል፡፡

የዓደዋ ድል በዓልን ስናከብር ሊታወሰን የሚገባው እውነትም ለአገር ወዳድነት ሲሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውን ሳይለዩ የተሳተፉባቸው ሁነቶች ታላቅ ታሪክ እንደሆኑ ነው፡፡ አገራዊ ድሎቻችን የሁላችንም ናቸው፡፡

ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ የአገራችን ገጽታ በብዙ መንገድ ተቀይሯል፡፡ የዘመኑ ትውልድ በአንፃራዊ ሰላምና የልማት ዕድገት ውስጥ የመኖር ዕድል አግኝቷል፡፡ ይህ ሁሉ በራሱ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ቢሆንም ወጣቱ ትውልድ እየመጣ ባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ተስፈኛ ከመሆን አልፎ የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ ሆኗል ማለት አይቻልም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ የብዙ ደሃ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የበቃ፣ ከዕድገቱ ጋር ተያይዞ የመጣው የመሠረተ ልማት አውታርም በአንፃራዊነት መላው አገሪቱን ያዳረሰ ቢሆንም፣ በዚያው መጠን ሥር ለሰደደ ሙስና ለከፍተኛ የዜጎች የኑሮ ደረጃ መራራቅና ከዚያም አልፎ ፈርጀ ብዙ ለሆኑ ማኅበራዊ ቀውሶች ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይም ዕድገቱን ተከትለው እየተስፋፉ በመጡ የአገራችን አነስተኛ ከተሞች የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ዕድሜአቸው ጎጆ ለመውጣት ቢደርስና የኮሌጅ ትምህርት ተከታትለው ለመመረቅ ቢበቁም፣ በአገሪቱ እየተፈጠረ ያለው የሥራ ዕድል ሊያረካቸው የሚችል አልሆነም፡፡ እነዚህ አነስተኛ ከተሞች የዜጎች ገቢ በፍጥነት እየጨመረ የመጣባቸው ከመሆናቸው አኳያ የሥርዓቱ ደጋፊ መሠረቶች እንደሚሆኑ ሲጠበቅ፣ በተቃራኒው የሥርዓቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መናኸሪያ ሲሆኑ ታይቷል፡፡

በእነዚህ ከተሞች በሥርዓት ላይ እያመፁ የሚገኙ ወጣቶችም ተኮትኩተው ያደጉበትን ፕሮፓጋንዳ መሠረት አድርገው የተቃውሞ ድምፃቸውን የሚያስተጋቡበት፣ በዋናነት በብሔረሰባዊ ማንነታቸው ተሰባስበው ነው፡፡ የሥርዓቱ የ26 ዓመታት የፕሮፓጋንዳ ቅኝት በዋናነት ልዩነትና ብሔረሰባዊ ማንነት ላይ ያተኮረ ስለነበር፣ የእነዚህ ወጣቶች ፍላጎትም በልማት ተስፋ ብቻ እንደሚሟላ በመታሰቡና አገራዊ አስተሳሰባቸውና ዕይታቸው እንዲያድግ ስላልሠራን፣ የሥርዓቱ አጋዥና አጋር ከመሆን ይልቅ የሥርዓቱ ባላንጣ የሚሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ እነዚህ የአገሪቱ ዋና ባለቤት የሆኑ ወጣቶች (ወደ 70 በመቶ የሕዝብ ቁጥር ይወክላሉ) ሐሳባቸው በአግባቡ የሚደመጥበት መድረክ በበቂ ሁኔታ ስለሌለ፣ ፖሊሲ በማውጣትና በመተግበር ሒደት ላይ የጎላ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ዕድል ስለሌለ፣ ከሁሉም በላይ በአገሪቱ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ እስከ አመራር ሰጪነት የሚያበቃ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ስላልተደረገ፣ ሥርዓቱን ለመደገፍ ሳይሆን ለማፍረስ የሚፈልጉ ሆነዋል፡፡ ወጣቶቹ የእያንዳንዱን ለውጥ ጥቅምና ጉዳት የሚመዝኑት ከአጠቃላይ አገራዊ ጥቅም አኳያ ሳይሆን፣ ከአካባቢያቸውና ከብሔረሰባዊ ማንነታቸው ጋር አያይዘው ስለሆነ ከዜግነትና ከኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ጋር የተያያዙ የጋራ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው የመወያየት ዕድል የሌላቸው ሆነዋል፡፡

ይህ እውነታ በትውልዱ ዙሪያ በብሔረሰባዊ ማንነትና በኢትዮጵያዊነት መካከል ሚዛን የጠበቀ አስተሳሰብ እንዲኖር ምን ያህል ከፍተኛ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀን የሚያሳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ለፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት በአገራችን የመጣው የኢኮኖሚ ለውጥ በጣም አስደሳችና አማላይ ቢሆንም፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱ የሚያሳካውን ግብ በተመለከተ ቆም ብለን ለማሰብ የምንገደድበት ወቅት ላይ እንደምንገኝ ይሰማኛል፡፡ በአጭር ጊዜ የሚለወጥ ባይሆንም በምን ሁኔታ ሁሉም ዜጋ የጋራዬ ነው ብሎ የሚያምንበት ፍትሐዊ ልማት ማምጣት እንደምንችል አገራዊ ውይይት በፍጥነት መጀመር አለብን፡፡

ለዘመናት ባሳለፍነው የመንግሥት ታሪክ ስንሰፋና ስንጠብ፣ ስንናከስና ስንለያይ፣ ስንጠናከርና ስንዳከም ኖረናል፡፡ በቅርብ ዘመን ታሪካችን ማለትም በንጉሡና በደርግ ዘመን ኢትዮጵያዊ ማንነት የገዘፈ ቦታ አግኝቶ በአንፃሩ ልዩነትና ብሔረሰባዊ ማንነት ቦታ ያጣበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም፣ ይህንን ሚዛን ያልጠበቀ ግንኙነት የማስተካከል ዕድል በኢሕአዴግ ዘመን አግኝተናል ማለት ይቻላል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን ኦሮሞ ሆኖ፣ አፋር ሆኖ፣ ሶማሌ ሆኖ፣ ወዘተ. በኢትዮጵያዊነት የመኩራት ዕድል ተገኝቷል፡፡ በየክልሉ ራስ ገዝ የሆኑ የሥልጣን ማዕከላት መፍጠር የቻሉ ብሔር ብሔረሰቦች በየራሳቸው ውስጥ ቀላል የማይባል የፖለቲካ ልሂቃን መፍጠር ችለዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ከፍተኛ ውጤትና ስኬት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ ረገድ እየመጣ ያለው ለውጥ ሚዛን የሳተበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑንም እያየን ነው፡፡ በሒደት ኢትዮጵያዊ አብሮነታችን ቦታ እያጣ ስለመጣ የፖለቲካ ታሪካችን ዋነኛ ትኩረት በብሔረሰባዊ ማንነት ላይ ያተኮረ ከመሆኑም በላይ፣ በእያንዳንዱ ለውጥ የእኔ ብሔር ምን ይጠቀማል? ወይስ ምን ይጎዳል? የሚለው ጥያቄ የበለጠ ቦታ እያገኘ መጥቷል፡፡

ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በራሱ ጎጂ ባይሆንም በጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታችንና በአገራዊ አንድነታችን ላይ ቀላል የማይባል ጥላ አጥልቷል፡፡ በሁለት ክልሎች መካከል ያለ ድንበር (ወሰን) አስተዳደራዊ ወሰን መሆኑ እየተረሳና እንደ አገራዊ ድንበር እየተቆጠረ የ‹‹ውጡልን›› ጥያቄ ሲያስከትል እያየን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ተከትሎም ደም መፋሰስ እየተከሰተ ነው፡፡ የአስተሳሰብ ዕድገት እንዲያመጡ በምንጠብቅባቸው ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሳይቀር በታሪካችን ዓይተናቸው የማናውቃቸው ዓይነት ብሔር ተኮር ግጭቶች (እስከ ግድያ የደረሱ) ማየት ጀምረናል፡፡ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን የዚህ ዓይነት ችግር ሰለባ ከሆኑ የአገራችን የወደፊት ዕድል ወደ ምን ዓይነት አደገኛ አዝማሚያ እየተገፋ እንደሆነ ያሳዩናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አደጋ መከላከል፣ ዜጎች በሰላምና በመቻቻል አብረው እንዲኖሩ ኃላፊነት ያለባቸው ባለሥልጣናትና ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ እየታየ አይደለም፡፡

በክልልና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ተናቦ መሥራት  እየቀረ ከመሆኑም በላይ፣ አሳሳቢ ውጥረቶችና ግጭቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ በፖለቲካ ኃይሎች መካከልም ሆነ በሕዝቡና በመንግሥት መካከል የተካረረ የፖለቲካ ውጥረት እንዲኖር ብልሹ የፕሮፓጋንዳ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ዓይነት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መገኘታችን፣ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎቻችንንም ሆነ አደረጃጀቶቻችንን ቆም ብለን እንድንፈትሽ የሚያስገድዱን ይመስለኛል፡፡ የማንኛውም ሰው የግልም ሆነ የቡድን ማንነት በታሪክ ሒደት ውስጥ የሚፈጠርና የሚቀየርም ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ከነበርንበት ዝቅተኛ የማኅበረሰብ ኢኮኖሚ ሁኔታ አኳያ የነበረን ማንነት፣ አሁን ራሱ ኢሕአዴግ ባመጣው የለውጥ ሒደት ጭምር በብዙ መንገድ የተቀየረ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከወቅቱ ማንነታችን ጋር የሚጣጣም የተሃድሶ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅብናል፡፡ ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያዊነትና በብሔረሰባዊ ማንነት፣ በማዕከላዊነትና በሥልጣን ክፍፍል፣ በአንድነትና በልዩነት መካከል ሚዛን የጠበቀ ሕግና ሥርዓት እንዲኖረን የሚያስችል አገራዊ የውይይትና የድርድር ሒደት ውስጥ በፍጥነት መግባት ይጠበቅብናል፡፡ ውጤታማ አገር ወዳድነት የሚገኘው ከከረረ አመለካከት ሳይሆን፣ ከሚዛናዊ አስተሳሰብ እንደሆነ ተረድተን ሁላችንም ከቆምንበት የጽንፍ ጫፍ ተመልሰን የአብሮነት አስተሳሰባችንን ማጠናከር አለብን፡፡

ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ለማሳካት ቃል ገብቶ ነበር፡፡ እነሱም ዴሞክራሲ፣ ፌዴራላዊ አስተዳደርና ልማት ናቸው፡፡ ከእነ ጉድለታቸውም ቢሆን ፌዴራላዊ አስተዳደርና ልማት ለኢሕአዴግ የተሳኩለት አጀንዳዎች ሲሆኑ፣ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሚገለጽ ዴሞክራሲ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ግን ኢሕአዴግ ተሳክቶለታል ማለት አይቻልም፡፡

ይህ በመሆኑ አገራችን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች፡፡ ኢሕአዴግ ስለዴሞክራሲ ያለው አስተሳሰብ የተዛባ ወይም የጠበበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የልማት ጥያቄ እስከተመለሰ ድረስ የዴሞክራሲ ጉዳይ ለሕዝብ ብዙም አሳሳቢ አይሆንም የሚል ዓይነት ውስጣዊ ዕይታ ያለው ይመስላል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁለቱንም ጉዳዮች ጎን ለጎን በማሳካት ነው እንጂ የአንዱን ብቻ በማሳካት ማርካት አይቻልም፡፡ የዴሞክራሲ ጥያቄ በኢትዮጵያ ሕዝብ መቀንቀን ከጀመረ ከ50 ዓመታት በላይ ስለሆነ፣ አሁን ሕዝቡ በሚገኝበት የማኅበረ ኢኮኖሚ ደረጃ ስለዴሞክራሲ የሚቀርብን ጥያቄ መግታትም ሆነ ማዘግየት አይቻልም፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ የአገራችን አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓት በአንድ ፓርቲ ብቻ መንቀሳቀስ እንዲችል ተደርጎ የተሠራ ነው፡፡ ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሕዝቡን የሚያገለግሉ ተቋማትን በብቃት ስላልፈጠርን፣ በፓርቲና በመንግሥት መካከል ግልጽ የሆነ የሥልጣን ክፍፍልና ቁጥጥር ስለሌለ፣ የፌዴራል አደረጃጀቱም ከኢሕአዴግ አባል ድርጅት ድርጅታዊ መዋቅር እንዲስማማ ተደርጎ የተደራጀ ስለሆነ የኢሕአዴግ ውስጣዊ ሁኔታ ሲናጋና ሲታመም ሁላችንም ለመታመም እንገደዳለን፡፡ በአጭር አነጋገር ኢትዮጵያና ሕዝቧ በብዙ ርቀት ከኢሕአዴግ በላይ የሆኑ ማንነቶች ሆነው እያሉ ያላግባብ በኢሕአዴግ ዕገታ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በኢሕአዴግ ህልውና ላይ የሚመጣ አደጋ ሁሉ የግድ በሕዝብና በአገር ላይ የሚመጣ አደጋ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከልማትና ከብሔርተኝነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የፖለቲካ ቀውሶች ሊፈቱ የሚችሉት ዴሞክራሲያዊ ሒደትን በማጠናከር ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ የሚያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ምንድናቸው? ክልላዊ ብሔርተኝነትና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን እንዴት አድርገን ማስማማት እንችላለን? በአጠቃላይ እንደ ዜጋና እንደ ሕዝቡ ምን ዓይነት ኢትዮጵያ እንድትኖረን እንፈልጋለን? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ እየተወያየን መፍትሔ ማምጣት የምንችለው የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማጠናከር ነው፡፡

አገራችን በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ በማደግና በመበልፀግ ተስፋ ውስጥ የምትገኝ ጠንካራ አገር ብትሆንም የፖለቲካ ሁኔታችን ግን በብዙ ውስብስብና አስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ የወደቀ ሆኗል፡፡ የገጠመን ቀውስ አንድ ቀጥተኛ ገጽታ ብቻ ያለው አይደለም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ፣ ሕዝብ ከገዥው ፓርቲ፣ ሕዝብ ከሕዝብ፣ ገዥ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግጭትና ፍጭት ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ የችግሩን ጥልቀትና ክብደት የምንረዳው በድብቅና በጨለማ ሲንተከተክ ቆይቶ ፈንድቶ ሲወጣ ነው፡፡ ችግሮቹ ቀድመው እንዳይከሰቱም ሆነ ከተከሰቱ በኋላ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያደርግ የውይይት ባህልም ሆነ ሕጋዊ ተቋም የሌለን ሆነናል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰላምንና መረጋጋትን ከልባቸው የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተስፋ ማጣት፣ በፍርኃትና በጭንቀት ውስጥ ለመውደቅ ተገደዋል፡፡ ይህንን ዓይነት ዋጋ ለመክፈል የተገደድነው ብሔረሰባዊ ማንነትን መሻገር የሚችሉ የጋራ እሴቶቻችን ስለበጣጠስናቸው፣ የጋራ የምንለው ጥያቄና ብሶት ሊያስተጋቡልን የሚችሉ ሲቪክ ማኅበራትን ከማጠናከር ይልቅ በማዳከማችን፣ ለሐሳብ ብዝኃነትና ለጤናማ ውይይት ተገቢ ትኩረትና ቦታ ባለመስጠታችን መሆኑ በገሃድ መታየት ችሏል፡፡ ችግራችን በዚህ መጠን የገዘፈ ቢሆንም የፖለቲከኞቻችን የወቅቱ ጭንቀት አገሪቱ ይህንን አደጋ እንዴት ተሻግራ ከወቅቱ የዓለማችን ሁኔታ ጋር ተጣጥማ ለመኖር ትብቃ? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ሳይሆን የሚቀጥለው ጠቅላይ ሚኒስትር ከየትኛው ብሔር ይሆናል? የትኛው ፓርቲ የውስጠ ፓርቲን ሽኩቻ አሸናፊ ሆኖ ሊያወጣ ይችላል? በሚሉት ጠባብ ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ሆኗል፡፡ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰባችንም ምን ያህል በከፍተኛ ፍጥነት እየተለወጠና እያደገ ከሚገኘው የዓለም ሁኔታ እየራቅን መምጣታችንን ያሳየናል፡፡

በአጠቃላይ የወቅቱን የአገራችንን የፖለቲካ ችግር በአግባቡ ለመፍታት ያልቻልነው እንደ ዜጋ፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲም ሆነ እንደ ሕዝብ ብዙ የወደቅናቸው ፈተናዎች ስላሉ ነው፡፡ እነዚህ ፈተናዎች ከድክመታችን ወጥተን ለማለፍ የምንችለው እውነተኛ አገር ወዳጆች በመሆን ነው፡፡ እውነተኛ አገር ወዳድ ዜጋ ወይም ድርጅት ስለሠራው ስህተትና ስላለበት ድክመት ለመናገር አይፈራም፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአገርና የሕዝብን ጥቅም ቀዳሚ አድርጎ ያያል፣ ዜጎችንና ሕዝብን ከልቡ ያዳምጣል፣ ስለመጪው ዘመንም ጠንካራ ተስፋና እምነት አለው፣ ስለአገሩ ጥቅም ሲልም ከማንም ጋር በፍቅርና በአንድነት አብሮ በመሥራት ይወስናል፡፡ ይህንን በማድረግም የገጠሙትን ፈተናዎች ሁሉ በፅናት እንደሚሻገራቸው ከልቡ ይተማመናል፡፡

ኢትዮጵያውያን በብዙ የጀግንነት ሒደት ውስጥ ያለፍን፣ በተለያዩ የአብዮት ሒደቶች የተፈተንና አምባገነናዊ ሥርዓቶች ሲፈራረቁብን የኖርን ሕዝቦች ብንሆንም፣ እስካሁን ግን አርበኛ አገር ወዳጆች እንጂ ምክንያታዊ አገር ወዳዶች ለመሆን አልበቃንም፡፡ ይህም በመሆኑ የነፃነት ባለታሪክ የመሆናችንን ያህል የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት ለመሆን አልቻልንም፡፡ ኢትዮጵያውያን በዚህ ሁሉ ድክመት ውስጥ ከገጠመን ፈተና ሊያሻግሩን የሚችሉ ብዙ ጠንካራ ጎኖች አሉን፡፡ በሥነ ምግባሩ የተደነቀና አገር ወዳድ የሆነ መከላከያ ሠራዊት አለን፡፡ ለሰላምና ለወንድማማችነት ቅድሚያ የሚሰጡ ሃይማኖትና ባህሎች አሉን፡፡ ከረሃብም ሆነ ከጦርነትና ከመከራ አሸናፊ ሆኖ የመውጣት ልምድ አለን፡፡ በእነዚህ ጠንካራ ጎኖቻችን ላይ ምክንያታዊ አገር ወዳድነት ከጨመርንበት የማንሻገረው ችግር ሊኖር አይችልም፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ ጥንካሬያችንን በመጠቀም ብዙ ፈተናዎችን በድል ተወጥተናል፡፡ እነዚህም ጥንካሬዎቻችን ብዝኃነታችን፣ ጥልቅ የሆነው የአገር ወዳድነት ስሜታችንና በብሔራዊ ተቋማቶቻችን ላይ ያለን ክብርና እምነት ነው፡፡ ችግሮቻችንን ለመፍታት ስንነሳ ከተለያዩ ክፍላተ ዓለም ልምዶችን ልንቀስም እንችላለን፡፡ ከውጭም የሚመጡ አዎንታዊ የሆኑ ምክሮችን እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን ይኼኛውን ችግራችንን ራሳችን በራሳችን ልንወጣው የሚገባ ፈተና ነው፡፡

ችግሮቻችንን በመፍታት ሒደትም በሰላማዊ መንገድ ሥልጣንን ስለማስተላለፍና የራሳችንን እሴቶች ሳንለቅ እንዴት ዴሞክራሲን መገንባት እንደምንችልና ለአፍሪካም ምሳሌ መሆን የሚችል ድርጊት እንፈጽማለን፡፡ ጠንካራና ዴሞክራሲያዊ የሆነች ኢትዮጵያ ለአኅጉራችን መነቃቃት ከመሆን ባለፈ ምሳሌ በመሆን የመሪነት ሚናዋን መወጣት ትችላለች፡፡

በአሁኑ ወቅት ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሕዝብን ለማዳመጥና ስህተቱን ለማረም ቆርጦ መነሳቱን እየነገረን ነው፡፡ የችግራችን የመፍትሔ አካል ለመሆን ሲሉ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይቀሩ ሥልጣናቸውን የመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በቅርቡ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኖረን ነው፡፡ ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ምክንያታዊ አገር ወዳድነትና ጀግንነት እንዲኖረን የሚጠይቅ ነውና አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የሚመረጡበት መመዘኛ፣ ከገጠመን ወቅታዊ አገራዊ ችግር ጋር የሚጣጣም መሆን ይገባዋል፡፡ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከምንም ነገር በላይ ምክንያታዊ አገር ወዳድነት፣ ሕዝብን ከልብ የማዳመጥ ቅን ልቦና፣ ከሌሎች ጋር አብሮ የመሥራት ሆደ ሰፊነት፣ በአንድ በኩል ለሕዝቡ ጥያቄ እውነተኛና ዘላቂ መፍትሔ የመስጠት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕግና ሥርዓትን የማስፈን ቁርጠኝነት እንጠብቃለን፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲህ ዓይነቱን ምክንያታዊ አገር ወዳድነት ተላብሰው ለወደፊቱ የጋራ ህልውናችን በጋራ ተባብረን ለመሥራት የሚያበቁን እንዲሆኑ እየተመኘን፣ እኛም እንደ ዜጋና እንደ ሕዝብ ለአካባቢያዊና ለቡድናዊ ስሜታችንና ፍላጎታችን ሳይሆን ለጋራ ጥቅማችንና ህልውናችን ቅድሚያ ሰጥተን የአገራችንን ወቅታዊ ችግር በውይይትና በመቻቻል መንፈስ ለመፍታት መዘጋጀት አለብን፡፡ ፈርጀ ብዙ ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚያስችለንን ሁሉን አቀፍ አገራዊ የውይይትና የምክክር ሒደትም ነገ ሳይሆን ዛሬ መጀመር አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የፖለቲካ ተንታኝ ሲሆኑ፣ ጽሐፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡