Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

የዛሬ ሁለት ዓመት የኅዳር ጽዮን ክብረ በዓል ከመድረሱ በፊት አንድ ወር ገደማ ቀደም ብዬ፣ አክሱምን ለመጀመርያ ጊዜ ስረግጥ የነበረኝን ስሜትና እጅግ መልካም የሆኑ ትውስታዎቼን በሌላ መጽሔት በቅርብ ጊዜ ጽፌ ነበር፡፡ ይሁንና ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የሪፖርተርን ድረ ገጽ ሳማትር ‹‹አስተያየት›› በሚለው ዓምድ ሥር ስለዓደዋና አካባቢው የተጻፈውን፣ ‹‹ጆሮዬን ወይስ ዓይኔን?›› በሚል ርዕስ በአንዲት ኢትዮጵያዊት የተጻፈውን እውነተኛ ትዝብት በማንበቤ ምክንያት ነው፡፡

እኔ የመሀል አገር ሰው ነኝ፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በአንድ የውጭ ድርጅት ተቀጥሬ እሠራ በነበረበት ጊዜ በመደጋገም ወደ ለ፣ ድሬዳዋና ባህር ዳር የመመላለስ ዕድሉን አግኝቼ የነበረ ቢሆንም አክሱምንና ዓደዋን የጎበኘሁት በራሴ ወጪና በራሴ ፕሮግራም ነበር፡፡

አሁን ላነሳ የፈለግኩት በጆሮ ስለሚነገረውና በዓይን ስለሚታየው መመሳሰል ወይም መለያየት አይደለም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ብጽፍ ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ያላለፈ ይሆንብኛል፡፡ ይኼ ጉዳይ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ተደጋግሞ የተነሳ ጆሮ ጠገብ ጉዳይ በመሆኑ፣ ስለዚህ ጉዳይ ማንሳትና መነጋገር ትርፉ ድካም ነው የሚሆንብኝ፡፡ ይሁንና ስለአካባቢው የሚነገረውን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ወሬ አለመጻፍም ትክክለኛ ሐሳብ አይመስለኝም፡፡

አንድ ማለዳ ካረፍኩበት ከሶሎዳ ሆቴል ተነስቼ ወደ ሰሜናዊ አቅጣጫ (አቅጣጫውም ዞሮብኝ ሊሆን ይችላል) በእግሬ ግራና ቀኙን እያየሁ ስሄድ አንድ ጦር ሠፈር የመሰለ ነገር በስተቀኝ ከአስፋልቱ ዳርቻ ተመለከትኩ፡፡ የመኪና መለማመጃ ምልክቶችንም ያየሁ ይመስለኛል፡፡  የዚያን ዘመን የጦር መሣሪያ (መድፍ ሳይሆን አይቀርም) ያየሁም ይመስለኛል፡፡ መጥፎ ትዝታዎችን አዕምሮዬ ለማስቀመጥ እጅግም ነው፡፡ በዚያች ማለዳ በድንገት የተከሰተውን መጥፎ አጋጣሚም እንደ ወትሮውዕምሮዬ በዝርዝር ያስቀረልኝ አይመስለኝም፡፡ የሆነ  ሆኖ ትኩረቴን የሳበው ስለዓደዋ የሚዘክር የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት ሥፍራ ነበር፡፡

መቼም እኛ አገር የተከለከለ ነገር ብዙ እንደሆነ ጠንቅቄ ስለማውቅ እያመነታሁ ጽሑፉን ለማንበብ ጠጋ እያልኩ፣ ዛፍ ጥላ ሥር የተቀመጠውን ጠብመንጃ የያዘ ወታደር በጨረፍታ እያየሁ ወደ መሠረት ድንጋዩ ተቃረብኩ፡፡ በመሠረተ ድንጋዩ ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ ለማንበብ ስጠጋ ዛፍ ሥር ሆኖ በዓይኑ ሲከታተለኝ የነበረ ወታደር ከመቀመጫው እመር ብሎ ተነስቶ ጠብመንጃውን ሊወድርብኝ እየዳዳው መጠጋት እንደማይቻል አምባረቀብኝ፡፡ ቸኩዬ ካሜራየን መዝዤ ቢሆን ኖሮ ምን እንደሚከተል አሰብኩና ሰውነቴ በቁጣ ሲግል ተሰማኝ፡፡ እንዲህም ሆኖ ራሴንም ለመቆጣጠር ጥረት አደረኩ፡፡

እውነት እላችኋለሁ ወታደሩ በእጁ ጠብመንጃውን እየነካካ ከመቀመጫው የተነሳ ቢሆንም አልፈራሁትም፡፡ ድንገት ብልጭ ያለውን ንዴቴን መቆጣጠር እየታገልኩ፣ ጽሑፉ ምን እንደሚል ለማየት እንደምፈልግ እየነገርኩት ለአፍታ ቆም ብዬ ወታደሩ ጋር ተፋጠጥን፡፡ የተጻፈን ነገር ሰው እንዳያነብ መከልከል ምን የሚሉት ፈሊጥ እንደሆነ ግር እንዳለኝ ነበር እግሬን የሰበሰብኩት፡፡

ቅድመ አያቴ ዓደዋ ዘምተዋል፡፡ የማላውቃቸው ቅድመ አያቴ  ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው በሕይወት መመለሳቸውን አባቴ በልጅነት ዘመኔ አጫውቶኝ ስለነበር፣ የአያቴን መቃብር እንዳላይ የተከለከልኩ ያህል ተሰምቶኝ ነበርና ነው ከዚህ ሞት ከሚተፋ ጠብመንጃ ከያዘ ወታደር ጋር ለአፍታም ቢሆን ተፋጥጬ የነበረው፡፡ ሰው እንዳይጠጋና ፎቶ እንዳይነሳ መመርያ ተሰጥቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን መንገድ ዳር የቆመን ነገር ፎቶ አታንሱ ማለት ዓይናችሁን በጨርቅ ታስራችሁ እለፉ የማለት ያህል ነው፡፡

እዚህ አዲስ አበባ አንድ የሚገርመኝ ነገር ነበር፡፡ 1990ዎቹ መጨረሻ ይመስለኛል መኪና ላይ ሆነን ሠርግ አጅበን ቪዲዮ ስንቀርፅ፣ ኢትዮጵያ ሆቴል ማዶ ያለው የመከላከያ ሚኒስቴር የካሜራው ሌንስ ውስጥ በመግባቱ ጥበቃ ላይ የነበረ አንድ ወታደር አስቆመን፡፡ የመከላከያ ሕንፃ በቪዲዮም ሆነ በካሜራ መቅረፅ ሕገወጥ መሆኑን ነግሮን ካሜራውን ተቀብሎን ያጠፋውን አጥፍቶ ቪዲዮውን መለሰልን፡፡

ያን ጊዜ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜና ዕወጃ በቴክኒክ ብልሽት ሥርጭቱ ሲቋረጥ፣ ከራሱ ከኢቲቪ ቴሌቭዥን ጣቢያ አናት ላይ ሆኖ ቁልቁል የተነሳው የመከላከያ ሕንፃ ዓይን ጠገብ ምሥል በቴሌቪዥን ስክሪን ያለጭቅጭቅ ይገባ ነበርና ጉዳዩን አንስተን ከወታደሩ ጋር እሰጥ አገባ ገብተን እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አሁን አሁን ኢቲቪ ከራሱ ሕንፃ አናት ላይ ቆሞ ያነሳውን የመከላከያ ሕንፃ ማሳየት ካቆመ ሰንበትበት ያለ ይመስለኛል፡፡

ዓደዋ ላይ የገጠመኝ ተመሳሳይ ነገር ነበር፡፡ መንገድ ዳር ላይመሠረት ድንጋይ አቁሞ ‹‹ፎቶ አታንሱ አጠገቡ ድርሽ አትበሉ›› የማለቱ ነገር አልተዋጠልኝም ነበርና ቀኔን ለአፍታም ቢሆን ረብሾት የነበረ ይመስለኛል፡፡ በመግቢያዬ ላይ ያነሳኋት አስተያየት ሰጪ ካነሱት ቁም ነገር ጋር በተቃራኒ የቆመ ሐሳብ መሆኑን ስገነዘብ ነው ይህን ጉዳይ ያነሳሁት፡፡ አስተያየት ሰጪዋ ኮሪያ በነበሩበት ጊዜ ኮሪያ የዘመቱ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በሚዘከሩበት ሙዚየም ተገኝተው የተደረገላቸውን ልዩ የክብር አቀባበል ሳስብ፣መሠረት ድንጋዩን ቆም ብሎ ለማየትና ለመታሰቢያ ፎቶ መነሳት የመከልከሉ ነገር ትዝ ሲለኝ ነው ይህንን የወሬ ቋንጣ ያነሳሁላችሁ፡፡

ከመሀል አገር ለኢትዮጵያ አንድነት የዘመቱትን ለእኔ መሰል አያቶች መታሰቢያ ይሆን ዘንድመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ቦታ ቆሜ እንዳላይና ፎቶግራፍ እንዳላነሳ መከልከሉ እንደ እግር እሳት ፈጅቶኝ ስለነበር ነው ከወታደሩ ጋር እሰጥ አገባ የገባሁት፡፡ ያም ሆነ ይህ ያሰብኩት ሳይሳካልኝ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ በንዴት ረዥም የእግር ጉዞ ማድረጌን ያወቅኩት፣ ከከተማው ዳርቻ ስደርስ ነበርና ደንበኛዬ የሆነው የአካባቢው ተወላጅ ወጣት የባጃጅ ሾፌር ጠርቼው ነበር ወደ መሀል ከተማ የተመለስኩት፡፡ ያጋጠመኝን የሚያበሳጭ ነገር ደንበኛዬ ለሆነው ለባጃጅ ሾፌሩ ስነግረው፣ ‹‹ አንተ ሰውየ አብደሃል እንዴ ቢያስሩህ የት ገባህ ይባላል?›› ነበር ያለኝ፡፡

መሀል ዓደዋ ስደርስ አገሬው ዱቃ እያለ የሚጠራውን አገር በቀል መጠጥ እየተጎነጨሁ ከታዳሚው ጋር ጨዋታ ስጀምር ነበር ንዴቴ ሙሉ በሙሉ ከስሞ የጠፋልኝ፡፡ አክሱምና ዓደዋ ከቆየሁባቸው ጥቂት ቀናት ያልተደሰትኩበት ጊዜ ቢኖር በዚያች ማለዳ ያሳለፍኳቸው ጥቂት ሰዓታት ብቻ ነበሩ፡፡ ይታያችሁ መንገድ ዳር አላፊ አግዳሚ የሚያየውንመሠረት ድንጋይና አጠገቡ የቆመውን የዚያን ዘመን መድፍ ለመታሰቢያ ፎቶ ብነሳ የሚደርሰው ጉዳት፡፡ አገሬው የሚጎበኙ ሥፍራዎችን እንድናይ በቂ መረጃ ከመስጠት በዘለለ ቦታውን ለማሳየት ወደ ኋላ የማይል ደግ ሕዝብ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት የገባበት ጉዳይ ህፀፁ ለምን እንደሚበዛ አላውቅም፡፡ እንዲያው ይህ ‹‹በአይቻልምና በክልክል ነው›› የታጠረ መስተንግዷችን መቼ ይሆን የሚሻሻለው?   

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቢሮ እንደ ሌሎቹ የመንግሥት ቢሮዎች ደካማ መሆኑ አገሪቱ በቱሪዝም የምትጠቀመው እዚህ ግባ የማይባልመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሰሞኑን ሁለት ቦታ ወፍራም ደመወዝ የተተከለለት የነቀዘ የመሥሪያ ቤቱ ቁንጮ ባለሥልጣን መኖሩን ሳነብ ምንም አልገረመኝም፡፡

(ተመስገን ጌትዬ፣ ከአዲስ አበባ)