Skip to main content
x
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በአምስት የአፍሪካ አገሮች የሚያደርጉትን ጉብኝት ከኢትዮጵያ እንደሚጀምሩ፣ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት አስታወቀ፡፡

ቲለርሰን ከየካቲት 27 ቀን እስከ መጋቢት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ፣ በጂቡቲ፣ በኬንያ፣ በናይጄሪያና በቻድ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ስቴት ዲፓርትመንት ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ከሚያደርጉባቸው አገሮች መሪዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩ፣ ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ ከሆነው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ጋርም ከአፍሪካ መንግሥታትና ሕዝቦች ጋር የአሜሪካን አጋርነት ለማጠናከር እንደሚወያዩም ተገልጿል፡፡

በተለይ አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር በፀረ ሽብርተኝነት፣ ሰላምና ፀጥታን ለማጠናከር፣ መልካም አስተዳደር ለማስፈን፣ እንዲሁም በንግድና በኢንቨስትመንት የጋራ ተጠቃሚነትን ለመፍጠርና ለመነጋገር ዕቅድ እንዳላቸው በመግለጫው ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር አገሪቱ በገጠማት ቀውስ ላይ እንደሚመክሩና የፕሬዚዳንት ዶናልድ አስተዳደርን መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል፡፡

በአዲስ አበባ በሚያደርጉት ቆይታ በሰላምና መረጋጋት ጉዳዮች ላይ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ የሰላም ጉዳይ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በአኅጉሪቱ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚመክሩና እንደሚወያዩ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ማለትም ሽብርተኝነትን ለመዋጋት፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደፊት የበለጠ በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩም አስታውቀዋል፡፡

ቲለርሰን በዚህ ጉብኝታቸው ከአሜሪካ ኤምባሲ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር ተገናኝተው የሚወያዩ ሲሆን፣ በአሜሪካ መንግሥት በሚደገፉ ፕሮግራሞች ላይ እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያና አሜሪካ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ 115 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡