Skip to main content
x
ጂቡቲ የዱባዩን የወደብ አስተዳዳሪ ኩባንያ ማሰናበቷ በኢትዮጵያ ላይ ሥጋት ደቅኗል

ጂቡቲ የዱባዩን የወደብ አስተዳዳሪ ኩባንያ ማሰናበቷ በኢትዮጵያ ላይ ሥጋት ደቅኗል

  • አለመግባባቱ ወጪና ገቢ ዕቃዎችን ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሊያዘገይ ይችላል ተብሏል

በጂቡቲ መንግሥትና በዱባዩ የወደብ አስተዳዳሪ ኩባንያ ዲፒ ወርልድ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ሳቢያ፣ የጂቡቲ መንግሥት ከኩባንያው ጋር የነበረውንና ለ14 ዓመታት የቆየ የወደብ አስተዳደር ስምምነት የጂቡቲ መንግሥት ማቋረጡ የተሰማው ሐሙስ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡

በሁለቱ ወገኖች አለመግባባት ሳቢያ በኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ዕቃዎች ላይ ሥጋት ሊፈጠር ይችል እንደሆነ ለኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቧል፡፡ አቶ መኮንን በሰጡት ምላሽ፣ በጂቡቲ መንግሥትና በዱባዩ ኩባንያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት የሁለቱ ወገኖች ጉዳይ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በዋናነት በምትገለገልበት የዶራሌህ ኮንቴይነር ማስተናገጃ ተርሚናል አገልግሎት ላይ ሥጋት እንዳላቸው አቶ መኮንን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ምንም እንኳ ዲፒ ወርልድ ግዙፍና በወደብ አስተዳደር ሥራው ትልቅ ስም ያካበተ ኩባንያም ቢሆን፣ ከጂቡቲ መንግሥት ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ሳቢያ፣ ነገሮች ወደ ቀድሞ ቦታቸው ተመልሰው እስኪገቡ በሚኖረው የሽግግር ወቅት የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ በመጠኑም ቢሆን ሊያስተጓጉል የሚችል አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ሆኖም በአጭር ጊዜ ውስጥ ነገሮች ተረጋግተው የወደብ አገልግሎቱም እንደነበረው ሊቀጥል እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ የገለጹት አቶ መኮንን፣ የወደቡ የሰው ኃይልና የሎጂስቲክስ ፋሲሊቲዎችም ወደፊት በደንብ እንደሚታዩ አብራርተዋል፡፡

የጂቡቲ መንግሥት ከዲፒ ወርልድ ጋር የነበረውን ግንኙነት ማቋረጡን ማስታወቁ ተከትሎ አብዛኛውን የኢትዮጵያን ገቢና ወጪ ዕቃዎች የሚያስተናግደውን የዶላራሌህ ኮንቴይነር ተርሚናል መንግሥት በራሱ ለማስተዳደር ፍላጎት ይኑረው አሊያም ሌላ ኩባንያ ሊቀጥር ስለማሰቡ የሚታወቅ ነገር እንደሌለም ከአቶ መኮንን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የጂቡቲ መንግሥት ከዲፒ ወርልድ ኩባንያ ጋር የነበረውን የሥራ ውል ለማቋረጥ የተገደደው በተደጋጋሚ ያደረገው ድርድር ከውጤት ሊደርስ ባለመቻሉ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የዱባይ ኩባንያ ሲያስተዳድረው የቆየውን ወደብ፣ በጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኦማር ጊሌህ ውሳኔ መሠረት መንግሥት እንደተረከበው ተገልጿል፡፡ የጂቡቲ መንግሥት ከኩባንያው ጋር የነበረው የሥራ ስምምነት መሻሻል እንዳለበት፣ ለአገሪቱ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባልም ከዚህ ቀደም የነበረው የወደብ አስተዳደር ስምምነት የጂቡቲን ሉዓላዊ ጥቅም የሚፃረሩ አንቀጾች ያሉበት በመሆኑ የስምምነት ለውጥ እንዲደረግ መጠየቁ ተሰምቷል፡፡ የጂቡቲ መንግሥት የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚፃረርና የሕዝብ ጥቅም የሚነካ ነው ያለው ጥሰት ምን እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር ስትራቴጂካዊ የተባሉ የመሠረተ ልማት ስምምነቶችን በሚመለከት አዲስ ሕግ ማውጣቷን ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአዲሱ ሕግ መሠረት የጂቡቲ መንግሥት ስትራቴጂካዊ የሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለማስተዳደርና የኦፕሬሽን ሥራዎችን ለመምራት የተገቡ ስምምነቶች ላይ ዳግም ድርድር እንዲካሄድ ከማድረግ ባሻገር እስከማቋረጥ የሚደርሱ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ይህንን ተከትሎም ከዲፒ ወርልድ ጋር የነበረውን ስምምነት ለማደስ የጂቡቲ መንግሥት ‹‹በቅንነት መንፈስ ያደረገውን ሙከራና በድርድር መፍትሔ ለማፈላለግ ሲያደርግ የነበረውን ጥረት የዲፒ ወርልድ አስተዳደር ውድቅ ያደረገው ያለምንም ምክንያት ነው፤›› በማለት በመግለጫው አስፍሯል፡፡

የአስተዳደር ሥራውንና የወደብ ኦፕሬሽን ተግባሩን ከኩባንያው መንጠቁን ይፋ ከማድረጉ በፊት የጂቡቲ መንግሥት ለመጨረሻ ጊዜ የእንደራደር ጥያቄ ያቀረበው ጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ወይም ፌብሩዋሪ 1 እንደነበር አስታውሶ፣ ከዲፒ ወርልድ ያገኘው ምላሽ ግን ኩባንያው ጉዳዩን በግልግል ዳኝነት ለማየት መፈለጉን የሚገልጽ ምላሽ ብቻ እንደነበር አስታውቋል፡፡ ይህ በመሆኑም መንግሥት ስምምነቱን በማፍረሱ የሚጠበቅበትን ካሳ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡

የጂቡቲን መንግሥት ውሳኔ የተቃወመው ዲፒ ወርልድ በበኩሉ፣ ድርጊቱ ፍትሐዊነትና ተገቢነት የጎደለው ሲል ከማጣጣሉም በላይ፣ መንግሥት ላለፉት 14 ዓመታት የነበረውን ስምምነት በማፍረስ አዲስ ስምምነት በጫና ለማስፈረም የተደረገ ነው ሲል ኮንኖታል፡፡ በመሆኑም ኩባንያው በለንደን የጀመረው የግልግል ዳኝነት ሒደት፣ በዶራሌህ ኮንቴይነር ተርሚናል ያለውን ንብረቱ በጂቡቲ መንግሥት ሲወረስበት ለደረሰው ጉዳት ጥበቃ እንዲሰጥለት በማሰብ የወሰደው ዕርምጃ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ዲፒ ወርልድ በዶራሌህ የኮንቴይነር ተርሚናል የ33 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ እንዳለው ከማስታወቁም ባሻገር፣ የለንደኑ የግልግል ዳኝነት አካል በሁለቱ ወገኖች መካከል ከዚህ ቀደም የነበረው ስምምነት ‹‹ፍትሐዊና ምክንያታዊ፤›› ነው በማለት ውሳኔ መስጠቱንም ኩባንያው ያወጣው መግለጫ አስፍሯል፡፡

በሁለቱ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በዚህ አኳኋን ከቀጠለ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ዕቃዎች በሚስተናዱበት ወደብ መጉላላት ሊከሰት እንደሚችል ከወዲሁ በርካታ አስመጪና ላኪዎችን ሥጋት ውስጥ እንደከተተ እየተገለጸ ነው፡፡ ወደቡ ለተወሰነ ጊዜ እንኳ አገልግሎት ቢያቋርጥ በተለይ ወደ ውጭ በሚላኩ ዕቃዎች ላይ የሚፈጠረው መጉላላት፣ በላኪዎችና በአገሪቱ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ኪሳራ ያሳሰባቸው ነጋዴዎች ብቻም ሳይሆኑ በዘርፉ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎችም ጉዳዩን በንቃት እንደሚከታተሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡