Skip to main content
x

በዋጋ ነገር እንነጋገር

በናታን ዳዊት

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግብይት መድረኮች ከወትሮው የተለየ ነገር እየተመለከትን ነው፡፡ ቀድሞም ቢሆን ሰበብ የሚፈልገው የግብይት ልምዳችን፣ ከሰሞኑ ያየንበት የዋጋ ጡዘት ግን የተለየ ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ገበያዎችንና መደብሮችን ለተመለከተ፣ ምርቶች ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ከዚህ ቀደም ከነበረው ዋጋ ይልቅ ምን ያህል እየናረ መምጣቱን መታዘብ ይቻላል፡፡ በገበያው ውስጥ የዋጋ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሚጠበቅም ነው፡፡ ሆኖም የዋጋ ጭማሪው  አሳማኝ ምክንያት ሊኖረው ይገባል፡፡

ምርቱ በበቂ ሁኔታ የማይገኝበት ወቅት ከሆነ ወይም የምርት አቅርቦት ከፍላጎት ጋር ካልተጣጣመ፣ በሚፈጠረው እጥረት ሳቢያ የዋጋ ጭማሪ ሊፈጠር ይችላል፡፡ እንደ ነዳጅ ያሉ በኢኮኖሚው ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ ሲደረግ፣ ለሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ የሚኖረው የዋጋ ጭማሪ ምክንያታዊነቱ አያጠያይቅም፡፡

ሰሞኑን ለምናየው የዋጋ ጭማሪ አገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ተፅዕኖ ሊደርግ ይችላል፡፡ በዚህ ሥጋት የገባው ሸማች፣ ለአስቤዛ የሚፈልገውን ምርት ነጋዴ በሚጠራለት ዋጋ ሸምቶ፣ ወፍጮ ቤት ሲያጨናንቅ መመልከት አንዱ ማሳያ ይሆናል፡፡ ይህ በራሱ ለገበያው ጡዘት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ፍላጎትም ሆነ አቅርቦት ከምርት እጥረት ብቻም ሳይሆን፣ ሻጭና ገዥ ነገ ሊኖር ይችላል ብለው በሚገምቱት ሁኔታም ጭምር ተፅዕኖ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ለምሳሌ ነገ አድማ ሊመታ ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ምርት አናገኝም ብሎ ያሰበ ሸማች ለዛሬ ከሚያስፈልገው በላይ ለመሸት ይገደዳል፡፡ ሻጭም ዛሬ ከነገ ይልቅ ጥሩ ዋጋ አገኛለሁ ብሎ ካሰበ ምርቱ ላይ ዋጋ ጭማሪ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

 እንዲህ ባሉ ምክንያቶች ሳቢያ የሸቀጦች እንቅስቃሴ ጤናማነት ሊጎድለው ይችላል፡፡ በእንዲህ ያሉ አቅርቦትና ፍላጎትን በሚፈታተኑ ጉዳዮች ሳቢያ ተደጋጋሚ የዋጋ ጭማሪ የሚታይባቸው ምርቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡

ይሁንና የምንዛሪ ለውጥ በመደረጉ የተነሳ የዋጋ ጭማሪው የሚስተዋለው ከውጪ በሚገቡት ላይ ብቻም አይደለም፡፡ በአገር ውስጥ ምርቶች ላይም ጭማሪው ተንሰራፍቷል፡፡ ከአራት ወራት በፊት ምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ፣ የዋጋ ለውጥ ሊከሠት እንደሚችል ቢገመትም፣ አሁን የታየው የዋጋ ለውጥ ግን ፖለቲካዊ ሁኔታው ታክሎበትም ቢሆን ከተገመተው በላይ መሆኑ ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል፡፡ እርግጥ ነው መንግሥት የዋጋ ለውጡን ያሰበው ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ዋጋ ለውጥ አኳያ ብቻ መሆኑ ግን ሸውራራ ግምት እንደነበረው ያመላከተ ነው፡፡ የፖለቲካ ትኩሳቱ በምርት እንቅስቃሴ፣ በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖ አልተነገርንም፡፡ እርግጥ ነው ፖለቲካዊ ችግር ይኖራል ብሎ መተንበይ ቀላል አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን አገሪቱ ያልተረጋጋችበት ወቅት መሆኑ እየታወቀ የምንዛሪ ለውጡ መደረጉ በራሱ መንግሥትን ሳያስተቸው አልቀረም፡፡   

የበርበሬ፣ የጥራጥሬና የተለያዩ ሸቀጦች ዋጋ ጨምሯል፡፡ የጤፍ ዋጋ ስለጨመረ እየተባለ በመደብሮች በአንድ እንጀራ ላይ ከአንድ ብር በላይ ጭማሪ አድርገዋል፡፡  ለኮንስትራክሽን ግንባታዎች እንደ ግብዓት የሚያገለግሉ ምርቶችም ቢሆኑ አልቀመስ ብለዋል፡፡ ብረት፣ ጎማ፣ የተሸከርካሪ መለዋዎች በጥቂት ወራት ውስጥ ያሳዩት የዋጋ ለውጥ ከሚገመተውም በላይ ነው፡፡

በኮንስትራክሽን ግብዓት ዕቃዎችና የመለዋወጫ ዕቃዎች ላይ የታየው የዋጋ ለውጥ፣ የምንዛሪ ለውጥ ከተመነበት ጊዜ ወዲህ ያለማቋረጥ ጨምሯል፡፡ የቤት ዕቃዎች አምራቾችም በ1250 ብር ይገዙት የነበረው ስፖንጅ፣ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ዋጋው አራት ጊዜ ያህል የዋጋ ለውጥ በማድረግ 1900 ብር ደርሷል፡፡ በአንድ ምርት ላይ ይህንን ጭማሪ የታየበት አጭር ጊዜ የለም እየተባለ ነው፡፡ ልጓም ያጣው የዋጋ ጭማሪ ግራ መጋባትን አስከትሏል፡፡

ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ወተት በአንዴ በግማሽ ሊትር እስከሁለት ብር መጨመሩ በእርግጥ አሳማኝ ነው?፡፡ የለስላሳ መጠጦች ዋጋ፣ መሠረታዊ ሸቀጦች ባይሆኑም የቢራ ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ግሮሠሪዎች ከፋብሪካ ዋጋ አኳያ ከፍተኛ ጭማሪ ተክለው ገበያውን ሲያጋግሉ መመልከታችን የጤነኝነት ነው? ያሰኛል፡፡ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሦስትና አራት ጊዜ የዋጋ ጭማሪ የተደረገባቸው ሸቀጣሸቀጦች ጉዳይ ሊያሳሰበን ይገባል፡፡

‹‹ከዚህ ወዲህ የስኳር ችግር የለም፤›› ብንባልም ምርቱ የሚገኘው በጥቁር ገበያ ሆኗል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተወሰነ ደረጃ የተከፋፈለው ስኳር፣ አቅርቦቱ የተጠቃሚውን ፍላጎት ያህል ባለመሆኑ፣ ነጋዴዎች የስኳር ዋጋን ከሚገባው በላይ ጨምረው እየሸጡ ነው፡፡ ያለገበያ እየቀረበ ያለው ስኳር በኩፖን ወይም በራሽን ካርድ ብቻ ይታደላል በመባሉ ካርድ የሌላቸውን ሲያማርር ታይቷል፡፡

ምግብ ቤቶች የምግብ ዝርዝራቸውን በአዲስ መልክ በጭማሪ ዋጋ ሲያሸበርቁ አይተናል፡፡ ከሳምንት በፊት የገዛነው የህጻናት ዳይፐር በአንድ ጊዜ ስምንት ብር ምሯል፡፡ ይህ ያሳሳበው አንድ ወላጅ ለምን እንዲህ ሆነ ብሎ ከባለመደብር ጋር ሲሟገት አይቻለሁ፡፡ ወር ሳይሞላ ሁለት ጊዜ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ ያየው ወላጅ አልገዛም ብሎ መሄድ አይችልም፡፡ የተባለውን ከፍሎ ይወስዳል፡፡ የምግብ ዘይት ከተነሳም፣ ነገሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ የዘይት ዋጋ ለምን ጨመረ በማለት የጠየቅኋቸው ባለመደብሮች፣ ፆም ስለገባ ነው ብለውኛል፡፡ አቅርቦቱ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ በሦስት ሳምንት ውስጥ የዘይት መረከቢያ ዋጋ ሁለት ጊዜ ጨምሮባቸዋል፡፡ በፆሙ ሰበብ ይሁን በሌላ ምክንያት ባይታወቅም በአንድ ኪሎ አተር ክክ ላይ የአሥር ብር ጭማሪ ተደርጎ ከ36 እስከ 40 ብር ተሸጧል፡፡ ዛላ በርበሬ ዋጋው በእጥፍ እንዲጨምር መደረጉም ታይቷል፡፡

አንዲህ ያሉ ፈጣን የዋጋ ለውጦች በሸማቹ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆናቸው ታይቶ፣ ከዚህም በላይ ተጽዕኖ ሳይከሰትና ጉዳቱ ሳይባባስ ነገሩን መመርመር ያሻል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የተደረገው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መቀሰኑ መልካም እንደሆነ መጠቀስ አለበት፡፡ በወቅቱ አንዳንድ የአትክልት ምርቶች በእጥፍ ዋጋቸው ጨምሮ የተሰቀለው ምርቶቹ ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ አልቻሉም በሚል ሰበብ እንደነበር ይታወሳል፡፡