Skip to main content
x
ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ማገዱ ተሰማ
የታገዱት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ጥላሁን

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ማገዱ ተሰማ

የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ላለፉት ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን በዋና ዳይሬክተር ሲመሩ የቆዩትን አቶ ዮሐንስ ጥላሁን ከሰኞ የካቲት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከሥራ እንዳገደ ተሰማ፡፡ ምክትላቸው አቶ የቻለ ምሕረት ድርጅቱን በውክልና እያስተዳደሩ እንዲቆዩ ወስኗል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ለአቶ ዮሐንስ መታገድ መንስዔ ከሆኑት ውስጥ፣ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በሚታዩ የአሠራር ችግሮች ላይ ማጣራት እንዲያደርግ በተሰየመው የአጣሪ ኮሚሽን ሪፖርት መነሻነት የቦርድ አመራሩ የጻፈው የውሳኔ ሐሳብ ነው፡፡ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ድንገተኛ ጉባዔ ያካሄደው የቦርድ አመራሩ የሱፐርቪዥን ኮሚቴ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም፤›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ሪፖርት ውስጥ የካቲት 12 እና የካቲት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በሁለት ምዕራፍ በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ፣ በምክትላቸው አቶ የቻለ ምሕረት ላይ፣ እንዲሁም በተቋሙ ማኔጅመንት አባላት ላይ የተደረገውን የማጣራት ሥራ አካቶ አቅርቧል፡፡

ከዚህም በተጓዳኝ 17 ያህል የሰነድ ማስረጃዎችን በግብዓትነት ያካተተው የሱፐርቪዥኑ ሪፖርት፣ ለአቶ ዮሐንስ ዕግድ ዋናው መነሻ ምክንያት እንደሆነ ታውቋል፡፡ አቶ ዮሐንስ መንግሥት ከመደበላቸው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ውጪ ቦርዱም የማያውቀው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ስምንት ሺሕ ዶላር ወርኃዊ ደመወዝ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ሲቀበሉ መቆየታቸውን የቱሪዝም ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የካቲት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሚኒስቴሩ በጻፉት ደብዳቤ ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይሁንና የአጣሪ ወይም የሱፐርቪዥን ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ አቶ ዮሐንስ ስምንት ሺሕ ዶላር ሲከፈላቸው የነበረው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ወልደ ማርያም (ዶ/ር) ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥር 1/A-66/171 ለዩኤንዲፒ በጻፉት ደብዳቤ አማካይነት ነው፡፡ አቶ ዮሐንስ ብቻም ሳይሆኑ በድርጅቱ የስትራቴጂክ ዕቅድና አስተዳደር ባለሙያዎች እንዲከፈል ጭምር ለዩኤንዲፒ ደብዳቤ ስለመጻፋቸው፣ በሱፐርቪዥኑ ሪፖርትና በቱሪዝም ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢው ተጠቅሷል፡፡

በዋና ዳይሬክተሩና በምክትላቸው ከቀረበው የእርስ በርስ ሽኩቻና በአሠራር አለመግባባት በተጨማሪ፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለዋና ዳይሬክተሩ ሁለት ደመወዝ እንዲከፈላቸው መፍቀዱ ብቻም ሳይሆን፣ የተቋሙን አቅም ለመገንባት የመጣው የዕርዳታ ገንዘብ ለደመወዝ ክፍያ መዋሉን ለቦርድ አለማሳወቁ ሚኒስቴሩን አስተችቶታል፡፡ የቦርዱን ውሳኔ በመንተራስ ሚኒስቴሩ በወሰነው መሠረት አቶ ዮሐንስ እንዲታገዱ ሲደረግ፣ በሌሎቹ የቱሪዝም ድርጅት ማኔጅመንት አባላት ላይ ውይይትና ግምገማ እየተደረገ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ቦርዱ በቱሪዝም ድርጅት ማኔጅመንትና በሚኒስቴሩ ላይ ካቀረበው ከፍተኛ ትችትና ወቀሳ በተጨማሪ፣ የድርጅቱ ማኔጅመንት አባላትም ቅሬታቸውን ሰንዝረውበታል፡፡ በሱፐርቪዥኑ ሪፖርት መሠረት የቦርድ አባላትን በቅርብ ካለማወቃቸው ጀምሮ ለቦርዱ የሚቀርቡለትን ሪፖርቶች አፅድቀው እንደማያውቁ፣ የቦርዱ ውሳኔዎችም ቀርበውላቸው እንደማያውቁ፣ የማኔጅመንት ስብሰባ እንደ ተቋም ተደርጎ እንደማያውቅ፣ ቦርዱ የተቋሙ ማኔጅመንት እንዲፈርስ እንደሚፈልግ እንደሚነገራቸው በመጥቀስ ቅሬታቸውን በቦርዱ ላይ አሰምተዋል፡፡ ‹‹ቦርዱ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የችግሩ አካል ነው ብለን ስለደመደምን ከቦርዱ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር አልሞከርንም፡፡ ስለቦርዱ በርካታ የተዛቡ መረጃዎች ይነገረን ስለነበረ ነው፤›› ማለታቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም በቦርዱ አሠራሮች ላይ ቅሬታ እንዳደረበት፣ ስለሚሠራው ሥራም ሆነ የአሠራር መዋቅር የሚጣረሱ አካሔዶች እንደሚታዩበት ምንጮች ተናግረዋል፡፡ 

ምንም እንኳ በሕግ አግባብ በሚታመንበት መንገድ ቢደረግ ሁለት ደመወዝ መከፈሉ በራሱ ችግር እንደሌለበት የሚገልጹ ቢኖሩም፣ ለተቋሙ አቅም ግንባታ በዕርዳታ የሚሰጥ ገንዘብን ለደመወዝ ክፍያ ማዋል ተገቢ ካለመሆኑም በላይ አቶ ዮሐንስ በሕግ እንዲጠየቁ ጭምር መጠየቁን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡