Skip to main content
x

የአገራችን የከፊል ጨለማና ብርሃን ጉዞ

በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)

አገራችን በመስቀለኛ መንገድ ትገኛለች፡፡ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚሸጋገሩበት ወይም ጥልቀት ወዳለው ቀውስ፣ ብሎም ወደ እርስበርስ ጦርነት ሊያመራም ይችላል፡፡ ልሂቃን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የሕዝቦችን የትግል ስጦታ ከተጠቀሙበት ዕድላችን የመጀመርያው ይሆናል፡፡

ይህ ትንተና ኢትዮጵያ ከእነ ችግሮቿ እስከ 2007 ዓ.ም. የነበሩት 25 ዓመታት የከፊል ብርሃን፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ በጨለማ እንደ ምንገኝ፣ ፖለቲካዊ ቀውስ ብሔር ተኮር ጥቃትን ማስከተሉና በልሂቃን መካከል መተማመን የጠፋበትና ሕገመንግሥቱ በግላጭ የተጣሰበት ሁኔታ መኖሩን ያስቀምጣል፡፡ ቀውሱ ተግዳሮቶች ቢኖሩትም በዋናነት ያረገዘው ሌላ ጊዜ የማይገኝ ከፍተኛ ዕድል ነው፡፡ ሕዝቦች ከእንግዲህ ወዲህ በፀረ ዴሞክራሲያዊ መንገድ አንገዛም ማለታቸው ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ለምነን፣ ተምረን፣ ሠልጥነንና በገንዘብ የማይገኝ ዕድል መሆኑንና ይህን ዕድል አድንቀን እንዴት እንጠቀምበት የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የካፒታሊዝምና የዴሞክራሲ ግንባታ በተመሳሳይ ጊዜ እያካሄደች የምትገኝ አገር በመሆኗ፣ የካፒታሊዝም ውጣ ውረድና ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር የሌሎች አገሮች ተሞክሮዎች በመዳሰስ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሒደት ያትታል፡፡ የጨለማ ዘመኑን ባህሪያት ከገለጸ በኋላ ያሉንን ከፍተኛ ዕድሎች የሚመለከት ከአድማስ ባሻገር በሚል ርዕስ መሠረታዊ ዕድሎችን ይተነትናል፡፡

እነዚህን ዕድሎች ተጠቅመን ከጨለማው ወደ ብርሃን ለመዝለል ምን መደረግ አለበት? የሚለውን አስቀምጦ ከሁሉም በላይ በፖለቲካ ጥበብ ወደ አማካይ ሐሳብ ማመቻመች (Compromise) እና የሚቻለውን ማድረግ (The Possible) መሆኑን፣ እውነተኛና የተሟላ ድርድር (Negotiation) ማድረግና መጨረሻም ወደ ስምምነት መድረስ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ ሒደቱ በተቃዋሚዎችና በኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን አጋር ድርጅቶችን የሚያካትትና ሕዝቦችን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት ይላል፡፡

የካፒታሊዝም ጉዞ ውጣ ውረድ

የካፒታሊዝም ዕድገት ያለማቋረጥ ቀጣይነት ያለው ሒደት አይደለም፡፡ አንዱ ደረጃ በአንዱ ላይ እየተረማመደ ቀጣይነትን እየወለደ የተለያዩ ባህሪያት ያሉት ደረጃዎችን አልፏል፡፡ አንዳንድ ምሁራን ደረጃዎቹ በግብርና ላይ ተመሠረተ የመካኒካዊ ኢንዱስትራላዊነትና ፋይናንሳዊ ካፒታሊዝም ብለው ይፈርጃሉ፡፡ አንዱ ደረጃ ዕድገት ካስመዘገበ በኋላ ወደ ቀውስ ይገባል፡፡ ከቀውስ በኋላ ሌላ ከፍተኛ ዕድገት ይታያል፡፡ ጉዞው የዕድገትና የቀውስ ሒደት ይሆናል፡፡

ማርክ ብሊዝ ማሶን የሚባለውን ተመራማሪ በመጥቀስ ዕድገትና ቀውሱን በአራት ከፋፍሎ ያስቀምጣል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1790 እስከ 1848 በእንፋሎት ኃይል የሚሠራ ፋብሪካዎች መቋቋም ተከትሎ የነበረው ዕድገትና እሱን መሠረት አድርጎ በ1820 ዓ.ም. አካባቢ የተፈጠረውን ድቀት (Depression) እንደ አንድ ደረጃ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ሁኔታ እ.ኤ.አ. በ1848 አብዮት ወልዶ የቡርዣ መደቦች ሥልጣን ላይ እንዲቆናጠጡ አደረገ፡፡ ሁለተኛ ዑደት እ.ኤ.አ. ከ1848 እስከ 1890 ይጓዛል፡፡ የባቡር መስመሮች መዘርጋት፣ የቴሌግራፍ ፈጠራና የባህር ጉዞ መስፋፋት ተከትሎ ከፍተኛ ዕድገት ተመዘገበ፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ በ1870 አካባቢ አሁንም ከፍተኛ ድቀት አጋጠመ፡፡ በሚቀጥሉት የተወሰኑ አሥር ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይል መፈልሰፍን ተከትሎ የጅምላ ምርት በመፈጠሩ የላብ አደሩ እንቅስቃሴ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበትና ካፒታል በከፍተኛ ደረጃ የተከማቸበት ዕድገት ተከሰተ፡፡ ካፒታሊዝም አደገ ተመነደገ ተባለ፡፡ ሆኖም ዕድገቱ ወደ ታላቅ ድቀት (Great Depression) አመራ፡፡ መጀመርያ ለአንደኛው የዓለም ጦርነት ከዚያም ከተወሰነ የሰላምና የዕድገት ጉዞ በኋላ ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ሆነ፡፡ ለበርካታ ሚሊዮን ሰዎች ሕልፈት ምክንያት ሲሆን፣ ግዙፍ የካፒታል ውድመት አስከተለ፡፡ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አራተኛው ዑደት በኤሌክትሮኒክስና በሲንተቲክ ፈጠራ ሌላ ከፍተኛ ዕድገት ታየ፡፡ ይህ እ.ኤ.አ. እስከ 1970 መጨረሻ የዘለቀው ዕድገት አዲስ የአመራረት አደረጃጀት ከማምጣቱም በላይ፣ የላብ አደሩን ተነፃፃሪ ልዕልና በማረጋገጡ የዋስትና መስተዳድር (Welfare State) በከፍተኛ ደረጃ መታየት ጀመረ፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ድቀት ባይታይም፣ የተለያዩ ቀውሶች እየታዩ ነው፡፡ እንደ ማሶን አባባል አራተኛው ዑደት ቆሟል፡፡

የኢኮኖሚ ቀውሶች ወደ ፖለቲካዊና የደኅንነት ቀውሶችን በማስቀጠል የተለያዩ ጦርነቶች ተከስተዋል፡፡ ማይክል ሪር (2008) የሚባለው ጸሐፊ ፓርተር የተባለውን ተመራማሪ ጠቅሶ እንደሚገልጸው፣ ከ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 20ኛው ምዕተ ዓመት ባለው ጊዜ በግምት አንድ ሺሕ የነበሩ ትንንሽ አገሮች ወደ 25 የአውሮፓ አገሮች ተጠቃለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 24 ቀን 1648 በዌስትራሊያ ስምምነት የተጠናቀቀው 194 አገሮች የተሳተፉበት የ30 ዓመታት ጦርነት ያበቃበት ነበር፡፡ ሆኖም የካፒታሊስታዊ ሥርዓት ቀውስ በመቀጠሉ አንደኛውንና ሁለተኛውን የዓለም ጦርነቶች  አስከተለ፡፡

ማርክ ብሊዝ ‹የካፒታሊዝም ቀውስ› በሚለው መጣጥፉ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተፈጠረው የጅምላ ዴሞክራሲ (Mass Democracy) ምክንያት፣ በካፒታሊዝምና በዴሞክራሲ ፖለቲካ ተፈጥሯዊ ግጭት ተፈጥሯል ይላል፡፡ ምክንያቱንም ሲያብራራ ካፒታሊዝም ሀብትን በገበያ መርህ ሲመድብ፣ ዴሞክራሲ ግን ሥልጣን በድምፅ ነው የሚመድበው፡፡ በእሱ አገላለጽ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በነበሩት ሦስት አሥር ዓመታት ዴሞክራሲ ሕጎችን ይወስን ነበር፡፡ ገበያውን በመግራት የላብ አደሩ መብቶች የሚረጋገጡበትና ማኅበራዊ ዋስትና በእጅጉ የተስፋፋበት ወቅት ነበር ይላል፡፡ ከሰባዎቹ መጨረሻ (ከ1970 እስከ 1980) በኋላ (የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋንና የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር ዘመን መሆኑን ያስተውሏል) ሉላዊ (Globalized) ያልተገራ (Deregulated) የአገሮች ድንበርና ያልተገደበ ካፒታሊዝም ላብ አደሩንና አደረጃጀቱን ማጥቃት ጀምረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተገላቢጦሽ የካፒታል ገበያ ዴሞክራቲክ መንግሥታት መከተል ያለባቸውን ሕጎች ማውጣት ጀምሯል፡፡ ዴሞክራሲ ሕግ ማውጣት ተስኖት የካፒታል ገበያ ተክቶታል ማለት ነው፡፡ ዕውቁ የዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስትና የቀድሞ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ሲቲግሊዝ ‹‹The Price of Inequality›› በሚል መጽሐፋቸው፣ የአሜሪካ ፖለቲካዊ ሥርዓት ከ‹‹አንድ ሰው አንድ ድምፅ›› ወደ ‹‹አንድ ዶላር አንድ ድምፅ›› እየተቀየረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ የካፒታል ገበያ ፖለቲካውን ሲቆጣጠረው ‹‹Of The People, For The People, By The People›› የነበረው ‹‹Of The 1%, For The 1%, By The 1%›› እንደተቀየረ ማለት አንድ በመቶሀብታሞች ፖለቲካውን እንደተቆጣጠሩት ያብራራል፡፡

ዊልያም ታብ (2008) የሚባለው ኢኮኖሚስት በዓለማችን አራት መሠረታዊ ቅራኔዎች እንዳሉ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ በመጀመርያ በአሜሪካ የጀመረው የፋይናንስ ሁከት ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ የማስማማቱን የሌሎች አገሮች መንግሥታት በኃይል ለመለወጥ ያደረገችው ሙከራና ያስከተለው ተቀባይነት የማጣት ሲሆን፣ ሁለተኛው መሠረታዊ ቅራኔ የዓለም ሕዝቦች ዓለማዊ ፋይናንሻልና የንግድ ሥርዓትን ውጤታማ በሆነ መንገድ መቋቋማቸው፣ በአዳዲስ የሥልጣን ማዕከላት (እንደቻይና ባሉት) ለጥቅም ግጭት የሚሆን ሁኔታ መፈጠሩን፣ የመጨረሻውና አራተኛው ቅራኔ የተዛባ የሀብት ክፍፍልና ያለውን ሀብት ያላግባብ መጠቀም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰ ያለው ውድመት ለቀጣይ ቀውስ ትልቅ ምክንያት እንደሚሆን ይገልጻል፡፡ ነዳጅ፣ ምግብና ውኃ በመሳሰሉት የሚደርሰው ጥፋት ብዙ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ካፒታሊዝም ቀውሶችን የመቋቋም ችሎታ ቢኖረውም ማሶን “Climate change may be the one only bullet that capitalism cannot doolge” ይላል፡፡

ዘጋርዲያን (2015) የሚባለው ጋዜጣ የዓለም ግማሹ ሀብት አንድ በመቶ በሚሆኑ ሰዎች እጅ እንዳለ ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ አሁንም ቢሆን ዓለማችን በዕድገት ቀውስ ዑደት ውስጥ እንዳለች በተለያዩ መንገዶች ተገልጿል፡፡ የካፒታል ገበያ ፖለቲካውን መምራቱ፣ ከአንድ በመቶ የማይበልጡትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስለሆነ የሀብት ክፍፍሉ ኢፍትሐዊነትና የሥራ ዕጦት የዓለማችን ቀጣይ ቀውስ ይሆናል፡፡

ሽግግር ወደ ዴሞክራሲ

ካፒታሊዝም ለዴሞክራሲ መሠረት ቢሆንም ብቸኛ አማራጭ አይደለም፡፡ እንደ ባሪንግተን ሙር (1966) ገለጻ ፋሺዝምና ዴሞክራሲ በካፒታሊስት ዘመን የሚታዩ የሥርዓቱ የተለያዩ ባህሪዎች ናቸው፡፡ ሀብታም አገር መሆን የግድ ወደ ዴሞክራሲ የማያሸጋግር መሆኑን የቻይናና የሳዑዲ ዓረቢያን ምሳሌ በመጥቀስ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የካፒታሊስት ውጣ ውረድና ሽግግር ወደ ዴሞክራሲ በአንድ ጊዜ ለመገንባት እየተጋች ላለች አገር ጠቃሚ ነው፡፡ አዶኔልና ሸሚተር (2013) ‹ከአምባገነን አገዛዝ የሚደረግ ሽግግር› በሚለው መጽሐፋቸው፣ ‹‹ሽግግር በሁለት ፖለቲካዊ ሥርዓቶች መሀል የሚገኝ ክስተት ነው፤›› ይሉታል፡፡ ከአምባገነን ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግርም የራሱ መለያ ባህሪ አለው፡፡ ጄራርድ ሚኒክ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግርና ዴሞክራሲን ማጠናከር የተለያዩ ባህሪያት አለው ይላሉ፡፡ ሽግግሩ በዋናነት ከዴሞክራሲያዊ ባህሪው ይልቅ ፀረ አምባገነንነት ባህሪው ያመዝናል፡፡ ወደ ተጠናከረ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር ግን የተወሳሰበ የተቋማት ግንባታ፣ የሥርዓቱ ሕጎች ተግባራዊ የሚሆኑበትና የራሱ የተለየ ስትራቴጂና ተዋንያን ያሉበት ነው፡፡

ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር ለአውሮፓውያንና ለአሜሪካውያን ረዥም ጊዜ የወሰደ ሒደት ሲሆን፣ በ20ኛው እና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለ ሽግግር ግን በተነፃፃሪ በአጭር ጊዜ እንዲፈጸም ዓለማዊና ውስጣዊ ሁኔታ ያስገድዳል፡፡ ሽግግሩ ከምናውቀውም ወደምናልመው የሚደረግ በመሆኑና አሮጌ አስተሳሰቦችን፣ አደረጃጀቶችንና አሠራሮችን እያስወገደ በአዳዲስ እየተካ የሚሄድ ነው፡፡ ላይ ታች ያለበት እርግጠኛ የማንሆንበት፣ ግራ መጋባት የሚበዛባት፣ ከፍተኛ ስህተቶች የሚፈጸሙበትና ፅንፈኛ አመለካከት የሚከሰትበት ጭምር ነው፡፡ ሽግግሩ የሚከሰትበት ሁኔታ ሜይንዋሪንግ (1992) ''Transaction, Extractions and Defeat'' ብሎ ሲገልጸው፣ ሐንቲንግተን ደግሞ (1991: 114-115) “Transformation Transplacement and Replacement” ብሎ ይገልጸዋል፡፡ ለውጥ (Transformation) ማለት በሥልጣን ላይ ያሉ ልሂቃን ዴሞክራሲን ለማምጣት መሪነቱን ሲጨብጡ ሲሆን፣መተላለፊያ የሚባለው በሥልጣን ላይ ያሉትና ተቃዋሚ ልሂቃን በጋራ ሆነው ለውጡን ሲያመጡት ነው፡፡ መተካት ደግሞ አምባገነናዊ መንግሥት ሲሸነፍ ወይም ሲወድቅና በተቃዋሚ ልሂቃን መሪነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር ሲጀምር ነው፡፡

እንደ ሐንቲንግተን ገለጻ ከሦስቱም መንገዶች ሽግግሩ የሚከሰትበት ሁኔታ በመተካት የሚደረገው ሽግግር ያልተለመደ (በጥናቱ ከተካተቱ 35 አገሮች በስድስቱ ብቻ የተከሰተ) ሲሆን፣ ዴሞክራሲን ለማጠናከር የሚደረገው ሽግግር ከባድ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡ የፖርቹጋል፣ የግሪክና የአርጀንቲና የመተካት ዓይነት ሲሆን፣ የስፔንና የብራዚል ሽግግር በለውጥ የተካሄደ መሆኑ ይገልጻል፡፡ በመተካት የሚደረግ ሽግግር አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ በመሆኑ የሁሉንም ጥቅሞች በሚያረጋግጥ መንገድ በግልግል የሚፈጽም ባለመሆኑ፣ በአሸናፊው ፍላጎት ብቻ የሚፈጸም ይሆናል፡፡ ተሸናፊ ኃይሎች የማደናቀፍ ሚና ስለሚኖራቸው የአሸናፊ ትዕቢት (Arrogance) ስለሚኖር ሽግግሩን ከባድ ያደርገዋል፡፡

ሽግግር በኢትዮጵያ

አገራችን ወደ ካፒታሊዝምና ዴሞክራሲ በተመሳሳይ ጊዜ ለመሸጋገር ደፋ ቀና እያለች ነው፡፡ ሁለቱም በአንድ ጊዜበመሆኑ አምባገንነት የተተካው በድርድር አለመሆኑ፣ ኢትዮጵያችን ልክ ሉዊስ ሞሪኖ (2001) ስለስፔን እንዳለው አንዳንድ አገሮች ብሔራዊ አምታች ሁኔታ (Dilemma) ሲያጋጥማቸው፣ ስፔን የገባችበት መንታ መንገድ ግን የብሔረሰቦች ጓዳ እንደሆነ ስፔን የምትታወቀው የብዙ አገሮች ስብስብ ወይም የብሔሮች ስብስብ በመሆኗ ነው፡፡ እንዳለው፣ ከላይ የተገለጸው አስቸጋሪ ሒደት ጋር ተዳምሮ ሽግግሩ በጣም የተወሳሰበ ያደርገዋል፡፡ ብዝኃነታችን ከፍተኛ ፀጋ ቢሆንም ያሉትን ተግዳሮቶች አሳንሶ ማየት አይገባም፡፡

በመጀመርያ በሽግግር ቻርተር በኋላም በሕገመንግሥታት መሠረት አስቸጋሪ ፈታኝ ጉዞ ተካሂዷል፡፡ ወታደራዊውን ሥርዓት በኃይል ከመጣል ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም፡፡ አገሪቱ በጦርነት የታመሰች፣ ኢኮኖሚዋ ክፉኛ የደቀቀና ምስቅልቅሏ የወጣች ነበረች፡፡ የዕዝ ኢኮኖሚ፣ በኋላም ቅይጥ ኢኮኖሚ ያደቀቀውን የአገሪቱ ሁኔታ ለመለወጥ መሠረታዊ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያመጣ ገበያ መር ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ተከትለን፣ እነሆ በጣም ፈጣን ከሆኑ አዳጊ አገሮች ተርታ ተሠልፈን እንገኛለን፡፡ በ1983 ዓ.ም. የዴሞክራሲ ፖለቲካ በዓለም እንደ አንድ መመዘኛ የሚታይበት ወቅት የነበረ በመሆኑ ጭምር፣ መሠረታዊ በሆኑ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የታጀበ፣ ይህን ለማስጠበቅ ፌዴራላዊ የመንግሥት አስተዳደር መከተል የጀመርንበትን ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ ለማድረግ በተደረገው እንቅስቃሴ ፌዴራላዊ ሥርዓት መሠረት እንዲይዝ በመደረጉ፣ ለ25 ዓመታት ያህል ሰላም የነገሠባት አገር ሆና ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ሕዝቦች መብቶቻቸውን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጋሬጣ እያጋጠማቸው በመሄዱ፣ ከ2007 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ በተለያዩ ደረጃ በሚታዩ ሁከቶች እየታመስን እንገኛለን፡፡ የሕዝቦች ሰብዓዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ደረጃ በደረጃ እየተጠናከሩ እንዲሄዱ ቢያስፈልግም፣ እነዚህን መብቶች ለማስጠበቅ ሕገ መንግሥቱ እርስ በርስ ለመናበብና ለመቆጣጠር (Check and Balance) የሚጠበቅበት አወቃቀር ቢያስቀምጥም፣ የሥራ አስፈጻሚው ፍፁም የበላይነት ነግሦ መንግሥትና ፓርቲ አንድና አንድ የሆኑበት፣ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲጠፉ በመደረጉ በከፍተኛ አደጋ ላይ እንገኛለን፡፡ አስገራሚው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ቢሆን አሳታፊ መሆኑ እየቀረ፣ በአገሪቱ የልማት ጉዞ የጋራ መግባባት እየጠፋ በመምጣቱ በሀብት ክፍፍል ከፍተኛ ልዩነት በመኖሩና የወጣቱ ሥራ አጥነት ተጨምሮ በከፍተኛ ሁከት ውስጥ እንገኛለን፡፡ ሲጠቃለል በአንድ በኩል ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት በሌላ በኩል ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንገኛለን፡፡

የጨለማ ዘመን

በአገራችን የሕዝቦች እንቅስቃሴ እንደ ጥቁር ነጥብ የሚታየው ዋናው ነገር ብሔር ተኮር ጥቃት ነው፡፡ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በ2010 ዓ.ም. አብረው ለብዙ ምዕተ ዓመታት በሰላምም በግጭትም ሲኖሩ በነበሩ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦች ያጋጠሙ መፈናቀሎች፣ ሞትና የንብረት ውድመት ዋናው ናቸው፡፡ ለማመን የሚያስቸግር ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ አትዮጵያዊያን ተፈናቅለዋል፡፡ በብሔራዊ የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን የቅርብ መረጃ መሠረት በመቶዎች የሚቆጠር ሕይወት እንዳለፈም ተሰምቷል፡፡ የወደመው ንብረት መጠን አሁንም አይታወቅም፡፡ በእነዚህ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል የደረሰው ጥቃትና መፈናቀል ምናልባትም በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅና የሚዘገንን ነው፡፡ ይህ ግን አሁን የተከሰተ አይደለም፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በፊትም ሆነ በኋላም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ መንገዶች ሲከሰት በጊዜው ተገቢው ዕርምት ሳይወሰድ ቀርቷል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ በተለይ በአማራ ተወላጆች ላይ እዚህም እዚያም ጥቃቶች ሲሰነዘሩ የነበሩት በሕግ በላይነት መሠረት መፍትሔ ስላልተበጀላቸው ነው ይህ ከፍተኛ አደጋ የደረሰው፡፡ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ከደረሰው ጥፋት በፊትም ሆነ በኋላም ብሔር ተኮር ጥቃት እየቀጠለ ነው፡፡ በጎንደር፣ በወልዲያ፣ ወዘተ. የታዩት በትግራይ ተወላጆች እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ ተወላጆች የደረሰው ጥቃት የጨለማው ጉዞ ተቀጥላ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ሁኔታውን የሚያጨልመው በዩኒቨርሲቲዎቻችን ብሔር ተኮር ጥቃት መታየቱና ግርግር መፈጠሩ ነው፡፡ የነገ መሪዎቻችን ተስፋዎቻቸውን አንድ ላይ አድርገው ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራትን ከመታገል ይልቅ እርስ በርስ መጋጨታቸው አሳሳቢ ነው፡፡

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት እየደረሰ ያለው የንብረት ውድመት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ከድህነት ማጥ ለመውጣት ደፋ ቀና እያለች የምትገኝ አገርን ያላትን ውስን ሀብት ማጥፋት ከበደልም የከፋ በደል ነው፡፡ መጥፋቱ ብቻ ሳይሆን የሚፈጥረው ሥጋት የሕዝቦችና የባለሀብቶችን ትጋት እንዲቀንስና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዳይመጣም ያግዳል፡፡ ልፍስፍስ መንግሥት መኖሩ አንዱ የጨለማ ጊዜ ማሳያ ነው፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ብሎም በሌሎች የደረሰው ጥቃትና ጥፋት ደረጃው ምን ያህል ነው? ዋናው አቀንቃኝ ማን ነው? ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ፌዴራል መንግሥት የት ነበር? የኦሮሚያና የሶማሌ ክልላዊ መንግሥታት ምን አደረጉን ምንስ አላደረጉም? ወዘተ. የሚሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተላበሰ፣ የሕግ የበላይነት የሚፈጥር የተረጋጋና ለወቅቱ የሚመጥን አጥጋቢ ምላሽ ያልተገኘበት ሁኔታ እናያለን፡፡ በቅርቡ ባጋጠሙ ችግሮች ጠቅላይ ሚኒስትር (የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ) አለው ወይ እስኪያስብል ማዕከል የማጣት ሁኔታም ታይቷል፡፡ በፌዴራልና በክልሎች የፀጥታ ኃይሎች መካከል ያለው ግንኙነት አሳሳቢ የሆነበት ሁኔታም እናያለን፡፡ በአስጨናቂ ቀውስ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች አንድነት ትርጉሙ ከፍተኛ ነው፡፡ ሕዝቦች በከፍተኛ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ባሉበት ወቅት ተቀባይነት ባለው መንገድ ወንጀለኞችን አለመለየት የልፍስፍስነት ማሳያ ነው፡፡ ተቀባይነት ያለውን የሕዝቦች ጥያቄ በተሟላና በወቅቱ ለመመለስ ከሕዝቡ ጋር በመማከር ከመፍታት ይልቅ ባለሥልጣናት አንዴ ግምገማ፣ ሌላ ጊዜ ስብሰባና ሥልጠና እያሉ እየተደበቁ ነው፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉ ተሃድሶ (ጥልቅ ተሃድሶ) ሲካሄድ ነበር፡፡ አይ ጥልቅ ተሃድሶ? ወይ በሚገባ አልተካሄደ፣ ሌላ ስብሰባ እንደ ገና ሂስና ግለሂስ እስከ ታች ለማውረድ ያው ስብሰባ ነበር፡፡ አገር እየተቃጠለች በግምገማ የሚደበቅ፣ ወንጀልና የሕዝቦች ተቀባይነት ያለው ጥያቄዎች ለያይቶ ለመመለስ ያልቻለ መንግሥት ሆኗል፡፡ ሕገ መንግሥት ማዕከል አድርጎ የሕዝቦችን ጥያቄዎች ከመመለስ ሕዝቦችን ሳያማክር ለጊዜው የሚታየውን ‹‹መፍትሔ›› ይሰጣል፡፡ መፍትሔው አልሠራ ሲል ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ››፡፡ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሉ ፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ የሚሻ መሆኑ የጠፋበት ይመስላል፡፡ የግምገማ ስብሰባ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገር እንዳንሆን ያሠጋል፡፡ ሁለተኛው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንገኛለን፡፡ በአንድ በኩል ለውጥ እናደርጋለን እየተበለ እስረኞችም እየተፈቱ ሉበት ሁኔታ መታወ ግራ ያጋባል፡፡ እሺ ይን ብለን እንቀበለው፡፡ ቀውሱ ምክንያት ፖለቲካዊ መፍትውም ፖለቲካዊ ነው፡፡ የሕዝቦች ሰብዊና ዴሞክራያዊ መብቶች ለማረጋገጥ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገመንግት ማክበር ነው፡፡ ስለዚህልክ እንዳለፈው አዋጅ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ እንዳይሆን መረታዊ ለውጥ ሚያመጣ መንገድ እንቅስቃሴው አሁን ይጀመር፡፡

እርስበርስ የሚወናጀሉ ፓርቲዎችን እያየን ነው፡፡ በገዥው ግንባር ውስጥ ያለው መጠራጠር የተጠራቀመ የኢዴሞክራሲያዊ ግንኙነት መግለጫ በመሆኑ፣ በአንድ ግምገማ እንደሚፈታ ታሳቢ ማድረግ የዋህነት ነው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ዶ/ር መረራ ጉዲና ለሸገር ታይምስ በሰጡት ቃለመጠይቅ እንደገለጹት፣ አንዱ የራሱን ጥፋት በሌላው እያላከከ የሚኖርበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ገዥው ፓርቲ ያለውን የስትራቴጂካዊ አመራር ችግር በሚያስቅ ሁኔታ በግምገማ የሚሞላ በሚያስመስል መንገድ እየሄደበት ነው፡፡ ከ‹‹ፀሐይ በታች›› ያሉት ችግሮች ቢገመግሙ እንኳ  ያለፉት መሠረታዊ ችግሮች ተገለጹ እንጂ፣ አሁን ካለንበት ፖለቲካዊ ቀውስ የምንወጣበት አጀንዳ (Transformation Agenda) ለሕዝቦች አልተገለጸም፡፡ አለ ከተባለም የ‹‹ጋን መብራት›› ነው የሚሆነው፡፡ ያለፈው እርግማን መፍትሔ ሊሆን አይችልምና፡፡ አሁን እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ከወዲሁ ሕገ መንግሥቱን ማዕከል እያደረጉ እንዳልሆነ ምልክቶች አሉ፡፡ የእስረኞችን መፈታት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንደ ጠቅላይ ሚኒስተር ሳይሆኑ እንደ ገዥው ፓርቲ ሊቀመንበር ነበር የገለጹት፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በወሰነው መሠረት ብለው ሲገልጹ አያፍሩም፡፡ ፖለቲካ ሌላ ሕግ ሌላ፣ ፓርቲ ሌላ፣ መንግሥት ሌላ መሆኑን ያልተገነዘበ አካሄድ በተለያዩ መንገዶች እየተነፀባረቀ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ከሁሉም በላይ ገዥ ሕግ ነው፡፡ ፓርቲና መንግሥት የሚለያዩበትን መንገድ ነው ያስቀመጠው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲከበር ብቻ ነው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩት፣ ሰላምም የሚነግሠው፡፡ ተቃዋሚዎች ያው ከገዥው ፓርቲ በባሰ ልፍስፍስ ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ለማረጋገጥ እያደረጉ ያሉትን ትግል ለመምራት ይቅርና ተቀራርበው መጓዝ አልቻሉም፡፡ እነሱም የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ የላቸውም፡፡ ኢሕአዴግ ቢወድቅ አማራጩ ምንድነው? አያሳዩንም፡፡ ስለጥላቻውና ኢሕአዴግ ስለመውደቁ እንጂ ከዚህ ጨለማ እንዴት እንወጣለን? የሚለውን የብርሃን ምልክት አያሳዩንም፡፡ ከጨለማ ወደ ጨለማ ነው የሚመሩን፡፡ ስለቀውስ በመዘርዘር ለተጨማሪ ቀውሶች ዕድገት ዕድል ይሰጣሉ፡፡ ጨለማ ያረገዘውን ዕድል በዋናነት ማጥናቱ ተገቢ ነው፡፡ ‹‹በጣም የሚጨልመው ሊነጋጋ ሲል ነው›› እንደሚለው የአገሬ ሰው፡፡ 

ከአድማስ ባሻገር

ኢትዮጵያ ላትመለስ እየተቀየረች ነው፡፡ በቀውስ ውስጥ ያሉትን ዕድሎች በሚገባ መርምሮ በማድነቅና በማስፋት ብቻ ነው አገራችን በምታከናውነው ግንባታ መሠረታዊ ለውጥ የሚገኘው፡፡ የአገራችን ሕዝቦች ከጫፍ እስከ ጫፍ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ካልሆነ አንገዛም እያሉ ነው፡፡ ቀስ በቀስ እየተፋፋመ መጥቶ የ2007 ዓ.ም. መቶ በመቶ የምርጫ ውጤት ክብሪት ሆኖ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ማዕበል አገራችንን እያናወጣት ይገኛል፡፡ ለመብቱ የሚታገል ጠያቂ ኅብረተሰብ ተፈጥሯል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የሰጠለትን መብቶች ማጣጣም ሲጀምር ሰላም እንደሰፈነ ሁሉ፡፡ መንግሥት እነዚህን መብቶች መከልከል ሲጀምር አይሆንም ብሎ መንግሥትን ማንቀጥቀጥ ጀምሯል፡፡ መንግሥት ያለው አማራጭ አንድና አንድ ነው፡፡ የሕዝቦችን መብት መቀበል ብቻ! በእኔ አመለካከት ፅንፈኞችና ወንጀሎች ሕዝብ ከሕዝብ ለማጋጨት የሚፈጸሙት ጥቃት መኮነን ያለበትና መንግሥት ዕርምጃ መውሰድ ያለበት ቢሆንም፣ የሕዝቦች ትግል ይዘቱ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የራሱን ድል ማጣጣም የማይችልና በድሮ የሚኖር መሆኑ ነው እንጂ፣ ጠያቂ ኅብረተሰብ መፈጠሩን የ25 ዓመታት አመራሩ ውጤት አድርጎ ሕዝብን መደገፍ ነበረበት፡፡ መፍራትና ለማፈን መሞከር በራሱ ላይ ጥፋት እንደ መጋበዝ ይቆጠራል፡፡ ኢትዮጵያ ላትመለስ ወደፊት እየተጓዘች ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ከማናቸውም ጊዜ በላይ ተጠናክሯል

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወደፊት እየመረሹ ናቸው፡፡ ለአንዳንድ ‹‹የሐበሻ›› ልሂቃን ስለኢትዮጵያ አንድነት ካልተዘመረ፣ ካልተሸለለና ልሙጡ የቀድሞ ባንዲራ (በእኩልነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር መሄድ እንደማንችል ሁሉ) ካልተውለበለቡና የቀድሞ ታሪክ (እነሱ የጻፉት) ማስተማሪያ ካልሆነ ኢኢትዮጵያዊነት ተዳክሟል ይላሉ፡፡ አንዳንድ ልሂቃን ደግሞ አሁን የሚታዩትን ብሔር ተኮር ጥቃቶች ጋርደዋቸው ከደርግ/ንጉሡ ዘመን በላይ ኢትዮጵያዊነት እንደተሸረሸረ ይናገራሉ፡፡ በእኔ እምነት ይህ ስህተት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ በቀጣይነት ማስተማር ይኖርብናል፡፡ ዋናው አንድነታችን የሚጠነክረው ግን ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ስንተጋ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንደ ማንኛውም ኅብረተሰባዊ ግንባታ አንድ ቦታየሚጀመር፣ አንድ ጊዜ እየተሸረሸረ ሌላ ጊዜ እያደገ፣ የተለያዩ ፈተናዎች እያጋጠሙት፣ አገር እስካልተበተነች ድረስ እየለመለመ የሚሄድ ኅብረተሰባዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከ500 ዓመታት በፊት የነበረው ኢትዮጵያዊነትና አሁን ያለው በይዘቱም በስፋትና በጥልቀቱም ይለያል፡፡ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ የሚተላለፍ እንደማናቸውም አስተሳሰብ እየሰፋ የሚሄድ ነው፡፡ የአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊነት በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ብቻ ነው መገለጽ የሚችለው፡፡ የዓደዋ ድል ነፃነታችንን ሲጠብቅልን አስበንም ሳናስበውም አሁን መጎናፀፍ አለብን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ጋር ባለው መሠረታዊ ትርጉሙ ነው የሚታየው፡፡ የሕዝቦቻችን እሴቶችን ኢትዮጵያዊነት እንዲለመልም ሲያደርጉ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ነው፡፡

የአሁኑ ኢትዮጵያዊነታችን ባለፈው ታሪካችን የተመሠረተ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ የሕዝቦች መስተጋብር የፈጠረው አስተሳሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነት በዋናነትና በወሳኝነት የሚለመልመው አሁን ባለው ሥርዓትና ወደፊት በምናየው ብርሃን ነው፡፡ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሚያጠናክሩ የኅብረተሰባችን የጋራ ባህል፣ አስተሳሰብ፣ ተግባርና ግንኙነት ኢትዮጵያዊነትን ሲያጠናክሩ በተቃራኒው ሲሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያዊነታችንን የሚሸረሽሩ ነው የሚሆኑት፡፡ ጋምቤላ፣ ወላይታ፣ አፋር፣ ወዘተ. ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ሊገነባ የሚችለው እንደ ሰው ማንነቱን የምታውቅለት ኢትዮጵያ ስትኖር ነው፡፡ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚቆጥሩት ገዥ መደቦች በሚገዟት ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ሊኖር አይችልም፡፡ ሰላም የማታስገኝለትና ልማትን የማታፋጥንለት አገር ባለችበት ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት ሊለመልም አይችሉልም፡፡ በትናንት ብቻ የሚገነባ ኢትዮጵያዊነት እንደ ጤዛ የሚበን ነው የሚሆነው፡፡ እንደ ደርግ መንግሥት በኢትዮጵያ አንድነት የሚዘምር፣ የሚሸልልና የሚተኩስ የኖረም የሚኖርም ያለ አይመስለኝም፡፡ በእኔ አመለካከት ደርግነት ፀረ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ የሕዝቦችን ድምፅ ሰርቆ ሥልጣን መያዝ ፀረ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ከእናት ጉያ ነጥቆ ወደ ጦርነት መማገድ፣ በኢትዮጵያ አንድነት ስም ለመብታቸው የሚታገሉትን ሕዝቦች መግደል፣ ንብረታቸውን ማውደምና በቀይ ሽብር ጭምር አንድ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ማጥፋት ፀረ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ የደቀቀ ኢኮኖሚ፣ በተለይ በ1977 ዓ.ም. ድርቅ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ዜጎች ማለቃቸው ፀረ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ደርግ ኢትዮጵያዊነትን ከማጠናር አኳያ የሠራው ሥራ አለ ከተባለ መሬትን የመንግሥት የሚያደርግ አዋጅ ማውጣቱና የሶማሊያ ወራሪን ድል ያደረገበት ክንውን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ምናልባት በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ በተለይ የደቡብ ምሥራቅና የደቡብ ምዕራብ ደቡብ ሕዝቦች ለመጀመርያ ጊዜ እንደ ሰው ተቆጥረው የሚያርሱት መሬት ማግኘታቸው ነው፡፡ እስከ 2008 ዓ.ም. በነበሩት 25 ዓመታት የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም፣ በመሠረቱ የሰላምና የልማት ዓመታት ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያዊነት ድብልቅልቅ ብርሃን የሚንፀባረቅበት ወቅት ነበር፡፡ ነገር ግን ዴሞክራሲው ቀስ በቀስ እየሰፋ ከመሄድ ይልቅ በእጅጉ እየጠበበ በመሄዱ አሁን ላለው ጨለማ ዳርጎናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊነትን ከዴሞክራሲ ለይቶ ለማየት አስቸጋሪ ነው፡፡ የዴሞክራሲ አለመኖር ኢትዮጵያዊነትን ማቅ አልብሶ ብሔር ተኮር ጥቃት በስፋት አስከተለ፡፡ ኢትዮጵያዊነት በከፍተኛ ደረጃ በጠነከረበት ሁኔታ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ከባቢ መፈጠሩ የሚሸረሸረው ክስተትም ሆነ ግዑዝ  ኢትዮጵያዊነት አይኖርም፡፡ እንደ ሁኔታው ላይና ታች የሚል እንጂ፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ በማናቸውም ጊዜ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ነው፡፡ በአንዳንድ ልሂቃን ዙሪያ ግን መቅበዝበዝ ይታይ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ነን አይደለንም፣ ከኢትዮጵያ ተገንጥለን እንኑር፣ ወዘተ. ቀላል በማይባል መጠን ይታይ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኦሮሞ ሕዝብ ባካሄደው ሰፊው ትግል እነዚያ እንገነጠላለን የሚሉት እንዲደበቁ አድርጓል፡፡ ግንድ እንዴት ይገንጠል በሚል፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ መሪዎች ወደ ሥልጣን በማምጣት ኢትዮጵያዊነት የበለጠ እንዲጠናከር አድርገዋል፡፡ ኦሮሞ የኢትዮጵያ ጂኦግራፊያዊ ማዕከል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት ማዕከል እንዲሆን የክልሉ አመራር ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተጎናፀፈው ሰላምና ልማት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የሰንደቅ ዓላማችን ተሸካሚ የፌዴራል ሥርዓቱ ዘብ እየሆነ ነው፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በተመሳሳይ ደረጃ የሚታዩ ናቸው፡፡ኢትዮጵያዊነት በከፍተኛ ደረጃ ባደገበት ሁኔታ ግን ጉድፍ ይታይበታል፡፡ ወጣቱ ራሱን ከፖለቲካ ለማግለል የነበረው መንፈስ በእጅጉ እየቀነሰ ነው፡፡ ዋና ተዋንያን መሆን ጀምሯል፡፡ ከሕዝቡ 70 በመቶ ወጣት በሆነባትና ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ በትምህርትና በሥራ ላይ ባለበት ተዋንያን መሆን ማለት፣ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ የመወሰን አቅሙ እያደገ ነው ማለት ነው፡፡ የሕዝቦች ትግል ማዕከል እየሆነ ነው፡፡ ሦስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር በአራት ኪሎ ሽርጉድ ብቻ የሚመረጥበት ሁኔታ እየቀነሰ የወጣቱ ተፅዕኖ እያደገ መምጣቱን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ከዚህ በላይ ተስፋ የሚሰጥ ጉዳይ ምን አለ?  የአገራዊ ማንነት መግለጫ አንዱ የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥንካሬና የአገሪቱን ሕዝቦች መምሰል (National Composition) ነው፡፡ ከእነ ብዙ ችግሩ በአገር ውስጥም በውጭም ጠንካራ መሆኑን ያስመሰከረ ነው፡፡ ሆኖም በአገር ደረጃ ኢዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ባለበትና ከሠለጠነበት አገርን መከላከል ወደ የውስጥ ፀጥታ ጉዳዮች ሊሰማራ ስህተት መፈጸሙ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ በኩል በአጠቃላይ በአገራችን ካለው ኢዴሞክራሲያዊ ሁኔታ በመነሳት ለሕገ መንግሥቱ የሚኖረው ታዛዥነት እንዲጠናከር የፀጥታ ዘርፍ ለውጥ ጊዜ ሳይሰጥ መደረግ ይገባዋል፡፡ ለውጥ ከተደረገ የኢትዮጵያውያን የበለጠ አለኝታ በመሆን ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠናክር ነው የሚሆነው፡፡ መታረም ያለበት ዋናው መረታዊ ችግር ግን ራዊቱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ብሎም የኢሕአዴግ መጨረሻ ሽግ ነው ሚለው ፀረ ሕገመንግአስተሳሰብና መመያ ነው።

በእኔ ግምት መከላከያችን በዘመናዊ የኢትዮጵያ ሠራዊት ታሪክ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የመሰለበት እንደ አሁኑ ጊዜ የለም፡፡ በታሪካዊ አጋጣሚ ምክንያት በሕገ መንግሥታችን መሠረት ሲቋቋም ከትግራይ ክልል በእጅጉ የበዛበት ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን ካልመሰለ ያለው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ ከመጀመርያው ጀምሮ ዕቅድ ወጥቶለት ለማመጣጠን ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፡፡ በዚህ ሒደት በርካታ የትግራይ ተወላጆች ሰለባ ሆነዋል፡፡ ማመጣጠን ለማረጋገጥ በርካታ ታጋዮች በቂ መቋቋሚያ ሳይደረግላቸው ተሰናብተዋል፡፡ በሠራዊት የቆዩትም ከእኩዮቻቸው ሲነፃፀሩ በማዕረግ ዝቅ እንዲሉ ተደርገዋል፡፡ የኤርትራ ወረራ በ1990 ዓ.ም. በመከሰቱ ግን በማሸጋሸግ የተሰናበቱትን እንደ ገና ወደ ዕዝ ለአገር ህልውና ማስገባት ጠቃሚ ስለነበር የታሰበውን የማመጣጠን ሥራ ሳያዛባው አልቀረም፡፡ ሆኖም የመከላከያ ሚኒስትሩ በ2005 ዓ.ም. ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት እስከ ሻለቃ ድረስ መመጣጠኑን ገልጸው ነበር፡፡ በቅርብ ጊዜ ፕሬዚዳንት ሙላቱ የሰጡዋቸው ሹመቶች በተለይ የብርጋዴር ጄኔራል ማዕረግ ጥንቅር ሳይ በእውነትም ይህ ሠራዊት እየተመጣጠነ ነው ያልኩት፡፡ በእኔ ግንዛቤ የሠራዊት የጀርባ አጥንት ከሻለቃ እስከ ብርጋዴር ጄኔራል ያለው ነው፡፡ የበታቾችንና ከፍተኛ ጄኔራሎችን የሚያውቅ ታክቲካልና ኦፕሬሽናል ግንባታ ጥሩ ከሆነ ስትራቴጂካዊ አስተሳሰብ የሚጀምር የሠራዊቱ አካል ይሆናል፡፡ በሰላም ጊዜ ከፍተኛ ጄኔራሎች ቢያዙም በቀውስ ጊዜ ግን የዚያ አካል ሁኔታ ነው የሚወስነው፡፡ በ1966 ዓ.ም. በነበረው ቀውስ በጄኔራሎቹ፣ በሻለቆችና ኮሎኔሎች አካባቢ የነበረው ሚና ያስታውሷል፡፡ ከብርጋዴር ጄኔራል ሹመት ጋር የምክትል ኤታ ማዦሮች ምደባ ሲታይ እውነትም ባልተጠበቀ ሁኔታ የአገራችን ሕዝቦች እየመሰለ ነው፡፡ ፕሮፌሽናል ግንባታው በጣም ጠንካራ ቢሆንም በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ (87፡1) ‹‹የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል፤›› የሚለውን ደረጃ በደረጃ ሟሟላት ነበረበት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጄኔራሎች ከትግራይ ስለበዙ ሠራዊቱ የወያኔ ነው ሲሉ፣ በተቃራኒው አንዳንድ የትግራይ ሰዎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ከትግራይ ስለሆነ በተለየ የእኛ ነው ይላሉ፡፡ እኔ ሁለቱም ስህተት ነው፣ ሞኝነት ነው የምለው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት የፀጥታው ዘርፍ የሚያስፈልገው ሆኖ ላይመለስ፣ ግን ተመጣጥኗል፡፡ በአገራችን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ሕዝቦቻችን ያለማቋረጥ ለመብቶቻቸው የሚያደርጉት ትግል ዋናው መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ በኢሕአዴግ ፈቃድ ብቻ መምጣት አይችሉም፡፡ ሆኖም የሕዝቦችን ትግል ማዳመጥ መቻል ለለውጡ መቀላጠፍ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ፣ ሲያደናቅፍም ጫናው ከፍተኛ ነው፡፡ እግሩ እየተቃጠለ፣ ጋንግሪን እየወረረው፣ ለማየትና ለመስማት ምንም ስሜት የሌለው ድርጅት እየሆነ ነው እንዴ ኢሕአዴግ? የሚለው ጥያቄ በሁላችንም የሚንሸራሸር ነበር፡፡ ጋንግሪኑ ራሱን ያጠፋዋል? ወይስ ቆርጦ ጥሎ ከሕዝቦች መብቶች ጋር ይቀራረባል ወይ? የሚለው ጥያቄ በሁላችን ዘንድ የነበረ ነው፡፡

ከኢሕአዴጎች ከ‹‹ፀሐይ በታች›› ያሉትን ችግሮች ዓይተናል ብለዋል፡፡ በእውነትም ዴሞክራሲ ማዕከል ተደርጎ የተዘረዘሩ ችግሮችን ማየትና መስማት ጀመረ እንዴ? የሚያኝ ነው፡፡ ከሕዝቦች ጋር ሊታረቅ ነው እንዴ እንድንል ያደርጋል፡፡ አሁንም በግምገማ ውስጥ ያሉ ስለሆነ ለውጡን ያላየነው ቢሆንም አንዳንድ ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡ በወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሎ የከሰሳቸውን ፖለቲከኞች ክስ ማቋረጥና የታሰሩትን መፍታት አዎንታዊ ዕርምጃ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ግምገማን የድርጅቱ ሊቀመንበርነት ሲያቀርብ በመሠረታዊ ጉዳዮች ቢስማሙም በተለያዩ ጉዳዮች እንደሚለያዩ የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡ አንዱ መሪ የተናገረውን መድገም አቋርጧል፡፡ ወጥነትና የዓላማ አንድነት አንድ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ እንኳን የአራት ድርጅቶች ጥምረት ሆኖ አንድ ወጥ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ቢሆንም እንኳን በሁሉም ነገር አንድ ዓይነት ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ጥርነፋ የሚባለው በተግባር ግን አምባገነናዊ ጥርነፋ የዴሞክራሲን ውበት በገዥዎቻችን እንዳናይ አደረገን እንጂ፣ በአንድ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ሰዎች መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ሲለያዩ በዴሞክራሲ አገሮች እያየን ነው፡፡ በአሜሪካዊ ሪፐብሊካን ፓርቲ ‹‹ቲ ፓርቲ››፣ በታላቋ ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት (Brixit) የነበረውን ልዩነት ያስተውሏል፡፡ አራቱ ሊቀመንበራት የሚስማሙበትን ብቻ ሳይሆን መጠነኛ ልዩነትም ዓሳይተዋል፡፡ የዴሞክራሲ ፍንጭ በውስጣቸው ዓይተናል፡፡ በአንድ አዕምሮና በአንድ አፍ መናገር ያቋረጡ መሆናቸው ትልቅ አዎንታዊ ፍንጭ ነው፡፡ ግምገማቸውን ቀደም ብለው የጨረሱት ሕወሓትና ኦሕዴድ የሰጡት መግለጫ በጠቅላላ የኢትዮጵያ ሁኔታንና የክልላቸውን ሁኔታ ባገናዘበ መንገድ አንድነት ላይ ብቻ መሆኑ ቀርቶ ልዩነት ያላቸው መሆኑንም ያሳያል፡፡ የጤና ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ጥርነፋ የሚባለው ሰይጣን እየበነነ ይመስላል፡፡

አምቦ ውስጥ ለዶ/ር መረራ ጉዲና የተደረገው አቀባበልና በቦታው የፖሊስ ኮማንደር ጥበቃ እያደረገ ሲታይ፣ የሕዝቡ እንቅስቃሴ ከተቋም አንፃር ምን ልዩነት ሊያመጣ እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡  የቀድሞ ፕሬዚዳንት የክቡር ነጋሶ ጊዳዳ አንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞችንና ክብራቸውን ለማስመለስ የተደረገው ውሳኔ፣ እንዲሁም ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን በአዲስ አበባ መስተዳደር (ፌዴራል) የተከለከለውን ኮንሰርት የማዘጋጀት መብቱን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መፍቀዱ የፌዴራሊዝም ውበት ነው፡፡ ዲክ ሐዋርድ የተባለው ተመራማሪ የፌዴራሊዝም እሴቶች (Values of Federalism) በሚለው መጣጥፍ፣ አሌክሳንደር ሐሚልተን “Power Being Always the Rival of Power” በሚለው አስተሳሰቡ፣ በአንደኛው ማለት በፌዴራል ወይም በክልል መብቱ ሲነጠቅ በአንደኛው መብትን ለማስጠበቅ እንደሚቻል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ጥቂት ምሳሌዎች ቢሆኑም አጠቃላይ አቅጣጫ የሚያሳዩ ቢሆን ጤናማነታቸውን ለመጠቆም ነው፡፡ ዲክ ሐዋርድ ከላይ በተገለጸው መጣጣፍ “States as Laboratories” በሚል ርዕስ ዳኛ ለዊዝ ብሪንዲስን ጠቅሶ አንድ ጀግና ክልል ለሁሉም የሚሆን ማስተማር የሚችል ዕርምጃ እንደሚወሰድ ይገልጻል፡፡ በፓርቲ ደረጃ ቢሆንም ሕወሓት ያደረገው ጥልቅና የተሟላ ግምገማ፣ ኦሕዴድ እያገኘው ያለ ተቀባይነትና በውጭና በውስጥ ላሉት ተቃዋሚዎች ጥሪ ማድረጉ አንዱ ከሌላው ሊማርበት የሚችል ነው፡፡ እንዳለ ለመውሰድ መሞከር ጥፋት ቢሆንም በቅንነት ለመማር ቢሞከር ጠቀሜታው ከፍተኛው ነው፡፡

አንድ በብዙዎች የሚነሳ ጉዳይ ተገደው ያደረጉት ግምገማ በመሆኑ ዋጋ የለውም የሚል ነው፡፡ ኢሕአዴግ የአማልክት ድርጅት አይደለም፡፡ እንደ ድርጅትም እንደ አባላትም ጥቅምና በሕዝቡ ዘንድ ቀጣይት ያለው ግጭት አለ፡፡ ሕዝቡ ነቅቶና ተደራጅቶ እንደ ማግኔት (Magnetic Field) አላላውስ ሲል ብቻ ነው ከዓላማው አንፃር ቀጥ ብሎ መሄድ የሚችለው፡፡ በሕዝብ ግፊት ጉድለቶቻችሁን ማመን በብዙ የማይዘወተር የጤና ድርጅት ምልክት ነው፡፡ ንጉሣዊ ሥርዓት የሁሉንም ችግሮች ምንጭ ውጫዊ (የአገር ውስጥና የውጭ) ሲያደርግ ሥርዓቱን ለማዳን ሕገ መንግሥት ቀርቦላቸው እንኳ ንጉሡ ሊቀበሉት አልፈለጉም፡፡ የደርግ ሥርዓትም እስኪወድቅ ድረስ የጄኔራሎችና የወታደሮች ድክመት እያለ ነበር የሚያመካኘው፡፡ ኢሕአዴግ የገመገመውን ፖለቲካዊ ሪፎርም ተግባራዊ ያደርገዋል የሚለውን ጉዳይ አብረን የምናየው ሆኖ፣ መሠረታዊ ስህተትን ማመን የመጀመርያ ዕርምጃ መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡

ምን መደረግ አለበት?

ዋናውና ወሳኙ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለመብታቸው እያደረጉ ያሉትን ትግል ሰላማዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ያለማቋረጥ ሲቀጥሉበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወንጀሎኞችን ለይተው ለሕግ የማቅረብ፣ ብሔር ተኮር ጥቃትን የመፀየፍ ባህላቸውን እንዲያስጎለብቱ የራሳቸው ማኅበራት ነፃ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡና በቅርቡ የሚደረገው ምርጫ ፍትሐዊና ተቀባይነት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ሐንቲገተን (1991፡164) ዴሞክራሲ የገነቡት አገሮች እንዴት ነው የተሠሩት? ብሎ ጠይቆ ራሱ ሲመልስ፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ሁሉም መሠረታዊ ጉዳዮች በውይይት፣ በድርድርና በግልግል በመስማመት ለመፍታት መቻል፣ በሰላማዊ ሠልፍ፣ በምርጫ ዘመቻና ክንውን፣ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች ውስጥ የሚገኙ ልሂቃን በድፍረት በመታግል ማስተባበር ሲችሉ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ መሠረታዊ የዴሞክራሲ አስተዳደርን ማዕከል በማድረግ ያካሄደው ግምገማ መነሻ እንጂ ከዚያ በላይ ጠቀሜታእንደሌለው አውቆ፣ የሰጠውን ተስፋ ጊዜ እንደሌለ በመረዳት በአስቸኳይ ወደ ሥራ መግባት አለበት፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉ በስብሰባ የደረሰውን የሕዝብ ስቃይ፣ የተቃጠለውን ሀብትና ጊዜ የሚያካክስ የተሟላ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ አዘጋጅቶ ከሕዝቡና ተቃዋሚዎችና ምሁራን ምላሽ በማግኘት፣ የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተጣሱበትን የአመለካከት፣ የአደረጃጀትና የፖሊሲ አሠራር ለማስተካከል ግልጽ የተግባር ስትራቴጂ ማውጣት ይጠይቃል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዥው ፓርቲ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታዎችን እንዳይወጡ የሚከላከል አመለካከት፣ አደረጃጀትና አሠራር፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ስትራቴጂ ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ምክር ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶችና ምርጫ ቦርድ ነፃነታቸው ተጠብቆ ለመሥራት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕጉ መሠረት በሙሉ አቅማቸውን እንዳይታገሉ የሚፈጠርባቸውን እንቅፋቶች በዝርዝር ነቅሶ መፍትሔ ለማስቀመጥ መደራደር ተገቢ ነው፡፡ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ለመፈጸም የመንግሥት ተቀባይነት (Legitimacy) ከፍተኛ ችግር አለበት፡፡ ስለዚህ ተቀባይነት ያለው ሕገ መንግሥቱን በሚተረጉም ግን ወጣ ባለ መንገድ ፖለቲካዊ ሒደት መጀመር፣ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን በምክረ ሐሳብ ያቀረቡት በተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሥር የሆነ ገለልተኛ ኮሚሽን ማቋቋም፡፡ ይህ መሆን ካልቻለ የዴሞክራሲ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተጠሪነቱ ለተወካዮቹ ምክር ቤት ማድረግ፡፡ ገለልተኛና ተዓማኒነት ባላቸው ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች እንዲመራ ማድረግ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታግለው የተጎናፀፉዋቸውን ድሎች ልሂቃን ተጠቅመው ከጨለማው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለመዝለል፣ ከሁሉም በላይ በፖለቲካ ጥበብ ለሌላ ሐሳብ ዕድል በመስጠት የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ፣ እውነተኛና የተሟላ ድርድር ማድረግና በመጨረሻም ወደ ስምምነት መድረስ ይገባል፡፡ ሒደቱ በተቃዋሚዎችና በኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን አጋር ድርጅቶችንና በኢሕአዴግ አራቱ ድርጀቶችና በሕዝቦች መሀል መሆን አለበት፡፡ ልሂቃን ወደ ድርድር፣ ግልግልና ስምምነት እንዳይደርሱ የሚያደርጉ የተለያዩ እንቀፋቶችን መቅረፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንደኛው ሁሉንም ነገር ነጭ ወይም ጥቁር፣ አንደኛው ከሌላው ጋር ሊታረቅ የማይችል፣ ቂመኝነትና ለጥፋት ተጋላጭነት ለግልግል እንቅፋት ነው፡፡ ሁለተኛ አሁን በአገራችን ያለው ግንዛቤ ነው፡፡ ሁለት ጫፍ የያዙ አመለካከቶች አሉ፡፡ ቀደም ብሎ የነበረው የሥልጣን ግንኙነት በመሠረቱ የተቀየረ መሆኑን ካለማወቅ (ካለመፈለግ) ድሮ እንደነበረው እንዳለ አድርጎ በመወሰድ በትዕቢት ለድርድር መቅረብ ነው፡፡ ሌላው አሁን ሕዝቦች የሰጡትን መብት (Mandate) በማጋነን በትዕቢት አዋርዶ ለመጣል የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕአዴግ ታጋይና የአየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡