Skip to main content
x
ለሜካናይዜሽን እርሻ የታጩት የአርሲ ባሌ ወጣቶች
በአርሲ ዞን በሜካናይዜሽን እርሻ ሥራ ለተሠማሩ ወጣቶች በብድር የቀረቡትን ትራክተሮች ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተስፋዬ መንግሥቴ ከክልልና ከዞን ኃላፊዎች ጋር በመሆን ጎብኝተው ወጣቶቹንም አነጋግረዋል

ለሜካናይዜሽን እርሻ የታጩት የአርሲ ባሌ ወጣቶች

የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋልታ ቢሆንም፣ ከዘመናዊ አሠራሮችና የአመራረት ስልቶች ጋር ያለው ቁርኝት ብዙ ይቀረዋል፡፡ ለዘመናት የዘለቀው የኢትዮጵያ ግብርና፣ ዛሬም በጥማድ በሬ፣ ይህም ካልተገኘ ፈረስና ሌላም የጋማ ከብት ሲብስም አራሹ ራሱን ከእንስሳቱ ጋር በማጣመር ሞፈርና ቀንበር እየጎተተ የሚያርስ ገበሬና ሁዳድ የበዛበት ግብርና ነው፡፡

ዘመናዊ የግብርና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅና ለማላመድ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም፣ ከዘርፉ ፍላጎት አንፃር ብዙኃኑ አርሶ አደር ደጅ አልደረሱም፡፡ ምናልባት የምርጥ ዘር አቅርቦትና ማዳበሪያ የመጠቀም ልማድ እየጨመረ ከመምጣቱ ባሻገር፣ በዘመናዊ መሣሪያዎች የታገዘ እርሻ በማረስ ወደተሻለ የአመራረት ዘዴ መራመድ የተራራ ጉዞ ሆኗል፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ዋና ግብዓቶች ከሚባሉት ውስጥ ትራክተርና ኮምባይነር የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ቁጥር ምን ያህል ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ከላይ ለተጠቀሰው ሐሳብ አስረጅ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ትራክተሮችና ኮምባይነሮች በማን እጅ እንደሚገኙ ሲታይም፣ አርሶ አደሩ ከእነዚህ መሣሪያዎች ጋር ያለው ጉድኝት ከቁጥር አይገባም፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ሀብቴ እንደሚገልጹት፣ በኢትዮጵያ ለእርሻ አገልግሎት የዋሉት ወይም እንደዋሉ የሚታሰቡት ትራክተሮች ቁጥር 14 ሺሕ ብቻ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ግን በግል ባለሀብቶች የተያዙ ናቸው፡፡ የኮምባይነሮች ቁጥርም ቢሆን 1180 ብቻ ነው፡፡ ይህም አገሪቱ በሜካይናይዝድ ግብርና በኩል የምትገኝበትን ደረጃ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ ኮምባይነሮች ውስጥ 1,100 በላይ የግል ባለሀብቶች ሲሆኑ፣ 21 ብቻ በተለያዩ ዩኒየኖች ንብረትነት የተመዘገቡ ናቸው፡፡ አሥር ያህሉ የመንግሥት መሆናቸው ታውቋል፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ከዚህ ቀደም የተደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚፈለገውን ውጤት ባያመጡም፣ የተለያዩ ጥረቶች ስለመደረጋቸው እየተገለጸ ነው፡፡ አዳዲስ ጅምሮች ተዘርገተዋል፡፡ የሜካናይዜሽን እርሻን ለማስፋፋት በዕቅድ ከተያዙ ሥራዎች መካከል፣ ወጣቶችን በግብርና አሠልጥኖ መሣሪያዎችን በማቅረብ አገልግሎቱን ማስፋፋት  አንዱ ነው፡፡

ይህንን ሥልት በመጠቀም በግብርና ትምህርት የሠለጠኑ ተማሪዎችን በማደራጀትና መሣሪያዎቹን በብድር በማቅረብ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ታስቦ፣ በአርሲ ዞን በተጀመረው እንቅስቃሴ መሠረት ለመጀመርያዎቹ ኢንተርፕራይዞች መሣሪያዎቹ ለወጣት ገበሬዎች ቀርበውላቸዋል፡፡  

ሰኞ የካቲት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የመጀመርያዎቹ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች በመሆን የተመረጡትና በአርሲ ዞን የተደራጁ አምስት ማኅበራት መሣሪያዎቹን መረከባቸውን በማስመልከት ጉብኝት ተደርጓል፡፡ አምስቱ ማኅበራት አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መሣሪዎች እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ማረሻዎች የተገጠሙላቸው ትራክተሮች ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ መግባታቸው ታውቋል፡፡ ወጣቶቹ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችላቸውን እነዚህን ትራክተሮች የግሪን ኢኖቬሽን ሴንተር (በጀርመኑ ተራድኦ ድርጅት ጂአይዜድ ሥር የሚገኝ) ፕሮጀክት ነው፡፡ ድጋፉን ለወጣቶቹ ማቅረብ የተቻለው ከጀርመን መንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት እንደሆነ ለማኅበራቱ የትራክተሮቹን ቁልፍ ያስረከቡት የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተስፋዬ መንግሥቴ ጠቅሰዋል፡፡

ግሪን ኢኖቬሽን በአርሲ ዞን በተመረጡ አካባቢዎች ዘመናዊ ግብርናን ለማስፋፋት የተለያዩ ሥራዎችን ለመተግበር ሲንቀሳቀስ የቆየ ፕሮጀክት ስለመሆኑ ተወስቷል፡፡ ዕውቀትን የማሻገር፣ የአቅም ግንባታና የዘመናዊ ግብርና ሥራዎችን ለማስፋፋት የሚደረሱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የተቋሙ ትኩረት እንደነበር ሚኒስትር ዴኤታው አስታውሰዋል፡፡ ይህ አካሄድ እንደሚፈለገው ሊፈጥን ስላልቻለ፣ አሠራሩን በመቀየር መሣሪያዎቹን ገዝቶ ለወጣቶች የማስተላለፍ አዲስ አሠራር ላይ ማተኮር እንደሚሻል በተደረገ ስምምነት መሠረት ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

ለአምስቱ ማኅበራት የተሰጠው የእርሻ መሣሪያ የአርሲና የባሌ ገበሬዎችን ችግር ባይፈታም፣ ለወጣቶች እንዲህ ባለው መንገድ መሣሪያዎቹን ማቅረቡ ግን ጠቀሜታ እንደማይጠፋው ታስቦ መደረጉን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ ለሌሎችም ምሳሌ እንደሆንና ለሌሎች አካባቢዎችም የሞዴል ሥራ እንደሚሆን ተስፋ ተደርጓል፡፡  

ወደፊትም በማኅበር ለሚደራጁ ወጣቶች በልማት ባንክ በኩል የተተገበረውን የሊዝ ፋይናንሲንግ ወይም የመሣሪያ ኪራይ የብድር ሥርዓት ተጠቃሚ በመሆን የሜካናይዜሽን ግብርናን ሊያስፋፉ እንደሚችሉም መንግሥት እምነት እንዳለው አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ በአርሲ ዞን 55 አባላትን ላካተቱት አምስቱ ማኅበራት የተሰጠው መሣሪያ እንደ ተጠቃሚዎቹ ሁሉ ሞዴል ፕሮጀክት ነው ተብሏል፡፡ ይኸው ጅማሮ ወደ ሌሎች ክልሎችም እንዲዛመት ለማድረግ ማኅበራቱ የሚያስመዘግቡት ውጤት ወሳኝ እንደሆነ በመሣሪያዎቹ ርክክብ ወቅት ተገልጿል፡፡

‹‹ግብርናን ለማዘመን የተሻሻሉ የእርሻ መሣሪያዎች ወሳኝ ናቸው፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የተደራጁ ወጣቶችን ወደ ሥራ ማስገባት ወይም ሥራ አጦች ሥራ እንዲያገኙ ማድረግ ዓላማው ቢሆንም፣ ወጣቶችን ተጠቅሞ ግብርናን ማዘመን ግን የረጅም ጊዜ ተልዕኮው ስለመሆኑም ተብራርቷል፡፡

የግሪን ኢኖቬሽን ሴንተር ፕሮጀክት በአርሲ ዞን የግብርና መሣሪያዎችን ወቅቱን በጠበቀ መንገድ ለአርሶ አደሩ ከማቅረብ ባሻገር፣ ገበሬው የእርሻ መሣሪያዎችን አዘውትሮ እንዲጠቀም ለማስቻል የሚተገበር ነው፡፡ በአዲሱ አሠራር መሠረትም ለተደራጁት ወጣቶች መሣሪያውን ከማቅረብ ባሻገር፣ መሣሪያቹን ለማንቀሳቀስ፣ ጥገና ለማድረግና ሌሎችም የቴክኒክ ችግሮች ሲኖሩ መፍታት የሚያስችላቸው ሥልጠና እንዳገኙ ተብራርቷል፡፡

ማሽኖቹን ለማንቀሳቀስ የኦፕሬተርነት ሥልጠና የአርሲ ወጣቶች ያገኙት ግን በአገሪቱ ብቸኛው በሆነው የትራክተርና የእርሻ መሣሪያዎች ኦፕሬተሮች ማሠልጠኛ ተቋም በኩል ነው፡፡ ወጣቶቹ ሻሸመኔ ከተማ በሚገኘው ካሌብ የዘመናዊ ግብርና ተሽካርካሪዎች ማሠልጠኛ ተቋም አማካይነት ሥልጠና ከተከታተሉ በኋላ፣ የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ማግኘታቸው ታውቋል፡፡ ወደ ሥራ ሲገቡም በግብርና መካናይዜሽን ዳይሬክቶሬት በተዘጋጀላቸው የንግድ ሥራ ዕቅድ መሠረት እንዲሠሩና የማሽነሪ ሊዝ ብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ታምሩ እንደሚገልጹት፣ ወጣቶቹ ዘመናዊ የግብርና አገልግሎቱን በብቃትና በጥራት እንዲሰጡ በማስፈለጉ ሚሊዮን ብሮችን የወጡባቸውን መሣሪያዎች አገልግሎት ሳይሰጡ ተሰናክለው እንዳይቀሩ ጭምር ለቴክኒሻኖች ሥልጠና በመስጠት የሜካናይዜሽን ግብርናን ወደፊት ማራመድ ይታሰባል፡፡ በሜካናይዝድ ግብርና የአገሪቱ ሞዴል  የሆኑት የአርሲና የባሌ አካባቢዎች በመስኩ ቀደምት ታሪክ ካላቸው ከኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ በደቡብ፣ በአማራ እንዲሁም በትግራይ ክልሎች በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወቅት የሜካናይዜሽን ግብርና ሙከራዎች ተደርገውባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህን በመንተራስም፣ አርሲ የሚካናይዝድ ግብርና ሞዴል መሆንዋ ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን፣ ለዓመታት እየዳበረ የመጣ ስለመሆኑ አስታውሰው፣ አሁንም ብዙ ለመሥራት ለሜካናይዜሽን እርሻ የሚውሉ ግብዓቶችን ማቅረቡ ጠቀሜታው እንደሚያይል ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

በኢኖቬሽን ማዕከሉ በኩል የተደረገው ጥረት ባይናቅም፣ የዞንና የክልል ኃላፊዎች ሲናገሩ እንደተደመጠው፣ ትራክተሮችን በብድር ለወጣቶች በመስጠት ዘመናዊ እርሻን ለማስፋፋት ሲደረግ የነበረው እንቅስቃሴ በተለያየ መንገድ ሲደነቃቀፍ ታይቷል፡፡ የአርሲ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱራሒም መሐመድ እንደጠቆሙት፣ ለወጣቶችና ለማኅበራት ከተሰራጩት ትራክተሮች ውስጥ አብዛኞቹ አገልግሎት ሳይሰጡ ለመቆም ተገደዋል፡፡ አንድ ዓመት ሳያገለግሉ ከጥቅም ውጪ የሆኑ እንዳሉም ተጠቅሷል፡፡ በምሳሌነት ከተጠቀሱት ውስጥም ከሜቴክ የተገዙ 18 ትራክተሮች ይገኙበታል፡፡ ትራክተሮቹ በመለዋወጫ ዕጦት ሥራ አቁመዋል፡፡ ጥገና ማግኘትም አልተቻለም፡፡ ይህም የሜካናይዜሽን ግብርናን ለማስፋፋት እየገጠሙ ካሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የኃላፊውን ሐሳብ የተጋሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በማሽነሪዎቹ አጠቃቀም ላይ ችግር ስለመከሰቱ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ትራክተሮች ያለ ዕድሜያቸው ከአገልግሎት ውጪ የመሆናቸው ነገር  በውይይቱ ወቅት በተደጋጋሚ ሲገለጽ ተደምጧል፡፡ ‹‹አንድ ትራክተር እስከ 15 ዓመታት ይሠራል፡፡ በአገራችን እስከ 30 ዓመት የሚሠሩ አንዳንድ ብራንዶች ታገኛላችሁ፤›› ያሉት አቶ ታምሩ፣ አሁን ግን ሁለት፣ ግፋ ቢል ሦስት ዓመት እንደሠሩ የሚቆሙ መኖራቸው፣ የሚታሰበውን ጥቅም ከማሳጣት ባሻገር የአገሪቱን ሀብት የሚጎዳበት አጋጣሚዎች ፈጥሯል፡፡ ዕዳቸው ሳይከፈል በየቦታው የሚቆሙ ትራክተሮች እየተበራከቱ ስለመምጣታቸው ብቻም ሳይሆን፣ ዕዳው ያልተከፈለው አበዳሪ ተቋም የማይሠሩትን መሣሪያዎች ወርሶ ለመቀመጥ መገደዱን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

በብድር ለሚቀርቡት የእርሻ መሣሪያዎች የብድር መመለሻ ጊዜ ሊራዘም ይገባል የሚል ጥያቄም ሲቀርብ ተደምጧል፡፡ ያለ ጊዜያቸው የሚበላሹ መሣሪያዎች ችግሮች በተለያዩ መንገዶች የሚገለጽም ነው ተብሏል፡፡ እንደ አቶ ታምሩ ገለጻ፣ አሁን በተለያዩ አቅጣጫ እየቀረቡ ያሉ ትራክተሮች ጥሩ ውጤት ከሌላቸው የሚስተካከሉበትን መንገድ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ መሣሪያዎች ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የመጡ በመሆኑ በቂ መለዋወጫና ጥራት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በመጀመርያ መሞከር ያለበት ብቁ ኦፕሬተሮችን ማዘጋጀት፣ ከዚያ በኋላ የጥገና አገልግሎት የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች በአግባቡ መተግበር አለባቸው ሲሉም ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ብቁ ኦፕሬተሮችን ማፍራት መሆኑን የገለጹት አቶ ታምሩ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ላለመስፋፋት ማነቆ ከሆኑት አንዱ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን የኮምፓይነር ትራክተር ማሠልጠኛ ያለመኖር አንዱ ጉድለት እንደሆነም ይታመናል፡፡ ከዚህ አንፃር እየተወሰደ ያለውን ሥራ በተመለከተ አቶ ታምሩ፣ ‹‹ማሠልጠኛ ተቋማት ኦፕሬተሮችን በሌብል ደረጃ ለማሠልጠን አዘጋጅተን በአላጌ ትምህርት ተጀምሯል፡፡ አሁን ወጣቶቹ የተመረቁበት የግል ማሠልጠኛ አለ፡፡ ከአላጌ ሌላ አጋርፋ፣ በውቅሮና በወርታ ተመሳሳይ ማዕከላት ለማቋቋም እየተሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከህንድ መንግሥት ጋር በመተባበርም በደብረ ብርሃን ኦፕሬተር ማሠልጠኛ ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ከኦፕሬተሮች ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ይቀርፋል ተብሏል፡፡

መሣሪያዎቹን በብድር የተረከቡት ማኅበራት ተወካዮች በበኩላቸው፣ ትራክተሮቹ እንደሚሰጣቸው የተነገራቸው ዓምና እንደነበር አስታውሰው፣ ዘግይቶም ቢሆን ዘንድሮ በማግኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ሆኖም ማረሻዎቹ ከትራክተሮቹ አቅም ጋር አልተመጣጠኑም በማለት የቴክኒክ ችግር እንዳለባቸው የሚጠቁም ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ የትራክተሮቹ ጉልበትና የማረሻው ጉልበት ባለመመጣጠኑም የእርሻ ሥራውን አዳጋች አድርጎታል በማለት የማኅበራቱ ተወካዮች ቅሬታቸውን መንግሥት እንዲያጤነው አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በፊት ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮች ከአሁን በኋላ እንደማያጋጥሟቸው እምነታቸውን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ ለሞዴል ማኅበራቱ አስፈላጊው ነገር ሁሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የአርሲ ዞን ኃላፊዎችም ይህንን እንደሚጠብቁ ገልጸው፣ በየቦታው በመለዋወጫ ዕጦት የቆሙ ትራክተሮችን ማንሳቱ ላይ ትኩረት ይደረግ ብለዋል፡፡ ወጣቶቹም ከኃላፊዎቹ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ አንስተዋል፡፡ ነገሩ ሁሉ በተስፋ የሚቀር ሳይሆን፣ የተገባው ቃል እንዲተገበር ጠይቀዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ በምላሻቸው የወዳደቁ ትራክተሮች ነፍስ ተዘርቶባቸው ወደ እርሻ እንዲገቡ እንሠራለን ብለዋል፡፡ የግል ባለሀብቱም ገብቶ እንዲሠራ ስለሚደረግ የሜካናይዜሽን ሥራው እንዲስፋፋ ይደረጋል ሲሉ አክለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶች እንዲዘጉ ይደረጋል፡፡ እነዚህ ሞዴል ወጣቶች የሚያስመዘግቡት ውጤት ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የተለያዩ ችግሮች ያሉበት ይህ ዘርፍ፣ በፍጥነት እንዲያድግ ለማድረግ አንዱ መልካም ዕድል የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ብዙ ሥራ ሊሠራ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ትልቅ ማነቆ የሆነውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ችግር ለመቅረፍ በቅርብ የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሰጥ የሚያስችል ማዕከልና ተንቀሳቃሽ ጋራዥ ጭምር እንዲኖር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በጥቂት አካባቢዎች የተወሰነውን የሜካናይዜሽን ግብርና የሚለውጥ አሠራር ስለመጀመሩ በሙሉ ልብ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረትም ጂኣይዜድ 150 የማሽን ኦፕሬተሮችን ለማሠልጠን መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡