Skip to main content
x
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና ከቡሩንዲ ጋር ትጋጠማለች
ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ እንድትገኝ፣ እንዲሁም ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረውን የሰውነት ቢሻው ዋሊያዎቹን የሚተካ ቡድን ከዘንድሮው የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ከሚካፈለው ቡድን ይገኝ ይሆን?

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና ከቡሩንዲ ጋር ትጋጠማለች

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ በመጀመርያው ዙር የሚገናኙትን ቡድኖች ይፋ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያን ከቡሩንዲ ጋር አገናኝቷል፡፡

ካፍ ሰሞኑን ይፋ እንዳደረገው ኢትዮጵያ የመጀመርያውን ዙር ማጣሪያ ለማለፍ በመጋቢት 21 እና 23፣ 2010 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ባንዱ በአዲስ አበባ ስትጫወት፣ የመልሱ ጨዋታ በቡጁምቡራ ከሚያዝያ 12 እስከ 14 ባሉት ቀናት ታከናውናለች፡፡ የኢትዮጵያና ቡሩንዲ አሸናፊ በሁለተኛው ዙር በግንቦት የሚገጥመው፣ አንደኛው ዙር ከዘለለው ከሱዳን ጋር ይሆናል፡፡

የመጨረሻው ዙር አላፊዎች ከሰኔ በኋላ ከታወቁ በኋላ የ2011 ዓ.ም. የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ተፎካካሪ ይሆናሉ፡፡ በሌሎቹ የመጀመርያ ዙር ምደባዎች ሞሪታኒያ ከሞሮኮ፣ ጊኒ ቢሳው ከሴራሊዮን፣ አልጄሪያ ከቱኒዚያ፣ ላይቤሪያ ከቤኒን፣ ጋቦን ከቶጎ ይጋጠማሉ፡፡ ዛምቢያ፣ ጊኒ፣ ናይጄሪያ፣ ጋምቢያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሊቢያ፣ አይቮሪኮስትና ሱዳን በቀጥታ ለሁለተኛ ዙር ያለፉ ናቸው፡፡

ዓምና ዛምቢያ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ሉካሳ ላይ ሴኔጋልን 2 ለ0 ረትታ ዋንጫውን ማንሳቷ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር አራት ጊዜ ስትካፈል ሁለቴ ለፍጻሜ ግማሽ በመድረስ አራተኛ በመሆን አጠናቃለች፡፡

‹‹ይድነቃቸው ተሰማ ዋንጫ›› (Tessema Cup) በሚል መጠሪያ በ1971 ዓ.ም.  (እ.ኤ.አ. 1979) የተጀመረው የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ አሸናፊዎች ለዓለም ወጣቶች ዋንጫ የሚያልፉበት አሠራር ነበር፡፡ ከ40 ዓመት በፊት ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ኢትዮጵያ የመጨረሻውን ጨዋታ ከአልጄሪያ ጋር አድርጋ ተሸንፋ ሳታልፍ መቅረቷ አይዘነጋም፡፡